በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሚካኤል አግሪኮላ—“ፈር ቀዳጅ የሆነ ሰው”

ሚካኤል አግሪኮላ—“ፈር ቀዳጅ የሆነ ሰው”

ሚካኤል አግሪኮላ​—“ፈር ቀዳጅ የሆነ ሰው”

ፊንላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

“የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በፊንላንዳውያን ባሕል፣ የሥነ ምግባር ደንቦችና አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ መጽሐፍ የለም።”​—⁠“ቢብሊያ 350—⁠የፊንላንድ መጽሐፍ ቅዱስና ባሕል”

በራስህ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉውን ወይም በከፊል ከ2, 000 በሚበልጡ ቋንቋዎች በመዘጋጀቱ ይህን መጽሐፍ የማግኘት ሰፊ አጋጣሚ አለህ። ይህ የሆነው ግን ያለ ምንም ልፋት አይደለም። በታሪክ ዘመናት ሁሉ በርካታ ወንዶችና ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስን ወደተለያዩ ቋንቋዎች ለመተርጎም ከባድ መሰናክሎችን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ሚካኤል አግሪኮላ ነው።

አግሪኮላ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፊንላንድ ቋንቋ የተረጎመ ምሑር ነው። የፊንላንዳውያን ባሕል አሁን የሚገኝበት ቦታ እንዲደርስ የእርሱ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች እርዳታ አበርክተዋል። ታዲያ ይህ ሰው ፈር ቀዳጅ ቢባል ምን ያስደንቃል!

አግሪኮላ የደቡባዊ ፊንላንድ ግዛት በሆነችውና ቶርስቢ ተብላ በምትጠራው መንደር በ1510 አካባቢ ተወለደ። አባቱ የእርሻ መሬት የነበረው ሲሆን ሚካኤልም አግሪኮላ የሚል ስያሜ ያገኘው ከዚሁ በመነሳት ነው፤ “ገበሬ” የሚል ትርጉም ያለው አግሪኮላ የተባለው ስም የላቲን ቃል ነው። አግሪኮላ ሁለት ቋንቋዎች በሚነገሩበት አካባቢ በማደጉ የስዊድንና የፊንላንድ ቋንቋዎችን እንደሚናገር ይገመታል። ከዚህም በተጨማሪ የቋንቋ ችሎታውን ለማሳደግ በቪቦርግ ከተማ በሚገኝ የላቲን ቋንቋ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚያም የፊንላንድ ካቶሊክ ጳጳስ ለሆኑት አቡነ ማርቲ ጸሐፊ ሆኖ በወቅቱ የፊንላንድ አስተዳደራዊ ማዕከል ወደ ነበረችው ወደ ቱርኩ ሄደ።

በዘመኑ የነበረው ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ

በአግሪኮላ ሕይወት ውስጥ በዚህ ወቅት በስካንዲኔቪያ አገሮች የነበረው ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። በካልማር በተደረገው ውል መሠረት የስካንዲኔቪያ አገሮች አንድ ላይ ለመዋሃድ የተስማሙ ቢሆንም ስዊድን ከዚህ ሕብረት ለመውጣት ትግል ጀምራ ነበር። በ1523 ጉስታቭ ቀዳማዊ የስዊድን ንጉሥ ሆኖ ዘውድ ጫነ። ይህ ደግሞ ፊንላንድ በስዊድኖች አገዛዝ ሥር ያለች አንድ ግዛት እንደመሆኗ መጠን የጎላ ተጽዕኖ ነበረው።

አዲሱ ንጉሥ ትኩረቱን ኃይሉን ወደ ማጠናከሩ ዞር አደረገ። ይህን እቅዱን ዳር ለማድረስም ከሰሜናዊ አውሮፓ ይነፍስ የነበረውን ሃይማኖታዊ የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንደ መሣሪያ በመጠቀም የሉተራንን እምነት የመንግሥት ሃይማኖት አደረገው። ካቶሊክን በመተው የሉተራንን ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ሲቀበል ከቫቲካን ጋር የነበረውን ግንኙነት አቋረጠ፣ የካቶሊክ ቀሳውስት የነበራቸውን ሥልጣን አሳጣቸው እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱን ሀብት ወረሰ። አሁንም ድረስ በስዊድንና በፊንላንድ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች የሉተራን ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው።

የፕሮቴስታንቶች አብይ ዓላማ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀርበው ስብከት በላቲን ቋንቋ ከሚሆን ይልቅ ሕዝቡ በሚናገረው ቋንቋ እንዲሆን ማድረግ ነበረ። ስለዚህ በ1526 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “አዲስ ኪዳን” በስዊድን ቋንቋ ታተመ። ይሁን እንጂ በፊንላንድ የፕሮቴስታንቶቹ እንቅስቃሴ ያሳደረው ተጽዕኖ ጠንካራ አልነበረም። ስለዚህም በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስን በፊንላንድ ቋንቋ መተርጎም ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም። ለምን?

“ከባድና አሰልቺ” ሥራ

ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በ16ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ከተጻፉት በጣም ጥቂት የካቶሊክ ጸሎቶች በቀር በፊንላንድ ቋንቋ የተጻፈ ምንም ዓይነት ሥነ ጽሑፍ አለመኖሩ ነው። ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ፊንላንድ ቋንቋ የመተርጎሙ ሥራ በንግግር የሚጠቀሙባቸው ብዙ ቃላት በጽሑፍ መልክ እንዲሰፍሩ ፊደላትን መቅረጽ እንዲሁም አዲስ ቃላትንና ሐረጎችን መፈልሰፍ ይጠይቅ ነበር። ይህም የሚከናወነው ቋንቋውን አስመልክቶ የተዘጋጀ መርጃ መጽሐፍ ሳይኖር ነው። ቢሆንም አግሪኮላ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ቆርጦ ተነሳ!

በ1536 የፊንላንድ ካቶሊክ ጳጳስ የሆኑት ስካይት፣ አግሪኮላን ተጨማሪ ሃይማኖታዊ ትምህርት እንዲቀስም እንዲሁም ቋንቋ እንዲያጠና ወደ ዊትንበርግ፣ ጀርመን ላኩት። ከ20 ዓመታት በፊት፣ ሉተር 95 የተቃውሞ ሐሳቦችን ጽፎ በዚሁ ከተማ በሚገኝ በግንብ በተሠራ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ በምስማር እንደሰቀለ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

አግሪኮላ በዊትንበርግ ቆይታው ከተላከበት ዓላማ የበለጠ ነገር ሠርቷል። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፊንላንድ ቋንቋ የመተርጎሙን ከባድ ሥራ ተያያዘው። በ1537 ለስዊድን ንጉሥ “አምላክ እያደረግሁት ባለሁት ጥናት እስከረዳኝ ድረስ ቀደም ብዬ የጀመርኩትን አዲስ ኪዳንን ወደ ፊንላንድ ሕዝብ ቋንቋ የመተርጎም ሥራ ለመቀጠል እጥራለሁ” በማለት ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ወደ ፊንላንድ ሲመለስ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆኖ መሥራት ቢጀምርም የትርጉሙን ሥራ ግን ገፋበት።

ከእርሱ ቀደም እንደነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ሁሉ የትርጉም ሥራው ለአግሪኮላም ከባድ ነበር። ሉተር እንኳን በአድናቆት “ዕብራውያን ጸሐፍትን ጀርመንኛ እንዲናገሩ ማድረግ እንዴት ያለ ከባድና አሰልቺ ሥራ ነው” ብሏል። አግሪኮላ የሌሎች ሰዎችን የትርጉም ሥራዎች መመልከቱ ይጠቅመው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ለእርሱ በዋነኝነት መሰናክል የሆነበት የፊንላንድ ቋንቋ ነበር። ምክንያቱም ይህ ቋንቋ በጽሑፍ አልሠፈረም ነበር።

ስለዚህም አግሪኮላ ምንም ዓይነት ንድፍ እንዲሁም በቂና አንድ ላይ የተሰባሰቡ የግንባታ ቁሳቁሶች ሳይኖሩት ቤት የሠራ ያህል ነው። ሥራውን ያከናወነው እንዴት አድርጎ ነው? አግሪኮላ በፊንላንድ ከሚነገሩ የተለያዩ ቀበሌኛዎች ቃላት መርጦ ካሰባሰበ በኋላ የአካባቢው ማኅበረሰብ በሚጠራቸው መንገድ በጽሑፍ አሰፈራቸው። በፊንላንድ ቋንቋ “መንግሥት፣” “ግብዝ፣” “ሥነ ጽሑፍ፣” “የጦር ሠራዊት፣” “ቅርጽ” እና “ጸሐፊ” የመሳሰሉትን ቃላት የፈለሰፈው እርሱ ነው። ጥምር ቃላትን እንዲሁም ከአንድ መሠረታዊ ቃል የተወሰዱ አንዳንድ ቃላትን ከመፍጠሩም በላይ ከተለያዩ ቋንቋዎች በተለይ ከስዊድን ቋንቋ ቃላትን ወስዷል። ከእነዚህ ቃላት መካከል እንከሊ (መልአክ)፣ ሂስቶርያ (ታሪክ)፣ ላምፑ (መብራት)፣ ማርቱየሪ (ሰማዕት) እና ፓልሙ (የዘንባባ ዛፍ) ይገኙበታል።

የአምላክን ቃል ለአገሬው ሰው ማድረስ

በመጨረሻም በ1548 የአግሪኮላ ሥራ የመጀመሪያ ክፍል ይኸውም ሴ ዩስ ቴስታሜንቲ (አዲስ ኪዳን) ታትሞ ወጣ። አንዳንዶች ይህ ትርጉም የተጠናቀቀው ከታተመበት ጊዜ አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ እንደሆነና በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንደዘገየ ያምናሉ። ምናልባትም አግሪኮላ አብዛኛውን የማሳተሚያ ገንዘብ የከፈለው ራሱ ሊሆን ይችላል።

ከሦስት ዓመት በኋላ ዳቪዲን ሳልታሪ (የዳዊት መዝሙር) የወጣ ሲሆን አግሪኮላ ይህንን መጽሐፍ የተረጎመው ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመተጋገዝ ሳይሆን አይቀርም። ሙሴ ከጻፋቸውና በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከሚገኙት የነቢያት መጻሕፍት መካከል አንዳንዶቹን በመተርጎም ደረጃም ግንባር ቀደም ነበር።

አግሪኮላ ያለበትን የአቅም ገደብ አምኖ በመቀበል በትሕትና እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ክርስቲያኖችም ሆናችሁ ፈሪሃ አምላክ ያላችሁ ወይም ይህን ቅዱስ መጽሐፍ የምታነቡ ሁሉ፣ ይህ መጽሐፍ በትርጉም ሥራ ምንም ተሞክሮ በሌለው ሰው የተተረጎመ እንደመሆኑ መጠን አንዳንድ ስህተቶች፣ እንግዳ የሆኑ ነገሮች፣ የማያስደስቱ ወይም አዳዲስ አባባሎችን ብታገኙ እባካችሁ አትዘኑብኝ።” የአግሪኮላ የትርጉም ሥራ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም ተራው ሰው በገዛ ቋንቋው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲደርሰው ለማድረግ ላሳየው ከፍተኛ ቅንዓት ምስጋና ሊቸረው ይገባል።

አግሪኮላ ትቶት ያለፈው ቅርስ

በኋላ ላይ የሉተራን ሃይማኖት ተከታይና የቱርኩ ጳጳስ የሆነው አግሪኮላ፣ በ1557 መጀመሪያ አካባቢ በስዊድንና በሩሲያ መካከል የነበረውን የድንበር ውዝግብ እንዲፈታ ወደ ሞስኮ ተልኮ በነበረው የልዑካን ቡድን ውስጥ ነበረበት። ተልእኮው የተሳካ ነበር። ይሁን እንጂ በመልስ ጉዞው ወቅት አግሪኮላ ያልታሰበ ሕመም አጋጠመውና በጉዞ ላይ እያለ በ47 ዓመቱ በሞት አንቀላፋ።

አንጻራዊ በሆነ መልኩ ስናየው አጭር በሆነው የሕይወት ዘመኑ በጠቅላላ 2, 400 ገጾች ያሏቸው በፊንላንድ ቋንቋ የተዘጋጁ አሥር ጽሑፎችን ለሕትመት አብቅቷል። እስካሁን ድረስ ብዙዎች ይህ “ፈር ቀዳጅ የሆነ ሰው” ለፊንላንዳውያን ባሕል እድገት ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ያምናሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፊንላንዳውያን ቋንቋም ሆነ ኅብረተሰቡ በሥነ ጥበብና በሳይንስ መስክ ትልቅ እመርታ አሳይቷል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ሚካኤል አግሪኮላ ለፊንላንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የአምላክ ቃል ብርሃን እንዲበራላቸው በማድረግ ጮራ ፈንጣቂ መሆን ችሏል። አግሪኮላ ከሞተ በኋላ ለእርሱ መታሰቢያነት በላቲን ቋንቋ በተዘጋጀ ጽሑፍ ላይ ሥራዎቹን በተመለከተ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል:- “ትቶት ያለፈው ቅርስ ተራ የኑዛዜ ወረቀት አይደለም። በዚህ ፈንታ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ ፊንላንድ ቋንቋ በመተርጎም ታላቅ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ሥራ አከናውኗል።”

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የፊንላንዳውያን መጽሐፍ ቅዱስ

በ1642 የፊንላንድ የመጀመሪያው የተሟላ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመ ሲሆን ይህ ትርጉም በአብዛኛው የተመሠረተው በሚካኤል አግሪኮላ ሥራዎች ላይ ነው። ከጊዜ በኋላም ይህ ትርጉም የፊንላንድ ሉተራን ቤተክርስቲያን ሕጋዊ መጽሐፍ ቅዱስ ሆነ። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱም መጽሐፍ ቅዱሱ አንዳንድ ጥቃቅን ማስተካከያዎች ቢደረጉበትም እስከ 1938 ግን እንዳለ ቆይቷል። በቅርብ ማሻሻያ የተደረገበት እትም የወጣው በ1992 ነው።

ከዚህኛው ሌላ በፊንላንድ ቋንቋ የሚገኘው ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ብቻ ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው በ1995 ነው። ከሃያ ዓመት በፊት ማለትም በ1975 ምሥክሮቹ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉምን አዘጋጅተው ነበር። በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ላይ የመጀመሪያው ቅጂ የሚያስተላልፈውን ሐሳብ በትክክል ለማስቀመጥ የሚቻለው ሁሉ ጥረት ተደርጓል። እስከ ዛሬ ድረስ 130,000,000 ያህል ቅጂዎች ታትመዋል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚካኤል አግሪኮላና የመጀመሪያው የፊንላንድ መጽሐፍ ቅዱስ። በ1910 የተዘጋጀ ፖስት ካርድ

[ምንጭ]

National Board of Antiquities/Ritva Bäckman

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአግሪኮላ “አዲስ ኪዳን”

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

National Board of Antiquities