በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቴምዝ ወንዝ የእንግሊዝ ውድ ቅርስ

የቴምዝ ወንዝ የእንግሊዝ ውድ ቅርስ

የቴምዝ ወንዝ የእንግሊዝ ውድ ቅርስ

ብሪታንያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

እንግሊዛውያን በማዕከላዊ ደቡብ እንግሊዝ ከሚገኙት ውብ የካትስዎልድ ኮረብቶች የሚነሳውን የቴምዝ ወንዝ ኦልድ ፋዘር ቴምዝ (አረጋዊው አባት ቴምዝ) በማለት በቁልምጫ ይጠሩታል። ከአራት ጅረቶች የሚነሳው ይህ ወንዝ 350 ኪሎ ሜትር ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ መፍሰሱን በቀጠለ መጠን ሌሎች ገባር ወንዞች ይቀላቀሉትና በስተ መጨረሻም ከሰሜን ባሕር ጋር ወደሚገናኝበት 29 ኪሎ ሜትር ስፋት ወዳለው ስፍራ ይደርሳል። አጭር ርቀት የሚጓዘው ይህ ወንዝ በእንግሊዝ ታሪክ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ በጣም የሚያስገርም ነው።

ጁልየስ ቄሳር በ55 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ እንግሊዝን ለመያዝ የመጀመሪያውን የሮማውያን ወራሪ ሠራዊት በመሪነት አዘመተ። በቀጣዩ ዓመት ወደ እንግሊዝ ለመመለስ ሲሞክር ግስጋሴው ታሜሲስ ብሎ በሰየመው ወንዝ ምክንያት ተገታ። ስለሆነም አገሪቱን ከ90 ዓመታት በኋላ የያዛት ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ቀላውዲዎስ ነበር።

በጊዜው የቴምዝ ዳርቻዎች ረግረጋማ የነበሩ ሲሆን የሮም ወታደሮች ከጊዜ በኋላ ወንዙ ከባሕሩ ጋር ከሚገናኝበት ቦታ አንስቶ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይኸውም ማዕበል በሚነሳበት ጊዜ የባሕሩ ውኃ ተገፍቶ የሚመጣበት የመጨረሻው ቦታ ላይ የእንጨት ድልድይ ሠሩ። ከዚህም በላይ በወንዙ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ ሎንዶኒየም የተባለች ወደብ አቋቋሙ። *

በቀጣዮቹ አራት መቶ ዓመታት ሮማውያን ከሌላው የአውሮፓ ክፍል ጋር የነበራቸውን የንግድ ግንኙነት በማጠናከር ከሜድትራንያን ባሕር አካባቢ የቅንጦት ዕቃዎችን ወደ አገራቸው ሲያስገቡ ቆይተዋል። ከዚህም በላይ ከሊባኖስ አጣና ያስመጡ ነበር። በተጨማሪም አገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ለንደን ሸቀጣ ሸቀጥ ለማጓጓዝ የቴምዝን ወንዝ መጠቀም ጀመሩ፤ በዚህ የተነሳ ወደተለያየ አቅጣጫ የሚያመሩ ዋና ዋና መንገዶች ያሏት ይህች ከተማ ትልቅ የንግድ መናኸሪያ ሆነች።

ድል አድራጊው ዊልያም ያሳደረው ተጽዕኖ

የሮም አገዛዝ ከፈራረሰና በ410 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሮም ሠራዊት የእንግሊዝን ምድር ለቅቆ ከወጣ በኋላ ለንደን ወና ሆነች፤ በቴምዝ ወንዝ ላይ ሲካሄድ የቆየው የንግድ እንቅስቃሴም ተዳከመ። የአንግሎ ሳክሰን ነገሥታት ከለንደን 19 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወንዙን በእግር ማቋረጥ በሚቻልበት አካባቢ በምትገኘው በኪንግስተን መንገሥ ጀመሩ። ይህ ሁኔታ፣ ኖርማንዳዊው ድል አድራጊ ዊልያም አካባቢውን እስከወረረበት እስከ 11ኛው መቶ ዘመን ድረስ ቀጠለ። ዊልያም በ1066 በዌስትሚንስተር ዘውድ ከጫነ በኋላ የንግዱን ማኅበረሰብና ወደ ወደቡ የሚገቡትን ነገሮች ለመቆጣጠር በማሰብ ሮማውያን በገነቡት ከተማ ውስጥ የለንደንን ግንብ ገነባ። በዚህ ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴው ማንሰራራት የጀመረ ከመሆኑም በላይ የለንደን የሕዝብ ብዛትም ወደ 30, 000 ገደማ አደገ።

ከዚህም በላይ ቅኝ ገዥው ዊልያም ከለንደን በስተ ምዕራብ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና አሁን ዊንዘር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በበሃ ድንጋይ ንጣፍ ላይ ትልቅ ሕንጻ ገንብቷል። ቴምዝን አሻግሮ ለማየት የሚያስችለው ይህ ሕንጻ ከጊዜ በኋላ የሳክሰን ነገሥታት መኖሪያ ሆኖ አገልግሏል። ተጨማሪ ግንባታዎችና ማስተካከያዎች የተደረጉለት የዊንዘር ጥንታዊ ሕንጻ እንግሊዝ ካሏት የቱሪስት መስህቦች መካከል አንዱ ሆኗል።

በ1209 በአውሮፓ ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የድንጋይ ድልድይ በለንደን በቴምዝ ወንዝ ላይ ተሠርቶ ተጠናቀቀ። ግንባታው 30 ዓመታት ፈጅቷል። ሱቆችና መኖሪያ ቤቶች ሌላው ቀርቶ የጸሎት ቤት ያለው ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ድልድይ ሁለት ተካፋች ድልድዮች እንዲሁም በደቡብ በኩል ባለው በሳውዝዋርክ ለጥበቃ የሚያገለግል ማማ አለው።

በ1215 የእንግሊዙ ንጉሥ ጆን (1167-​1216) ታዋቂውን የማግና ካርታ ውል ያጸደቀው ለዊንዘር ቅርብ በሆነችውና በቴምዝ ወንዝ ዳርቻ በምትገኘው ራኒሜድ ነበር። ይህ ሁኔታ የዜጎቹን በተለይም ደግሞ የለንደን ነዋሪዎችን መብት ለማክበር እንዲሁም በወደቡ ላይም ሆነ በነጋዴዎች መካከል ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ ለመፍጠር ዋስትና እንዲሰጥ አስገድዶታል።

ቴምዝ ያስገኘው ብልጽግና

በቀጣዮቹ መቶ ዓመታት ቴምዝ ላይ የሚካሄደው ንግድ እድገት እያሳየ ሄደ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ እየጨመረ የመጣው የንግድ እንቅስቃሴ ከወንዙ አቅም በላይ መሆን ጀመረ። ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመት በፊት ቴምዝ ማስተናገድ የሚችለው 600 መርከቦችን ብቻ የነበረ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ጭነታቸውን ለማራገፍ ወደብ ላይ ቆመው የሚጠባበቁት መርከቦች ብዛት ከ1, 775 በላይ ይደርስ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ መጨናነቅ የዝርፊያ ድርጊት እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል። ጨለማን ተገን ያደረጉ ዘራፊዎች እንደልባቸው ለመስረቅ እንዲያመቻቸው መርከቦችን ከታሰሩበት ይፈቷቸዋል፤ ትንንሽ ጀልባዎችም መተዳደሪያ ገቢ የሚያገኙት ከመርከብ ላይ የተሰረቁ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በማመላለስ ነበር። ይህን ችግር ለማስወገድ ለንደን ለዓለማችን የመጀመሪያ የሆነውን የወንዝ ላይ የፖሊስ ኃይል አቋቋመች። ይህ የፖሊስ ኃይል እስከ አሁን ድረስ ይሠራል።

በወደቦች ላይ የሚታየውን መጨናነቅ ለማቃለል ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልግ ነበር። በመሆኑም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የእንግሊዝ ፓርላማ በወንዙ ዳርቻዎች ባሉ ዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ በዓለም ካሉት ሁሉ የላቁ ግዙፍ ወደቦችን ለመሥራት ተስማማ። በ1800ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሰሪ የንግድ ወደቦች፣ የለንደን ወደብ እንዲሁም የዌስትና ኢስት ኢንዲያ ወደቦች ግንባታ በቅድሚያ የተጠናቀቀ ሲሆን ቀጥሎም በ1855 ሮያል ቪክቶሪያ እንዲሁም በ1880 ደግሞ ተጓዳኙ የሆነው ሮያል አልበርት ወደቦች ሥራቸው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

ቀዳማዊ ማርክ እና ኢዘምባርድ ኬ ብሩኔል የተባሉ አባትና ልጅ መሃንዲሶች በ1840 የዓለማችንን የመጀመሪያ የውኃ ውስጥ መተላለፊያ በመሥራት የቴምዝን ሁለት ዳርቻዎች ማገናኘት ቻሉ። አራት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መተላለፊያ ታላቋ ለንደን ካሏት የመሬት ውስጥ የባቡር መንገዶች አንዱ ሆኖ አሁን ድረስ ያገለግላል። በ1894 ደግሞ ትልቅ የቱሪስት መስህብ የሆነው ታወር ድልድይ ተሠርቶ ተጠናቀቀ። ይህ ድልድይ በምሰሶዎቹ መካከል ግዙፍ መርከቦችን ለማሳለፍ እንዲችል ለሁለት ተከፍቶ 76 ሜትር የሚያህል ስፋት ይኖረዋል። በተጨማሪም 300 የሚያህሉ ደረጃዎችን ከወጣህ ከፍ ብሎ በሚገኘው ጠበብ ያለ መተላለፊያ ላይ እየተንሸራሸርክ በወንዙ ዳርቻ ያለውን አስደናቂ ውበት መቃኘት ትችላለህ።

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የለንደን ወደቦች፣ በከተማይቱ ያለውን የንግድ ሸቀጥ ለመጫን የሚመጡ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄዱ በእንፋሎት የሚሠሩ መርከቦችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም ነበራቸው። በንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ስም የተሰየመው የመጨረሻው ወደብ ግንባታ በ1921 ሲጠናቀቅ ለንደን “በዓለም ደረጃ ቀዳሚ የሆነ ግዙፍና ጥሩ ትርፍ የሚያስገኝ የወደብ ከተማ” ለመሆን በቃች።

በቤተ መንግሥቶች የታጀበና በሙዚቃ ዝግጅት የደመቀ ወንዝ

ለንደን በማደግ ላይ በነበረችበት ወቅት መንገዶቿ ያን ያህል መሻሻል የሚታይባቸው አልነበሩም፤ እንዲያውም በደንብ ያልተነጠፉና ብዙውን ጊዜ በክረምት ወራት ለመጓዝ አስቸጋሪ ነበሩ። በመሆኑም ፈጣንና ምቹ የሆነው የመጓጓዣ መስመር የቴምዝ ወንዝ ብቻ ነበር። ይህ ደግሞ ቴምዝ ለአያሌ ዓመታት እጅግ የተጨናነቀ ‘አውራ ጎዳና’ ሆኖ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል። የጀልባ ቀዛፊዎች በወንዙ ዳርቻና በደረጃዎች ላይ ሆነው ተሳፋሪዎቻቸውን ወደተለያዩ የወንዙ ዳርቻዎች ለመውሰድ አሊያም የቴምዝ ገባር ወደሆኑት ፍሊትና ዎልብሮክ ለማድረስ እየተተራመሱ በጩኸት “ኦርስ!” (“መቅዘፊያችሁን!” ማለት ነው) ሲሉ መስማት የተለመደ ነበር። የፍሊትና የዎልብሮክ ወንዞች በአሁኑ ጊዜ ባይኖሩም በስማቸው የተሰየሙ የለንደን አውራ ጎዳናዎች አሉ።

ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ ለንደን ወደ ወንዝ የሚያደርሱ ደረጃዎች ያሏቸው ግርማ ሞገስ የተላበሱ ቤተ መንግሥቶች ሲሠራላት በብዙ ነገሮች ቬኒስን መምሰል ጀመረች። በቴምዝ ዳርቻዎች መኖር በንጉሣውያን ቤተሰቦች ዘንድ እንደ ፋሽን ይታይ እንደነበር በግሪንዊች፣ በኋይትሆልና በዌስትሚንስተር ያሉት ቤተ መንግሥቶች ይመሰክራሉ። በተመሳሳይም የሃምፕተን ኮርት ቤተ መንግሥት ለእንግሊዝ ነገሥታትና ንግሥቶች በመኖሪያነት ያገለገለ ሲሆን የዊንዘር ሕንጻም ቢሆን እንዲሁ የንጉሣዊ ቤተሰቦች መኖሪያ መሆኑን ቀጥሏል።

በ1717 ጆርጅ ፍሬድሪክ ሃንድል የንጉሣውያን ቤተሰቦች በሚያደርጉት የውኃ ላይ ሽርሽር ቀዳማዊ ጆርጅን ለማስደሰት “ዎተር ሚዩዚክ” የተባለ ሙዚቃ አቀናብሮ ነበር። አንድ ጋዜጣ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሲዘግብ የንጉሡ ጀልባ “ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ጀልባዎች ከመታጀቧ የተነሳ መላው ወንዝ በጀልባዎች ተሸፍኖ ነበር ለማለት ይቻላል” ብሏል። ንጉሡን ከያዘችው ጀልባ ቀጥሎ ባለችው ጀልባ ላይ 50 ሙዚቀኞች የነበሩ ሲሆን እነዚህ ሙዚቀኞች ከዌስትሚንስትር እስከ ቼልሲ ያለውን 8 ኪሎ ሜትር ሲጓዙ ሃንድል ያቀናበረውን ሙዚቃ ለሦስት ጊዜ ደጋግመው ተጫውተውታል።

ለመዝናኛ የሚያገለግል ወንዝ

የዌስትሚንስተር ድልድይ በ1740ዎቹ ዓመታት እስከተገነባበት ጊዜ ድረስ ቴምዝን በእግር ለማቋረጥ የሚያስችለው ብቸኛ አማራጭ የለንደን ድልድይ ነበር። ከጊዜ በኋላ የለንደን ድልድይ በአዲስ መልክ የተሠራ ሲሆን በመጨረሻም በ1820ዎቹ በሌላ ድልድይ እንዲተካ ተደረገ። በድልድዩ ንጣፎች ላይ ያሉትን 19 ቅስቶች ደግፈው የያዙት መጀመሪያ ላይ የተገነቡት ቋሚዎች ውኃው እንደ ልብ እንዳይፈስ ያግዱት ነበር። በዚህ ምክንያት ድልድዩ በኖረባቸው 600 የሚያህሉ ዓመታት ውስጥ የቴምዝ ወንዝ በጥቂቱ ለስምንት ጊዜ ያህል ወደ በረዶነት ተቀይሯል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲከሰት በግግር በረዶው ላይ የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን የሚያካትት ታላቅ “የበረዶ ላይ መዝናኛ” ይዘጋጃል። የበሬ ሥጋ ይጠበሳል እንዲሁም የንጉሣውያን ቤተሰቦች እየተመገቡ ሲዝናኑ ይታያሉ። “ከቴምዝ የተገዙ” የሚል ምልክት የተለጠፈባቸው መጻሕፍትና መጫወቻዎች በሽሚያ ይገዛሉ። ወደ በረዶነት በተለወጠው ወንዝ ላይ ለጊዜው በተገነቡ የኅትመት መሣሪያዎች አማካኝነት ጋዜጦች ሌላው ቀርቶ የጌታን ጸሎት የያዙ በራሪ ወረቀቶች ይታተማሉ!

በዛሬው ጊዜ፣ በየዓመቱ በጸደይ ወራት በኦክስፎርድና በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጀልባ ቀዘፋ ውድድር ይደረጋል። በዚህ ወቅት በፐትኒንና በሞርትሌክ የቴምዝ ወንዝ ዳርቻዎች ተሰብስቦ የሚጠባበቀው ሕዝብ፣ በየጀልባው በስምንት ረድፍ ተደርድረው የተቀመጡት ተወዳዳሪዎች ከ20 ደቂቃ በሚያንስ ጊዜ ውስጥ 7 ኪሎ ሜትር የሆነውን ርቀት ሲሸፍኑ ሲመለከት የድጋፍ ጩኸቱን ያሰማቸዋል። የመጀመሪያው ውድድር የተከናወነው በ1829 ሲሆን ውድድሩም ሽቅብ ወደ ሄንሊ ከተማ መቅዘፍ ነበር። ውድድሩ ወንዙ ወደሚፈስበት አቅጣጫ እንዲካሄድ ከተወሰነ በኋላ ሄንሊ በአውሮፓ በጥንታዊነቱና በታዋቂነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን የንጉሣውያን ቤተሰቦች የጀልባ ውድድር አስተናግዳለች። ከ1, 600 ሜትር በላይ ርዝመት ባለው የመወዳደሪያ ቦታ ላይ የጀልባ ቀዘፋ ለማካሄድ በዓለማችን ውስጥ አሉ የተባሉ ወንድና ሴት ቀዛፊዎች ወደ አካባቢው ይጎርፋሉ። በአሁኑ ጊዜ ይህ የበጋ ስፖርት ውድድር በኅብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል።

ብሪታንያን ለሚጎበኙ አገር ጎብኚዎች የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ ቴምዝን አስመልክቶ እንደሚከተለው ይላል:- ቴምዝ “በተለይ በእንግሊዝ ገጠራማ አካባቢዎች ያሉ ሸለቆዎችን፣ ጫካዎችን፣ ሜዳዎችን፣ የመኳንንት ማረፊያ ቤቶችን፣ ውብ መንደሮችንና ትንንሽ ከተሞችን አቆራርጦ ሲያልፍ ላየው የተለየ የደስታ ስሜት ይፈጥራል። . . . ብዙውን ጊዜ የወንዙን ዳርቻዎች ተከትሎ የሚሄድ የመኪና መንገድ ባይኖርም ጠባብ የእግረኛ መንገድ ግን ይገኛል። ስለሆነም አንድ አሽከርካሪ ከተሞች ውስጥ በወንዙ ዳር ዳር በመንዳት ይደመም ይሆናል፤ የቴምዝን እውነተኛ ውበት ለማድነቅ ከፈለገ ግን በጀልባ አሊያም በእግር መጓዝ ይኖርበታል።”

እንግሊዝን ለመጎብኘት አስበሃል? ከሆነ ቴምዝን ለመጎብኘትና ባለው ታሪክ ለመደሰት እንድትችል ጊዜ መድብ። በወንዙ መነሻ ላይ ከሚገኘው ውብ ገጠር አንስቶ ባሕር ውስጥ እስከሚገባበት አካባቢ ድረስ በርካታ ነገሮችን ማየት፣ ማከናወንና ማወቅ ትችላለህ! ቴምዝን በመጎብኘትህ ፈጽሞ አትቆጭም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 ለንደን የሚለው ስያሜ የመጣው ሎንዶኒየም ከሚለው የላቲን ቃል ቢሆንም ሁለቱም ስያሜዎች የተገኙት ሊን እና ዲን ከተሰኙት የሴልቲክ ቃላት ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ ቃላት በአንድ ላይ ሲጠሩ “ሐይቅ ዳር ያለች ከተማ [ወይም ጠንካራ ይዞታ]” የሚል ትርጉም ይሰጣሉ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሥነ ጽሑፍ እና ቴምዝ

እንግሊዛዊው ደራሲና ጸሐፊ ተውኔት ጄሮም ክላፕካ ጄሮም ስሪ ሜን ኢን ኤ ቦት በተባለው ጽሑፉ ላይ የቴምዝን አስደሳች ገጽታ አስፍሯል። ይህ ጽሑፍ ከውሻቸው ጋር ሆነው የእረፍት ጊዜያቸውን ለማሳለፍ ከኪንግስተን እስከ ኦክስፎርድ በጀልባ ስለተጓዙ ሦስት ጓደኛሞች ይተርካል። በ1889 የተጻፈው ይህ መጽሐፍ በብዙ ቋንቋ የተተረጎመ ሲሆን እስካሁን ድረስ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ “የተዋጣለት አስቂኝ መጽሐፍ” ነው።

በአዋቂዎችም ሆነ በልጆች ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ሌላው የስነ ጽሑፍ ሥራ ደግሞ ዘ ዊንድ ኢን ዘ ዊሎውስ የተባለው መጽሐፍ ነው። በ1908 ተጽፎ የተጠናቀቀው ይህ መጽሐፍ የተደረሰው በቴምዝ ዳርቻ በምትገኘው የፓንበርን ከተማ ይኖር በነበረው ኬነዝ ግሬም ሲሆን፤ የሚተርከውም በወንዙ ውስጥና ዳርቻ ስለሚኖሩ የምናባዊ ፈጠራ እንስሳት ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን /ሥዕል]

የንጉሡና የቴምዝ ግድድር

በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሲገዙ የነበሩት ቀዳማዊ ጀምስ የለንደን ከተማ አስተዳደር 20,000 ፓውንድ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር። የከተማው ከንቲባ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ንጉሡ እንደሚከተለው ሲሉ አስፈራሩት:- “አንተንም ሆነ ከተማህን ለዘላለሙ አንኮታኩታችኋለሁ። ፍርድ ቤቶቼን ቤተ መንግሥቴንና ፓርላማዬን ወደ ዊንቼስተር ወይም ወደ ኦክስፎርድ አዛውሬ ዌስትሚንስተርን ባድማ አደርጋታለሁ። ከዚያ ምን እንደሚውጥህ እናያለን!” ለዚህ ማስፈራሪያ ከንቲባው እንዲህ በማለት ምላሹን ሰጠ:- “የለንደን ነጋዴዎች ዘወትር የሚጽናኑበት አንድ ነገር አላቸው፤ ግርማዊነትዎ ቴምዝን ይዘው መሄድ አይችሉም።”

[ምንጭ]

Ridpath’s History of the World (Vol. VI) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )

እንግሊዝ

ለንደን

ቴምዝ ወንዝ

[ምንጭ]

ካርታ:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቢግ ቤን እና በለንደን፣ ዌስትሚንስተር የሚገኘው የምክር ቤቱ መቀመጫ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከድንጋይ የተሠራው የለንደን ድልድይ፣ 1756

[ምንጭ]

Old and New London: A Narrative of Its History, Its People, and Its Places (Vol. II) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1803 የተሳለው ይህ ሥዕል የቴምዝን ወንዝና ወደብ ላይ የቆሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦችን ያሳያል

[ምንጭ]

Corporation of London, London Metropolitan Archive

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1683 የተከናወነውን የበረዶ ላይ መዝናኛ የሚያሳይ ሥዕል

[Credit Line]

From the book Old and New London: A Narrative of Its History, Its People, and Its Places (Vol. III) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ