በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ሠራሽ እጅና እግር ማዕከልን መጎብኘት

የሰው ሠራሽ እጅና እግር ማዕከልን መጎብኘት

የሰው ሠራሽ እጅና እግር ማዕከልን መጎብኘት

ኒው ዚላንድ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ዌሊንግተን፣ ኒው ዚላንድ በሚገኘው የሰው ሠራሽ እጅና እግር ማዕከል ቀጠሮ የያዝኩት በሁለት ምክንያቶች ነበር። አንደኛ፣ ሰው ሠራሽ እግሬ ጥቂት ጥገና ያስፈልገው ነበር። ሁለተኛ፣ ሰው ሠራሽ እጅና እግር እንዴት እንደሚሠራ ይበልጥ ማወቅ እንድችል ማዕከሉን መጎብኘት ፈልጌ ነው።

ሐኪሜ ማዕከሉን ለመጎብኘት ያቀረብኩትን ጥያቄ በደስታ ተቀበለ። ጉብኝቱ ጥሩ እውቀት እንዳገኝ የረዳኝ ከመሆኑም በላይ በዚህ መስክ የተሠማሩ ጥበበኛና ትጉ ባለሙያዎች ለሚያደርጉት ጥረት የነበረኝን አድናቆት ከፍ አድርጎልኛል።

የጎደለን የሰውነት ክፍል በሰው ሠራሽ አካል መተካት ፕሮስቲሲስ ይባላል። ከዚህ ሙያ ጋር ተያያዥነት ያለው የእውቀት ዘርፍ ፕሮስቴቲክስ የሚባል ሲሆን ይህ እውቀት ያለው ባለሙያ ደግሞ ፕሮስቴቲስት ተብሎ ይጠራል።​—ኢንሳይክሎፒዲያ ኤንድ ዲክሽነሪ ኦቭ ሜድስን፣ ነርሲንግ ኤንድ ኧላይድ ሄልዝ፣ ሰርድ ኤዲሽን

ሰው ሠራሽ እግር የሚሠራው እንዴት ነው?

ወደ ማዕከሉ ከሚሄዱት ታካሚዎች ውስጥ አብዛኞቹ ሰው ሠራሽ እግር የሚፈልጉ ናቸው። ሥራው የሚጀመረው፣ እርጥብ ጀሶ ውስጥ የተነከረ ፋሻ በተቆረጠው እግር ላይ በመጠቅለልና እንዲደርቅ በማድረግ ነው። ከደረቀ በኋላ ከሰውየው አካል ላይ ተነቅሎ ይወጣና ውስጡ ጀሶ በማፍሰስ ተቆርጦ ከቀረው ቦታ ጋር አንድ ዓይነት የሆነ ቅርጽ ይሠራል። በዚህ ናሙና በመጠቀም የሰውየውን እግር ከሰው ሠራሹ እግር ጋር የሚያገጣጥመው ነገር ይሠራል። በዚህ መንገድ የተቆረጠው እግር ይሰጥ የነበረውን ግልጋሎት ሙሉ በሙሉ ሊተካ የሚችል ሰው ሠራሽ እግር መሥራት ይጀመራል። የተቆረጠውን ሰውነት ጫፍ ለመለካትና በልኩ ለመሥራት የሚረዱ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን በቅርቡ መጠቀም ተጀምሯል። ከዚያም በቀረው የሰውየው እግር ላይ በትክክል እንዲገጥም ተደርጎ በማሽን ይቀረጻል።

በማዕከሉ ውስጥ የሚከናወነውን ሥራ ከተመለከትሁ በኋላ ሌላ ቦታ ተዘጋጅተው የሚመጡ ሰው ሠራሽ የአካል ክፍሎች አየሁ። ካየኋቸው አስደናቂ ነገሮች መካከል በሙቀት አማካኝነት ቅርጽ ወጥቶለት ለበሽተኛው እንዲመች ተደርጎ ሊበጅ ከሚችል የፕላስቲክ ሶኬት ጋር የሚገጥም ሃይድሮሊክ ጉልበት ይገኝበታል። እንዲህ ያሉትን ሰው ሠራሽ የሰውነት ክፍሎች ናሙና በስፋት የያዙ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰበሰቡ ካታሎጎች በማዕከሉ ይገኛሉ።

ከዚያም መግጠሚያው፣ ጉልበቱ፣ ቆዳውና መዳፉ እንደ ተፈጥሮ እግር እንዲያራምዱ የመጨረሻው የማስተካከያ ሥራ ይከናወናል። በመቀጠልም የፕላስቲክ ሽፋን ይደረግለታል። ይህም የሰው ሠራሹን እግር “አጥንቶች” ለመሸፈን ይረዳል። ሰው ሠራሹ እግር ከቀረው የሰውነት ክፍል ጋር እንዲመሳሰል ለማድረግ ይቀባባል።

በሽተኛው ያለስጋት መርገጥ እንዲችል ልምምድ ካደረገ በኋላ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኝ የአጥንት ሐኪም እንዲያየው ዝግጅት ይደረጋል። በዚህ መንገድ ሰውየው የተገጠመለትን እግር ጥሩ አድርጎ ይጠቀምበት እንደሆን ባለሙያዎች የመጨረሻውን ማጣሪያ ያደርጋሉ።

ሕፃናት ታካሚዎችና አትሌቶች

በጉብኝት ላይ ሳለሁ አንዲት ትንሽ ልጅ ላይ ዓይኔ አረፈ። የተቆረጠውን ሰውነቷንና ሰው ሠራሽ እግሯን ስታሳየን ምንም አላፈረችም። ቆየት ብሎም ምንም ሳይመስላት ስትዘል አየኋት።

እኔን የሚያክመኝ ባለሙያ፣ እጃቸውን ወይም እግራቸውን ስላጡ ሕፃናት ምን እንደሚናገር ለመስማት ጓጓሁ። አንድ ትንሽ ሰው ሠራሽ እጅ አሳየኝና የስድስት ወር ዕድሜ ባላቸው ሕፃናት እጅ ላይ እንደሚገጠም ነገረኝ። ለስድስት ወር ልጅ የሚሆን እጅ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ? ልጆቹ ካደጉ በኋላ ሰው ሠራሽ እጅ ወይም ክንድ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ከወዲሁ ለማለማመድ ነው። እንዲህ ያለውን ሥልጠና ካላገኙ በአንድ እጃቸው ብቻ እየተጠቀሙ ስለሚያድጉ ወደፊት በሁለቱ እጆቻቸው መጠቀም ሊያስቸግራቸው እንደሚችል ነገረኝ።

በአውሮፓ የሚገኝ አንድ ፋብሪካ በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ተደርጎ በነበረው የአካል ጉዳተኞች የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ለተካፈሉ አትሌቶች የሚሆኑ ሰው ሠራሽ እጆችና እግሮች በቅርቡ በኮንቴነር ልኮ እንደነበር ሰማሁ። እነዚህ ሰው ሠራሽ አካላት ለተወዳዳሪዎች በነጻ የታደሉ ሲሆን በውድድሩ የሚካፈሉትን ለመርዳት ባለሙያዎች ከኒው ዚላንድም ጭምር ወደ ቦታው ተጉዘው ነበር።

በተለይ አንዳንዶቹ ሰው ሠራሽ እጆችና እግሮች ለአትሌቶች ተብለው የተዘጋጁ ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ አንድ ናሙና ተመለከትኩ። ይህ የተመለከትኩት መዳፍና ቁርጭምጭሚት የተሠራው ልክ እንደ ተፈጥሮ እግር ለመስፈንጠር በሚያስችል ልዩ ነገር ነው።

በቅርብ ጊዜ የታየው መሻሻል

ወደፊት በዚህ ሙያ ረገድ ምን መጠበቅ ይቻላል? ሐኪሜ፣ በኒው ዚላንድ አንድ ሰው ብቻ እየተጠቀመበት ስላለ በኮምፒውተር የሚመራ ሰው ሠራሽ እግር ነገረኝ። ይህ ሰው ሠራሽ እግር በውስጡ ባሉት የግፊት መለኪያዎች አማካኝነት ይንቀሳቀሳል። በዚህ መንገድ ከተፈጥሮው ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ መራመድ ይቻላል።

በአንዳንድ አገሮች ጥሩ ችሎታ ያላቸው የአጥንት ሐኪሞች ኦስቲዮኢንቲግሬሽን የሚባል ዘዴ እየሞከሩ ነው። የሰውየው ሰውነት ሲቆረጥ አንድ ልዩ ብረት በተቆረጠው ቦታ ይገባል፤ ይህም ሰው ሠራሹን አካል ከተቆረጠው አካል ጋር ለማጋጠም ይረዳል። ይህ ዘዴ ጥቅም ላይ ከዋለ ከተቆረጠው ቦታ ጋር የሚመሳሰል ቅርጽም ሆነ የሰው ሠራሹ ሰውነት መግጠሚያ አያስፈልግም።

ከዚህም በላይ ተመራማሪዎች አንድ ሰው በማሰብ ብቻ ሰው ሠራሽ አካሉን መቆጣጠር እንዲችል መልእክት ተቀባይ ነርቮቹ ተቀናጅተው የሚሠሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ምርምር በማድረግ ላይ ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች ጥቂት አገሮች ውስጥ ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች የሌላ ሰው እጅ ተተክቶላቸዋል፤ ነገር ግን ይህ ሕክምና የተደረገላቸው ሰዎች ሰውነታቸው እንዳይቆጣ በቀረው የሕይወት ዘመናቸው መድኃኒት እንዲወስዱ ስለሚገደዱ ነገሩ አወዛጋቢ ሆኗል።

ሰው ሠራሽ እጅ በመግጠም ረገድ ማዮኤሌክትሮኒክስ የተባለ ዘዴ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ኤሌክትሮዶች፣ በክንድ ጡንቻዎች ውስጥ ካሉት ነርቮች መልእክት ይቀበላሉ። እነዚህ መልእክቶች ወደ ኤሌክትሪክ ኃይልነት ይለወጡና በሰው ሠራሹ እጅ ውስጥ ለሚገኙት መልእክት ተቀባይ አካላት ይተላለፋሉ። ከሰው ሠራሽ ክንድ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የተገኘው መሻሻል ደግሞ እጁን ባጣው ግለሰብ ላይ የተገጠመውን ሰው ሠራሽ እጅ በኮምፒውተር አማካኝነት ማሠራት ነው።

ሰው ሠራሽ እጅና እግር በመሥራት ረገድ ቴክኖሎጂ ባሳየው እድገት በጣም በመገረም፣ ሐኪሜ ሰው ሠራሹን አካል ከተፈጥሮ ሰውነት ጋር ሲያወዳድረው ምን እንደሚሰማው ጠየቅኩት። ምንም ሳያቅማማ የተፈጥሮ እጅና እግር በጣም እንደሚበልጥ አረጋገጠልኝ። ይህ አባባሉ መዝሙራዊው “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” በማለት ለፈጣሪው በጸሎት የተናገራቸውን ቃላት አስታወሰኝ።​—⁠መዝሙር 139:14

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

[ሥዕሎች]

ጡንቻዎች በሚያስተላልፉት መልእክት አማካኝነት ፍጥነትን መቆጣጠርና መያዝ የሚችሉ ማዮኤሌክትሪክ እጆች

[ምንጭ]

እጆች:- © ኦቶ ቦክ የጤና ማዕከል

[ሥዕሎች]

ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤት በሆነው በዚህ ጉልበት ውስጥ የሚገኘው ኮምፒውተርና ማግኔት ግለሰቡ እንደፈለገው እንዲንቀሳቀስ ይረዳዋል

[ምንጭ]

ጉልበት:- photos courtesy of Ossur

[ሥዕል]

ሰው ሠራሽ እግሩን የሚሸፍነው ፕላስቲክና ቁርጭምጭሚቱ በውስጥ በኩል ሲታይ ይህን ይመስላል

[ምንጭ]

ኦቶ ቦክ የጤና ማዕከል

[ምንጭ]

1997 Visual Language

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰው ሠራሽ እግር ሲስተካከል

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰው ሠራሽ እግር ለሕመምተኛው ሲገጠም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አካል ጉዳተኛ ሕፃናትን ለማለማመድ የሚረዳ ትንሽ እጅ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ2004 በተካሄደው የአካል ጉዳተኞች ኦሎምፒክ ውድድር ላይ በ100 ሜትር ያሸነፈው ሯጭ ርቀቱን የጨረሰው በ10.97 ሴኮንድ ሲሆን የተጠቀመው ከካርቦን ፋይበር በተሠራ ሰው ሠራሽ እግር ነበር

[ምንጭ]

Photo courtesy of Ossur/Photographer: David Biene

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ኦቶ ቦክ የጤና ማዕከል