በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ የሆነው ቀይ የደም ሕዋስ

አስደናቂ የሆነው ቀይ የደም ሕዋስ

አስደናቂ የሆነው ቀይ የደም ሕዋስ

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ደማችን ቀይ እንዲሆን የሚያደርገውና በደም ሥራችን ውስጥ በብዛት የሚገኘው ሕዋስ ቀይ የደም ሕዋስ በመባል ይታወቃል። በአንዲት ጠብታ ደም ውስጥ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቀይ የደም ሕዋሶች ይገኛሉ። ይህ ሕዋስ በአጉሊ መነጽር ሲታይ መሐሉ ክፍት ሳይሆን ድፍን ሆኖ ትንሽ ሰርጎድ ያለ ዶናት ወይም ቦምቦሊኖ ይመስላል። በእያንዳንዱ ሕዋስ ውስጥ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሄሞግሎቢን ሞለኪውሎች ይገኛሉ። እያንዳንዱ የሄሞግሎቢን ሞለኪውል ደግሞ ማራኪ የሆነ ክብ ቅርጽ ያለው ሲሆን 10, 000 ከሚያህሉ የሃይድሮጅን፣ የካርበን፣ የናይትሮጅን፣ የኦክስጅንና የሰልፈር አተሞች እንዲሁም ደም ኦክስጅን የመሸከም ችሎታ እንዲኖረው ከሚያደርጉ አራት ከባድ የብረት አተሞች የተሠራ ነው። ሄሞግሎቢን ካርበን ዳይኦክሳይድ ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ወደ ሳንባ የሚያደርገውን ጉዞ ያፋጥንለታል፤ ከዚያም ሳንባ ወደ ውጪ ያስወጣዋል።

የቀይ የደም ሕዋስ ሌላው አስደናቂ ክፍል ደግሞ ሕዋሰ ክርታስ (ሴል ሜምብሬን) ነው። ይህ አስደናቂ ሽፋን ሕዋሱ የተለያዩ ዓይነት ቀጫጭን ቅርጾችን እንዲይዝ ያስችለዋል። ስለሆነም ቀይ የደም ሕዋሶችህ በጣም ጠባብ በሆኑ የደም ሥሮችህ ውስጥ እንኳ ሳይቀር ማለፍና ማንኛውም የሰውነትህ ክፍል ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ይችላሉ።

ቀይ የደም ሕዋሶች የሚመረቱት በአጥንቶችህ መቅኒ ውስጥ ነው። አዲስ የተመረተው ሕዋስ አንዴ ወደ ደም ሥርህ ከገባ በኋላ በልብህና በሌሎች የአካል ክፍሎችህ ውስጥ ከ100, 000 ጊዜ በላይ ሊዘዋወር ይችላል። ከሌሎች ሕዋሶች በተለየ መልኩ ቀይ የደም ሕዋስ ኒዩክለስ የለውም። ይህም ኦክስጅንን ለመሸከም የሚያስችል ሰፋ ያለ ቦታ እንዲኖረውና ክብደቱም ቀላል እንዲሆን ያደርገዋል። ልብህ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ቀይ የደም ሕዋሶች በቀላሉ በሰውነትህ ውስጥ ማሰራጨት የሚችለው ለዚህ ነው። ሆኖም ኒዩክለስ ስለሌላቸው የውስጥ ክፍሎቻቸውን ማደስ አይችሉም። በዚህም ምክንያት ቀይ የደም ሕዋሶችህ ከ120 ቀናት ገደማ በኋላ መዳከምና የመለጠጥ ችሎታቸውን ማጣት ይጀምራሉ። ትላልቅ የሆኑትና ፋጎሳይት ወይም “ሴል በሊታዎች” በመባል የሚታወቁት ነጭ የደም ሕዋሶች እነዚህን ያረጁ ሕዋሶች ይበሏቸውና የብረት አተሞችን ያመነጫሉ። በቁጥር አነስተኛ የሆኑት እነዚህ የብረት አተሞች ከማጓጓዣ ሞለኪውሎች ጋር በመጣበቅ አዳዲስ ቀይ የደም ሕዋሶች እንዲሠሩባቸው ወደ መቅኒ ይወሰዳሉ። በእያንዳንዷ ሴኮንድ መቅኒህ ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ አዳዲስ ቀይ የደም ሕዋሶችን አምርቶ ወደ ደም ሥርህ ይልካል!

በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ቀይ የደም ሕዋሶችህ በድንገት ሥራቸውን ቢያቆሙ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ትሞታለህ። ደስታ አግኝተን በሕይወት እንድንኖር ላስቻለን ለዚህ ድንቅ የፍጥረት ሥራው ይሖዋ አምላክን እጅግ ልናመሰግነው ይገባናል! መዝሙራዊው “እግዚአብሔር ሆይ፤ መረመርኸኝ፤ ደግሞም ዐወቅኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች” በማለት በተናገረው ሐሳብ እንደምትስማማ አያጠራጥርም።​—⁠መዝሙር 139:​1, 14

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቀይ የደም ሕዋስ

ሕዋሰ ክርታስ

ሄሞግሎቢን

(ጎልቶ ሲታይ)

ኦክስጅን