በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለውን ችግር ተቋቁሞ መኖር

የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለውን ችግር ተቋቁሞ መኖር

የዕድሜ መግፋት የሚያስከትለውን ችግር ተቋቁሞ መኖር

“ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ እርሱም በመከራና በሐዘን የተሞላ ነው፤ ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።” (መዝሙር 90:​10 የ1980 ትርጉም ) ሦስት ሺህ ዓመት ያስቆጠረው ይህ ስሜት የሚነካ መዝሙር ዕድሜ መግፋት ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ፈታኝ ሁኔታ መሆኑን ያረጋግጣል። በሕክምናው መስክ ከፍተኛ እድገት የተደረገ ቢሆንም አሁንም ‘መከራና ሐዘን’ የሚያስከትሉ አንዳንድ የዕድሜ መግፋት ገጽታዎች አሉ። ለመሆኑ የትኞቹ ናቸው? አንዳንዶች እነዚህ የሚያስከትሏቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች የተቋቋሙትስ እንዴት ነው?

ዕድሜ መግፋት የአእምሮ ችሎታን አይቀንስም

ሰባ ዘጠኝ ዓመት የሆናቸው ሃንስ “ትልቁ ስጋቴ መጃጀት ደረጃ እንዳልደርስ ነው” ሲሉ ጭንቀታቸውን ገልጸዋል። እንደ በርካታ አረጋውያን ሁሉ ሃንስም የመርሳት ችግር እንዳይገጥማቸው ይሰጋሉ። በጥንት ዘመን የኖረ አንድ ባለ ቅኔ “የወርቅ ሳሕን” ብሎ የጠራውን ማለትም ብዙ ትዝታዎች የያዘውን አእምሯቸውን እንዳይስቱ ይፈራሉ። (መክብብ 12:​6) ሃንስ “የማሰብ ችሎታ መቀነስ ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የማይቀር ችግር ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

እርስዎም እንደ ሃንስ ስም መርሳት መጀመርዎ ወይም አንዳንድ ነገሮች እየተዘነጋዎ መምጣታቸው አእምሮዎ እያሽቆለቆለ መሆኑን እንደሚያሳይ ይሰማዎ ይሆናል። ይሁንና መርሳት በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰት ይችላል። እንዲሁም በዕድሜ የገፉ ሰዎች የአእምሮ ችሎታቸው ላይ ለውጥ ቢያጋጥማቸውም መዘባረቅ ጀምረዋል ማለት ላይሆን ይችላል። * በኋለኞቹ ዓመታት አንዳንድ ነገሮችን መርሳት የተለመደ ቢሆንም በኒው ዮርክ የስቴትን አይላንድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ የባሕርይ ሳይንስ ክፍል ዋና ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ማይክል ሌቪ “አብዛኞቹ አረጋውያን እስከ ሕይወታቸው ማብቂያ ድረስ አእምሯቸው ሙሉ በሙሉ ጤነኛ” ሆኖ እንደሚቀጥል ጽፈዋል።

እርግጥ ነው ወጣቶች አንዳንድ መረጃዎችን በፍጥነት በማስታወስ ረገድ በአብዛኛው ከአረጋውያን የተሻለ ችሎታ አላቸው። ይሁን እንጂ “ፈጣን የማሰብ ችሎታን ወደ ጎን ገሸሽ ካደረግነው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከወጣቶች ያልተናነሰ የማስታወስ ችሎታ አላቸው” በማለት የነርቭ ሐኪም የሆኑት ሪቻርድ ሬስታክ ተናግረዋል። እንዲያውም ጤናማ አእምሮ ያላቸው አረጋውያን ተገቢ የሆነ ትምህርትና ሥልጠና ካገኙ መማር፣ ማስታወስ እንዲሁም አንዳንድ ችሎታዎችን ማዳበር ይችላሉ።

የማስታወስ ችግርና በሕክምና ሊረዱ የሚችሉ ሁኔታዎች

ይሁንና አንድ ሰው ከባድ የመርሳት ችግር ቢኖርበትስ? እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥም እንኳ ግለሰቡ መዘባረቅ ጀምሬያለሁ ብሎ ለመደምደም መቸኮል የለበትም። በኋለኞቹ ዓመታት የሚከሰቱ በሕክምና ሊረዱ የሚችሉ ብዙ ችግሮች የመርሳት እክልና ድንገተኛ ግራ የመጋባት ስሜት ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ የጤና መዛባቶች አብዛኛውን ጊዜ “እርጅና” ወይም “መጃጀት” እንደሆኑ ተደርገው በተሳሳተ መንገድ ይወሰዳሉ። ትክክለኛ መረጃ የሌላቸው የጤና ባለሞያዎችም ተመሳሳይ አመለካከት የሚይዙበት ጊዜ አለ። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በዕድሜ የገፉትን ታካሚዎች ስሜት የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ ተገቢ የሆነ ሕክምና እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል። ከእነዚህ የጤና እክሎች መካከል አንዳንዶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

በድንገት የሚከሰት አጥርቶ ማሰብ አለመቻል የተመጣጠነ ምግብ ካለማግኘት፣ ከድርቀት፣ ከደም ማነስ፣ በጭንቅላት ላይ ከሚደርስ ጉዳት፣ ከታይሮይድ ዕጢዎች ችግር፣ ከቫይታሚን እጥረት፣ መድኃኒት ከሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳት ወይም የአካባቢ ለውጥ ከሚያስከትለው ግራ መጋባት የተነሳ ሊደርስ ይችላል። ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ውጥረት የመርሳት ችግርን የሚያስከትል ሲሆን ተላላፊ በሽታዎች ደግሞ አረጋውያን አጥርተው ማሰብ እንዳይችሉ የሚያደርጉ የታወቁ መንስኤዎች ናቸው። በተጨማሪም በሐዘን ስሜት መዋጥ በአረጋውያን ሕሙማን ላይ የመርሳት ችግርና ግራ መጋባት ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ “ግራ የመጋባቱ ሁኔታ እየተባባሰ ከሄደ ጉዳዩን በቸልታ ማየት ወይም ግለሰቡ ጃጅቷል ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም” በማለት ዶክተር ሌቪ ተናግረዋል። የተሟላ የሕክምና ምርመራ ማድረግ የበሽታዎቹን ዋነኛ መንስኤ ለማወቅ ይረዳል።

በሐዘን የመዋጥን ስሜት መቋቋም

በሐዘን የመዋጥ ስሜት ለሰው ዘሮች ሌላው ቀርቶ ለታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አዲስ ነገር አይደለም። ከሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ያዘኑትን ነፍሳት አጽናኗቸው” በማለት ምክር መስጠት አስፈልጎት ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:​14 NW ) በዚህ አስጨናቂ ዘመን መጽናኛ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። የሚያሳዝነው ግን አረጋውያን የሚያጋጥማቸውን በሐዘን የመዋጥ ስሜት አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሳያውቁላቸው ወይም በትክክል ሳይረዱላቸው ይቀራሉ።

ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ በቀላሉ ይከፋሉ እንዲሁም ተለዋዋጭ ባሕርይ ይኖራቸዋል የሚል ሰፊ ተቀባይነት ያገኘ የተሳሳተ አመለካከት ስላለ ሌሎች ሰዎችም ሆኑ አረጋውያኑ ራሳቸው ይህንን ሁኔታ የተለመደ የእርጅና ክፍል አድርገው ይወስዱታል። አረጋውያንን ማከም [እንግሊዝኛ] የተባለው መጽሐፍ “እውነታው ግን ይህ አይደለም። በአረጋውያን ላይ የሚከሰተው በሐዘን የመዋጥ ስሜት ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የእርጅና ክፍል አይደለም” በማለት ገልጿል።

ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ስር የሰደደ በሐዘን የመዋጥ ስሜት አልፎ አልፎ ከሚከሰት የትካዜ ስሜት ፈጽሞ የተለየ ሲሆን ለከባድ ጉዳት ሊዳርግ የሚችል አደገኛ በሽታ በመሆኑ በቸልታ ሊታለፍ አይገባም። ይህ ችግር ቶሎ ካልታከሙት እየተባባሰ ሊሄድና ሥር ሊሰድ ስለሚችል አንዳንድ ተስፋ የቆረጡ በሽተኞች ሕይወታቸውን ለማጥፋት ሙከራ ያደርጋሉ። ዶክተር ሌቪ በሐዘን መዋጥ በአረጋውያን በሽተኞች ላይ የሚያደርሰውን አሳዛኝ ክስተት በተመለከተ “በቀላሉ ሊድን የሚችለው የአእምሮ ሕመም መልኩን ለውጦ ለሞት ሊዳርግ መቻሉ ነው” በማለት ገልጸዋል። ይህ ችግር ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ ታማሚው የስነ ልቦና ሐኪም ዘንድ ሄዶ መታየት አለበት። *​—⁠ማርቆስ 2:​17

በሐዘን ስሜት የተዋጡ ግለሰቦች ይሖዋ “እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ” እንደሆነ ሊነገራቸው ያስፈልጋል። (ያዕቆብ 5:​11) እርሱ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።” (መዝሙር 34:​18) በእርግጥም ይሖዋ ‘ሐዘንተኞችን በማጽናናት’ ረገድ አቻ አይገኝለትም።​—⁠2 ቆሮንቶስ 7:​6

የማትጠቅሙ እንደሆናችሁ አይሰማችሁ

ታማኙ ንጉሥ ዳዊት ከ3, 000 ዓመታት በፊት “በእርጅናዬ ዘመን አትጣለኝ፤ ጒልበቴም ባለቀበት ጊዜ አትተወኝ” በማለት ጸልዮ ነበር። (መዝሙር 71:​9) በ21ኛው መቶ ዘመንም አረጋውያን እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያጠቃቸው ሲሆን የማይጠቅሙ ተደርገው እንዳይታዩ ይሰጋሉ። የጤና ችግር አቅም ስለሚያሳጣቸው በቀላሉ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት የሚያሳድርባቸው ሲሆን በጡረታ መገለላቸው ደግሞ አልረባም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።

ይሁን እንጂ ልናደርጋቸው የማንችላቸውን ነገሮች እያሰብን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ መሥራት በምንችላቸው ነገሮች ላይ ማተኮራችን ለራሳችን ጥሩ ግምት እንዲኖረንና ጠቃሚ እንደሆንን እንዲሰማን ያደርጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት ላይ ‘መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ትምህርት በመከታተል እድገት ማድረግ፣ በማኅበራዊ ድርጅቶች ውስጥ ተሳታፊ መሆንና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ማድረግ’ ጥሩ መሆኑን ገልጿል። በስዊዘርላንድ የሚኖሩትና ዳቦ ከመጋገር ሥራቸው ጡረታ የወጡት ኧርነስት የተባሉ የይሖዋ ምሥክር ‘መማር በመቀጠል እድገት ማድረግ’ የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። በ70ዎቹ ዓመታት እያሉ ኮምፒውተር ለመግዛትና አጠቃቀሙን ለመማር ወሰኑ። በእርሳቸው ዕድሜ የሚገኙ ብዙ አረጋውያን ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን ዘመናዊ መሣሪያዎች በሚፈሩበት ወቅት እርሳቸው እንዲህ ማድረግ የፈለጉት ለምንድን ነው? እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “ዕድሜዬ እየገፋ ሲሄድ አእምሮዬን ንቁ እንደሆነ ማቆየት አንደኛው ምክንያቴ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥልቅ ጥናት ሳደርግና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ለማከናውነው ሥራ ሊረዳኝ የሚችለውን ቴክኖሎጂ ለማወቅ ነው።”

ራስን ውጤታማ በሆኑ ሥራዎች ማስጠመድ አረጋውያን የሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች እንዲሟሉላቸው ሊያደርግ ይችላል። ከእነዚህም መካከል ትርጉም ያለው ሕይወትና እርካታ እንዲሁም በተወሰነ መጠን ገቢም ሊያስገኝላቸው ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን ለሰው ልጆች “በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ [እንዲሁም] ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ” ከአምላክ የተሰጠ ችሮታ እንደሆነ ተናግሯል።​—⁠መክብብ 3:​12, 13

የቻልነውን ያህል መሥራት

በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ አረጋውያን እውቀትን እንዲሁም የሥነ ምግባርና መንፈሳዊ እሴቶችን ለተከታይ ትውልድ ያስተላልፋሉ። ንጉሥ ዳዊት “አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ” በማለት ጽፏል።​—⁠መዝሙር 71:​18

ታዲያ አረጋውያን በጤና ወይም በተለያዩ ሁኔታዎች አቅማቸው ውስን ቢሆንስ? ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ ያበሳጫቸው ሣራ የሚባሉ 79 ዓመት የሆናቸው የይሖዋ ምሥክር የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነገሩት። እርሱም “የጻድቅ ሰው ጸሎት ኀይል አለው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አስታወሳቸው። (ያዕቆብ 5:​16) በመቀጠልም እንዲህ አላቸው “እርስዎ ባለፉት ዓመታት ከአምላክ ጋር ጥብቅ ዝምድና መሥርተዋል። በግል ለእያንዳንዳችን ቢጸልዩልን እርስዎ ከመሠረቱት ዝምድና ሌሎቻችን ተጠቃሚ መሆን እንችላለን።” አክሎም “እህት ሣራ ስለ እኛ እንዲጸልዩልን እንፈልጋለን” አላቸው። ይህንን ሲሰሙ በጣም ተበረታቱ።

አረጋዊቷ ሣራ እንደተገነዘቡት ሁሉ በዕድሜ የገፉ ሌሎች ብዙ አረጋውያንም ሌሎችን ወክለው ቀንና ሌሊት በጸሎት መትጋታቸው ሕይወታቸውን የሚያረካና ትርጉም ያለው ያደርግላቸዋል። (ቈላስይስ 4:​12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​5) ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ለሌሎች በጸለዩ መጠን ‘ጸሎት ሰሚ’ ወደ ሆነው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል።​—⁠መዝሙር 65:​2፤ ማርቆስ 11:​24

የአቅም ገደብ ቢኖርባቸውም ተሞክሯቸውንና ጥሪታቸውን ለሌሎች ለማካፈል ቸሮች የሆኑ አረጋውያን ላሉበት ማኅበረሰብ ትልቅ ሀብት ናቸው። “ሽበት የክብር ዘውድ ነው፤ የሚገኘውም በጽድቅ ሕይወት ነው” የሚለውን ቃል እውነተኝነት ያረጋግጣሉ።​—⁠ምሳሌ 16:​31

ሆኖም በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞልናል? ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። በኋለኞቹ ዓመታት የተሻለ ሕይወት ይኖረናል ብለን በእርግጠኝነት መጠባበቅ እንችላለን?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ “ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ከሆናቸው ሰዎች 90 በመቶ የሚሆኑት የመዘባረቅ ችግር አያጋጥማቸውም” ሲሉ ገልጸዋል። በዚህ ረገድ እርዳታ ለማግኘት የመስከረም 22, 1998 ንቁ! (እንግሊዝኛ) “የኦልዛይመር በሽታ​—⁠ሥቃዩን ማስታገስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.13 ንቁ! መጽሔት የትኛውንም ዓይነት ሕክምና ደግፎ አይናገርም። ክርስቲያኖች የሚያደርጉት የትኛውም ዓይነት ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። በጥር 8, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) እትም ላይ የወጣውን “የስሜት መለዋወጥ የሚያስከትለውን ችግር መረዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አብዛኛውን ጊዜ አረጋውያን በጥድፊያ በተሞላው በዚህ ዘመናዊ ዓለም ውስጥ እንደተረሱ ይሰማቸዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አረጋውያንን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው?

ክብራቸውን በመጠበቅ። “አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂ በኀይለ ቃል አትናገረው። . . . እንዲሁም አሮጊቶችን እንደ እናቶች” ቁጠር።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​1, 2

በጥሞና በማዳመጥ። ‘ለመስማት የፈጠናችሁ፣ ለመናገር የዘገያችሁ፣ ለቁጣም የዘገያችሁ’ ሁኑ።​—⁠ያዕቆብ 1:​19

ችግራቸውን በመረዳት። “ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ። ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ።”​—⁠ 1 ጴጥሮስ 3:​8, 9

ማበረታቻ በሚያስፈልጋቸው ወቅት ስሜታቸውን በመረዳት። “ባግባቡ የተነገረ ቃል፣ በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ ነው።”​—⁠ምሳሌ 25:​11

በምትዝናኑበት ወቅት እነርሱንም በመጋበዝ። “እንግዶችን ተቀበሉ።”​—⁠ሮሜ 12:​13

ተግባራዊ የሆነ እርዳታ በመስጠት። “ማንም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በእርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።”​—⁠1 ዮሐንስ 3:​17, 18

ትዕግሥተኛ በመሆን። “ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።”​—⁠ቈላስይስ 3:​12

ለአረጋውያን እንክብካቤ በማድረግ አምላክ “ሽማግሌውን አክብር” ብሎ ላወጣው መሥፈርት ያለንን አክብሮት እናሳያለን።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​32

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የተሟላ የሕክምና ምርመራ ማድረግ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል