በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

▪ የስፔን መንግሥት ከሚሰበስበው ቀረጥ ውስጥ 0.5 በመቶ የሚሆነውን እንደ ከፋዩ ምርጫ ለበጎ አድራጊዎች አሊያም ደግሞ ለካቶሊክ ድርጅቶች ለመስጠት ወሰነ። ከስፔናውያን መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ካቶሊክ ነን ቢሉም ቀረጡ ለቤተ ክርስቲያኗ እንዲሰጥ የወሰኑት 20 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው።ኤል ፓዪስ፣ ስፔን

▪ ኢንስቲትዩት ኦቭ አክቱዋሪስ ባዘጋጀው የሕይወት ሠንጠረዥ መሠረት “በ30 ዓመት ሲጋራ አጫሽ መሆን የወንድን አማካይ ዕድሜ በ5 ዓመት ተኩል የሴትን ደግሞ ከ6 ዓመት ተኩል በላይ ይቀንሳል።” ነገር ግን በ30 ዓመታቸው ማጨስ የሚያቆሙ ሰዎች ከሲጋራ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ ሕመሞች የመሞት አጋጣሚያቸው በእጅጉ ይቀንሳል።ዘ ታይምስ፣ እንግሊዝ

▪ በ2004 የዓለም የነዳጅ ፍጆታ በ3.4 በመቶ ከፍ ብሏል፤ ይህም በቀን 82.4 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ጥቅም ላይ ይውላል ማለት ነው። ከተጨመረው ፍጆታ ውስጥ ግማሽ ያህሉን የሚጠቀሙት ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ሲሆኑ ዩናይትድ ስቴትስ 20.5 ሚሊዮን በርሜል፣ ቻይና ደግሞ 6.6 ሚሊዮን በርሜል በቀን ይጠቀማሉ።ቫይታል ሳይን 2005፣ ዎርልድዋች ኢንስቲትዩት

“እናትህን አድንቅ”

ትምህርት ቤት ለመግባት የደረሱ ሁለት ልጆች ያሏት አንዲት ካናዳዊት የቤት እመቤት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያን ጨምሮ ለምታከናውነው ሥራ ሁሉ ቢከፈላት በዓመት የ130, 000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ደሞዝተኛ ልትሆን እንደምትችል ስለ ሥራ ትንታኔ የሚሰጡ ሰዎች ይገምታሉ። ቫንኩቨር ሰን የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው ይህ ስሌት የተገኘው በአሁኑ ጊዜ ባለው አማካይ የደሞዝ መጠን ሲሆን “በሳምንት 100 ሰዓት ማለትም ስድስት ቀናት 15 ሰዓትና አንድ ቀን ደግሞ 10 ሰዓት እንደምትሠራ” ተደርጎ ታስቦ ነው። ቤት ውስጥ የምትውል አንዲት እናት እንደ ሞግዚት፣ አስተማሪ፣ ሹፌር፣ የቤት ሠራተኛ፣ ወጥ ቤት፣ አስታማሚ፣ የጥገና ሠራተኛ እና የመሳሰሉትን ሆና ትሠራለች። ጋዜጣው “እናትህን አድንቅ፤ ምክንያቱም እየሠራች ያለችው ዝቅተኛ ደሞዝ እየተከፈላት ሊሆን ይችላል” የሚል ምክር ሰጥቷል።

የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በተመለከተ ግራ የተጋቡ ወጣቶች

“የራሳቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርት እየፈጠሩ” ያሉ ወጣት ፊንላንዳውያን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን በዚያው አገር የሚገኘው ዩቨስኩላ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው መግለጫ ያሳያል። ብዙውን ጊዜ በዘመናችን ያሉ “ሰዎች ልክ ከገበያ ዕቃ የሚገዙ ይመስል የሚያምኑባቸውን ነገሮች ከዚህም ከዚያም ያሰባስባሉ” በማለት ዘገባው ገልጿል። አንዳንድ ጊዜ ይህን ተከትሎ የሚመጣው ውጤት እርስ በርሱ ይጋጫል። ለምሳሌ ያህል ወጣቶቹ፣ ሁሉም ሰው እኩል ሀብትና ብልጽግና ሊኖረው እንደሚገባ ቢያምኑም “ዓይን ያወጣና ጭካኔ የተሞላበት ውድድር ማድረግ እንደሚገባ ማሰብ ጀምረዋል።”

ፕሪዮን ያለበት ደም መውሰድ የሚያስከትለው አደጋ

ፍሬንች ሄልዝ ኤንድ ሴፍቲ ኤጀንሲ ፎር ሜዲካል ፕሮዳክትስ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው ደም ሲወሰድ ፕሪዮን ማለትም የተበላሸ ፕሮቲን ወደ ደም ወሳጁ ሰውነት ‘ሊገባ ይችላል’ የሚለውን መላ ምት፣ ‘መግባቱ አይቀርም’ ወደሚል ደረጃ ከፍ አድርጎታል። ፕሪዮን የሚባሉት የፕሮቲን ሞለኪዩሎች፣ ሰዎችን የሚያጠቃውና በተለያየ መልክ የሚከሰተውን ክሮይትስፌልት ያኮፕ (ቪሲጄዲ) የተባለ በሽታ እንደሚያስከትሉ ይገመታል። እስከ አሁን መድኃኒት ያልተገኘለትና የሰውን የነርቭ ሕዋሶች የሚያጠቃው ይህ ገዳይ በሽታ፣ ቦቫይን ስፖንጂፎርም ኢንሴፈሎፐቲ ወይም በአብዛኛው የእብድ ላም በሽታ ተብሎ ከሚጠራው በሽታ ጋር ይመሳሰላል። ሁኔታው ቀደም ሲል ይታሰብ ከነበረው ይበልጥ አደገኛ እንደሆነ የተገለጸው በብሪታንያ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች፣ ክሮይትስፌለት ጃኮፕ የተባለ በሽታ የተላለፈባቸው ደም ሲወስዱ ሳይሆን እንዳልቀረ ከተረጋገጠ በኋላ ነው። የበሽታው ምልክት መታየት ከመጀመሩ በፊት አንድ ሰው ይህ በሽታ እንዳለበት ለማወቅ የሚያስችል አስተማማኝ ምርመራ የለም።

የመቅጠን ምኞት

ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ “የአምስት ዓመት ልጆች ሳይቀሩ በሰውነታቸው እንደማይደሰቱና ቀጭን መሆን እንደሚፈልጉ” በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው ጥናት እንዳረጋገጠ ዘግቧል። ዘገባው ከአምስት እስከ ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን አውስትራሊያውያን ልጃገረዶችን ያካተተ ጥናት ይጠቅሳል። ጥናቱ ከተካሄደባቸው ልጃገረዶች ግማሽ የሚያህሉት በጣም ቀጭን መሆን እንደሚፈልጉ የገለጹ ሲሆን ከዚህ ጋር የሚመጣጠን ቁጥር ያላቸው ልጃገረዶች ደግሞ “ክብደት ከጨመሩ ምግብ እንደሚቀንሱ” ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አንዲት ሴት ስለ ሰውነት ቅርጽ የተሳሳተ አስተሳሰብ መያዝ “በቀሪው የሕይወት ዘመን ራስን ዝቅ ወደ ማድረግ፣ ወደ ጭንቀትና የተዛባ የአመጋገብ ልማድ ወደ ማዳበር ሊመራ ይችላል” በማለት ተናግረዋል።