ልጅ በሚሞትበት ጊዜ
ልጅ በሚሞትበት ጊዜ
▪ የልጅ ሞት ለወዳጅ ዘመዶቹ በተለይ ደግሞ ለወላጆቹ እጅግ አሳዛኝ ነው። አንዲት እናት የ16 ዓመት ልጇ በደረሰበት አሳዛኝ አደጋ ምክንያት ተቃጥሎ በሞተ ጊዜ “አምላክ በልጆቻችን ምትክ እንድንሞት አሊያም አብረናቸው እንድናንቀላፋ አይፈቅድልንም” በማለት በምሬት ተናግራለች።
ይሁን እንጂ ይህች እናት ተስፋ ቢስ አልነበረችም። በዚህም ምክንያት “አምላክ ስለ ሞት እውነታውን ነግሮናል፤ ይህ ደግሞ እኔና ባለቤቴ ከልክ በላይ እንዳናዝን ወይም ሚዛናችንን እንዳንስት አድርጎናል” ብላለች። አክላም “በልጃችን ላይ ይህ እንዲደርስ ያደረገው አምላካችን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ሙታንን የማስነሳት ዓላማ አለው። ልጃችን ሕያው፣ ጤናማና ደስተኛ ሆኖ በጓደኞቹና በቤተሰቡ መካከል ሲኖር በዓይነ ሕሊናችን ይታየናል” በማለት ተናግራለች።
አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት ያላቸው ሰዎችም እንኳ መጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። ይህች እናት ብዙ ወዳጆቿ ስላጽናኗት አመስጋኝ ናት። እንዲህ ብላለች:- “ከወዳጆቻችን ያገኘናቸው አብዛኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችና የደግነት መግለጫዎች የምትወዱት ሰው ሲሞት ከሚለው ብሮሹር የመነጩ ናቸው። የአካባቢያችን ሰዎች ሁሉ ምን እንደተሰማንና ከዚህም በኋላ ቢሆን ምን ሊሰማን እንደሚችል በተሻለ መንገድ እንዲረዱልን ይህን ብሮሹር እንዲያነቡት እናበረታታቸዋለን።”
እርስዎ ወይም አንድ የሚያውቁት ሰው የምትወዱት ሰው ሲሞት የሚለውን ብሮሹር በማንበብ መጽናኛ ማግኘት ትችሉ ይሆናል። ይህን ብሮሹር ማግኘት ከፈለጉ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች ውስጥ አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።
□ የምትወዱት ሰው ሲሞት የተባለውን ብሮሹር አንድ ቅጂ ላኩልኝ።
□ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።