በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወዳጃችንም ጠላታችንም የሆነው ሻጋታ!

ወዳጃችንም ጠላታችንም የሆነው ሻጋታ!

ወዳጃችንም ጠላታችንም የሆነው ሻጋታ!

ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

አንዳንድ የሻጋታ ዓይነቶች ሕይወት ለማዳን የሚውሉ ሲሆን ሌሎች ግን ለሕልፈተ ሕይወት ይዳርጋሉ። የተወሰኑ ሻጋታዎች ፎርማጆ (ቺዝ) እና ወይን ጥሩ ጣዕም እንዲኖራቸው ለማድረግ ያገለግላሉ፤ ሌሎች ዓይነቶች ግን ምግብን ሊመርዙ ይችላሉ። ጥቂት የሻጋታ ዝርያዎች በግንድ ላይ የሚበቅሉ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ መታጠቢያ ቤቶችንና መጻሕፍትን ያበላሻሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሻጋታ የማይገኝበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል፤ ይህንን ዓረፍተ ነገር በምታነብበት ቅጽበት እንኳ የፈንገስ ሕዋስ በአፍንጫህ ቀዳዳ ውስጥ ይኖር ይሆናል።

ሻጋታ በሁሉም ቦታ የሚገኝ መሆኑን ከተጠራጠርክ ቁራጭ ዳቦ ውሰድና ክፍቱን (ማቀዝቀዣ ውስጥም ቢሆን) አስቀምጥ። ብዙም ሳይቆይ ዳቦውን ጥጥ የሚመስል ለስላሳ ነገር ሸፍኖት ትመለከታለህ፤ ዳቦው ሻግቷል ማለት ነው!

ሻጋታ ምንድን ነው?

ሻጋታ ከፈንገስ ዝርያዎች ይመደባል። ፈንገስ ሻጋታን፣ እንጉዳይን፣ እርሾንና በእፅዋት ላይ ሻጋታ መሰል ነገር እንዲኖር የሚያደርገውን በሽታ ጨምሮ ከ100, 000 በላይ ዝርያዎች አሉት። ከእነዚህ መካከል በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሕመም ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የሚታወቁት 100 የሚያህሉት የፈንገስ ዝርያዎች ብቻ ናቸው። የተቀሩት አብዛኞቹ የፈንገስ ዝርያዎች፣ የሞቱ ነገሮች እንዲፈራርሱ በማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን እፅዋት እንደገና ሊጠቀሙበት በሚችሉት መልኩ ያዘጋጃሉ። በዚህ መንገድ በሕያዋን ፍጥረታት መካከል የሚገኘው አንዱ ሌላውን የሚመገብበት እሽክርክሪት እንዲቀጥል የጎላ ድርሻ ያበረክታሉ። ሌሎች ደግሞ ለጋራ ጥቅማቸው ሲሉ እፅዋት ከአፈር ውስጥ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። ጥቂት የፈንገስ ዝርያዎች ግን ጥገኛ ሕዋሳት ናቸው።

ሻጋታ በሕይወቱ መጀመሪያ ላይ፣ በዓይን የማይታይና አየር ውስጥ የሚገኝ ሕዋስ ነው። ይህ ሕዋስ፣ ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ትክክለኛ ሙቀትና እርጥበት ባለው ለምግብነት ተስማሚ በሆነ አካል ላይ ካረፈ ሃይፋ በመባል የሚታወቁ ጥጥ መሰል ሕዋሳት በመሥራት ማደግ ይጀምራል። ሃይፋ የተባሉት ነገሮች ቡድን ሲመሠርቱ የሚፈጠረው እርስ በርሱ የተጠላለፈ ለስላሳ ነገር ማይሲሊየም ተብሎ ይጠራል፤ ይህ በዓይን ሊታይ የሚችለው ሻጋታ ነው። ሻጋታ በመታጠቢያ ቤት ሸክላዎች መጋጠሚያ ላይ በሚያድግበት ጊዜ የቆሻሻ ወይም የእድፍ መልክ ሊኖረውም ይችላል።

ሻጋታ በጣም በከፍተኛ ፍጥነት የመራባት ችሎታ አለው። ራይዞፐስ ስቶለኒፈር ተብሎ በሚጠራው በተለመደው የዳቦ ሻጋታ ላይ የሚታዩት ጥቃቅን ጥቁር ነጠብጣቦች ስፖራን​ጂያ የሚባሉ የፈንገስ ሕዋሳት ናቸው። አንዷ ጥቁር ነጥብ ከ50, 000 በላይ የፈንገስ ሕዋሳት የምትይዝ ሲሆን እነዚህ እያንዳንዳቸው ደግሞ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ከመቶ ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የፈንገስ ሕዋሳት ሊያራቡ ይችላሉ! በተጨማሪም ሻጋታ ተስማሚ ሁኔታ ካገኘ በመጻሕፍትና በግንድ ላይ እንዲሁም በቦት ጫማ ውስጥ በቀላሉ ይራባል።

ሻጋታ “የሚመገበው” እንዴት ነው? ሰዎችና እንስሳት በመጀመሪያ ከተመገቡ በኋላ ምግቡን በመፍጨት ከሰውነታቸው ጋር እንዲዋሃድ ያደርጋሉ፤ ሻጋታ ግን ይህን ሂደት የሚያከናውነው በተቃራኒው ነው። ሻጋታ፣ አንድ ሕይወት ያለው ሞለኪውል ሊመገበው ከሚችለው በላይ ግዙፍ ወይም ውስብስብ ከሆነበት ለመፍጨት የሚያገለግል ኢንዛይም በማመንጨት ሞለኪውሎቹን ከበታተናቸው በኋላ ይመገባቸዋል። ከዚህም በላይ ሻጋታ ምግብ ፍለጋ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ስለማይችል የሚኖረው በምግቡ ላይ መሆን አለበት።

ሻጋታ ማይኮቶክሲን የሚባሉ መርዛማ ንጥረ ነገሮች ማመንጨት የሚችል ሲሆን እነዚህም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለእነዚህ ንጥረ ነገሮች የምንጋለጠው ስንተነፍስ፣ ስንበላና ስንጠጣ ወይም ቆዳችን ላይ ሲያርፉ ነው። ይሁን እንጂ ሻጋታ በጣም ጠቃሚ ጎኖችም ስላሉት ሁልጊዜ ጎጂ ነው ማለት አይቻልም።

የሻጋታ ጠቃሚ ጎን

በ1928፣ አሌክሳንደር ፍሌሚንግ የተባሉት ሳይንቲስት አረንጓዴ ሻጋታ ጀርሞችን የማጥፋት ኃይል እንዳለው በአጋጣሚ ተመለከቱ። ከጊዜ በኋላ ፔኒሲሊየም ኖታተም ተብሎ የተሰየመው ይህ ሻጋታ ባክቴሪያዎችን የሚገድል ቢሆንም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ግን ምንም ጉዳት እንደማያስከትል ተረጋገጠ። ይህ ግኝት “ከዘመናዊ መድኃኒቶች ሁሉ በርካታ ሕይወት እንዳተረፈ” የሚነገርለትን ፔኒሲሊን የተባለውን መድኃኒት ለመሥራት መንገድ ጠርጓል። ፍሌሚንግ፣ ሃዋርድ ፍሎሬ እና ኧርነስ ቼይን ከተባሉ የምርምር ባልደረቦቻቸው ጋር ላከናወኑት ሥራ ሦስቱም በ1945 በሕክምና መስክ የኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሻጋታ መድኃኒትነት ያላቸው ሌሎች በርካታ ንጥረ ነገሮችን ያስገኘ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ለደም መርጋት፣ ማይግሬን በመባል ለሚታወቀው ኃይለኛ ራስ ምታት እንዲሁም ፓርኪንሰንስ ዲዚዝ ለሚባለው የነርቭ ሕመም የሚሰጡት መድኃኒቶች ይገኙበታል።

ሻጋታ ለምግብ ጥሩ ጣዕም በመስጠት ረገድም ጥቅም አለው። ፎርማጆን (ቺዝ) እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ብሪ፣ ካምምበርት፣ ብሉ ቺዝ፣ ጎርገንዞላ፣ ሮክፈርት እንዲሁም ስቲልተን የተባሉት የፎርማጆ ዓይነቶች የየራሳቸው ለየት ያለ ጣዕም ሊኖራቸው የቻለው ፔኒሲሊየም በተባለው ሻጋታ ምክንያት መሆኑን ታውቅ ነበር? በተመሳሳይም ሻጋታ የአሳማ ሥጋን ለማጣፈጥ እንዲሁም ሶይ ሶስ ለሚባለው የምግብ ማጣፈጫም ሆነ ለቢራ ጥሩ ጣዕም ለመስጠት ያገለግላል።

ሻጋታ ወይን ለመጥመቅም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አለ። ትክክለኛ የሆኑት የወይን ፍሬዎች በተገቢው ጊዜ ከተቆረጡና በእያንዳንዱ ዘለላ ላይ ተስማሚ መጠን ያለው ፈንገስ የሚገኝ ከሆነ ጣፋጭ ወይን መጥመቅ ይቻላል። ቦትራይተስ ሲኒሪያ የተባለው ሻጋታ በወይን ፍሬዎቹ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን እንዲጨምር ስለሚያደርግ ጥሩ ጣዕም ይሰጠዋል። ወይኑ እንዲፈላ በሚቀመጥበት መጋዘን ደግሞ ክላዶስፖሪየም ሴላር የተባለው ሻጋታ ወይኑ የበለጠ ግሩም ጣዕም እንዲኖረው ያደርጋል። ሃንጋሪያውያን ወይን አምራቾች ‘ምርጥ የሆነ ሻጋታ ድንቅ ወይን ያስገኛል’ የሚል ምሳሌያዊ አባባል አላቸው።

የሻጋታ ጎጂ ገጽታ

አንዳንድ የሻጋታ ዓይነቶች ጎጂ መሆናቸው ከታወቀ ቆይቷል። በስድስተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አሦራውያን ክላቪሲፐስ ፐርፑሪያ በተባለው ሻጋታ በመጠቀም የጠላቶቻቸውን የውኃ ጉድጓዶች ይመርዙ ነበር። ይህም ጥንታዊ ባዮሎጂያዊ የጦር ስልት መሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ በአጃ ላይ የሚበቅለው ይኸው የሻጋታ ዝርያ በመካከለኛው መቶ ዘመን ብዙ ሰዎች በሚጥል ሕመም፣ ሰውነትን በኃይል በሚያቃጥል ስሜት፣ በማይሽር ቁስል እንዲሁም በቅዠት እንዲሠቃዩ አድርጓቸዋል። ዛሬ ኧርገቲዝም በመባል የሚጠራው ይህ በሽታ በወቅቱ የቅዱስ አንቶኒ እሳት ይባል ነበር፤ የዚህ ዓይነት ስያሜ የተሰጠው በበሽታው የተጠቁ ብዙ ሰዎች ተአምራዊ ፈውስ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ በፈረንሳይ ወደሚገኘው የቅዱስ አንቶኒ መቅደስ ይጓዙ ስለነበረ ነው።

በአሁኑ ጊዜ ካንሰር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ከሚታወቁት ንጥረ ነገሮች ሁሉ ኃይለኛው አፍለቶክሲን የተባለ ከሻጋታ የሚመጣ መርዝ ነው። በአንድ የእስያ አገር ውስጥ በየዓመቱ 20, 000 ሰዎች በዚህ መርዝ ምክንያት ይሞታሉ። ይህ ገዳይ ንጥረ ነገር ዘመናዊ ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያዎችን ለመሥራት ውሏል።

ያም ሆኖ ግን፣ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተራ ለሆኑት የሻጋታ ዓይነቶች በመጋለጣችን የተነሳ በሰውነታችን ላይ የሚታዩት ምልክቶች በጤናችን ላይ የሚያስከትሉት የከፋ ጉዳት የለም። ዩሲ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር “አብዛኞቹ ሻጋታዎች፣ ልታሸቷቸው ብትችሉም እንኳ ጎጂ አይደሉም” ብሏል። አብዛኛውን ጊዜ በሻጋታ ምክንያት ጤንነታቸው ሊታወክ ከሚችል ሰዎች መካከል እንደ አስም ያለ የሳንባ ችግር ወይም አለርጂ ያለባቸው፣ ኬሚካል የማይስማማቸው አሊያም በሽታ የመከላከል ኃይላቸው የተዳከመ ሰዎች እንዲሁም በግብርና ሥራ የተሰማሩና ከፍተኛ መጠን ላለው ሻጋታ የሚጋለጡ ሰዎች ይገኙበታል። አራስ ልጆችና አረጋውያንም በሻጋታ ምክንያት ጤንነታቸው የመቃወሱ አጋጣሚ ሰፋ ያለ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ የካሊፎርኒያ የጤና አገልግሎት ክፍል እንደገለጸው ለሻጋታ የተጋለጠ ሰው የሚከተሉት ምልክቶች ሊታዩበት ይችላሉ:- ‘እንደ ማፈን፣ የመተንፈስ ችግር እንዲሁም ቁርጥ ቁርጥ ያለ ትንፋሽ የመሳሰሉ የመተንፈሻ አካላት ችግሮች፣ የአፍንጫና የሳይነስ መታፈን፣ የዓይን መቆጣት (ማቃጠል፣ እንባ ማዘል ወይም መቅላት)፣ ደረቅና የሚፍቅ ሳል፣ የአፍንጫ ወይም የጉሮሮ መቁሰል፣ የቆዳ መቆጣትና ሽፍታ።’

በሕንፃዎች ውስጥ የሚፈጠር ሻጋታ

በአንዳንድ አገሮች ሻጋታን ለማጥፋት ሲባል ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ወይም ቤቶችና ቢሮዎች እንደተለቀቁ መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። በ2002 መባቻ ላይ በስቶክሆልም፣ ስዊድን አዲስ የተከፈተውን የዘመናዊ ሥነ ጥበብ ሙዚየም በሻጋታ ምክንያት መዝጋት ግድ ሆኖ ነበር። የዚህን ሕንፃ ሻጋታ ለማጥፋት አምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገደማ ፈጅቷል። ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ መከሰት የጀመረው ለምንድን ነው?

ለችግሩ ሁለት ነገሮች አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን እነርሱም የግንባታ ቁሳቁሶችና ንድፎች ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጥቅም ላይ የሚውሉት የግንባታ ቁሳቁሶች በቀላሉ ለሻጋታ የሚጋለጡ ዓይነት ናቸው። ጂፕሰም ቦርድ ለዚህ እንደ ምሳሌ ይሆነናል። መሃሉ እርጥበት ስለሚይዝ ረዘም ላለ ጊዜ እርጥብ ሆኖ ከቆየ ሻጋታው መባዛትና ማደግ ይችላል።

የቤት ንድፎችም ተለውጠዋል። ከ1970ዎቹ ዓመታት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ይሠሩ የነበሩት አብዛኞቹ ሕንፃዎች፣ በኋላ ላይ ከተሠሩት ሕንፃዎች አንጻር ቀዝቀዝ ያሉና አየር ለማስገባት አመቺ ነበሩ። በኋላ ላይ ግን ኃይል ለመቆጠብ ሲባል፣ ከሕንፃው ወደ ውጭ የሚወጣውንም ሆነ ከውጪ ወደ ውስጥ የሚገባውን ሙቀት ለመቀነስ እንዲሁም ሕንፃው እንደልብ አየር የሚያስተላልፍ እንዳይሆን ለማድረግ የሚያስችል የግንባታ ለውጥ ተደረገ። ስለዚህ አሁን ውኃ ሲገባ ሕንፃው ረዘም ላለ ጊዜ እርጥበቱን ይዞ ስለሚቆይ ሻጋታ እንዲያድግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ይህንን ችግር ማስወገድ የሚቻልበት መፍትሔ ይኖር ይሆን?

ከሻጋታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስወገድ ወይም ቢያንስ ለመቀነስ በጣም ውጤታማ የሆነው ዘዴ በሕንፃው ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ንጹሕና ደረቅ እንዲሆኑ እንዲሁም እርጥበት እንዳይኖር ማድረግ ነው። የሆነ ቦታ ላይ እርጥበት መያዝ ከጀመረ ጊዜ ሳታጠፉ ቦታውን ካደረቃችሁት በኋላ በድጋሚ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር አስፈላጊውን ለውጥ ወይም ጥገና አድርጉ። ለምሳሌ፣ ጣሪያውም ሆነ አሸንዳው ንጹሕና ጥሩ እድሳት የሚደረግለት መሆን አለበት። የቤቱ መሠረት አካባቢ ውኃ እንዳይጠራቀም መሬቱ ተዳፋት እንዲሆን አድርጉ። አየር ማቀዝቀዣ መሣሪያ ካላችሁ ሁልጊዜ አጽዱት።

አንድ መመሪያ ጽሑፍ “ሻጋታን ለመቆጣጠር ቁልፉ እርጥበትን መቆጣጠር ነው” ብሏል። ቀለል ያሉ ጥንቃቄዎች ማድረግህ አንተንም ሆነ ቤተሰብህን ጎጂ ከሆነው የሻጋታ ገጽታ ይጠብቃችኋል። በአንዳንድ መንገዶች ሻጋታ እንደ እሳት ነው። ጉዳት ሊያስከትል ቢችልም ከፍተኛ ጥቅም ሊሰጥም ይችላል። ዋናው ነገር እንዴት እንጠቀምበታለን እንዲሁም እንቆጣጠረዋለን የሚለው ነው። ስለ ሻጋታ ገና ብዙ ልንማረው የምንችለው ነገር እንዳለ አይካድም። ሆኖም ድንቅ ስለሆኑት የአምላክ ፍጥረታት ማወቃችን ጥቅሙ ለእኛው ነው።

[በገጽ 14, 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሻጋታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል?

መጽሐፍ ቅዱስ “የለምጽ ደዌ . . . በአንድ ቤት” ማለትም በሕንፃው ላይ ስለመኖሩ ይጠቅሳል። (ዘሌዋውያን 14:34-48 የ1954 ትርጉም ) ይህ ደዌ “እየፋገ የሚሄድ ለምጽ” ተብሎም የተጠራ ሲሆን አንድ ዓይነት ሻጋታ ሊሆን እንደሚችል ሐሳብ ተሰንዝሯል፤ ሆኖም ይህን ሐሳብ በተመለከተ ጥርጣሬዎች አሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን የአምላክ ሕግ የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡ፣ በውስጥ በኩል ያለው የቤቱ ግድግዳ በሙሉ እንዲፋቅና እንደተበከለ የሚጠረጠረውን ነገር በሙሉ ከከተማው ውጭ ባለ ‘ርኩስ ስፍራ’ እንዲጥሉት ያዝዝ ነበር። ከዚህም በኋላ ይህ ደዌ እንደገና ከታየ ቤቱ እንዳለ እንደ ርኩስ ተቆጥሮ ይፈርስና ቁሳቁሶቹ ይጣላሉ። ይሖዋ የሰጠው ዝርዝር መመሪያ ለሕዝቡ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ስለ ደኅንነታቸው የሚያስብ መሆኑን ያሳያል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ከሻጋታ የተሠሩ መድኃኒቶች የብዙዎችን ሕይወት አትርፈዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ጂፕሰም ቦርድ እርጥበት ስለሚይዝ ሻጋታ እንዲራባ መንገድ ይከፍታል