አልሃምብራ—በግራናዳ የሚገኝ የሙስሊሞች ዕንቁ
አልሃምብራ—በግራናዳ የሚገኝ የሙስሊሞች ዕንቁ
ስፔን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“በዚህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሕንፃ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አንዳንዶቹ እውነተኛ ሌሎቹ ደግሞ የተጋነኑ በርካታ አፈ ታሪኮችና ወጎች ተነግረዋል፤ ከፍቅር፣ ከጦርነትና ከልዑላን ቤተሰብ ጋር የተያያዙ ብዛት ያላቸው ዘፈኖችና የፍቅር ዜማዎች በአረብኛም ሆነ በስፓንኛ ተቀናብረዋል!”–ዋሽንግተን ኧርቪንግ፣ የ19ኛው መቶ ዘመን አሜሪካዊ ጸሐፊ
ለእነዚህ ቃላት መጻፍ ምክንያት የሆነው ዝነኛ ቦታ፣ የስፔን ከተማ ለሆነችው ለግራናዳ ድምቀት የሚጨምርላት አልሃምብራ የተባለው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ቤተ መንግሥት ነው። አልሃምብራ በደቡብ አውሮፓ የሚገኝ የአረብ ወይም የፋርስ የግንባታ ሞዴል ነው። ይህን በግንብ የታጠረና በጣም የሚያምር ቤተ መንግሥት የገነቡት ሙስሊም ሙሮች ናቸው። ሙሮች በስፔን ለበርካታ መቶ ዘመናት የዘለቀ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። *
በትውልዱ አረብ የሆነው አሚር ዛዊ ቤን ዚሪ በ11ኛው መቶ ዘመን ራሱን የቻለውን የግራናዳ መንግሥት አቋቋመ። ይህ መንግሥት ለ500 ዓመታት ገደማ የዘለቀ ሲሆን በዚህ ጊዜ በሥነ ጥበብም ሆነ በባሕል ከፍተኛ እድገት አድርጓል። በመጨረሻ ወደ ፍጻሜው የመጣው ካቶሊክ የሆኑት ንጉሥ ፈርዲናንድና ንግሥት ኢዛቤላ በስፔን የሙስሊሞች አገዛዝ እንዲያከትም ባደረጉበት በ1492 ነበር።
የሙሮች ከተማ የሆነችው ግራናዳ በሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችው ኮርዶባ በ1236 በሕዝበ ክርስትና ወታደሮች ድል ከተደረገች በኋላ ነበር። በዚህ ጊዜ ግራናዳ በስፔን የሚኖሩ ሙስሊሞች ዋና ከተማ የተደረገች ሲሆን በየተራ የተነሱት ገዥዎችም በርካታ የቤተ መንግሥት ሕንፃዎች ያቀፈውን አልሃምብራን ገንብተዋል። አውሮፓ ውስጥ እንደዚህ የመሰለ ቦታ ፈጽሞ አይገኝም። በዚህ ቀልቡ የተማረከ አንድ ጸሐፊ “በመላው ዓለም በአስደናቂነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሕንፃ ነው” ሲል ገልጾታል።
አልሃምብራ የሚገኝበት አካባቢ ራሱ የሕንፃዎቹን ያህል ግርማ ሞገስ የተላበሰ ነው። ከ3, 400 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸውና አናታቸው በበረዶ የተሸፈነው የሲራ ኔቫዳ ተራሮች ከበስተ ኋላው ገዝፈው ይታያሉ። አልሃምብራ ራሱ ደግሞ የተቀመጠው ከግራናዳ 150 ሜትር ከፍታ ባለው ሳቢካ በተባለ በጫካ የተሸፈነ ረዥም ኮረብታ ላይ ነው። በ14ኛው መቶ ዘመን የኖረው ኢበን ዛምራክ የተባለ ገጣሚ ልክ አንድ ባል ሚስቱን በአድናቆት ትክ ብሎ እንደሚያያት ያህል ኮረብታውም ግራናዳን ቁልቁል ይመለከተዋል ሲል ገልጿል።
በከተማ ውስጥ ያለ ሌላ ከተማ
በአረብኛ “ቀዩ” የሚል ትርጉም ያለው አልሃምብራ የሚለው ስም ሙሮች ከውጭ በኩል ያለውን የግንቡን ክፍል ለመገንባት የተጠቀሙበትን ጡብ ቀለም የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ይሁንና አንዳንዶች፣ የአልሃምብራ የግንባታ ሥራ የተካሄደው “የሚነድድ ችቦ በሚፈነጥቀው ብርሃን” እንደሆነ የአረብ የታሪክ ምሑራን የሚናገሩትን መቀበል ይመርጣሉ። በማታ የሚታየው ይህ የእሳት ነጸብራቅ ግድግዳዎቹ ቀይ ቀለም እንዲኖራቸው እንዳደረገና ስሙ የተገኘውም ከዚህ እንደሆነ ይናገራሉ።
አልሃምብራ ቤተ መንግሥት መባሉ ሲያንሰው ነው። እንዲያውም በግራናዳ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሌላ ከተማ ሊባል ይችላል። ብዙ ርቀት በሚሸፍነው የግንብ አጥር ውስጥ የመናፈሻ ቦታዎች፣ ነጠል ብለው የሚገኙ ቤቶች፣ በርካታ የቤተ መንግሥት ሕንፃዎች፣ አልካሳባ ወይም ምሽግ ብሎም ትንሽ ከተማ (በአረብኛ መዲና ይባላል) ይገኛሉ። በሙሮች ንድፍ የተሠራው የአልሃምብራ ክፍል እንዲሁም ከጊዜ በኋላ የተገነቡት ተጨማሪ ሕንፃዎች፣ በአውሮፓ የተሐድሶ ዘመን ከተገነቡት ጠንካራና በጥንቃቄ የተሠሩ ሕንፃዎች ጋር በአንድነት ሲታዩ አልሃምብራ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ውበትና ውስብስብ የአረብ ሥነ ጥበብ እንዲንጸባረቅበት አድርገዋል።
አልሃምብራ፣ ሙሮችና የጥንት ግሪኮች በሚጠቀሙበት የግንባታ ዘዴ የተሠራ መሆኑ ከፍተኛ ውበት አላብሶታል። በመጀመሪያ፣ የሚያምር ሕብርና መጠን እንዲሁም ያልተወሳሰበ የግንባታ ስልት በመጠቀም የድንጋዩን ቀለምና ይዘት ሳይለውጡ ሕንፃውን ይገነባሉ። ከዚያ በመቀጠል በሚያምር ሁኔታ የተገነባውን ሕንፃ ያስውቡታል። አንድ ባለሙያ “ሙሮች ሕንፃውን ራሱን ማስጌጥ እንጂ ሕንፃውን ለማስዋብ ተጨማሪ ነገር መሥራት አያስፈልግም የሚለውን የሥነ ሕንፃ ጠበብት የሚከተሉትን የግንባታ ሥራ ተቀዳሚ ደንብ ሲሠሩበት ቆይተዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
አልሃምብራን መጎብኘት
ወደ አልሃምብራ የሚገባው የፈረስ ጫማ የሚመስል ቅርጽ ባለው የፍትሕ በር ተብሎ በሚጠራ ግዙፍ ቅስት በኩል በማለፍ ነው። የበሩ ስም በሙስሊሞች የግዛት ዘመን እምብዛም ከባድ ላልሆኑ ችግሮች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት በዚህ ቦታ ይሰየም የነበረውን ችሎት ያስታውሰናል። የከተማ በር ላይ ተቀምጦ ፍርድ መስጠት በመካከለኛው ምሥራቅ የተለመደ ባሕል የነበረ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተጠቅሷል። *
እንደ አልሃምብራ ያሉት አረቦች የሚገነቧቸው ቤተ መንግሥቶች ውስብስብ የሆነ ጌጥ የሚሠራላቸው በስቱኮ ነው። የእጅ ባለሞያዎቹ ይህን ማጣበቂያ የማሰሪያ ቅርጽ ያስይዙትና
በተመሳሳይ ቅርጽ ብዙ ጊዜ ይደጋግሙታል። አንዳንድ በሚያምር ሁኔታ የተገነቡ ቅስቶች ተለክተው የተሠሩ ከላይ ወደታች የተንጠለጠሉ ድንጋዮች ይመስላሉ። ሌላው የቤተ መንግሥቱ ገጽታ ዚልኢዝ የሚባሉት ነገሮች ሲሆኑ እነዚህም ውስብስብ ንድፍ ያላቸው የተቆራረጡ ደማቅ የግድግዳ ንጣፎች ናቸው። እነዚህ ንጣፎች የግድግዳውን ታችኛ ክፍል ደማቅ በሆኑ ቀለማት ያስዋቡት ሲሆን ከላይ ካለው ደብዘዝ ያለ የስቱኮ ቀለም ጋር ጥሩ ቅንጅት ይፈጥራሉ።በአልሃምብራ ከሚገኙት ግቢዎች መካከል በጣም የሚያምረው የአንበሶች ግቢ የሚባለው ሲሆን “በስፔን ከሚገኙት ሁሉ የላቀ በጣም አስደናቂ የአረቦች የሥነ ጥበብ ሥራ” እንደሆነ ተገልጿል። በአገሪቱ የታተመ ለጎብኚዎች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “አስመስሎ ወይም በድጋሚ ለመሥራት የማይቻል እውነተኛ የሥነ ጥበብ ሥራ እንደሆነ የሚያሳይ መስህብ አለው። . . . አንድ ሰው በግራናዳ በሚገኘው በዚህ ግቢ ውስጥ ሲሆን የሚያድርበት ስሜት ይህ ነው።” በእብነ በረድ የተሠሩ 12 አንበሶች በተሸከሙት ውኃ የያዘ ገንዳ ዙሪያ እኩል መጠን ያላቸው ቅስቶችና ቀጫጭን አምዶች ይገኛሉ። ይህ ስፔን ውስጥ ብዙዎች ፎቶግራፍ ከሚያነሷቸው ቦታዎች አንዱ ነው።
መንፈስ የሚያድሱ መናፈሻዎች
ከዚህ በተጨማሪ በአልሃምብራ መናፈሻዎች፣ ፏፏቴዎችና የመዋኛ ገንዳዎች ይገኛሉ። * ኤንሪኬ ሶርዶ የሙሮች ስፔን በሚለው መጽሐፋቸው ላይ “የአረቦች የመናፈሻ አሠራር የገነት ቅምሻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። በቦታው እስላሞች እንደነበሩ የሚጠቁሙ ብዙ ነገሮች ማየት ይቻላል። ስፔናዊው ጸሐፊ ጋርሲያ ጎሜዝ “ቁርዓን ላይ፣ የሙስሊሞች ገነት የጠሩ ወንዞች ውኃ የሚያጠጡት . . . አትክልት የሞላበት መናፈሻ እንደሆነ በዝርዝር ተገልጿል” ሲሉ ዘግበዋል። በበረሃ ለሚኖሩ ሰዎች ውኃ ብርቅ ቢሆንም አልሃምብራ ውስጥ የውኃ ፍጆታ በጣም ከፍተኛ ነው። የመናፈሻውን ንድፍ ያወጡት ሰዎች ውኃ አካባቢውን ሊያቀዘቅዝ እንደሚችልና ሲፈስ የሚያሰማው ድምፅ ለጆሮ እንደሚጥም ተገንዝበው ነበር። ጥርት ያለውን ሰማይ የሚያንጸባርቁት አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸው የውኃ ገንዳዎች ቦታው ሰፊና ብሩህ ሆኖ እንዲታይ ያደርጋሉ።
* ይህ ቪላ በፊት ከአልሃምብራ ቤተ መንግሥት ጋር በድልድይ ይገናኝ የነበረ ሲሆን የግራናዳ ገዥዎች የሚዝናኑበት ቤት ሆኖ አገልግሏል። በዚያ ያለ መተላለፊያ የውኃ ደረጃ ወደሚባለው ቦታ ያደርሳል። በዚህ ቦታ ጎብኚዎች በሚያዩት ብርሃንና የቀለም ዓይነት እንዲሁም በሚያሸቱት የተለያዩ የአበቦች መዓዛ ስሜታቸው ይማረካል።
ከአልሃምብራ ብዙም ሳይርቅ ሳቢካ አጠገብ በሚገኘው ሴሮ ዴል ሶል በሚባለው ኮረብታ ላይ ኼኔራሊፌ የሚባል ለብቻው ያለ የሙሮች ቪላ ቤትና መናፈሻ ይገኛል። አረቦች አካባቢውን የሚያስውቡበትን መንገድ በተመለከተ ለአብነት ሊጠቀስ የሚችለው ኼኔራሊፌ “በዓለም ላይ ካሉ በጣም የሚያምሩ መናፈሻዎች አንዱ” እንደሆነ ተገልጿል።ሙሮች እርማቸውን ያወጡበት ቦታ
የግራናዳ የመጨረሻው ንጉሥ ቦአብዲል (ሙሐመድ አሥራ አንደኛ) እጅ ሰጥቶ ከተማዋን ለፈርዲናንድና ለኢዛቤላ ከለቀቀ በኋላ እርሱና ቤተሰቡ ተሰድደው ሄዱ። ከተማዋን ለቅቀው ከሄዱ በኋላ አሁን ኤል ሱስፒሮ ዴል ሞሮ (ሙሮች እርማቸውን ያወጡበት ቦታ) በመባል የሚጠራ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ለጥቂት ጊዜ እንደቆሙ ይነገራል። በጣም የሚያምረውን ቀዩን ቤተ መንግሥታቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ዞር ብለው ሲመለከቱ የቦአብዲል እናት “እንደ ወንድ ማስጣል ላልቻልከው ከተማ እንደ ሴት አልቅስላት!” እንዳለችው ይተረካል።
በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ አልሃምብራን ከሚጎበኙ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ወደዚያ ቦታ ይሄዳሉ። ከዚህ ቦታ ሆነው እነርሱም እንደ ቦአብዲል በዘውድ ላይ ያለ ዕንቁ ከሚመስለው የአረቦች ቤተ መንግሥት ሥር የሚገኘውን የግራናዳን ከተማ አሳምረው መቃኘት ይችላሉ። አንድ ቀን አንተም ግራናዳን የመጎብኘት አጋጣሚ ካገኘህ የመጨረሻው የሙሮች ንጉሥ የተሰማውን ሐዘን መረዳት ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.4 በ711 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአረብና የበርበር ወታደሮች ስፔን የገቡ ሲሆን በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በሙስሊሞች ቁጥጥር ሥር ሆኖ ነበር። በሁለት ምዕተ ዓመት ጊዜ ውስጥ ኮርዶባ የተባለችው ከተማ አውሮፓ ውስጥ በስፋቷና ምናልባትም በሥልጣኔዋ ቀዳሚ ለመሆን በቅታለች።
^ አን.13 ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለሙሴ “በአገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና አለቆችን ሹም፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድ ይፍረዱ” የሚል መመሪያ ሰጥቶት ነበር።—ዘዳግም 16:18 የ1954 ትርጉም
^ አን.17 የፋርስና የባይዛንታይን የመናፈሻ ዓይነቶችን በስፔንም ሆነ በመላው የሜድትራኒያን ክልል ያስተዋወቁት አረቦች ናቸው።
^ አን.18 ይህ ስም የተገኘው “ጄኔት አል አሪፍ” ከሚለው አረብኛ ቃል ሲሆን አንዳንድ ጊዜ “ከፍታ ቦታ ላይ ያሉ መናፈሻዎች” ተብሎ ተተርጉሟል። ሆኖም ቃሉ “የንድፍ አውጪው መናፈሻ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አልካሳባ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንበሶች ግቢ
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኼኔራሊፌ መናፈሻዎች
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የውኃ ደረጃ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የመስመሩ ንድፍ:- EclectiCollections
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከላይ ካለው በስተቀር ሌሎቹ ፎቶዎች በሙሉ:- Recinto Monumental de la Alhambra y Generalife
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁሉም ፎቶዎች:- Recinto Monumental de la Alhambra y Generalife
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]
ከላይ ያሉት ፎቶዎች:- Recinto Monumental de la Alhambra y Generalife; ከታች ያለው ፎቶ:- J. A. Fernández/San Marcos