ይህ ዓለም መጨረሻው ምን ይሆን?
ይህ ዓለም መጨረሻው ምን ይሆን?
በሚቀጥሉት 10, 20 ወይም 30 ዓመታት ምን ይመጣ ይሆን? በሽብርተኝነት በሚታወቀው በዚህ ዘመን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ አስፈሪ ሊሆን ይችላል። ቴክኖሎጂ በፍጥነት በማደግ ላይ ነው። ድንበር የለሹ የንግድ ሥርዓት አብዛኞቹን መንግሥታት እርስ በርስ እንዲደጋገፉ አድርጓል። የዓለም መንግሥታት በመተባበር ብሩህ የወደፊት ጊዜ እንዲኖር ያደርጉ ይሆን? አንዳንድ ሰዎች፣ መንግሥታት በ2015 ድህነትንና ረሃብን እንደሚያስወግዱ ብሎም የኤድስ ስርጭት እንዲገታ እንደሚያደርጉ አልፎ ተርፎም ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የማያገኙትን እንዲሁም የደረቅ ቆሻሻና የፍሳሽ ማስወገጃ የሌላቸውን ሰዎች ቁጥር በግማሽ እንደሚቀንሱ ተስፋ ያደርጋሉ።—“ብሩህ አመለካከት ከእውነታው አንጻር ሲታይ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ይሁን እንጂ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ያላቸው አመለካከት ብዙውን ጊዜ ከእውነታው የራቀ ነው። ለምሳሌ፣ ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በፊት አንድ ባለሞያ በ1984 ገበሬዎች በውኃ ውስጥ በሚሠሩ ትራክተሮች በመጠቀም የውቅያኖሶችን ወለል እንደሚያርሱ የተናገሩ ሲሆን ሌላ ባለሞያ ደግሞ የመኪና አደጋን ለመቀነስ እንዲቻል በ1995 መኪኖች ኮምፒውተር እንደሚገጠምላቸው ተናግረዋል። ሌላ ባለሞያም በ2000፣ 50, 000 የሚያህሉ ሰዎች በጠፈር ላይ መሥራትና መኖር ይችላሉ ብለው ነበር። እውነት ነው እንደነዚህ የመሳሰሉ ነገሮችን የተነበዩ ሰዎች አሁን ሲያስቡት ምነው ዝም ባልን ኖሮ ይሉ ይሆናል። አንድ ጋዜጠኛ “ጊዜ እያለፈ በሄደ መጠን፣ የዓለም ጠበብት የተባሉ ሰዎች ምንም የማያውቁ መሆናቸው በግልጽ እየታየ መጥቷል” ሲል ጽፏል።
ሊመራን የሚችል “ካርታ”
ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ መቋጫ የሌለው ግምታዊ ሐሳብ ቢሰነዝሩም አንዳንድ ጊዜ ግን ራእያቸው የተመሠረተው በእውነታው ሳይሆን በመላ ምት ላይ ነው። ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ለማወቅ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
ነገሩን በምሳሌ እንመልከት። በማታውቀው አገር ውስጥ በአውቶቡስ እየተጓዝክ ነው እንበል። አካባቢውን ስለማታውቅ መጨነቅ ትጀምራለህ። እንዲህ እያልክ ትጠይቅ ይሆናል:- ‘አሁን ያለሁት የት ነው? በእርግጥ ይህ አውቶቡስ የሚጓዘው በትክክለኛው አቅጣጫ ነው? ያሰብኩት ቦታ ለመድረስ ምን ያህል ይቀረኛል?’ ትክክለኛውን ካርታ እየተመለከትክና በመስኮት የመንገድ ምልክቶችን እየተከታተልህ ለጥያቄዎችህ መልስ ማግኘት ትችላለህ።
የወደፊቱን ሁኔታ ሲያስቡ ለሚጨነቁ ለብዙ ሰዎች ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እንዲህ እያሉ ይጠይቁ ይሆናል:- ‘ወዴት እያመራን ነው? የያዝነው ጎዳና ዓለም አቀፋዊ ወደሆነ ሰላም የሚያመራ ነው? ከሆነ የታሰበበት ቦታ ላይ የምንደርሰው መቼ ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ ልክ እንደ
ካርታው ከላይ ላሉት ጥያቄዎች መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። ይህንን መጽሐፍ በደንብ በማንበብና “በመስኮት” ከውጭ ያለውን የዓለም ሁኔታ በመከታተል በአሁኑ ጊዜ የት እንደምንገኝና ወዴት እያመራን እንዳለን ይበልጥ ለማወቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ ዛሬ ያሉብን ችግሮች እንዴት እንደጀመሩ መመልከት ያስፈልገናል።አሳዛኝ የሆነ ጅምር
አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ፍጹም አድርጎ እንደፈጠራቸውና ገነት በሆነ አካባቢ እንዳኖራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ለዘላለም እንጂ ለ70 ወይም ለ80 ዓመታት ብቻ ለመኖር አልነበረም። አምላክም “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው። የአምላክ ዓላማ አዳም፣ ሔዋንና ዘሮቻቸው መላዋን ምድር ገነት እንዲያደርጓት ነበር።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:8, 15, 22
ሆኖም አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ዓመጹ። በዚህም ምክንያት መኖሪያቸው የነበረችውን ገነት አጡ። ከዚህም በተጨማሪ አካላዊና አእምሯዊ ሁኔታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሄደ። አዳምና ሔዋን እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር መሞቻቸው እየተቃረበ ነበር። ለምን? ምክንያቱም በፈጣሪያቸው ላይ ጀርባቸውን በማዞር ኃጢአት ስለሠሩና “የኀጢአት ደመወዝ ሞት” ስለሆነ ነው።—ሮሜ 6:23
አዳምና ሔዋን ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ከወለዱ በኋላ በመጨረሻ ሞቱ። ታዲያ ልጆቻቸው የአምላክን የመጀመሪያ ዓላማ ሊፈጽሙ ይችላሉ? የወላጆቻቸውን አለፍጽምና በመውረሳቸው ምክንያት ይህን ማድረግ አይችሉም። እንዲያውም ኃጢአት ከአንዱ ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ስለሚተላለፍ ሁሉም የአዳም ዘሮች፣ እኛም ጭምር ኃጢአትና ሞት ወርሰናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል” በማለት ይናገራል።—ሮሜ 3:23፤ 5:12
አሁን ያለንበትን ሁኔታ ማወቅ
አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ የሰው ልጆች እስከ ጊዜያችን ድረስ የቀጠለ ረዥምና አስከፊ ጉዞ ጀመሩ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሰው ልጅ “ለከንቱነት ተዳርጎአል” ብሏል። (ሮሜ 8:20) ይህ አባባል የሰዎችን ትግል በደንብ አድርጎ ይገልጸዋል! ከአዳም ዘሮች መካከል በሳይንሱ ዓለም በጣም ድንቅ ችሎታ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች፣ በሕክምና እና በቴክኖሎጂ መስክ አዳዲስ ሐሳብ የሚያፈልቁ የተዋጣላቸው ሰዎች ይገኛሉ። ሆኖም ማናቸውም ቢሆኑ አምላክ ለሰው ልጆች የነበረውን ዓላማ ይኸውም ዓለም አቀፍ ሰላምም ሆነ ፍጹም ጤንነት ማምጣት አልቻሉም።
የአዳምና ሔዋን ዓመጽ እያንዳንዳችንን በግለሰብ ደረጃ ይነካናል። ከእኛ መካከል የፍትሕ መጓደል፣ የወንጀል ፍርሃት፣ ከባድ ሕመም የሚያስከትለው ሥቃይ ወይም ደግሞ የምንወደው ሰው ሲሞት የሚደርስብን ጥልቅ ሐዘን ያልነካው ማን አለ? ሕይወታችንን በሰላም እየመራን ያለን ሲመስለን በድንገት አንድ አሳዛኝ ነገር ይገጥመናል። አስደሳች አጋጣሚዎች ቢኖሩም እንኳ የእምነት አባት የነበረው ኢዮብ እንደገለጸው “ሰው፣ ዘመኑ አጭርና በመከራ የተሞላ ነው።”—ኢዮብ 14:1
የሰውን ልጆች ሕይወት አጀማመርና አሁን ያለንበትን አሳዛኝ ሁኔታ ስንመለከት የወደፊቱ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ሊመስለን ይችላል። ሆኖም አምላክ ይህ ሁኔታ ለዘላለም እንዲቀጥል እንደማይፈቅድ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጥልናል። አምላክ ለሰው ልጆች የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ኢሳይያስ 55:10, 11) ይህ ሁኔታ በቅርቡ እንደሚፈጸም እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
ወደ ግቡ ያደርሳል። (መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ጊዜ ‘የመጨረሻው ዘመን’ ብሎ በመጥራት የምንኖረው ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ እንደሆነ ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይህ አባባል የፕላኔቷ ምድርና በውስጧ ያለው ሕይወት በአጠቃላይ መጨረሻቸው መድረሱን የሚጠቁም አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሥርዓቱ መደምደሚያ ማለትም በአሁኑ ጊዜ ሐዘን የሚያስከትሉብን ሁኔታዎች መጨረሻ መድረሱን ማመልከቱ ነው። (ማቴዎስ 24:3) መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ጊዜ በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን ሁኔታዎችና ሰዎች የሚኖሯቸውን ባሕርያት ይገልጻል። በገጽ 8 ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ የተጠቀሱትን ሁኔታዎች ልብ በል፤ ከዚያም “በመስኮት” ከውጭ ያለውን የዓለም ሁኔታ ተመልከት። ካርታችን የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ አሁን ያለንበት ዘመን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ ሥርዓቱ መደምደሚያ የተቃረበ መሆኑን ይጠቁመናል። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላስ ምን ይሆናል?
የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል?
አዳምና ሔዋን ካመጹ በኋላ አምላክ “ፈጽሞ የማይፈርስ” መንግሥት የማቋቋም ዓላማ እንዳለው ወዲያውኑ አሳወቀ። (ዳንኤል 2:44) ብዙ ሰዎች በተለምዶ አባታችን ሆይ ተብሎ በሚጠራው ጸሎት ላይ ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ ተምረዋል፤ ይህ መንግሥት ለሰው ልጆች ይህ ነው የማይባል በረከት ያመጣላቸዋል።—ማቴዎስ 6:9, 10
የአምላክ መንግሥት በልብ ውስጥ የሚኖር ግልጽ ያልሆነ ሐሳብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሰማይ ያለ እውን መስተዳድር ሲሆን በምድር ላይ ከፍተኛ ሥራ ያከናውናል። አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ለሰው ልጆች ሊፈጽምላቸው ቃል የገባውን ነገር እንመልከት። አምላክ በመጀመሪያ ‘ምድርን ያጠፏትን እንደሚያጠፋ’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 11:18) ለእርሱ ታዛዥ ለሆኑት ሰዎችስ ምን ያደርግላቸዋል? በጽሑፍ የሰፈረው ቃሉ፣ ይሖዋ “እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም” ይላል። (ራእይ 21:4) ይህን ማድረግ የሚችል ሰው ይኖራል? ለሰው ልጆች ገና ከጅምሩ ያሰበውን ነገር መፈጸም የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።
የአምላክ መንግሥት ከምታመጣቸው በረከቶች መጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? ዮሐንስ 17:3 እንዲህ ይላል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ በሆነ የትምህርት መርሐ ግብር አማካኝነት ይህንን እውቀት ለሌሎች በማስተማር ሥራ ይካፈላሉ። አገልግሎታቸውን ወደ 230 ገደማ በሚሆኑ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ ሲያከናውኑ ጽሑፎቻቸው ደግሞ ከ400 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይታተማሉ። ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግህ በአካባቢህ ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“እናንተ ‘ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም’ የምትሉ እንግዲህ ስሙ። [ሕይወታችሁ] ነገ የሚሆነውን እንኳ አታውቁም።”—ያዕቆብ 4:13, 14
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ጀምሮ የሰውን ዘር ታሪክ ይገልጻል። የሰው ልጅ ሕይወት እንዴት እንደጀመረ እንዲሁም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ጭምር ይነግረናል። ካርታውን በደንብ እንደምናጠናው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳትም በጥልቅ ማጥናት ይኖርብናል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ኃጢአት” የተሳሳተ ድርጊትን ወይም ክፉ የማድረግ ዝንባሌን ያመለክታል። ስንወለድ ጀምሮ ኃጢአተኞች መሆናችን በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።”—መክብብ 7:20
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ጥቁር ነጥብ ያለበት ወረቀት ፎቶ ኮፒ ለማንሳት ብትፈልግ በሁሉም ኮፒዎች ላይ ጥቁሩ ነጥብ ይኖራል። እኛም የአዳም ዝርያዎች ወይም ኮፒዎች እንደመሆናችን መጠን የኃጢአት ነጥብ አለን። ልክ “የመጀመሪያው” ሰው አዳም የነበረው ዓይነት ምልክት አለብን
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
መጽሐፍ ቅዱስ ሰው “አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል” ይገልጻል። (ኤርምያስ 10:23) ይህ ደግሞ ሰዎች ለዓለም ሰላም ለማምጣት ያደረጉት ጥረት ውድቅ የሆነው ለምን እንደሆነ የሚያሳይ ነው። የሰው ዘር ከአምላክ ተለይቶ ‘አካሄዱን በራሱ አቃንቶ ለመምራት’ እንዲችል ተደርጎ አልተፈጠረም
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙራዊው ለአምላክ “ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” ብሎታል። (መዝሙር 119:105) ልክ እንደ መብራት መጽሐፍ ቅዱስም ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ሲያጋጥመን ጥበብ ያለበት እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል። ‘ለመንገዳችን ብርሃን’ በመሆን ከፊታችን ያለውን መንገድ ስለሚያሳየን የወደፊቱ ጊዜ ለሰው ልጆች ምን እንደያዘ ለመረዳት እንችላለን
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ብሩህ አመለካከት ከእውነታው አንጻር ሲታይ
በመስከረም 2000፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገሮች በ2015 ሊደርሱባቸው ያሰቧቸውን በርካታ እቅዶች በአንድ ድምፅ አጽድቀዋል። ከእነዚህም መካከል ከታች የተዘረዘሩት ይገኙበታል:-
▪ በቀን ከአንድ የአሜሪካ ዶላር ባነሰ ገቢ የሚኖሩና በረሃብ የሚሠቃዩ ሰዎችን ቁጥር በግማሽ መቀነስ።
▪ ሁሉም ልጆች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት እንዲጨርሱ ማድረግ።
▪ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ የጾታ እኩልነት እንዲኖር ማድረግ።
▪ ከአምስት ዓመት በታች ባለው ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ሕጻናት ላይ የሚከሰተውን ሞት 66 በመቶ መቀነስ።
▪ የእናቶችን ሞት 75 በመቶ መቀነስ።
▪ የኤች አይ ቪ/ኤድስን እንዲሁም እንደ ወባ ያሉ የሌሎች ከባድ በሽታዎችን ስርጭት መግታት።
▪ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ የማያገኙ ሰዎችን ቁጥር 50 በመቶ መቀነስ።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ግቦች ሊደረስባቸው የሚችሉ ናቸው? ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ የጤና ባለሞያዎች ቡድን ሁኔታዎቹን በ2004 እንደገና ከገመገሙ በኋላ፣ ከፍተኛ መሻሻል ይኖራል የሚለው ብሩህ አመለካከት ከእውነታው የራቀ ስለሆነ ሚዛናዊ መሆን አለብን በማለት ደምድመዋል። በ2005 የዓለም ሁኔታ የተባለው መጽሐፍ መቅድም እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “ድህነት አብዛኞቹ አካባቢዎች እንዳያድጉ እንቅፋት መሆኑን ቀጥሏል። ኤች አይ ቪ/ኤድስን የመሰሉ በሽታዎች ስርጭት እየጨመረ መምጣቱ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ በብዙ አገሮች በሚገኙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ከባድ የጤና ችግር እያስከተለ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ መከላከል በሚቻል ውኃ ወለድ በሽታ ምክንያት 20 ሚሊዮን የሚያህሉ ሕጻናት ሞተዋል። በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ እንዲሁም በቂ የደረቅ ቆሻሻና የፍሳሽ ማስወገጃ የሌላቸው በመሆኑ በየዕለቱ በችግርና ንጽሕና በጎደለው ሁኔታ ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ።”
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
‘የመጨረሻው ዘመን’ አንዳንድ ገጽታዎች
ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ጦርነት።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:4
ረሃብ።—ማቴዎስ 24:7፤ ራእይ 6:5, 6, 8
ቸነፈር።—ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8
የክፋት መግነን።—ማቴዎስ 24:12
የምድር መበላሸት።—ራእይ 11:18
ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ።—ሉቃስ 21:11
የሚያስጨንቅ ጊዜ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
ከመጠን ያለፈ የገንዘብ ፍቅር።—2 ጢሞቴዎስ 3:2
ለወላጆች አለመታዘዝ።—2 ጢሞቴዎስ 3:2
የተፈጥሮ ፍቅር መጥፋት።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
ከአምላክ ይልቅ ተድላን መውደድ።—2 ጢሞቴዎስ 3:4
ራስን አለመግዛት።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
መልካም የሆነውን አለመውደድ።—2 ጢሞቴዎስ 3:3
ከፊታችን የተደቀነውን አደጋ አለማስተዋል።—ማቴዎስ 24:39
ዘባቾች የመጨረሻውን ዘመን ማስረጃዎች አለመቀበላቸው።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
ስለ አምላክ መንግሥት በመላው ምድር መሰበክ።—ማቴዎስ 24:14
[ምንጮች]
© G.M.B. Akash/Panos Pictures
© Paul Lowe/Panos Pictures
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ የታወቁ ናቸው