ወደፊት አስደሳች ጊዜ ይመጣ ይሆን?
ወደፊት አስደሳች ጊዜ ይመጣ ይሆን?
ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ይጓጓሉ። ከእኛ መካከል የሚቀጥለው ወር፣ ዓመት ወይም ደግሞ የዛሬ አሥር ዓመት ምን እንደሚያጋጥመው ለማወቅ የማይፈልግ ማን አለ? ጉዳዩን ይበልጥ ሰፋ ባለ መልኩ ስንመለከተው ደግሞ የዛሬ 10, 20 ወይም 30 ዓመት ዓለማችን ምን ትመስል ይሆን?
የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ሆኖ ይታይሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እንደዚህ ዓይነት አመለካከት አላቸው፤ እነዚህን ሰዎች በሁለት ጎራ ልንከፍላቸው እንችላለን። እነርሱም:- ወደፊት ሁኔታዎች እንደሚሻሻሉ ለማመን የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎች እና ሌሎች አማራጮች ሁሉ አስጨናቂ ስለሆኑ ብቻ የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ይሆናል የሚሉ ሰዎች ናቸው።
እርግጥ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ ምንም መልካም ነገር የማይታያቸው አንዳንድ ሰዎችም አሉ። ከእነዚህም መካከል የምንኖርባት ምድር ድምጥማጧ እንደሚጠፋ መናገር የሚያስደስታቸው የጥፋት ነቢያት ይገኙበታል። በእነርሱ አመለካከት ከዚህ ጥፋት የሚተርፉ ቢኖሩ እንኳ ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
አንተስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን አመለካከት አለህ? ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ የሚታይህ ጥፋትና እልቂት ነው ወይስ ሰላምና ደኅንነት? ሰላምና ደኅንነት እንደሚመጣ የምትጠብቅ ከሆነ ተስፋህ የተመሠረተው በምን ላይ ነው? እንደዚህ ዓይነት አመለካከት የያዝከው የወደፊቱ ጊዜ አስደሳች እንዲሆን ስለምትመኝ ብቻ ነው ወይስ እንዲህ ብለህ ለማመን የሚያስችል አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ አለህ?
መዓት እንደሚመጣ ከሚተነብዩ ሰዎች በተለየ መልኩ የንቁ! መጽሔት አዘጋጆች የሰው ልጆች ከምድር ገጽ ይጠፋሉ ብለው አያምኑም። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱ ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን ለማመን የሚያስችል ጠንካራ ማስረጃ ይሰጠናል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
U.S. Department of Energy photograph