የመኖሪያ ቤት እጦት መንስኤው ምንድን ነው?
የመኖሪያ ቤት እጦት መንስኤው ምንድን ነው?
“በዓለም ዙሪያ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት የላቸውም” ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት አድርጓል። ይህ አኃዝ ትክክል ከሆነ ከ60 ሰዎች ውስጥ አንዱ በቂ ነው ሊባል የሚችል መጠለያ የለውም! ይሁንና የችግሩን ስፋት በትክክል ማወቅ ያስቸግራል። ለምን?
ሰዎች የቤት እጦት ለሚለው ቃል የሚሰጡት ፍቺ እንደየአካባቢው ይለያያል። ስለ ችግሩ የሚያጠኑ ሰዎች የሚጠቀሙበት ዘዴና የሚያጠኑበት ዓላማ ለቃሉ በሚሰጡት ፍቺ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። የሚሰጡት ፍቺ ደግሞ በሚያወጡት አኃዛዊ መረጃ ላይ ለውጥ ያመጣል። ይህ ደግሞ የችግሩን እውነተኛ ገጽታ ለማወቅ የሚደረገውን ጥረት በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰፈራ ማስተባበሪያ ማዕከል ያሳተመው ስትራቴጂስ ቱ ኮምባት ሆምለስነስ የተባለው መጽሐፍ፣ የመኖሪያ ቤት እጦት እንዳለባቸው የሚጠቀሱት በአካባቢው “በቂ ነው ከሚባለው በታች የሆነውን ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ የሌላቸው” ሰዎች እንደሆኑ ገልጿል። አንዳንዶች በጎዳናዎች ወይም መፈራረስ በጀመሩ ያረጁ ቤቶችና ሕንጻዎች ውስጥ ሲኖሩ ሌሎች ደግሞ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ባዘጋጁዋቸው ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ይኖራሉ። እንደዚሁም ከጓደኞቻቸው ጋር ጥገኛ ሆነው የሚኖሩም አሉ። ይህ ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ ሁኔታው ምንም ይሁን ምን “አንድ ሰው መኖሪያ ቤት የላቸውም ከሚባሉ ሰዎች ጋር መፈረጁ፣ ለተጎጂው ‘አንድ ነገር መደረግ እንዳለበት’ ይጠቁማል።”
ወደ 40 ሚሊዮን ገደማ የሕዝብ ብዛት ባላት በፖላንድ ከ300,000 የሚበልጡ ሰዎች መኖሪያ ቤት እንደሌላቸው ይገመታል። እነዚህ ሰዎች በተወሰነ አካባቢ ስለማይመዘገቡና ከቦታ ቦታ ስለሚዘዋወሩ ቁጥራቸውን በትክክል የሚያውቅ የለም። አንዳንዶች አኃዙ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ይጠጋል የሚል እምነት አላቸው!
የቤት እጦት ችግር በጣም የተስፋፋ በመሆኑ ምናልባት አንተም የምታውቀው ሰው የችግሩ ሰለባ ይሆናል። የቤት ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚገጥማቸው ውጣ ውረድ በርካታ ጥያቄዎችን ያስነሳል። እነዚህ ሰዎች ተስማሚ መኖሪያ ቤት ያጡት ለምንድን ነው? መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት የሚችሉት እንዴት ነው? ማን ሊረዳቸው ይችላል? በተጨማሪም የቤት እጦት ያለባቸው ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው?
በመኖሪያ እጦት መንገላታት
ሳብሪና * ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ድህነት ባጠቃው ሃርለም በሚባል አካባቢ የምትኖርና ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ነች። ትምህርቷን ከአሥረኛ ክፍል ያቋረጠችው ይህች ሴት የአሥር ወር፣ የሦስት ዓመትና የአሥር ዓመት ዕድሜ ካላቸው ወንዶች ልጆቿ ጋር የከተማው ማዘጋጃ ቤት ለረጅም ጊዜ መኖሪያ ቤት ላልነበራቸው ሰዎች ባዘጋጀው አንድ መኝታ ክፍል ባለው አፓርታማ ውስጥ ትኖራለች። ከተማው ይህን ዝግጅት ያደረገው የተሻለ መኖሪያ ቤት የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት ነው።
ሳብሪና ከእናቷ ቤት የወጣቸው ከአሥር ዓመት በፊት ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከወንድ ጓደኛዋ፣ ከሌሎች ጓደኞቿና ከዘመዶቿ ጋር ትኖር ነበር። ችግሩ ሲከፋባት ደግሞ በከተማው መጠለያዎች ውስጥ መኖር ጀመረች። ሳብሪና እንዲህ ብላለች:- “የምሠራው አልፎ አልፎ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ሹሩባ እየሠራሁ ገንዘብ አገኛለሁ። ያም ሆኖ አብዛኛውን ወጪዬን የምሸፍነው ከመንግሥት በማገኘው ድጎማ ነው።”
የሚገርመው ሳብሪና መቸገር የጀመረችው ጥሩ የሚባል ሥራ አግኝታ በአንድ ሆቴል በጽዳት ሠራተኝነት ስትቀጠር እንደነበር ፓረንትስ መጽሔት ዘግቧል። ሠርታ የምታገኘው ደሞዝ በቂ እንደሆነ ተደርጎ ስለታሰበ ከመንግሥት የምታገኘው ድጎማ ቆመባት። ሆኖም ደሞዟ ለቤት ኪራይ፣ ለምግብ፣ ለልብስ፣ ለትራንስፖርት፣ ልጆቿን ለመንከባከብና ሌሎች ወጪዎቿን ለመሸፈን የሚበቃ አልነበረም። በመሆኑም የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሏ የቤቱ ባለቤት ሊያስወጣት ሞከረ። በዚህም ምክንያት ሳብሪና ሥራዋን በመልቀቅ አሁን ያለችበትን መኖሪያ እስክታገኝ ድረስ ለጊዜያዊ መጠለያነት በተዘጋጀ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረች።
ሳብሪና እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች:- “ሁኔታው ለልጆቼም አስቸጋሪ ነበር። የመጀመሪያው ልጄ ሦስት ጊዜ ትምህርት ቤት ለመቀየር ተገድዷል። አንድ ዓመት ባይደግም ኖሮ አሁን አምስተኛ ክፍል ይሆን ነበር። . . . ከቦታ ቦታ ተንከራተናል።” ሳብሪና መንግሥት ግማሹን ወጪ የሚሸፍንበትን ቤት ለማግኘት ተመዝግባ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ምንም መሄጃ የሌላቸው ብዙ ሰዎች ሳብሪናን እድለኛ እንደሆነች አድርገው ይመለከቷት ይሆናል። ይሁን እንጂ ቤት የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች እነዚህን በመሰሉ መጠለያዎች ውስጥ መኖራቸው ችግራቸውን እንደሚፈታላቸው አይሰማቸውም። ፖሊሽ ከሚውኒቲ ኸልፕ ኮሚቲ የተባለ ድርጅት እንደገለጸው አንዳንዶች “በመጠለያዎቹ ውስጥ ያለውን ሥርዓትና ደንብ ስለሚፈሩ” እዚያ እንዲገቡ የሚቀርብላቸውን ጥያቄ አይቀበሉም። ለምሳሌ ያህል ቤት የሌላቸውን ለመርዳት ታስበው በተዘጋጁ ማረፊያዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እንዲሠሩ እንዲሁም ከአልኮል መጠጥና ከአደንዛዥ ዕፅ እንዲርቁ ይጠበቅባቸዋል። ይሁንና እነዚህን ደንቦች ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሚሆነው ከስንት አንዱ ነው። በመሆኑም ቤት የሌላቸው ሰዎች እንደየወቅቱ ሁኔታ በባቡር ጣቢያዎች፣ በደረጃዎች ሥር፣ በምድር ቤቶች አልፎ ተርፎም መናፈሻዎች ውስጥ ባሉ ወንበሮች ላይ፣ በድልድዮች ሥር እንዲሁም ኢንዱስትሪ ባለባቸው አካባቢዎች ይተኛሉ። ይህ በየትኛውም የዓለም ክፍል በግልጽ የሚታይ ችግር ነው።
የቤት እጦትን አስመልክቶ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ በፖላንድ ይህ ችግር እንዲከሰት አስተዋጽኦ ያደረጉትን ነገሮች በዝርዝር አስፍሯል። ከእነዚህ ውስጥ ከሥራ መፈናቀል፣ ዕዳ ውስጥ መዘፈቅና የቤተሰብ ችግሮች ይገኙባቸዋል። አረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞችና የኤድስ ሕሙማን መኖሪያ ቤት ለማግኘት ይቸገራሉ። መኖሪያ ቤት የሌላቸው ብዙ ሰዎች የአእምሮና የአካል ችግር ይኖርባቸዋል አሊያም ደግሞ ሱሰኞች ይሆናሉ፤ በተለይ በመጠጥ ሱስ ይጠመዳሉ። መኖሪያ የሌላቸው አብዛኞቹ ሴቶች ከባሎቻቸው የኮበለሉ ወይም ከቤታቸው የተባረሩ አሊያም ደግሞ ዝሙት አዳሪዎች የነበሩ ናቸው። መኖሪያ ቤት የሌለው ሰው ሁሉ አሳዛኝ ታሪክ ያለው ይመስላል።
የችግሩ ሰለባዎች
የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ስፔሻሊስት የሆኑት ስታኒስዋቫ ጎሊኖፍስካ እንዲህ ብለዋል:- “እዚህ [ፖላንድ ውስጥ] በፍላጎቱ ቤት አልባ የሆነ ሰው የለም። . . . ከዚህ ይልቅ የኑሮ አለመሳካት የሚፈጥረውን የተስፋ መቁረጥ ስሜትና የመኖር ፍላጎት ማጣትን ተከትሎ የመጣ ችግር ነው።” ብዙውን ጊዜ ለቤት እጦት የሚዳረጉት *
በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ችግሮቻቸውን ማሸነፍ እንደማይችሉ የሚሰማቸው ሰዎች ይመስላሉ። ለአብነት ያህል፣ አንዳንዶች ከእስር ቤት ሲፈቱ ቤታቸው በአሳዛኝ ሁኔታ በሥርዓት አልበኞች ፈራርሶ ጠብቋቸዋል። ሌሎች ከቤታቸው ተባርረዋል። በርካታ ሰዎች ደግሞ በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ መኖሪያቸውን አጥተዋል።ፖላንድ ውስጥ ጥናት ከተደረገባቸው መኖሪያ የሌላቸው ሰዎች መካከል 50 በመቶ የሚሆኑት ቤታቸው ችግር የማያጣው ቢሆንም እንኳ ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከትዳር ጓደኞቻቸው ጋር ይኖሩ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ከቤታቸው ተባርረዋል ወይም በሚደርስባቸው አስከፊ ችግር ሳቢያ ቤታቸውን ጥለው ለመውጣት ተገደዋል። በራሳቸው ምርጫ ከቤት የወጡት 14 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው።
አንዳንዶቹ የተወሰነ ጊዜ በመጠለያዎች ውስጥ ካሳለፉ በኋላ ራሳቸውን በመቻል መኖሪያ ቤት አግኝተዋል። ሌሎቹ ደግሞ ችግሩን መፍታት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ለዚህ ችግር በከፊል ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች የአእምሮ ወይም የአካል ሕመም፣ ለሱስ ተገዢ መሆን፣ የሥራ ፍላጎት ማጣት፣ ስንፍናና በቂ ትምህርት አለማግኘት ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወይም ብዙዎቹ ችግሮች አንድ ላይ ተዳምረው ሰዎቹን ለከባድ የቤት እጦት ዳርጓቸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙት ቤት የሌላቸው ሰዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት አንድ አትራፊ ያልሆነ ድርጅት “ሆምለስ ሲስተም” (ቤት የሌላቸው ሰዎች ዘዴ) በማለት የጠራውን ዘዴ ይጠቀማሉ። እነዚህ ሰዎች ችግሩ ሲብስባቸው ወደ መጠለያ፣ ሆስፒታል አልፎ ተርፎም እስር ቤት ይገቡና ሁኔታው ቀለል ሲልላቸው ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ። ብዙውን ጊዜ ይህን ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች ችግሩን ለማስወገድ ታስቦ ከተመደበው የአገሪቱ በጀት 90 በመቶ የሚሆነውን እንደሚጠቀሙ ይነገራል።
ቤት የሌላቸውን ለመርዳት ምን እርምጃ ተወስዷል?
አንዳንድ መጠለያዎች ቤት የሌላቸው ሰዎች ከችግራቸው እንዲላቀቁ የሚያስችላቸውን እርዳታ ለመስጠት ታስበው የተቋቋሙ ናቸው። በእነዚህ
መጠለያዎች ውስጥ ያሉ ግለሰቦች በመንግሥት የሚረዱበት፣ ከሌሎች ድርጅቶች የገንዘብ ድጎማና የሕግ ድጋፍ የሚያገኙበት፣ ከቤተሰባቸው ጋር የሚገናኙበት አሊያም አንዳንድ መሠረታዊ ክህሎቶችን የሚቀስሙበት ዝግጅት ይደረግላቸው ይሆናል። ለንደን ውስጥ ወጣቶችን ለመርዳት የተቋቋሙ ማዕከላት የአመጋገብ ልማድን፣ የምግብ አበሳሰልን፣ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤንና ሥራ ማግኘት የሚቻልባቸውን ዘዴዎች በሚመለከት ምክሮችን ይለግሳሉ። ምክሩ የሚሰጥበት ዓላማ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው አክብሮት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ራሳቸውን የመቻል ፍላጎታቸው እንዲጨምር በመርዳት በዘላቂነት የግል መኖሪያ አግኝተው ተረጋግተው እንዲኖሩ ለማስቻል ነው። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ምስጋና ሊቸረው ይገባል።ይሁን እንጂ አንድ ሰው መጠለያ ውስጥ መግባቱ ያለበትን መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍ ያስችለዋል ማለት አይደለም። በዋርሶ የሚኖር ያትሴክ የሚባል ቤት የሌለው ሰው የመጠለያ ሕይወት ነዋሪዎቹን ከውጪው ዓለም ጋር እንዲቀራረቡ የሚረዳ እንዳልሆነ ገልጿል። ያትሴክ በመጠለያዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች እርስ በርስ ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች ሰዎች ጋር እምብዛም ስለማይቀራረቡና ስለማይጨዋወቱ “የተዛባ አስተሳሰብ” እንዳላቸው ይሰማዋል። አክሎም “ከውጪው ዓለም የነጠለን ይህ መጠለያ አዋቂዎች የሚኖሩበት የልጆች ማሳደጊያ ሆኖብናል” በማለት ተናግሯል። እንደ እርሱ አስተሳሰብ ከሆነ አብዛኞቹ የመጠለያው ነዋሪዎች “ጤናማ አእምሮ የላቸውም።”
በፖላንድ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ቤት የሌላቸው ሰዎች ከሚሰሟቸው መጥፎ ስሜቶች ሁሉ የከፋው ብቸኝነት ነው። እነዚህ ሰዎች ባለባቸው የገንዘብ ችግርና በኅብረተሰቡ ዘንድ በሚሰጣቸው ዝቅተኛ ግምት ሳቢያ ራሳቸውን ዋጋ ቢስ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ። ስለሆነም አንዳንዶች ችግራቸውን ለመርሳት መጠጥ ያዘወትራሉ። ያትሴክ “ሁኔታዎች ይለወጣሉ የሚል የተስፋ ጭላንጭል በማጣታችን ምክንያት ብዙዎቻችን ካለንበት አስከፊ ሁኔታ ለመውጣት ጥረት ማድረግ
እንችላለን የሚለው እምነታችን ቀስ በቀስ ጠፍቷል” ሲል ተናግሯል። ውጫዊ ገጽታቸው፣ ድህነታቸው፣ ራሳቸውን አለመቻላቸው እንዲሁም መኖሪያ ቤት የሌላቸው የመሆኑ ሐቅ በሃፍረት እንዲሸማቀቁ ያደርጋቸዋል።የሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ፍራንሲስ ጄገዲ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የምንነጋገረው በቦምቤይና [ሙምባይ] በካልካታ መንገዶች ላይ ደሳሳ መጠለያ ቀልሰው ስለሚኖሩትም ይሁን በሚቆረቁሩት የለንደን አውራ ጎዳናዎች ላይ ተኝተው ስለሚታዩት ወይም ደግሞ በብራዚል ስላሉት የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች፣ ቤት የሌላቸው ሰዎች ያሉበት አሳዛኝ ሁኔታ እንኳን ሊኖሩበት ይቅርና ሲያስቡት የሚከብድ ነው።” ከዚያም እኚህ ሰው አክለው እንዲህ ብለዋል:- “የችግሩ መንስኤ ምንም ይሁን ምን አንድ ሰው ‘ዓለም ይህ ሁሉ ሀብትና ጥበብ እያለው እንዲሁም በቴክኖሎጂ መጥቆ ሳለ በቤት እጦት የሚሰቃዩ ሰዎችን ችግር መፍታት የተሳነው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ደግሞ ደጋግሞ ማንሳቱ የማይቀር ነው።”
የቤት እጦት ያለባቸው ሰዎች በሙሉ ቁሳዊ እገዛ ብቻ ሳይሆን ልባቸውን የሚያረጋጋላቸውና መንፈሳቸውን የሚያነቃቃላቸው እርዳታ እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ይህ ዓይነቱ እርዳታ ሰዎች ለቤት እጦት የሚዳርጓቸውን ብዙዎቹን ችግሮች ተጋፍጠው እንዲያሸንፉ ኃይል ይሰጣቸዋል። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ይህን መሰሉን እርዳታ ከየት ማግኘት ይችላሉ? የቤት እጦት የሚያስከትለው አሳዛኝ ሁኔታ የሚያቆምበት ጊዜስ ይኖር ይሆን?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.8 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.15 በምድር ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወይም በጦርነት ምክንያት መኖሪያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል። እነዚህ ሰዎች ስላሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት በጥር 22, 2002 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ስደተኞች—መኖሪያ ያገኙ ይሆን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የከፋ ድህነት ያስከተለው ችግር
በሕንድ አውራ ጎዳናዎች ላይ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ይኖራሉ። ቀደም ሲል የተደረጉት ጥናቶች በሙምባይ ብቻ 250,000 የሚያህሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ። ብቸኛ መጠለያቸው አንድ ጎኑ በአቅራቢያቸው ካለ ሕንጻ ጋር ታስሮ በሌላኛው ወገን ደግሞ ቋሚ እንጨት ላይ የተወጠረ ሸራ ነው። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ርካሽ የሆኑትን በከተማው ዳርቻ የሚገኙ ቤቶች ከመከራየት ይልቅ እዚህ መኖር የመረጡት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በከተማው መሃል ትንንሽ ዕቃዎችን በመነገድ፣ ሸቀጣ ሸቀጦችን በማዞር፣ በሚጎተት ጋሪ ሰው በማመላለስ አሊያም ቆርቆሮ ያለው በማለት ስለሚተዳደሩ ነው። ስትራቴጂስ ቱ ኮምባት ሆምለስነስ የተባለው መጽሐፍ “እነዚህ ሰዎች ምንም ምርጫ የላቸውም፤ ድህነታቸው ከዕለት ጉርሳቸው አልፎ ቤት ለመከራየት የሚያስችል ገንዘብ እንዳይኖራቸው አድርጓል” ሲል ገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ ከተማ በሚገኝ አንድ ባቡር ጣቢያ ውስጥ 2,300 የሚያህሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ይኖራሉ። በባቡር መጠበቂያ ወለሉ ላይ ብጫቂ ብርድ ልብስ አንጥፈው አሊያም የካርቶን ቤት ውስጥ ይተኛሉ። ብዙዎቹ ሥራ የላቸውም እንዲሁም ሥራ የማግኘት ተስፋቸው ተሟጧል። በከተማው የተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎችም ከዚሁ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች የውኃ፣ የመብራትና የመጸዳጃ ቤት እጥረት አለባቸው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በሽታ በፍጥነት እንዲዛመት በር ይከፍታል።
ከላይ የጠቀስናቸውን ጨምሮ በሌሎች አገሮች ውስጥ በተመሳሳይ ሁኔታ የሚኖሩ ሰዎችን ለቤት እጦት የዳረጋቸው ዋነኛው ምክንያት የከፋ ድህነት ነው።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የዘመናዊው ኅብረተሰብ ድክመቶች
በተባበሩት መንግሥታት የሰፈራ ማስተባበሪያ ማዕከል የታተመው ስትራቴጂስ ቱ ኮምባት ሆምለስነስ የተባለው መጽሐፍ የምንኖርበት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ሁሉም ሰው መኖሪያ ቤት እንዲኖረው ለማስቻል በሚደረገው ጥረት ረገድ ያለበትን ድክመት በዝርዝር አስቀምጧል። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል:-
● “የመኖሪያ ቤት እጦት ጉዳይ ሲነሳ በዋነኝነት የሚጠቀሰው ችግር ሰዎች ተስማሚ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብታቸውን ሙሉ በሙሉ ለማስከበር መንግሥታት በቂ ገንዘብ መመደብ አለመቻላቸው ነው።”
● “ትክክለኛ ደንብ አለመኖሩና አጥጋቢ ውጤት የሚያስገኝ ፕላን አለመቀረጹ በድህነት የሚማቅቀው አብዛኛው ሕዝብ ቤት እንዳይኖረው ትልቅ እንቅፋት ሆኗል።”
● “የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ሰዎች መኖራቸው መንግሥት እያንዳንዱ ዜጋ ቤት እንዲኖረው ለማድረግ የሚመድበው ገንዘብና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ አለመደልደላቸውን ያሳያል።”
● “የመኖሪያ ቤት ችግር በጣም የተባባሰው ፖሊሲዎች በሚቀረጹበት ጊዜ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት፣ የቤቶች ዋጋ መናር፣ የዕፅ ተጠቃሚዎች መብዛት እንዲሁም በቀላሉ የጥቃት ሰለባ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አካላዊና አእምሯዊ ጤንነት ትኩረት አለመስጠት የሚያስከትለው ከፍተኛ ተጽዕኖ ችላ ስለሚባል ወይም እንደቀላል ነገር ስለሚታይ ነው።”
● “በቀላሉ የጥቃት ሰለባ የሚሆኑ ሰዎችን የሚረዱ ባለሙያዎች የሚሠለጥኑበትን መንገድ ማሻሻል በጣም አስፈላጊ ነው። ቤት የሌላቸው ሰዎችን በተለይም የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን ለኅብረተሰቡ ሸክም እንደሆኑ ሳይሆን እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ ያልዋለ ትልቅ ሀብት እንደሆኑ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል።”
[ሥዕል]
ከሁለት ልጆቿ ጋር የምትለምን አንዲት እናት፣ ሜክሲኮ
[ምንጭ]
© Mark Henley/ Panos Pictures
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፕሪቶርያ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኘው የቀድሞ ባቡር ጣቢያ ቤት የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩበት መጠለያ ሆኗል
[ምንጭ]
© Dieter Telemans/Panos Pictures
[በገጽ 22 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
በስተ ግራ:- © Gerd Ludwig/Visum/Panos Pictures; ከጀርባ:- © Mikkel Ostergaard/Panos Pictures; በስተ ቀኝ:- © Mark Henley/Panos Pictures