በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነቴ የያዘኝን ከባድ በሽታ እንድቋቋም ረድቶኛል

እምነቴ የያዘኝን ከባድ በሽታ እንድቋቋም ረድቶኛል

እምነቴ የያዘኝን ከባድ በሽታ እንድቋቋም ረድቶኛል

ጄሰን ስቱዋርት እንደተናገረው

“በጣም አዝናለሁ ሚስተር ስቱዋርት፤ አንዳንድ ጊዜ ሉ ጌሪግ እየተባለ የሚጠራው ኤማያትሮፊክ ላተራል ስክለሮስስ ወይም ኤ ኤል ኤስ ይዞሃል።” * ከዚያም ዶክተሩ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ መንቀሳቀስም ሆነ መናገር እንደሚሳነኝ እንዲሁም ውሎ አድሮ በሽታው ለሞት እንደሚዳርገኝ በመግለጽ ወደፊት የሚጠብቀኝን አሳዛኝ ሁኔታ ነገረኝ። “በሕይወት የምቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?” በማለት ጠየቅኩት። እርሱም “ምናልባት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት” ሲል መለሰልኝ። በዚህ ጊዜ ገና 20 ዓመቴ ነበር። የነገረኝ ነገር አሳዛኝ ቢሆንም በብዙ መንገድ እንደተባረክሁ ያህል ሆኖ ተሰማኝ። እንዲህ ሊሰማኝ የቻለው ለምን እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

መጋቢት 2, 1978 በካሊፎርኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ በምትገኘው ሬድዉድ በምትባል ከተማ ተወ​ለድኩ። ጂም እና ካቲ ስቱዋርት የተባሉት ወላጆቼ ከወለዷቸው አራት ልጆች መካከል እኔ ሦስተኛ ልጅ ነኝ። ለአምላክ ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው ወላጆቻችን እኔን፣ ማቲውን፣ ጄኒፈርንና ጆናተንን ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ አክብሮት እንዲኖረን አድርገው አሳድገውናል።

ከቤት ወደ ቤት ማገልገል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የቤተሰባችን ልማዶች እንደነበሩ አስታውሳለሁ። እንዲህ ባለ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ ማደጌ በይሖዋ አምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረኝ አድርጎኛል። ሆኖም እምነቴ በምን መልኩ እንደሚፈተን አልተገነዘብኩም ነበር።

የልጅነት ሕልሜ እውን ሆነ

በ1985 አባቴ ቤቴል የሚባለውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት እንድንጎበኝ መላ ቤተሰባችንን ይዞ ወደ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ሄደ። በጊዜው ገና የሰባት ዓመት ልጅ የነበርኩ ቢሆንም ቤቴልን ከሌሎች ቦታዎች ልዩ የሚያደርገው አንድ ነገር እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር። በዚያ እያንዳንዱ ሰው ሥራውን በደስታ ያከናውናል። ይህን ስመለከት ‘ሳድግ ቤቴል ገብቼ መጽሐፍ ቅዱሶችን በማተም ይሖዋን አገለግላለሁ’ ብዬ አሰብኩ።

በጥቅምት 18, 1992 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ በድጋሚ ቤቴልን እንድጎበኝ ይዞኝ ሄደ። በዚህ ወቅት ግን ትልቅ ልጅ ሆኜ ስለነበር በዚያ የሚከናወነው ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብ አላዳገተኝም። ወደ ቤት ስመለስ ቤቴል ለመግባት ያለኝን ምኞት ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጬ ተነሳሁ።

በመስከረም 1996 የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ቤቴል ለመግባት ያለኝን ግብ ከዳር ለማድረስ ስል ራሴን በመንፈሳዊ ነገሮች አስጠመድኩ። በየዕለቱ የማደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤንና የግል ጥናቴን ይበልጥ አጠናከርኩ። ማታ ማታ በካሴት የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮችን የማዳመጥ ልማድ ነበረኝ። ከእነዚህ ንግግሮች ውስጥ አንዳንዶቹ በመጪው ገነትና በትንሣኤ ተስፋ ላይ የጸና እምነት ኖሯቸው ሞትን የተጋፈጡ ክርስቲያኖችን ተሞክሮ ያወሱ ነበር። (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:​3, 4) ብዙም ሳይቆይ ሁሉንም ንግግሮች በቃሌ ያዝኳቸው። ይሁንና እነዚህ የሚያንጹ ታሪኮች ብዙም ሳይቆይ ለገጠመኝ ሁኔታ ምን ያህል እንደሚጠቅሙኝ አልተገነዘብኩም ነበር።

ሐምሌ 11, 1998 ከብሩክሊን የተላከ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው ቤቴል ገብቼ እንድሠራ የሚጋብዝ ነበር። ከአንድ ወር በኋላ ቤቴል ገባሁ። ከዚያም ወደ ጉባኤዎች የሚላኩ መጻሕፍት በሚዘጋጁበት ጥረዛ ክፍል ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚህ ጊዜ የልጅነት ሕልሜ እውን ሆነ። እንደተመኘሁት ቤቴል ገብቼ ‘መጽሐፍ ቅዱሶችን በማተም ይሖዋን ማገልገል’ ቻልኩ!

የበሽታው ምልክት መታየት ጀመረ

ቤቴል ከመግባቴ አንድ ወር ገደማ ቀደም ብሎ የቀኝ እጄን አመልካች ጣት ሙሉ በሙሉ መዘርጋት እንዳቃተኝ አስተውዬ ነበር። እንዲሁም በዚሁ ጊዜ አካባቢ የመዋኛ ገንዳ የማጽዳት ሥራዬን ሳከናውን ቶሎ ይደክመኝ ጀመር። በዚህ ጊዜ እየሰነፍኩ እንዳለሁ ተሰምቶኝ ነበር። የሚገርመው ከዚያ በፊት የበለጠ ጉልበት የሚጠይቁ ከባድ ሥራዎችን እንኳ ሳይቀር ያለምንም ችግር ማከናወን እችል ነበር።

ቤቴል ከገባሁ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሕመሙ ምልክቶች እየተባባሱ መጡ። በደረጃ ላይ ሽቅብ ቁልቁል እየተሯሯጡ በትጋት ከሚሠሩት ጠንካራ ወጣቶች እኩል መሥራት አልሆነልኝም። በጽሑፍ ጥረዛ ክፍሉ ውስጥ የተሰጠኝ ሥራ ገና ያልተጠረዙ የመጽሐፍ ክፍሎችን ማንሳትንም ይጨምር ነበር። ሆኖም ይህን ሳደርግ ወዲያውኑ ይደክመኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የቀኝ እጄ ይጎብጥ ጀመር። ከዚህም በላይ አውራ ጣቴ እየመነመነ ሄዶ ብዙም ሳይቆይ ከናካቴው ማንቀሳቀስ ተሳነኝ።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ማለትም ቤቴል በገባሁ ልክ በሁለተኛው ወር ዶክተሩ በኤማያትሮፊክ ላተራል ስክለሮስስ በሽታ መያዜን ነገረኝ። ከዶክተሩ ቢሮ እየወጣሁ ሳለ በቃሌ ይዣቸው የነበሩትን ንግግሮች ማስታወስ ጀመርኩ። የአምላክ መንፈስ ከእኔ ጋር ስለነበረ መሆን አለበት ከጥቂት ዓመታት በኋላ የመሞቱ ሐሳብ አላስፈራኝም። ከዚህ ይልቅ ወደ ውጪ ወጥቼ ወደ ቤቴል የሚወስደኝን መኪና መምጣት እጠባበቅ ጀመር። ሁኔታውን ስነግራቸው ቤተሰቦቼ ስሜታቸው እንዳይጎዳ ይሖዋ እንዲረዳቸው ጸለይኩ።

በመግቢያው ላይ እንደገለጽኩት በጊዜው እንደተባረክሁ ያህል ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር። ቤቴል ለመግባት የነበረኝ የልጅነት ሕልም ተሳክቶልኛል። ያን ዕለት ምሽት በብሩክሊን ድልድይ ላይ እየተንሸራሸርኩ ግቤ ላይ እንድደርስ የረዳኝን ይሖዋን አመሰገንኩት። እንዲሁም ይህን አሰቃቂ መከራ መቋቋም እንድችል እንዲረዳኝ ከልብ ለመንሁት።

ብዙ ጓደኞቼ እኔን ለመርዳትና ለማበረታታት ከያሉበት ደወሉልኝ። ደስተኛ ለመሆንና ለነገሮች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ለማድረግ እጥር ነበር። ይሁንና ምርመራ ካደረግሁ ከሳምንት በኋላ በስልክ ተገናኝተን ሁኔታውን ለእናቴ ሳጫውታት ምንም አለመፍራቴ ጥሩ መሆኑን ከገለጸችልኝ በኋላ ማልቀስም ቢሆን ምንም ስህተት እንደሌለበት ነገረችኝ። ገና ይህን ተናግራ ሳትጨርስ መንሰቅሰቅ ጀመርኩ። ሳልመው የነበረውን ሁሉ በድንገት ላጣው እንደሆነ ተገነዘብኩ።

እማማና አባባ ወደ ቤት ሊወስዱኝ ጓጉተው ስለነበር በጥቅምት ወር መገባደጃ ላይ አንድ ቀን ሳላስበው ወደ ቤቴል መጡ። የሚቀጥሉትን ጥቂት ቀናት ቤቴልን አስጎበኘኋቸው እንዲሁም ከጓደኞቼ፣ ከአረጋውያንና በቤቴል ብዙ ጊዜ ከቆዩ ወንድሞች ጋር አስተዋወቅኳቸው። ከወላጆቼ ጋር በቤቴል ውስጥ የቆየሁባቸው እነዚህ ውድ ጊዜያት በሕይወቴ ውስጥ ካሳለፍኳቸው አስደሳች ትዝታዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው።

ያገኘኋቸው በረከቶች

ከዚያን ጊዜ አንስቶ የይሖዋ በረከት አልተለየኝም። መስከረም 1999 በሕይወቴ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር አቀረብኩ። ከዚያም በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ሌሎች በርካታ ንግግሮችን የመስጠት መብት አግኝቻለሁ። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ አንደበቴ መተሳሰር ስለጀመረ ሕዝብ ንግግር ማቅረቤን ለማቆም ተገደድኩ።

ሌላው በረከት ደግሞ ቤተሰቦቼ እንዲሁም መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ያሳዩኝ ከፍተኛ ፍቅርና ያደረጉልኝ ድጋፍ ነው። መቆም እያቃተኝ ሲመጣ ጓደኞቼ እጄን ይዘውኝ አገልግሎት እንሄድ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤታችን ድረስ እየመጡ ይንከባከቡኝ ነበር።

ካገኘኋቸው እጅግ ታላላቅ በረከቶች አንዷ ባለቤቴ ኧማንዳ ነች። ከቤቴል በተመለስኩበት ወቅት ወዳጅነት መሠረትን፤ እኔም በመንፈሳዊ ብስለቷ ይበልጥ ተማረክሁ። ዶክተሩ የሰጠኝን አስተያየት ጨምሮ ስላለብኝ በሽታ በዝርዝር አስረዳኋት። ለጋብቻ መጠናናት ከመጀመራችን በፊት ለበርካታ ጊዜያት አብረን አገልግለናል። በኋላም ነሐሴ 5, 2000 ተጋባን።

ኧማንዳ እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች:- “በጄሰን የተማረክሁት አምላክን ስለሚወድና ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅንዓት ስላለው ነው። አረጋውያንም ሆኑ ትንንሽ ልጆች በአጠቃላይ ሁሉም ሰዎች ለማለት ይቻላል በቀላሉ ይቀርቡታል። እኔ በተፈጥሮዬ ዝምተኛና ቁጥብ ነኝ፤ እሱ ደግሞ በጣም ተጫዋች፣ ፈገግታ የማይለየውና ተግባቢ ነው። በባሕርያችን ሁለታችንም መሳቅ መጫወት ስለምንወድ ብዙ አስደሳች ጊዜያትን አብረን አሳልፈናል። ለረጅም ጊዜ የምንተዋወቅ ያህል ሆኖ ስለሚሰማኝ ከእርሱ ጋር ስሆን በጣም ይቀለኛል። ጄሰን ስለያዘው በሽታም ይሁን ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል በዝርዝር አስረድቶኛል። ሆኖም ሁኔታው እስከፈቀደልን ድረስ አብረን አስደሳች ጊዜ ማሳለፍ እንደምንችል አሰብኩ። ከዚህም በላይ በዚህ ዓለም ውስጥ ሕይወት አስተማማኝ አይደለም። ጥሩ ጤንነት ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ ‘ጊዜና አጋጣሚ’ ምን ሊያደርስባቸው እንደሚችል አይታወቅም።”​—⁠መክብብ 9:11 NW

መግባቢያ ዘዴዎችን መፈለግ

የምናገረውን ነገር መስማት አስቸጋሪ እየሆነ ሲሄድ ኧማንዳ እንደ አስተርጓሚ ሆና ታገለግለኝ ጀመር። ጭራሽ መናገር ሲሳነኝ ለየት ያለ የመግባቢያ ዘዴ ፈጠርን። ኧማንዳ ፊደሎችን በተርታ ስትጠራልኝ እኔ ደግሞ የምፈልገው ፊደል ላይ ስትደርስ ዓይኔን አርገበግባለሁ። ከዚያም ያንን ፊደል በአእምሮዋ ትይዝና ወደሚቀጥለው ትሸጋገራለች። በዚህ ዓይነት ሁኔታ የዓረፍተ ነገሩን እያንዳንዱን ቃል እነግራታለሁ። እኔና ኧማንዳ ይህን ዓይነቱን መንገድ ተጠቅመን በደንብ መግባባት ቻልን።

ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባውና አሁን ከሌሎች ጋር ለመግባባት የሚያስችለኝ ላፕቶፕ ኮምፒውተር አግኝቻለሁ። ይህ ኮምፒውተር ለመናገር የፈለግኩትን ማንኛውንም ነገር ስጽፍ ጮክ ብሎ ይናገራል። እጆቼን ማንቀሳቀስ ስለማልችል የጉንጬን እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ መልእክት የሚያስተላልፍ የጨረር መመዝገቢያ በኮምፒውተሩ ላይ ተገጥሞለታል። በኮምፒውተሩ ስክሪን አንድ ጥግ ላይ ፊደሎችን የያዘ አንድ ሣጥን ይመጣል። በዚህ መንገድ ጉንጬን በማንቀሳቀስ የፈለግኩትን ፊደል መርጬ መጻፍ እችላለሁ።

በዚህ ኮምፒውተር በመታገዝ ባለቤቴ መስክ አገልግሎት ላይ ላገኘቻቸው መጽሐፍ ቅዱስ መማር ለሚፈልጉ ሰዎች ደብዳቤዎችን እጽፋለሁ። እንዲሁም ቀደም ብዬ መግቢያዎችን በመዘጋጀት ከቤት ወደ ቤት እየሄድኩ ሰዎችን ማናገርና መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት እችላለሁ። በዚህ መንገድ ዘወትር አቅኚ ሆኜ ማገልገሌን ቀጠልኩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ አገልጋይ በሆንኩበት ጉባኤ ውስጥ ንግግሮችን ማቅረብና ሌሎች የማስተማር ኃላፊነቶችን የመወጣት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።

የተጫዋችነት መንፈስ ይዞ መቀጠል

አንዳንድ አስጨናቂ ሁኔታዎች ይገጥሙናል። እግሮቼ አቅም እያጡ ሲሄዱ በተደጋጋሚ እወድቅ ጀመር። ወደ ኋላዬ በመውደቄ ምክንያት ከአንድ ጊዜ በላይ ራሴ ተፈንክቷል። ጡንቻዎቼ ስለማይተጣጠፉ ልክ እንደተገነደሰ ዛፍ እወድቅ ነበር። ይህን የሚያዩ ሌሎች ሰዎች ደንግጠው እኔን ለመርዳት ይሯሯጣሉ። ይሁንና ድንጋጤያቸውን ለማብረድ ስል ብዙውን ጊዜ በሁኔታው እቀልዳለሁ። የተጫዋችነት መንፈሴን እንዳላጣ ሁልጊዜ ብርቱ ጥረት አደርጋለሁ። ሌላ ምን ማድረግ እችላለሁ? በሕይወቴ ውስጥ ስላጋጠመኝ አስቸጋሪ ሁኔታ ልበሳጭ እችል ነበር፤ ሆኖም እንዲህ ማድረጉ ምን ይጠቅመኛል?

አንድ ምሽት ከኧማንዳና ከሌሎች ሁለት ጓደኞቻችን ጋር ወጣ ብለን በመንሸራሸር ላይ ሳለን ድንገት ወደ ኋላዬ ወደቅኩና መሬቱ ጭንቅላቴን መታኝ። በዚህ ጊዜ ሦስቱም በጣም ደንግጠው ቁልቁል የተመለከቱኝ እስካሁን ድረስ ትዝ ይለኛል፤ ከዚያም ከመካከላቸው አንዱ ደኅንነቴን ጠየቀኝ።

እኔም “ደህና ነኝ፤ ኮከቦችን እያየሁ ነው” በማለት መለስኩለት።

እርሱም “ትቀልዳለህ እንዴ?” ሲል በድጋሚ ጠየቀኝ።

እኔም ወደ ሰማይ እያመለከትኩ “እውነቴን ነው፣ እስቲ ተመልከት፤ እጅግ ውብ ናቸው” ብዬ ስመልስለት ሁሉም ሳቁ።

የሚያጋጥሙኝን ዕለታዊ ችግሮች መቋቋም

የሰውነቴ ጡንቻዎች እየመነመኑ በሄዱ መጠን ችግሩም ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ሄደ። መመገብ፣ ገላዬን መታጠብ፣ መጸዳጃ ቤት መጠቀም እንዲሁም ልብሴን መቆለፍ የመሳሰሉ ቀላል ሥራዎች አድካሚና ተስፋ አስቆራጭ እየሆኑብኝ መጡ። አሁን ያለሁበት ሁኔታ በጣም በመባባሱ ያለረዳት መንቀሳቀስ፣ መናገር፣ መመገብና መተንፈስ የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። ፈሳሽ የሆኑ ምግቦችን ለመውሰድ የሚያስችል ቱቦ ከሆዴ ጋር ተያይዟል። የምተነፍሰውም በጉሮሮዬ ላይ በተገጠመልኝ ለመተንፈስ የሚረዳ ቱቦ አማካኝነት ነው።

ሁኔታው ከአቅሜ በላይ እስኪሆን ድረስ ማንንም ላለማስቸገር የወሰንኩ ቢሆንም ኧማንዳ ከጎኔ ተለይታ አታውቅም። ከጊዜ ወደ ጊዜ የእርሷ እርዳታ የሚያስፈልገኝ ብሆንም እንኳ አንድም ቀን ከሰው እንዳነስኩ ሆኖ እንዲሰማኝ አድርጋ አታውቅም። ሁልጊዜ ክብሬን ትጠብቅልኛለች። እኔን ለመንከባከብ የምታደርገው ጥረት በእርግጥ አስደናቂ ነው፤ ይሁንና ቀላል እንዳልሆነም አውቃለሁ።

ኧማንዳ የሚሰማትን እንዲህ ስትል ትገልጻለች:- “የጄሰን ሕመም እየተባበሰ የመጣው ቀስ በቀስ በመሆኑ እኔም እርሱን እንዴት መንከባከብ እንዳለብኝ በሂደት ተምሬአለሁ። የመተንፈሻ ቱቦ ስለተገጠመለት የ24 ሰዓት እንክብካቤ ይሻል። ሳምባው ላይ የሚጠራቀመውን አክታና ምራቅ በመምጠጫ መሣሪያ አማካኝነት በየጊዜው ማስወገድ ያስፈልጋል። ስለዚህ ሁለታችንም ብንሆን ጥሩ እንቅልፍ መተኛት አንችልም። አንዳንድ ጊዜ የብቸኝነትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይሰማኛል። ዘወትር አንድ ላይ ብንሆንም ሐሳብ ለሐሳብ መግባባት አስቸጋሪ ሆኖብናል። በጣም ተጫዋች የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የሚንቀሳቀሱት ዓይኖቹ ብቻ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ቀልደኛና ፈጣን አእምሮ ያለው ሰው ነው። ሆኖም ድምፁን መስማት ይናፍቀኛል። እንደ በፊቱ እንዲያቅፈኝና እጆቼን እንዲይዝ እፈልጋለሁ።

“አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ችግሩን እንዴት መቋቋም እንደቻልኩ ይጠይቁኛል። እውነት ነው፣ ይህ መከራ በይሖዋ ላይ መታመን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አስተምሮኛል። በራሴ ታምኜ ቢሆን ኖሮ መተንፈሻ እንዳጣሁ ሆኖ እስኪሰማኝ ድረስ በችግሮቹ በተዋጥኩ ነበር። ሁኔታዬን በትክክል ሊረዳልኝ የሚችለው ይሖዋ ብቻ በመሆኑ ወደ እርሱ መጸለዬ ጠቅሞኛል። የጄሰን ወላጆችም ቢሆኑ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥተውኛል። ትንሽ ፋታ ስፈልግ አሊያም አገልግሎት ስወጣ ዘወትር እኔን ለማገዝ ፈቃደኞች ናቸው። የጉባኤያችን ወንድሞችና እህቶች ላደረጉልኝ እርዳታና ድጋፍ እጅግ አመስጋኝ ነኝ። ሌላው የረዳኝ ነገር በዚህ ዓለም ውስጥ ያለው ማንኛውም ችግር “ቀላልና ጊዜያዊ” መሆኑን ማወቄ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:​17) ትኩረቴን ይሖዋ ሁሉንም ችግሮች በሚያስወግድበት አዲስ ዓለም ላይ ለማድረግ እጥራለሁ። እነዚህ ሁሉ ውጥረቶች ሲወገዱና ጄሰን እንደ ቀድሞው ጤነኛ ሲሆን በደስታ አነባ ይሆናል።”

የመንፈስ ጭንቀትን መታገል

ራሴን መርዳት ተስኖኝ በዚህ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጬ በመዋሌ ምክንያት ተስፋ የምቆርጥባቸው ጊዜያት እንዳሉ አልክድም። አንድ ቀን በእህቴ ቤት በተደረገ የቤተሰብ ግብዣ ላይ የተከሰተው ሁኔታ አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል። ምግብ ስላልበላሁ በጣም ርቦኝ ነበር። ሌሎቹ ግን ሀምበርገርና የተቀቀለ የበቆሎ እሸት ይበሉ ነበር። እነርሱ እንደዛ ሲበሉና ከልጆች ጋር ሲጫወቱ እኔ በጭንቀት ተዋጥኩ። ‘ይህ ትክክል አይደለም! እኔ ይህን ሁሉ ነገር ያጣሁት ለምንድን ነው’ እያልኩ አስብ ጀመር። በዚህ ሁኔታ ሌሎቹ እንዲረበሹ ስላልፈለግሁ እንባዬን መቆጣጠር እንድችል እንዲረዳኝ ይሖዋን በጸሎት ለመንኩት።

በታማኝነት መጽናቴ ይሖዋ ‘ለሚሰድበው ለሰይጣን መልስ መስጠት እንዲችል’ አጋጣሚ እንደሚፈጥር በማሰብ ራሴን አጽናናሁ። (ምሳሌ 27:11 የ1954 ትርጉም ) እንዲህ ብዬ ማሰቤ በቆሎ ከመብላትም ሆነ ከልጆች ጋር ከመጫወት ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነ ጉዳይ መኖሩን እንዳስተውል ስላስቻለኝ ብርታት አገኘሁ።

እንደ እኔ ዓይነት ታማሚ ሰው ስለራሱ ችግሮች ብቻ እያውጠነጠነ በቀላሉ ሊቆዝም እንደሚችል መረዳት አያዳግተኝም። ያም ሆኖ ሁልጊዜ ‘የጌታ ሥራ የበዛልኝ’ መሆኔ ጠቅሞኛል። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ራሴን በአገልግሎት ማስጠመዴ ያለብኝን ችግር እያብሰለሰልኩ የምቆጭበት ጊዜ እንዳይኖረኝ አድርጓል። ሌሎች በይሖዋ እንዲያምኑ በመርዳቱ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረጌ የላቀ ደስታ አስገኝቶልኛል።

ጭንቀትን ለመዋጋት የረዳኝ ሌላም ነገር አለ። ይህም ታማኝ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች ስለ አምላክ መንግሥት መመሥከራቸውን አናቆምም በማለታቸው ለእስር እንደተዳረጉ እንዲያውም አንዳንዶቹ በአንድ ክፍል ውስጥ ለብቻቸው እንደታሰሩ በሚገልጹ ተሞክሮዎች ላይ ማሰላሰሌ ነው። እኔም መኝታ ክፍሌን ልክ እንደ እስር ቤት ራሴን ደግሞ በእምነቱ የተነሳ እንደታሰረ እስረኛ አድርጌ አስብ ነበር። ከአንዳንዶቹ ወንድሞች በተለየ መልኩ እኔ ያለሁበትን የተመቻቸ ሁኔታ ለማሰብ እጥራለሁ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንደልብ አገኛለሁ። በአካልም ይሁን በስልክ በክርስቲያን ጉባኤዎች ላይ መካፈል እችላለሁ። የማገልገል ነፃነት አለኝ። ከጎኔ የማትለይ ውድ ባለቤት አለችኝ። በዚህ መንገድ ማሰላሰሌ ምን ያህል እንደተባረክሁ እንዳስተውል ረድቶኛል።

ሐዋርያው ጳውሎስ “ተስፋ አንቈርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ፣ ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” በማለት የተናገራቸው ቃላት በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ትርጉም አላቸው። በእርግጥ የእኔም ውጫዊ ሰውነት እየጠፋ ሄዷል። ሆኖም ተስፋ ላለመቁረጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ። የእምነት ዓይኔን በመጪው አዲስ ዓለም ውስጥ በምናገኛቸው በረከቶችና ‘በማይታዩት ነገሮች ላይ’ መትከሌ ብርታት ሰጥቶኛል፤ በዚያን ጊዜ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሚያደርገኝ አውቃለሁ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:16, 18

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በሽታው ስለሚያስከትለው ችግር ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በገጽ 27 ላይ የሚገኘውን “ኤ ኤል ኤስን በተመለከተ የቀረቡ አንዳንድ መረጃዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[በገጽ  27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ኤ ኤል ኤስን በተመለከተ የቀረቡ አንዳንድ መረጃዎች

ኤ ኤል ኤስ ምንድን ነው? ኤ ኤል ኤስ የኤማያትሮፊክ ላተራል ስክለሮስስ ምሕጻረ ቃል ነው። ይህ በሽታ በፍጥነት የሚሰራጭ ሲሆን በአከርካሪና ከኋላ ባለው የአእምሮ ታችኛው ክፍል ላይ የሚገኙትን ቀስቃሽ ሕዋሰ ነርቮች ወይም ሞተር ኒውሮንስ (የነርቭ ሕዋስ) ያጠቃል። ቀስቃሽ ሕዋሰ ነርቮች ከአእምሮ በመላው አካል ውስጥ ወደሚገኙት ተገዥ ጡንቻዎች (ቮለንተሪ መስልስ) መልእክት ያስተላልፋሉ። በሽታው ቀስቃሽ ሕዋሰ ነርቮች እንዲዳከሙ ወይም እንዲሞቱ ስለሚያደርግ ሰውነት ቀስ በቀስ ሽባ እየሆነ ይሄዳል። *

ይህ በሽታ የሉ ጌሪግ በሽታ ተብሎ የሚጠራው ለምንድን ነው? ሉ ጌሪግ በ1939 በበሽታው የተያዘና በኋላም በ1941 በ38 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈ ታዋቂ አሜሪካዊ ቤዝቦል ተጫዋች ነበር። በአንዳንድ አካባቢዎች ይህ በሽታ ቀስቃሽ ሕዋሰ ነርቭን የሚያጠቃ በሽታ በመባል ይታወቃል። ይህ አጠራር ኤ ኤል ኤስን ጨምሮ ሌሎች ዓይነት በሽታዎችንም ያጠቃልላል። አንዳንዴ ደግሞ ይኸው በሽታ በ1869 የበሽታውን ምንነት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ባደረገው ፈረንሳዊ ኒውሮሎጂስት ስም የቻርኮት በሽታ በመባል ይጠራል።

የበሽታው መንስኤ ምንድን ነው? የዚህ በሽታ መንስኤ በትክክል ተለይቶ አይታወቅም። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ በሽታው ከቫይረስ፣ ከፕሮቲን እጥረት፣ ከዘር ውርስ ችግሮች (በተለይ በዘር ለሚተላለፍ ኤ ኤል ኤስ)፣ ክብደት ያላቸው የብረት አተሞች በሰውነት ውስጥ ከመብዛት፣ ከኒውሮቶክሲን (በተለይ ለጉዋማኒያን ኤ ኤል ኤስ)፣ ከሰውነት የመከላከያ አቅም መዛባት እንዲሁም ከኢንዛይም ችግር ጋር ተያይዞ ሊመጣ ይችላል።

በሽታው በሕመምተኛው ላይ ምን ያስከትላል? በሽታው ሥር እየሰደደ ሲሄድ ጡንቻዎች ይዝላሉ እንዲሁም መላው ሰውነት መመንመን ይጀምራል። ቀጥሎም በሽታው የመተንፈሻ አካላት እንዲዳከሙ ስለሚያደርግ የታማሚው ሕልውና ለመተንፈስ በሚያስችለው ሌላ መሣሪያ ላይ የተመካ ይሆናል። በሽታው የሚያጠቃው ቀስቃሽ ሕዋሰ ነርቮችን ብቻ በመሆኑ የሕመምተኛውን አእምሮ፣ ሁለንተናዊ ባሕርይ አሊያም የማገናዘብና የማስታወስ ችሎታ እንዲቃወስ አያደርግም። ከዚህም በላይ የስሜት ሕዋሳቱ በተገቢው ሁኔታ ስለሚሠሩ ማየት፣ ማሽተት፣ መቅመስ፣ መስማትና መዳሰስ ይችላል። በሽታው ብዙውን ጊዜ ታማሚውን ለኅልፈተ ሕይወት የሚዳርገው ምልክቶቹ መታየት ከጀመሩ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሲሆን 10 በመቶ የሚያህሉት ሕመምተኞች በበሽታው ከተያዙበት አንስቶ አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ በሕይወት መቆየት ይችላሉ።

የሚሰጠው ሕክምና ምንድን ነው? ይህ በሽታ እስካሁን መድኃኒት አልተገኘለትም። ሐኪሞች ከበሽታው ምልክቶች ጋር ተያይዘው የሚመጡትን አንዳንድ ችግሮች ለማስታገስ የሚያስችሉ መድኃኒቶችን ያዝዙ ይሆናል። እንደ በሽታው ምልክቶችና ደረጃ አካልን፣ ሙያዎችንና የንግግር ችሎታን ለማዳበር የሚረዱ ሕክምናዎችን ጨምሮ የተለያዩ የተሐድሶ ፕሮግራሞችን መከታተል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.48 ይህ በሽታ በአብዛኛው በሦስት ይከፈላል:- እነዚህም ስፖራዲክ ኤ ኤል ኤስ (በጣም የተለመደ ነው)፣ በዘር የሚተላለፍ (ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት ታማሚዎች በሽታው የሚተላለፍባቸው በዘር ነው) እንዲሁም ጉዋማኒያን (ጉዋምና በአካባቢው ያሉ ደሴቶች በብዛት በበሽታው ይጠቃሉ) በመባል ይታወቃሉ።

[ምንጭ]

ሉ ጌሪግ:- Photo by Hulton Archive/Getty Images

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1985 ቤቴልን ስንጎበኝ

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከኧማንዳ ጋር በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመግባባት የሚያስችለኝ ልዩ ዓይነት ላፕቶፕ ኮምፒውተር

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጉባኤያችን ውስጥ ንግግር ሳቀርብ