በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባው ለምንድን ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያችን አድርገን ልንጠቀምበት የሚገባው ለምንድን ነው?

“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ [እና] ለማቅናት . . . ይጠቅማሉ።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:16

ለሕይወትህ መመሪያ አድርገህ የምትከተለው ምንን ነው? በዛሬው ጊዜ በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማለት ይቻላል ስፍር ቁጥር የሌለው ምክር ይገኛል። ያም ሆኖ በርካታ ሰዎች ከተጻፈ ዘመናት ያስቆጠረውን መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርገው ይጠቀማሉ።

ይሁን እንጂ መረጃ እንደልብ በሚገኝበትና ቴክኖሎጂ በረቀቀበት በዚህ ዘመን አብዛኛው ሰው ለመጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ ነው። ከፍተኛ አክብሮት ያተረፉ አንዳንድ አስተማሪዎችና ሳይንቲስቶች መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ አልፎበታል የሚለውን ሐሳብ ይደግፋሉ። እነዚህ ሰዎች ትክክል ናቸው? አንድ ሰው ስፍር ቁጥር የሌላቸው መመሪያዎች ባሉበት በዚህ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርጎ መጠቀም ያለበት ለምንድን ነው?

እውነትን ያዘለ መጽሐፍ

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ አረፍ ብሎ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ተወያይቶ ነበር። በዚህ ጊዜ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል” አላት። (ዮሐንስ 4:24) እነዚህ ቃላት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው ምን ዓይነት አምልኮ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የምናቀርበው አምልኮ በእውነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ከተፈለገ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ራሱ ከገለጸው ሐሳብ ጋር መጣጣም ይኖርበታል። የአምላክ ቃል እውነትን ይዟል።​—⁠ዮሐንስ 17:17

ብዙ ሃይማኖቶች በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ ቢናገሩም እንኳ እያንዳንዳቸው የሚያስተምሩት ትምህርት ለየቅል እንደሆነ መመልከት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ‘መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምንድን ነው?’ በሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ ግራ መጋባት ተፈጥሯል። ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ነው ወይስ የእግዚአብሔር ልጅ? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ ወይስ የለም? ሙታን የሚቀጡበት ሲኦል የሚባል ቦታ አለ? በእርግጥ ሰይጣን የሚባል አካል አለ? ክርስቲያን መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? ድርጊታችንም ሆነ አስተሳሰባችን በአምላክ ፊት ለውጥ ያመጣል? እውነተኛ ፍቅር ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም እንደ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ ይችላል? የአልኮል መጠጥ መጠጣት ስህተት ነው? * የተለያዩ ሃይማኖቶች እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ እውነታውን እንደሚያስተምሩ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ። ስለሆነም ሁሉም እውነት ናቸው ብለን መደምደም አንችልም።​—⁠ማቴዎስ 7:21-23

ታዲያ ስለ አምላክና እርሱን ስለሚያስደስተው የአምልኮ ዓይነት እውነቱን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ከባድ የጤና ችግር ስላጋጠመህ ቀዶ ሕክምና አስፈልጎሃል እንበል። ምን ታደርጋለህ? አንተ በምትፈልገው የቀዶ ሕክምና ዘርፍ ከተሰማሩት ሐኪሞች መካከል የተሻለውን ለማግኘት የተቻለህን ሁሉ ጥረት ታደርጋለህ። የሐኪሙን የችሎታ ማረጋገጫና ያካበተውን ልምድ ካጤንክ በኋላ በአካል አግኝተኸው ታነጋግረዋለህ። በመጨረሻም በተመለከትካቸው መረጃዎች ላይ ተመርኩዘህ የተሻለ ሐኪም መሆኑን ካረጋገጥክ በኋላ እምነትህን በእርሱ ላይ በመጣል ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግልህ ትስማማለህ። ሌሎች የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ ሐኪም ላይ እምነት እንድትጥል ያደረገህ ጠንካራ መሠረት አለህ።

በተመሳሳይም የቀረቡልህን መረጃዎች በሐቀኝነትና በጥንቃቄ ከመረመርክ በኋላ በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መገንባት ትችላለህ። (ምሳሌ 2:1-4) በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኘው አምልኮ የትኛው ነው? ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያስችል ሁለት አማራጭ አለህ። እርስ በርሱ የሚጋጨውን ትምህርትና የሰዎችን አስተያየት አሊያም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ምን እንደሚል ልትመረምር ትችላለህ።

ትክክለኛና ተግባራዊ መመሪያ

መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከመረመርክ ‘ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸውና ጠቃሚ መሆናቸውን’ የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ታገኛለህ። * (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር በተጻፉ ትንቢቶች የተሞላ ነው። ታሪክ ደግሞ እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ይመሠክራል። (ኢሳይያስ 13:19, 20፤ ዳንኤል 8:3-8, 20-22፤ ሚክያስ 5:2) መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መጽሐፍ ባይሆንም እንኳ ከሳይንስ አንጻር ስንመለከተው ትክክለኛ ነው። ሳይንቲስቶች ተፈጥሮንና ጤናን በተመለከተ የደረሱባቸው እውነታዎች ከሺህ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሰፍረው ይገኛሉ።​—⁠ዘሌዋውያን 11:27, 28, 32, 33፤ ኢሳይያስ 40:22

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ሕይወትን፣ አካላዊና አእምሯዊ ጤንነትን፣ ሥራንና ሌሎች የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን በተመለከተ በርከት ያሉ ተግባራዊ ምክሮችን ይዟል። ምሳሌ 2:​6, 7 እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል። እርሱ ለቅኖች ድልን [“ተግባራዊ ጥበብን፣” NW ] ያከማቻል።” መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ አድርገህ በመጠቀም የማስተዋል ችሎታህ ‘መልካሙን ከክፉው እንዲለይ’ ልታሠለጥነው ትችላለህ።​—⁠ዕብራውያን 5:14

በተጨማሪም የአምላክ ቃል የሕይወትን ዓላማ እንድናውቅ ይረዳናል። (ዮሐንስ 17:3፤ የሐዋርያት ሥራ 17:26, 27) በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮች ምን ትርጉም እንዳላቸው ያብራራል። (ማቴዎስ 24:3, 7, 8, 14፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አምላክ ክፋትን ከምድር የሚያስወግደው እንዲሁም የሰው ልጆች ፍጹም ጤንነትና የዘላለም ሕይወት አግኝተው የሚኖሩት እንዴት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል።​—⁠ኢሳይያስ 33:24፤ ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 21:3, 4

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም ትክክለኛና እምነት የሚጣልበት የጥበብ ምንጭ መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ ተመልክተዋል። የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች በሁሉም እትሞች ላይ የሚወጣውን “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት” የሚለውን አምድ እንድትመረምር ይጋብዙሃል። እንዲህ ካደረግህ ለሕይወትህ መመሪያ ለማግኘት ከሁሉም የተሻለው ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨማሪ መረጃዎች ማግኘት ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ንቁ! መጽሔት “የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት” በሚለው አምዱ ሥር እነዚህንና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን አንድ በአንድ ይዞ ይወጣል።

^ አን.12 መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት መጻፉን ለማረጋገጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ —⁠የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

አምላክ የሚቀበለው ምን ዓይነት አምልኮ ነው?​—⁠ዮሐንስ 4:24

ከአምላክ ጥበብ ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብሃል?​—⁠ምሳሌ 2:1-4

▪ መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ ለሆነ መመሪያ ምንጭ ነው የምንለው ለምንድን ነው?​—⁠ዕብራውያን 5:14