በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምንድን ነው?
“የእጄን አንጓዎች ክፉኛ ስለቆረጥኳቸው መሰፋት አስፈልጎኝ ነበር። በወቅቱ ለሐኪሙ እጄን በአምፑል እንደቆረጥኩ ነግሬው ነበር፤ ይህ እውነት ቢሆንም ሆን ብዬ እንዳደረግሁት ግን አልገለጽሁለትም።”— ሳሻ፣ 23 ዓመት
“ወላጆቼ የቆረጥኳቸውን የሰውነቴን ክፍሎች ተመልክተው ነበር፤ ሆኖም እነርሱ ያዩት ብዙም ያልጎዳኋቸውንና የተቧጨሩ የሚመስሉትን ብቻ ነው። . . . አንዳንድ ጊዜ አይተው ቢጠይቁኝም እንኳን ምን እንደሆነ ስለማይገባቸው አንድ ሰበብ ፈጥሬ እነግራቸዋለሁ። . . . እንዲያውቁብኝ አልፈልግም።”— ኤርየል፣ 13 ዓመት
“ከ11 ዓመቴ ጀምሮ ሰውነቴ ላይ ጉዳት ሳደርስ ኖሬአለሁ። አምላክ ለሰው አካል አክብሮት እንዳለው አውቃለሁ፤ ይህን ማወቄ ግን ሰውነቴ ላይ ጉዳት ከማድረስ እንድቆጠብ አላደረገኝም።”— ጄኒፈር፣ 20 ዓመት
ምናልባት እንደ ሳሻ፣ ኤርየል ወይም ጄኒፈር * ያለ ሰው ታውቂ ይሆናል። ይህ ሰው የትምህርት ቤት ጓደኛሽ፣ እህትሽ አሊያም ወንድምሽ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንቺ ራስሽ ሰውነትሽ ላይ ጉዳት ታደርሺ ይሆናል። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰውነታቸውን በመቁረጥ፣ በማቃጠል እንዲሁም አካላቸውን እየደበደቡ ሰንበር እንዲወጣባቸው በማድረግ፣ ቆዳቸውን በመቧጨር ወይም ደግሞ እነዚህን በመሰሉ ሌሎች መንገዶች ሆነ ብለው ራሳቸውን እንደሚጎዱ ይገመታል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። *
እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን የሚጎዱት በእርግጥ ሆን ብለው ነው? ቀደም ሲል ብዙዎች እንዲህ ያለውን ድርጊት ለየት ካለ ፋሽን ወይም ከአጉል አምልኮ ጋር ያያይዙት ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስን በተመለከተ ያለው ግንዛቤ በአስገራሚ ሁኔታ እያደገ መጥቷል፤ ይህ ድርጊት የራስን ሰውነት መቁረጥ ወይም መተልተልን ይጨምራል። ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ቁጥርም እንዲሁ ጨምሯል። ማይክል ሆለንደር የተባሉ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ የሕክምና ማዕከል ዲሬክተር “ክሊኒክ ውስጥ የሚሠሩ ሐኪሞች ሁሉ ችግሩ እየጨመረ መሆኑን ይናገራሉ” በማለት ገልጸዋል።
በራስ ሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ በአብዛኛው ለሞት ባይዳርግም አደገኛ ነው። ለምሳሌ ያህል ቤት የተባለችውን ሴት እንመልከት። “ሰውነቴ ላይ ጉዳት የማደርሰው በምላጭ ነው። ሁለት ጊዜ ሆስፒታል ገብቻለሁ። እንዲያውም
አንድ ጊዜ ሰውነቴን በጣም ስለቆረጥኩት ድንገተኛ ክፍል መግባት አስፈልጎኝ ነበር” ብላለች። በዚህ ችግር እንደሚሠቃዩት በርካታ ሰዎች ሁሉ ቤት ትልቅ ሰው ከሆነች በኋላም ሰውነቷ ላይ ጉዳት ማድረሷን አላቆመችም። “ይህን ማድረግ የጀመርኩት በ15 ዓመቴ ነው፤ አሁን 30 ዓመት ሆኖኛል” በማለት ተናግራለች።በራስሽ ሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስ ችግር አለብሽ? ወይም ደግሞ የዚህ ችግር ሰለባ የሆነ የምታውቂው ሰው አለ? ከሆነ ተስፋ አትቁረጪ። ምክንያቱም እርዳታ ማግኘት ይቻላል። በሚቀጥለው የንቁ! መጽሔት እትም በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የማድረስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች እንዴት መርዳት እንደሚቻል እንመለከታለን። * በመጀመሪያ ግን ይህ ችግር ስላለባቸው ሰዎችና እንዲህ የሚያደርጉት ለምን እንደሆነ ማንሳቱ ተገቢ ነው።
የችግሩ ተጠቂዎች የተለያየ ምክንያት አላቸው
በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወይም አካላቸውን የሚቆርጡ ሰዎችን በአንድ ጎራ መፈረጅ ያስቸግራል። አንዳንዶቹ ችግር ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የተደላደለ ኑሮ ካለበትና ደስተኛ ከሆነ ቤተሰብ የወጡ ናቸው። አንዳንዶቹ በትምህርታቸው አጥጋቢ ውጤት የማያመጡ ቢሆንም አብዛኞቹ ጎበዝ ተማሪዎች ናቸው። አንዳንድ ሰዎች መከራና ሥቃይ እየተፈራረቀባቸውም እንኳ ችግር ያለባቸው እንደማይመስሉ ሁሉ፣ የገዛ አካላቸውን የሚጎዱ ሰዎችም ብዙውን ጊዜ ችግር እንዳለባቸው የሚጠቁም ምንም ነገር አይታይባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ “በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል” ይላል።—ምሳሌ 14:13
ከዚህም በላይ በአካላቸው ላይ የሚያደርሱት የጉዳት መጠን የአንዱ ከሌላው ይለያል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጥናት እንዳሳየው አንዳንድ ግለሰቦች ሰውነታቸውን የሚቆርጡት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአማካይ በቀን ሁለት ጊዜ እንዲህ ያደርጋሉ። የሚገርመው ነገር በአንድ ወቅት ይታሰብ ከነበረው በተቃራኒ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በርካታ ወንዶች አሉ። ያም ሆኖ ችግሩ በስፋት የሚታየው በጉርምስና ዕድሜ በሚገኙ ልጃገረዶች ላይ ነው። *
በገዛ አካላቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉበት የተለያየ ምክንያት ይኑራቸው እንጂ ተመሳሳይ የሚያደርጓቸው አንዳንድ ባሕርያት አሉ። በወጣቶች ላይ የሚያተኩር አንድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች በአብዛኛው አቅም እንደሌላቸው ይሰማቸዋል፣ ለሌሎች ስሜታቸውን አውጥተው መግለጽ ይቸግራቸዋል፣ ብቸኝነት ያጠቃቸዋል ወይም ሰው ያገለላቸው ይመስላቸዋል፣ ፍርሃት ይሰማቸዋል እንዲሁም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው መመልከት ይቀናቸዋል።”
አንዳንዶች፣ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ፍርሃትና ስጋት ያለባቸው ወጣቶች ሁሉ ተመሳሳይ ስሜት ሊያድርባቸው እንደሚችል ይናገሩ ይሆናል። ነገር ግን ሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርስ ሴት ያለባት ትግል ይበልጥ ከባድ ነው። አንዲት ሴት ጭንቀቷን በቃላት መግለጽና ለምስጢረኛዋ መንገር ካዳገታት፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ያለባት ጫና አሊያም ደግሞ በቤቷ ውስጥ የሚከሰት አለመግባባት ከአቅሟ በላይ ይሆንባታል። በዚህ ጊዜ ችግሯ መፍትሔ አልባ እንደሆነና የምታናግረው ሰው እንደሌለ ታስባለች። እንዲሁም ጭንቀቷን መቋቋም እንደማትችል ይሰማታል። በመጨረሻ አንድ ነገር ብልጭ ይልላታል፤ አካሏ ላይ ጉዳት በማድረስ ከስሜት ሥቃይዋ ጥቂት እፎይታ እንደምታገኝና ቢያንስ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ኑሮዋን በሰላም መምራት እንደምትችል ይታያታል።
ሰውነታቸውን የሚቆርጡ ሰዎች ከስሜት ሥቃያቸው ለመገላገል ይህን መንገድ የሚመርጡት ለምንድን ነው? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በአንድ ሐኪም ቢሮ ውስጥ መርፌ ለመወጋት በምትዘጋጅበት ወቅት ምን እንደሚከሰት ወደ አእምሮህ አምጣ። ሐኪሙ መውጋት ሲጀምር የመርፌው ሕመም እንዳይሰማህ ለማድረግ ስትል ሰውነትህን ቆንጥጠህ ወይም በጥፍርህ ወግተህ አታውቅም? መጠኑ ከፍተኛ ይሁን እንጂ በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርስ ሴትም የምታደርገው ነገር ተመሳሳይ ነው። ይህ ድርጊቷ ሐሳቧ በስሜት ሥቃይዋ ላይ እንዳያተኩርና እፎይታ እንድታገኝ ያደርጋታል። የስሜት ጭንቀቱ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስ የሚለው አካላዊ ሥቃይ ይመረጣል። በሰውነቷ ላይ ጉዳት የምታደርስ አንዲት ሴት የገዛ
አካልን መቁረጥን “ለፍርሃቴ ያገኘሁት መድኃኒት” ብላ የጠራችው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም።“ጭንቀትን ለመቋቋም የሚያስችል ዘዴ”
ስለ ችግሩ የማያውቁ ሰዎች፣ በገዛ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ የራስን ሕይወት የማጥፋት ሙከራ ሊመስላቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን ሁኔታው ይህ አይደለም። በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች የሚታተም መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት ሳብሪና ሶሊን ዋይል “በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ሰዎች የሚሞክሩት ሥቃያቸውን ለማስታገሥ እንጂ ሕይወታቸውን ለማጥፋት አይደለም” በማለት ጽፈዋል። ስለዚህ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ በራስ ሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስን “ሕይወት ማጥፊያ ዘዴ ሳይሆን ‘ሕይወት አድን መንሳፈፊያ’” እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። ድርጊቱንም “ጭንቀትን ለመቋቋም የሚያስችል ዘዴ” ብሎ ሰይሞታል። ምን ዓይነት ጭንቀት?
በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አብዛኞቹ ሰዎች በልጅነታቸው በተፈጸመባቸው በደልና ችላ በመባላቸው ወይም እነዚህን በመሳሰሉ ምክንያቶች አንድ ዓይነት የስሜት መቃወስ እንደነበረባቸው ተረጋግጧል። በቤተሰብ መካከል የሚፈጠር ግጭት ወይም የወላጆች ጠጪ መሆን ሌላው የችግሩ መንስኤ ነው። አንዳንዶች ደግሞ የችግራቸው መነሾ የአእምሮ ሕመም ነው።
ተጨማሪ ችግሮችም ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ሤራ ከራሷ ፍጽምናን በመጠበቅ ራስን የመውቀስ ችግር እንደነበረባት ተናግራለች። ከባድ ስህተት ፈጽማ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሚረዷት ጊዜም እንኳን በየዕለቱ በምትፈጽማቸው ስህተቶች ይህ ነው የማይባል የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማት ነበር። ሤራ እንዲህ ብላለች:- “በራሴ ላይ ‘ጥብቅ መሆን’ እንዳለብኝ አስብ ነበር፤ ራሴን የምገሥጸው በሰውነቴ ላይ ጉዳት በማድረስ ነበር። ‘ራሴን የምገሥጽበት’ መንገድ ፀጉሬን መንጨትን፣ የእጄን አንጓና ክንዶቼን መቁረጥን እንዲሁም ሰውነቴ ትልልቅ ሰንበር እስኪያወጣ ድረስ ራሴን መደብደብን ይጨምር ነበር፤ በተጨማሪም የፈላ ውኃ ውስጥ እጄን መክተትን፣ በቅዝቃዜ ወቅት ካፖርት ሳልለብስ ከቤት ውጪ መቀመጥንና ምንም ምግብ ሳልበላ መዋልን በመሳሰሉ መንገዶች ራሴን እቀጣ ነበር።”
ሤራ የገዛ ሰውነቷን መጉዳቷ ለራሷ የነበራትን ከባድ ጥላቻ የሚያንጸባርቅ ነው። እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ ለፈጸምኳቸው ስህተቶች ይቅርታ እንዳደረገልኝ ባውቅም እንዲህ እንዲያደርግ የማልፈልግባቸው ጊዜያት ነበሩ። መሠቃየት የምፈልገው ራሴን በጣም እጠላ ስለነበር ነው። ይሖዋ፣ ሕዝበ ክርስትና እንደምታምንበት እሳታማ ሲኦል ያለ የሰዎች ማሠቃያ ቦታ በሐሳቡ እንኳ እንደሌለ ባውቅም ለእኔ ብቻ የሚሆን አንድ እንዲያዘጋጅ እመኝ ነበር።”
“የሚያስጨንቅ ጊዜ”
አንዳንዶች፣ እንዲህ የመሰሉ አእምሮን የሚረብሹ ድርጊቶች ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ መታየት የጀመሩት ለምንድን ነው ብለው ይጠይቁ ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን ያለነው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ እንደሆነ ያውቃሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በመሆኑም ወጣቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ የሰዎች ባሕርይ በቃላት ለመግለጽ በሚያዳግት መልኩ እየተቀየረ መሆኑን ሲሰሙ አይደነቁም።
መጽሐፍ ቅዱስ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም ) አስቸጋሪ የሆነው የጉርምስና ዕድሜ አንዳንድ ጊዜ አሳዛኝ ከሆነ የሕይወት ገጠመኝ ጋር ተዳምሮ፣ ሰዎች በገዛ አካላቸው ላይ ጉዳት ማድረስን ጨምሮ ሌሎች ጎጂ ድርጊቶችን የመፈጸም ልማድ እንዲያዳብሩ ያደርጋቸዋል። ብቸኝነት የሚሰማትና የምታዋየው ሰው እንደሌለ የምታስብ አንዲት ወጣት እፎይታ ለማግኘት ሰውነቷን መቁረጥ ትመርጥ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ድርጊት እፎይታ ቢሰጥ እንኳ ለአጭር ጊዜ ነው። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ችግሮች ተመልሰው መምጣታቸውና በገዛ ሰውነት ላይ በድጋሚ ጉዳት ማድረስ አይቀርም።
በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎች በአብዛኛው ይህን ድርጊታቸውን ማቆም ቢፈልጉም በጣም ይከብዳቸዋል። አንዳንዶች ይህን ልማዳቸውን ማቆም የቻሉት እንዴት ነው? ይህ ጉዳይ በየካቲት 2006 ንቁ! መጽሔት ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . . ” አምድ ሥር በሚወጣው “የገዛ አካሌን ከመጉዳት መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?” በሚለው ርዕስ ውስጥ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.6 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.6 በገዛ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ ሲባል ሰውነትን ከመበሳት ወይም ከመነቀስ ይለያል። ሰዎች ሰውነታቸውን የሚነቀሱት ወይም የሚበሱት ለፋሽን ብለው እንጂ ስሜታቸው አስገድዷቸው አይደለም። የነሐሴ 2000 ንቁ! መጽሔት ገጽ 20 እና 21ን ተመልከት።
^ አን.9 ዘሌዋውያን 19:28 “ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ” ይላል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ አረማዊ ልማድ ይከናወን የነበረው፣ ሙታንን ይቆጣጠራሉ ተብለው የሚታመኑ አማልክትን ለማስደሰት ተብሎ ሲሆን ይህ ድርጊት በዚህ ርዕስ ውስጥ ከምንነጋገርበት ጉዳይ የተለየ ነው።
^ አን.12 በገዛ ሰውነት ላይ ጉዳት ስለማድረስ ስንጠቅስ በሴት ጾታ የተጠቀምነው ለዚህ ነው። ነገር ግን በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሰው መሠረታዊ ሐሳብ ለሁለቱም ጾታዎች ይሠራል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ አንዳንድ ወጣቶች በሰውነታቸው ላይ ጉዳት ማድረስን የሚመርጡት ለምንድን ነው?
▪ ይህንን ርዕስ ካነበብሽ በኋላ ወደ አእምሮሽ የመጡ ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ጥሩ መንገዶች አሉ?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሣቅ ጊዜ እንኳ ልብ ይተክዛል።”—ምሳሌ 14:13
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህ ሰዎች የሚሞክሩት ሥቃያቸውን ለማስታገሥ እንጂ ሕይወታቸውን ለማጥፋት አይደለም”
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1