የመኖሪያ ቤት እጦት መፍትሔው ምን ይሆን?
የመኖሪያ ቤት እጦት መፍትሔው ምን ይሆን?
“ለአንድ ሰው ዓሣ ብትሰጠው ለዕለቱ ትመግበዋለህ፤ ዓሣ ማጥመድ ብታስተምረው ግን ዕድሜ ልኩን ትመግበዋለህ።” ይህ አባባል ለአንድ ሰው ቁሳዊ እርዳታ መስጠት ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ ጥቅም እንደሌለው ይጠቁማል። እንዲያውም ሰዎች ችግራቸውን መፍታትና ፍላጎታቸውን ማርካት የሚችሉበትን መንገድ እንዲያውቁ መርዳቱ የተሻለ ነው። ብዙ ሰዎች የተሳካ ሕይወት ለመምራት የሚያስችሉ ክህሎቶችን ሌላው ቀርቶ የተለያዩ አመለካከቶችንና የአኗኗር ዘዴዎችን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች የቤት እጦት ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ውጤታማ የሆነው መንገድ ከሁሉ ስለተሻለው የሕይወት ጎዳና ማስተማር እንደሆነ ያምናሉ። ይህም ሲባል የሰው ልጆች ፈጣሪ የሰጠውን ከሁሉ የላቀ ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት ማለት ነው። ከእርሱ የተሻለ መካሪ ማን ሊኖር ይችላል? ምክሩ ለመኖሪያ ቤት እጦት ሊዳርጉ የሚችሉ ብዙዎቹን ችግሮች እንዲያስወግዱ ሰዎችን እየረዳቸው ነው። እንዲሁም መኖሪያ ቤት የሌላቸው ልበ ቅን ሰዎች ይህን ችግራቸውን እንዲቋቋሙ ያግዛቸዋል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበባችን ብቻ ያሉብን ችግሮች በሙሉ ይወገዳሉ ማለት አይደለም። ይሁንና
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ገንዘብን ከሚያባክኑ ጎጂ ልማዶች ተላቅቀው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸውና የሚያስከብር ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል።በርካታ ሰዎች በጎጂ ሱሶች በመያዛቸው፣ በተደጋጋሚ ወንጀል በመፈጸማቸው፣ በገንዘብ ችግር ውስጥ በመዘፈቃቸው ወይም ደግሞ ቤተሰባቸው በመፍረሱ ምክንያት ቤታቸውን አጥተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ስላሉት ጉዳዮች መፍትሔ የሚሆን ተግባራዊ ምክር ይሰጣል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ በማድረጋቸው ለሕይወት ያላቸው አመለካከትም ሆነ አጠቃላይ ባሕርያቸው ተለውጧል። እውነት ነው፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ብቻውን ከመኖሪያ ቤት እጦት ጋር ለተያያዙ ለሁሉም ችግሮች እልባት ያስገኛል ማለት አይደለም። ከተፈጥሮ አደጋ፣ ከሕመም፣ ከድህነት፣ ከጎጂ ሱሶችና እነዚህን ከመሳሰሉ ሌሎች ችግሮች ለመገላገል ሌላ ዓይነት እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ባሉ ችግሮች የሚሠቃዩ ሰዎችን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም እንኳ ችግሮቹን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግደው የሰው ልጅ ፈጣሪ መሆኑን አይዘነጉም። ይሁንና ፈጣሪ እነዚህን ችግሮች በእርግጥ ያስወግዳቸዋል?
የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ
የመኖሪያ ቤት እጦት በቅርቡ ይወገዳል ብለን ተስፋ የምናደርግበት አጥጋቢ ምክንያት አለን። እንዲህ የምንለው ከምን ተነስተን ነው? እስቲ አስበው:- ይሖዋ አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ግሩም የሆነ መኖሪያ አዘጋጅቶላቸው ነበር። አምላክ በገነት ውስጥ ያስቀመጣቸው ሲሆን የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ አሟልቶላቸዋል። ፈጣሪያቸውን ቢታዘዙ ኖሮ ገነትን እስከ ምድር ዳር ድረስ ማስፋት ይችሉ ነበር። ልጆቻቸው ሁሉ ነገር ተሟልቶላቸውና ምቹ መኖሪያ አግኝተው መኖር በቻሉ ነበር። ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች ጋር በፍቅርና በኅብረት ይኖር ነበር። ይህ የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሲሆን አሁንም ሐሳቡ አልተለወጠም።—መዝሙር 37:9-11, 29
ከዚህም በላይ አምላክ ያሰበውን ሁሉ ያላንዳች ችግር ከግብ ማድረስ ይችላል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው የራሱ መኖሪያና የተትረፈረፈ ቁሳዊ ነገር የሚኖረው ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል። እርግጥ ይህ ከመሆኑ በፊት ሰዎች አሁን ያሉበት ሁኔታ መለወጥ ይኖርበታል። አምላክ በሰው ልጅ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት ይህን ዓይነቱን ለውጥ ያመጣል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ሲነግራቸው በአእምሮው የያዘው ይህን ነበር።—ማቴዎስ 6:9, 10
በአምላክ መንግሥት ፍትሐዊ አገዛዝ ሥር ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች የሚከተለው ትንቢት እውን ሲሆን ይመለከታሉ:- “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ . . . ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . እኔ የመረጥኋቸው፣ በእጃቸው ሥራ ለረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋል።” (ኢሳይያስ 65:21, 22) በሌላ አነጋገር ቤት የሌለው ሰው አይኖርም።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ እርዳታ ለመስጠት ይጥራሉ። ኢየሱስ እንዳዘዘው ሁሉ በፍቅር ተነሳስተው ሌሎችን የቻሉትን ያህል የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (ማቴዎስ 22:36-39) ሌሎችን ለመርዳት ያላቸው ከፍተኛ ፍላጎት በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ቤት ንብረታቸውን ላጡ ሰዎች የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ገፋፍቷቸዋል። *
የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም ሰው መርዳት እንደማይችሉ ያውቃሉ። በፖላንድ መኖሪያ ቤት ለሌላቸው በተዘጋጀ መጠለያ ውስጥ የሚኖረው ያትሴክ ቤት የሌላቸውን ሰዎች አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል:- “አንዳንዶቹ ቁጡዎች ወይም ደግሞ በዕፅ ሱስ የተያዙ ናቸው። ሌሎች ደግሞ አምላክ እንደማያስብላቸው ስለሚሰማቸው ስለ ሃይማኖት መነጋገር አይፈልጉም። ይሁንና ለአምላክ ቃል ጥሩ ምላሽ የሚሰጡም አሉ።”
እንዲህ ካደረጉት መካከል ያትሴክ አንዱ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ለማወቅ በመጣር ላይ ይገኛል።ለአምላክ ቃል መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሰጠው ሌላው ቤት የሌለው ሰው ሮማን ሲሆን እርሱም የኤድስ ሕመምተኛና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የጎዳና ተዳዳሪ ነበር። ሮማን የገጠመውን ሁኔታ በማስታወስ እንደሚከተለው ብሏል:- “ማኅበራዊ አገልግሎት ወደሚሰጥበት ተቋም በገባሁበት ወቅት የይሖዋ ምሥክሮች በአቅራቢያው እንደሚሰበሰቡ አላወቅሁም ነበር። ብዙም ሳይቆይ መንገድ ላይ አግኝተው ያወያዩኝ ጀመር፤ በዚህ ጊዜ አምላክ ቤት የሌላቸው ሰዎች የሚያሰሙትን ጩኸት በቸልታ እንደማይመለከት ገለጹልኝ። በተጨማሪም በስብሰባቸው ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ።”—መዝሙር 72:12, 13
ሮማን የሰማው ነገር ምን ስሜት አሳደረበት? “ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንደምችልና አምላክ ውድ አድርጎ እንደሚመለከተኝ ተገነዘብኩ። አሳቢ የሆኑ አዳዲስ ጓደኞችን ሳገኝ ችግሬን ማብሰልሰል የተውኩ ከመሆኑም በላይ የባሕርይ ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ለአምላክ ካደረብኝ ፍቅር የተነሳ ማጨስ አቆምኩ እንዲሁም በጽድቅ መንገድ ላይ መራመድ እንድችል ይረዳኝ ዘንድ አምላክን በጸሎት ለመንኩት።”
ሮማን ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርጎ ብዙም ሳይቆይ በመጠመቅ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል። የእምነት ባልንጀሮቹና የአካባቢው ባለ ሥልጣናት ባደረጉለት ድጋፍ ተስማሚ መኖሪያ ለማግኘት ችሏል። ሮማን እንደሚከተለው ሲል በደስታ ተናግሯል:- “ልቤ በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ በደስታ ተሞልቷል። ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረኝ ወደረዳኝ ወደ አፍቃሪው አምላክ ይበልጥ ቀርቤአለሁ። እርሱ ወንድሞችና እህቶች የሞሉበት ግሩም ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የምኖርበት ቤትም ሰጥቶኛል!”
መኖሪያ የሌላቸው ሰዎች ተስፋቸው ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች የመኖሪያ ቤት እጦት ያለባቸውን ጨምሮ ለሰዎች ሁሉ የርኅራኄ ስሜት ለማሳየት ይጥራሉ። በተጨማሪም ስለ መጪው የተሻለ ጊዜ የሚናገረውንና አሁንም ቢሆን የሰዎችን ሕይወት የሚለውጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች ለማካፈል ይጓጓሉ።—ዮሐንስ 8:32
መጽሐፍ ቅዱስ “የተጣመመው ሊቃና አይችልም” ይላል። (መክብብ 1:15) እውነት ነው፣ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞችና ባለ ሥልጣናት የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ የቤት እጦትንና ድህነትን የመሰሉ ሥር የሰደዱ ችግሮችን ማጥፋት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ በሚጀምረው በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ፍጹም በተስተካከለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ማረጋገጫ ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.9 ለምሳሌ ያህል ንቁ! መጽሔት በጥር 8, 1993 ገጽ 14-21 (እንግሊዝኛ)፤ በኅዳር 2001 ገጽ 13-17 እንዲሁም በኅዳር 2003 ገጽ 10-15 እትሙ ላይ ያሰፈራቸውን ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የራሽን መቀበያ ካርድ የያዘች በስደት የምትኖር ሶማሊያዊት እናት
[ምንጭ]
© Trygve Bolstad/Panos Pictures
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቤት የሌላቸው ሰዎች ከምንም በላይ ተስፋቸውን የሚያለመልም ነገር ይሻሉ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ቤት የሌለው ሰው አይኖርም