በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለንቁ! አንባቢያን

ለንቁ! አንባቢያን

ለንቁ! አንባቢያን

ከዚህ እትም ጀምሮ በንቁ! መጽሔት አጠቃላይ ይዘት ላይ አንዳንድ ለውጦች ይኖራሉ። ይሁንና ለውጥ የተደረገው በተወሰኑ ነገሮች ላይ ሲሆን አብዛኛው ነገር ግን እንዳለ ይቀጥላል።

ንቁ! ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የነበረውን ዓላማ እንደያዘ ይቀጥላል። ገጽ 4 ላይ እንደተገለጸው ይህ መጽሔት “ለመላው ቤተሰብ የሚጠቅም እውቀት ይገኝበታል።” ንቁ! በዓለም ላይ የሚከሰቱ ሁኔታዎችን በማጤን፣ የተለያየ ባሕል ስላላቸው ሰዎች በመናገር፣ ድንቅ ስለሆኑ የፍጥረት ሥራዎች በመግለጽ፣ ስለ ጤና በማውሳት ወይም በመስኩ ላልተሰማሩ ሰዎች ስለ ሳይንስ በማብራራት በዙሪያችን ያለው ዓለም ምን ላይ እንደደረሰ አንባቢዎቻችንን ማስገንዘቡን ይቀጥላል።

ንቁ! በነሐሴ 22, 1946 እትሙ ላይ “የዚህ መጽሔት ተቀዳሚ ዓላማ እውነትን በጥብቅ መከተል ነው” በማለት ቃል ገብቶ ነበር። ንቁ! ይህን ቃሉን ሳያጥፍ በተጨባጭ ሐቅ ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችን ለማቅረብ ምንጊዜም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ለዚህም ሲባል ርዕሶቹ ትክክለኛ መረጃ የያዙ እንዲሆኑ የተሟላ ጥናትና ጥንቃቄ የተሞላበት እርማት ይደረግባቸዋል። ይሁንና ይህ መጽሔት ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ በሌላ መንገድም ‘እውነትን በጥብቅ እንደሚከተል’ አሳይቷል።

ንቁ! ምንጊዜም አንባቢዎቹን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሲመራ ቆይቷል። ከዚህ እትም አንስቶ ግን ከበፊቱ በበለጠ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ርዕሶችን ያቀርባል። (ዮሐንስ 17:​17) በተጨማሪም ንቁ! መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ጠቃሚ ምክር መከተል በዛሬው ጊዜ ትርጉም ያለውና አርኪ ሕይወት እንዴት እንደሚያስገኝ የሚገልጹ ርዕሶች ማውጣቱን ይቀጥላል። ለምሳሌ ያህል፣ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” እና “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት” በሚሉት አምዶች ሥር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ በርካታ መመሪያዎች ቀርበዋል። እነዚህ አምዶች አሁንም የዚህ መጽሔት ቋሚ ክፍል ሆነው ይቀጥላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ንቁ! ዓመጽ የነገሠበት ይህ ሥርዓት በቅርቡ ተወግዶ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ ለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ አንባቢያን ትኩረት እንዲሰጡ መርዳቱን ይቀጥላል።​—⁠ራእይ 21:​3, 4

ሌላስ ምን የተለየ ነገር ይኖራል? ከዚህ እትም አንስቶ ንቁ! ከሚወጣባቸው 82 ቋንቋዎች መካከል በአብዛኞቹ የሚታተመው በወር አንዴ ይሆናል (ከዚህ ቀደም በብዙ ቋንቋዎች በወር ሁለት ጊዜ ይታተም ነበር)። * ከ1946 አንስቶ በቋሚነት ሲወጣ የቆየው “ከዓለም አካባቢ” የሚለው አምድ አሁንም በእያንዳንዱ እትም ላይ ይኖራል። ሆኖም የሚሸፍነው ገጽ ከሁለት ወደ አንድ ይቀነሳል። ከዚህ በተጨማሪ ገጽ 31 ላይ “መልስህ ምንድን ነው?” የሚል አእምሮን የሚያሠራ አዲስ ቋሚ ገጽታ አካትተናል። ይህ አምድ ምን ይዞ ይወጣል? እንዴትስ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ?

የዚህን እትም ገጽ 31 እስቲ ተመልከት። በዚያ ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ ክፍሎች የወጣቶችን ትኩረት የሚስቡ ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ የቆዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን የማስታወስ ችሎታ የሚፈትኑ ይሆናሉ። “ዘመኑ መቼ ነበር?” የሚለው ክፍል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ሰዎች መቼ እንደኖሩና ዓበይት ክንውኖች የተፈጸሙት መቼ እንደሆነ የጊዜ ቅደም ተከተሉን እንድታውቁ ይረዳችኋል። የአብዛኞቹ ጥያቄዎች መልሶች በዚያው እትም በተወሰነ ገጽ ላይ ተገልብጦ የሚጻፍ ሲሆን “ከዚህ እትም” በሚለው ክፍል ሥር ያሉት ጥያቄዎች መልሶች ደግሞ መጽሔቱ ውስጥ በተለያዩ ገጾች ላይ ይገኛሉ። መልሶቹን ከማንበባችሁ በፊት ለምን ጥቂት ምርምር አታደርጉም? ከዚያም ያገኛችሁትን እውቀት ለሌሎች ማካፈል ትችላላችሁ። በተጨማሪም “መልስህ ምንድን ነው?” የሚለውን ይህን አዲስ ገጽታ ከቤተሰባችሁ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ለማድረግ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ።

ከዛሬ 60 ዓመት ገደማ በፊት ንቁ! እንዲህ ሲል ቃል ገብቶ ነበር:- “በዚህ መጽሔት ላይ ከአንድ አገር ብቻ ሳይሆን ከዓለም ዙሪያ የተገኙ ርዕሰ ጉዳዮችን ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል። ይዘቱ በሁሉም አገር የሚኖሩ ልበ ቅን ሰዎችን የሚማርክ ይሆናል። . . . የመጽሔቱ ይዘትም ሆነ የሚያቀርበው መረጃ . . . ወጣት አዋቂ ሳይል ለብዙዎች ግንዛቤ የሚያሰፋና ትምህርት ሰጪ እንዲሁም ማራኪ ይሆናል።” በዓለም ዙሪያ የሚገኙ አንባቢዎች ንቁ! የገባውን ቃል እን​ደፈጸመ ይስማማሉ። ደግሞም በዚህ መልኩ እንደሚ​ቀጥል ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።

አዘጋጆቹ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በአንዳንድ ቋንቋዎች ንቁ! የሚታተመው በሦስት ወር አንዴ ስለሆነ በዚህ ደብዳቤ ላይ የተብራሩት አምዶች በሁሉም እትሞች ላይ ላይገኙ ይችላሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በ1919 “ዘ ጎልደን ኤጅ” ይባል ነበር፤ ከዚያም በ1937 ስሙ ተቀይሮ “ኮንሰሌሽን” የተባለ ሲሆን በ1946 ደግሞ “ንቁ!” የሚል ስያሜ ተሰጠው

[በገጽ 4 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

“ንቁ!” ከረጅም ጊዜ አንስቶ አንባቢዎቹን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሲመራ ቆይቷል

[ምንጮች]

መሣሪያዎቹ:- U.S. National Archives photo; የተራበ ሕጻን:- WHO photo by W. Cutting