በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለዘላለም ወጣት ሆኖ መኖር!

ለዘላለም ወጣት ሆኖ መኖር!

ለዘላለም ወጣት ሆኖ መኖር!

ከኢየሱስ ጎን ያለው ሰው ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይሞታል። ይህ ግለሰብ “ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” ሲል ለመነው። ኢየሱስም “እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” በማለት መለሰለት። (ሉቃስ 23:​42, 43) እውነት ነው፣ ይህ ስሙ ያልተጠቀሰ ሰው የሞተው ከእርጅና ጋር ተያይዞ በሚመጣ በሽታ ምክንያት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ወንጀለኛ በመሆኑ ሞት ስለተፈረደበት ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ግለሰብ ላይ ከደረሰው አስከፊ ሁኔታ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ትልቅ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ።

ይህ ሰው ያሳየውን ከፍተኛ እምነት ለማድነቅ እንገደዳለን! ምንም እንኳ ኢየሱስ ራሱ ከጎኑ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ ያለ ቢሆንም ሰውየው ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛ ምንም አልተጠራጠረም። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ እርሱን አንድ ቀን በመልካም ሊያስበው እንደሚችል እምነት ነበረው። ይህ ሞት የተፈረደበት ሰው ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድራት ውብ ገነት ውስጥ ለመኖር ከሞት ሲነሳ እስቲ አስበው!

የሰው ዘር ሞት ተፈርዶበት ከነበረው ከዚህ ወንጀለኛ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። እንዴት? በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ እንገኝ ሁላችንም የኃጢአትን ደሞዝ እንከፍላለን እንዲሁም መዳን የምንችልበት ዝግጅት ያስፈልገናል። (ሮሜ 5:​12) እንደ ወንጀለኛው ሁሉ እኛም የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ለመጠባበቅ ክርስቶስ ኢየሱስን መመልከት ይኖርብናል። ይህም በኋለኞቹ ዓመታት ከሚከሰቱት የጤና ችግሮች ለመገላገል ተስፋ ማድረግን ይጨምራል! ደግሞም ኢየሱስ የሰው ዘሮች በአጠቃላይ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹም ሆነው ለዘላለም እንደሚኖሩ ተስፋ ሰጥቷል።​—⁠ዮሐንስ 3:​16, 36

ለወጣቶችም ሆነ ለአረጋውያን ሁሉም ነገር አዲስ ይሆናል

የክርስቶስ መንግሥት ምድርን ሲያስተዳድር በእርሷ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ‘በታላቅ ሰላም ሐሤት ያደርጋሉ።’ (መዝሙር 37:​11) ማንም “ታምሜአለሁ” አይልም። (ኢሳይያስ 33:​24) ጋሬጣ ሆነው የቆዩብን አካላዊ ጉዳቶች በሙሉ ተወግደው በምትኩ “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 35:​6) በዕድሜ የገፉ ሰዎች የወጣትነት ጉልበታቸውን መልሰው ያገኛሉ፤ ሥጋቸውም “እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል።”​—⁠ኢዮብ 33:25

ይሁንና እንዲህ ዓይነት ተስፋ ይፈጸማል ብሎ መጠበቅ ምክንያታዊነት ነው? አብሮት ተሰቅሎ ለነበረው ወንጀለኛ በገነት የመኖር ተስፋ ስለሰጠው ሰው መለስ ብለህ አስብ። በተደጋጋሚ ጊዜ ሕዝቡ ሽባና ጉንድሽ የሆኑ እንዲሁም ማየትና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ወደ ኢየሱስ ያመጡ ነበር። እርሱም በደስታ ‘ደዌንና ሕመምን ሁሉ ይፈውስ’ ነበር። (ማቴዎስ 9:​35, 36፤ 15:​30, 31፤ ማርቆስ 1:​40-42) የእርሱ መንግሥት ምን እንደሚያከናውን በተጨባጭ አሳይቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል። (ሉቃስ 7:​11-17፤ ዮሐንስ 11:​38-44) ይህን በማድረግ “መቃብር ውስጥ ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል” በማለት የገባውን ቃል አጠናከረው።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ የሐዋርያት ሥራ 24:​15

አዲስ አካል፣ ጥርት ያለ እይታ፣ የአእዋፋት ዝማሬና የደስታ ድምፅ የሚያዳምጥ ጆሮ፣ እጅና እግር ከበሽታ ተላቅቆ እንዲሁም ጤናማ አእምሮ ይዘህ በገነት ውስጥ ከሞት ስትነሣ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። የእርጅና ዘመን ይዞት የሚመጣው “የጭንቀት ጊዜ” ለዘላለሙ ይወገዳል። (መክብብ 12:​1-7፤ ኢሳይያስ 35:​5, 6) ሞት እንኳ ሳይቀር ‘ይደመሰሳል’፤ አዎን፣ ‘በድል ይዋጣል።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​26, 54

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ክስተቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አንጻር ስናያቸው እርጅና ወደሚጠፋበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረብን እንደሆነ እንረዳለን። (ማቴዎስ 24:​7, 12, 14፤ ሉቃስ 21:​11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) በአምላክ ላይ እምነት ጥለው እርሱን ሲያገለግሉ የነበሩ አረጋውያን ለዘላለም ወደ ወጣትነት ጉልበታቸው የሚመለሱበት ጊዜ በጣም ቀርቧል!

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አእምሮህን አሠራው!

አካላዊ እንቅስቃሴ ጡንቻን እንደሚያጠነክር ሁሉ አእምሮን ማሠራትም አንጎልን ያጎለብታል። አእምሮን ለማነቃቃት አዳዲስ ነገሮችን መሥራት ይኖርብናል። ከዚህ በታች የአንጎል ሴሎች እርስ በርሳቸው ግንኙነት እንዲፈጥሩም ሆነ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ቀርበዋል።

▪ ከዚህ በፊት የማታደርጋቸው የነበሩ አዳዲስ ነገሮችን ለማድረግ ጥረት አድርግ። እነዚህም የሥነ ጥበብ ሥራዎችን መሥራት፣ እንቆቅልሽ፣ ጂክሶው ፐዝል እና ክሮስ ወርድ ፐዝል የመሳሰሉትን ጨዋታዎች መጫወት፤ እንዲሁም አዲስ ቋንቋ መማርን ሊያካትቱ ይችላሉ።

▪ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ተቀራረብ። በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግና ከሰዎች ጋር መግባባት ሕይወት አሰልቺ እንዳይሆንብህ ከመርዳቱም በላይ አእምሮን ያጎለብታል።

▪ መንፈሳዊነትህን ኮትኩት። “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።”​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

▪ ጥሩ ጥሩ ጽሑፎችን አንብብ፤ ከዚያም ያነበብከውን ነገር ለሌላ ሰው ተናገር።

▪ የአጭርና የረጅም ጊዜ የማስታወስ ችሎታህን ለማሠራት ከሬዲዮና ከቴሌቪዥን የምታዳምጣቸውን ዜናዎች አስታውስ እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ጋር አያይዛቸው።

▪ ቴሌቪዥን ለመክፈት፣ ስልክ ለመደወል እና ጥርስህን ለመቦረሽ አዘውትረህ የማትሠራበትን እጅ ተጠቀም (አዘውትረህ በቀኝ እጅህ የምትሠራ ከሆነ በግራህ፤ በግራህ የምትሠራ ከሆነ ደግሞ በቀኝ እጅህ መጠቀም ማለት ነው)።

▪ በተቻለህ መጠን በቀን ውስጥ ሁሉንም የስሜት ሕዋሶችህን አሠራቸው።

▪ በአቅራቢያህም ይሁን በርቀት የሚገኙ አስደናቂ ቦታዎችን ለማወቅና ለመጎብኘት ጣር።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በሥቃይ የተሞላው የእርጅና ዘመን በቅርቡ ጠፍቶ በምትኩ ለዘላለም ወጣት ሆኖ የሚኖርበት ዓለም