ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
የኃይል ምንጭ (ግንቦት 2005) በምኖርበት አገር የቤንዚን ዋጋ እያሻቀበ ነው፤ “ብክለት የማያስከትል የኃይል ምንጭ ማግኘት እንችል ይሆን?” የሚል የሽፋን ርዕስ ይዞ ለወጣው ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ። ይሖዋ አምላክ ወደፊት በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ “ሰው ሁሉ ከምድር በርካታ ሀብት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል” የሚለው ሐሳብ በጣም ያጽናናል።
ኤም. ኤን.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ተራሮች—አለ እነርሱ መኖር የማንችለው ለምንድን ነው? (ሐምሌ 2005) ግራንድ ቲቶንስ የተባሉትን ተራሮች መጎብኘቴ በሕይወቴ ውስጥ በጣም ካስደመሙኝ አጋጣሚዎች አንዱ ነበር። ስለ ተራሮች አስፈላጊነት ማንበቤ ግን የበለጠ አስደንቆኛል። በምድራችን ላይ የሚገኙት ተራሮች ለምን እንደሚጠቅሙና የፈጠራቸውን ድንቅ አምላክ በተመለከተ አሁን ከበፊቱ የበለጠ ግንዛቤ አለኝ።
ጄ. ጂ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የይሖዋ ፍጥረታት ያላቸውን ውበት ስመለከት ምን እንደሚሰማኝ ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል። ሰዎች ዓመጸኞች ሆነው በአካባቢ ላይ ብክለት ቢያደርሱም እንኳ አንድ ሰው ተራሮች በመኖራቸው ሊያመሰግንና ሊደሰት ይችላል። በመዝሙር 72:16 ላይ ቃል በተገባው መሠረት በቅርቡ ምን እንደሚከሰት ለሌሎች መንገር ያስደስተኛል።
አር. ሲ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የወጣቶች ጥያቄ . . . የጉልበት ሥራ መሥራት ያለብኝ ለምንድን ነው? (ሚያዝያ 2005) አባቴ በሚያስተዳድረው አንድ ቀለም ቀቢ ድርጅት ውስጥ እሠራለሁ፤ ሆኖም አንድ ሰው እንዲህ ያለው ሥራ የአእምሮ እውቀት የሚጠይቅ እንዳልሆነ ነገረኝ። ይሁን እንጂ በዚያ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ ኢየሱስና ጳውሎስ የእጅ ሙያ እንደነበራቸው ተጠቅሷል። አሁን ሥራዬን ከበፊቱ በበለጠ ትጋት ለመሥራት ተበረታትቻለሁ። በትልልቅ ስብሰባ አዳራሾችና በመንግሥት አዳራሾች ግንባታ ላይ ይህንን ችሎታዬን መጠቀም ስለምፈልግ ሙያውን ጠንቅቄ ለማወቅ እሻለሁ።
ኤም. ዋይ.፣ ጃፓን
በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሐሳቦች በጣም አበረታተውኛል! የመኖራችን ተቀዳሚ ዓላማ ይሖዋ አምላክን ማገልገል እንደሆነና የምመርጠው የሥራ ዓይነት ከዚህ ዓላማ ጋር የሚስማማ መሆን እንዳለበት አሳስቦኛል። ይህ ድንቅ ትምህርት በቤት ውስጥ መሠራት የሚገባቸውን ነገሮች በራሴ ተነሳሽነት በማከናወን ረገድ ማሻሻያ እንዳደርግ አነሳስቶኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ ለጉልበት ሥራ ያለውን አመለካከት እንዳስተውል ረድቶኛል።
ዋይ. ኬ.፣ ሩሲያ
ሕይወት የተገነባበት አስደናቂ ሰንሰለት (መጋቢት 2005) የ15 ዓመት ወጣት ነኝ። ትምህርት ቤት ውስጥ በባዮሎጂ ክፍለ ጊዜ ኢነርጂ ሚታቦሊዝም በሚል ርዕስ ትምህርት እየተሰጠ ነው። ይህንን መጽሔት ትምህርት ቤት ይዤው ስሄድ የባዮሎጂ አስተማሪያችን ጽሑፉ የያዘውን ሐሳብና ስዕሎቹን በመጠቀም ትምህርቱን አብራራልን። ክፍለ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉም ይህን መጽሔት ማግኘት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። ይህ ርዕሰ ትምህርት ይሖዋ ምን ያህል ጥበብ እንዳለው በግልጽ ያስገነዝባል። ይሖዋ ሊወደስ እንደሚገባው ምንም አያጠያይቅም። ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ ይሖዋን የሚያመሰግንበትን ጊዜ በጉጉት እጠብቃለሁ!
ዋይ. ቢ.፣ ሩሲያ