በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የገዛ አካሌን ከመጉዳት መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

የገዛ አካሌን ከመጉዳት መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

የገዛ አካሌን ከመጉዳት መታቀብ የምችለው እንዴት ነው?

ጭንቀቴን መቆጣጠር ያቅተኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን እንዲህ ለማድረግ የሚረዳኝ አንድ ዘዴ አገኘሁ፤ እርሱም ሰውነቴ ላይ ጉዳት ማድረስ ነው።”​— ጄኒፈር፣ 20 ዓመት *

ስጨነቅ ሰውነቴን እቆርጣለሁ። የማለቅሰው እንዲህ በማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ደስታ ይሰማኛል።”​— ጄሲካ፣ 17 ዓመት

ለመጨረሻ ጊዜ ሰውነቴን የቆረጥኩት ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ነው። ይህ ለእኔ ረጅም ጊዜ ነው። ይህን ድርጊቴን ሙሉ በሙሉ አቆማለሁ ብዬ አላስብም።”​— ጄሚ፣ 16 ዓመት

ጄኒፈር፣ ጄሲካና ጄሚ አይተዋወቁም፤ ነገር ግን ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። ሦስቱም የስሜት ሥቃይ አለባቸው። እንዲሁም የተስፋ መቁረጥ ስሜታቸውን የሚቋቋሙበት ተመሳሳይ ልማድ አዳብረዋል። ጄኒፈር፣ ጄሲካና ጄሚ ሰውነታቸውን በመጉዳት ጊዜያዊ እፎይታ ያገኛሉ። *

ሰውነትን መጉዳት እንግዳ ድርጊት ቢመስልም በአሥራዎቹ ዕድሜ በሚገኙና በሌሎች ወጣቶች ዘንድ በሚያስገርም ሁኔታ የተለመደ ድርጊት ሆኗል፤ ይህ ድርጊት የራስን ሰውነት መቁረጥን ወይም መተልተልን ይጨምራል። የካናዳው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ “ወላጆችን የሚያስፈራ፣ [የትምህርት ቤት] አማካሪዎችን ግራ የሚያጋባና ሐኪሞችን የሚፈታተን” ችግር እንደሆነ ገልጿል። አክሎም በሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ “ሐኪሞች ኃይለኝነታቸውን ከመሠከሩላቸው ሱሶች መካከል አንዱ ሊሆን ችሏል” ብሏል። አንቺ ይህ ችግር አለብሽ? ወይም የዚህ ልማድ ተገዥ የሆነ የምታውቂው ሰው አለ? ከሆነ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

በመጀመሪያ ሰውነትሽን እንድትጎጂ የሚያስገድድሽን ምክንያት ለማወቅ ሞክሪ። ሰውነትን መቁረጥ በምትደናገጪበት ወቅት የምትፈጽሚው ድንገተኛ ድርጊት እንዳልሆነ አስታውሺ። ብዙውን ጊዜ ውጥረትን ለመቋቋምና የስሜት ሥቃይን ለማስታገስ ተብሎ የሚፈጸም ድርጊት ነው። ስለዚህ ራስሽን እንደሚከተለው እያልሽ ጠይቂ:- ‘ሰውነቴ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምን ዓላማ ነው? ሰውነቴን የመቁረጥ ፍላጎት በሚቀሰቀስብኝ ወቅት የማስበው ስለ ምንድን ነው?’ ምናልባት ከቤተሰብሽ ወይም ከጓደኞችሽ ጋር በተያያዘ እንድትጨነቂ ያደረገሽ ሁኔታ አለ?

በዚህ መንገድ ራስሽን ለመመርመር ድፍረት እንደሚጠይቅብሽ ምንም አያጠራጥርም። የምታገኚው ጥቅም ግን ላቅ ያለ ነው። ብዙውን ጊዜ በሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስን ልማድ ለማቆም ከሚወሰዱት እርምጃዎች የመጀመሪያው ይህ ነው። ሆኖም የችግሩን መነሻ ከማወቅ የበለጠ ነገር ማድረግ ያስፈልግሻል።

ሌሎችን ማማከር ያለው ጥቅም

አካልሽን የመጉዳት ልማድ ካለብሽ ለምታምኚውና ብስለት ላለው ጓደኛሽ የሚያስጨንቁሽን ነገሮች ማካፈልሽ ጠቃሚ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ሥጉ ልብ ሰውን በሐዘን ይወጥራል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 12:25) ምስጢርሽን ለሌሎች ማካፈልሽ የሚያስፈልጉሽን አጽናኝ የሆኑ መልካም ቃላት እንድታገኚ አጋጣሚ ይከፍትልሻል።​—⁠ምሳሌ 25:11

ከማን ጋር መነጋገር ትችያለሽ? ብስለት ያለው፣ ጥበበኛና አዛኝ የሆነ በዕድሜ የሚበልጥሽ ሰው መርጠሽ ማነጋገሩ ጠቃሚ ነው። ክርስቲያኖች “ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ ይሆናል። በበረሓም እንደ ውሃ ምንጭ፣ በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ ይሆናል” የተባለላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ አለላቸው።​—⁠ኢሳይያስ 32:2

ምስጢርሽን ለሌላ ሰው ማካፈል ሊያስፈራሽ እንደሚችል እሙን ነው። የሣራ ዓይነት ስሜት ሊሰማሽም ይችላል። እንዲህ በማለት የተሰማትን ሳትደብቅ ተናግራለች:- “መጀመሪያ ላይ ማንንም ሰው ማመን አስቸግሮኝ ነበር። ሰዎች ካወቁኝ ማለትም እውነተኛ ማንነቴን ከተረዱ ሊጠሉኝና ሊሸሹኝ ይችላሉ ብዬ አስብ ነበር።” ይሁንና ምስጢሯን ለሌሎች በማካፈሏ በምሳሌ 18:24 ላይ የሚገኙትን “ከወንድም አብልጦ የሚቀርብ ጓደኛም አለ” የሚሉትን ቃላት እውነተኝነት ማየት ችላለች። “ምስጢሬን ያካፈልኳቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ ሰውነቴን የመጉዳት ልማዴን በተመለከተ ምንም ዓይነት ነገር ብነግራቸው በጭራሽ አይወቅሱኝም። እንዲያውም ጠቃሚ ምክሮችን አካፍለውኛል። ሳዝንና ጨርሶ ዋጋ እንደሌለኝ ሲሰማኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምክንያታዊ የሆኑ ሐሳቦችን እያነሱ ያጽናኑኝ ነበር” ብላለች።

አንቺም በሰውነትሽ ላይ ጉዳት የማድረስ ችግር ካለብሽ ጉዳዩን አንስተሽ ከአንድ ሰው ጋር ለምን አትወያዪም? ፊት ለፊት መነጋገር የሚከብድሽ ከመሰለሽ ደብዳቤ በመጻፍ ወይም ስልክ በመደወል ሐሳብሽን መግለጽ ትችያለሽ። ምስጢርሽን ለሌሎች ማካፈል ከችግርሽ ለመላቀቅ የሚረዳሽ ጠቃሚ እርምጃ ነው። ጄኒፈር “በጣም ያስፈልገኝ የነበረው ነገር ተስፋዬ ጭልምልም ባለበት ጊዜ ላናግረው የምችል ከልብ የሚያስብልኝ ሰው መኖሩን ማወቅ ነው” ብላለች። *

የጸሎት አስፈላጊነት

ዶና አንድ መሰናክል አጋጥሟት ነበር። በአንድ በኩል የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ይሰማታል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰውነቷን መቁረጧን እስካላቆመች ድረስ አምላክ እንደማይረዳት ታስብ ነበር። ዶናን የረዳት ምንድን ነው? አንዱ ነገር በ1 ዜና መዋዕል 29:17 ላይ ባለው ይሖዋ አምላክ ‘ልብን እንደሚመረምር’ በሚናገረው ሐሳብ ላይ ማሰላሰሏ ነው። ዶና እንዲህ ብላለች:- “ይሖዋ፣ ሰውነቴን መቁረጤን የማቆም ልባዊ ፍላጎት እንዳለኝ ያውቃል። እንዲረዳኝ ወደ እርሱ መጸለይ ከጀመርኩ በኋላ በጣም የሚገርም ሁኔታ መከሰት ጀመረ። ሰውነቴን ላለመቁረጥ ያለኝ ፍላጎት ቀስ በቀስ እየተጠናከረ መጣ።”

ብዙ መከራ ይፈራረቅበት የነበረው መዝሙራዊው ዳዊት “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 55:22) አዎን፣ ይሖዋ ጭንቀትሽን ያውቃል። ከዚህም በላይ ‘ስለ አንቺ ያስባል።’ (1 ጴጥሮስ 5:7) ውስጥሽ የሚፈርድብሽ ከሆነ ይሖዋ ‘ከልብሽ ይልቅ ታላቅ እንደሆነና ሁሉን ነገር እንደሚያውቅ’ አስታውሺ። አዎን፣ ለምን ሰውነትሽን እንደምትጎጂና ይህን ልማድሽን ማቆም የተቸገርሽው በምን ምክንያት እንደሆነ ያውቃል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) ወደ ይሖዋ በጸሎት ከቀረብሽና ልማድሽን ለማቆም ጥረት የምታደርጊ ከሆነ እርሱ በእርግጥ ‘ይረዳሻል።’​—⁠ኢሳይያስ 41:10

ምናልባት ልማዱ ቢያገረሽብሽስ? ይህ ቢሆን ችግሩ ከአቅምሽ በላይ ሆኗል ማለት ነው? በጭራሽ! ምሳሌ 24:16 “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” ይላል። ዶና ይህን ጥቅስ በማስታወስ “ከሰባት ጊዜ በላይ ወድቄአለሁ፤ ይሁንና ተስፋ አልቆረጥኩም” ብላለች። ዶና መንፈሰ ጠንካራነት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝባለች። ካረንም ያደረገችው እንዲሁ ነው። “የችግሩን ማገርሸት እንደ ጊዜያዊ መሰናክል እንጂ እንደ ሽንፈት አድርጌ መመልከት እንደሌለብኝ በመገንዘቤ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ሁሉ ጥረቴን እንደ አዲስ እጀምራለሁ” ብላለች።

ተጨማሪ እርዳታ ሲያስፈልግ

ኢየሱስ ‘ሕመምተኞች ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው’ ተናግሯል። (ማርቆስ 2:17) የገዛ አካልን የመጉዳት ልማድ መንስኤ አካላዊ ወይም አእምሯዊ ሕመም እንደሆነ ለማረጋገጥና ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት ብዙውን ጊዜ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማማከር አስፈላጊ ነው። * ጄኒፈር አፍቃሪ የሆኑ የጉባኤ ሽማግሌዎች ካደረጉላት ድጋፍ ጋር የማይጋጭ እንዲህ ያለ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት ተገንዝባ ነበር። ሽማግሌዎች ስላደረጉላት ድጋፍ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “ሽማግሌዎች ሐኪሞች ባይሆኑም በጣም ይደግፉኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በራሴ ላይ ጉዳት እንዳደርስ ውስጤ ቢገፋፋኝም ይህንን ስሜት በይሖዋ ድጋፍ፣ በጉባኤው እርዳታና ችግሩን ለመቋቋም እንደሚረዱ በተማርኳቸው ዘዴዎች በመታገዝ መቋቋም ችያለሁ።” *

ይህን ሰውነት የመጉዳት ልማድ፣ ችግርሽን እንድትቋቋሚ በሚረዳ ሌላ ዘዴ የመተካት ችሎታ ማዳበር እንደምትችይ እርግጠኛ ሁኚ። አንቺም ልክ እንደ መዝሙራዊው “አካሄዴን እንደ ቃልህ ቀና አድርግልኝ፤ ኀጢአትም በላዬ እንዲሠለጥን አትፍቀድ” በማለት ጸልዪ። (መዝሙር 119:133) ይህ ልማድሽ በድጋሚ እንዳይከሰት መቆጣጠር ስትችዪ እርካታ የምታገኚ ከመሆኑም በላይ ለራስሽ አክብሮት ይኖርሻል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.6 የገዛ አካልን ስለመጉዳት እንዲሁም ድርጊቱ ምንን እንደሚያካትትና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በጥር 2006 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . በገዛ አካሌ ላይ ጉዳት የማደርሰው ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ መመልከት ይቻላል።

^ አን.14 ስሜትሽን እንዴት በቃላት መግለጽ እንደምትችዪ ለመለማመድ አንዳንድ ጊዜ ሐሳብሽን በጽሑፍ ማስፈር ትችያለሽ። የመጽሐፍ ቅዱስን መዝሙሮች የጻፉት ከባድ ጭንቀት ያጋጠማቸው ሰዎች ሲሆኑ የሚሰማቸውን ጸጸት፣ ብስጭትና ሐዘን በቃላት አስፍረዋል። ለምሳሌ ያህል መዝሙር 6ን13ን42ን55ንና 69ን መመልከት ትችያለሽ።

^ አን.20 አንዳንድ ጊዜ በራስ ሰውነት ላይ ጉዳት ማድረስ ሌላ ሁኔታን ተከትሎ የሚመጣ ችግር ነው፤ ከእነዚህም መካከል የመንፈስ ጭንቀት፣ ባይፖላር ዲስኦርደር እና ኦብሰሲቭ ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር የተባሉ ሕመሞች ወይም ደግሞ የተዛባ ያመጋገብ ልማድ ይገኙበታል። ንቁ! ይሄ ሕክምና ይሻላል ይሄ አይሻልም የሚል ሐሳብ አይሰጥም። ክርስቲያኖች የሚያደርጉት ማንኛውም ሕክምና ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የማይጋጭ መሆኑን ማረጋገጥ አለባቸው።

^ አን.20 በራስ ሰውነት ላይ ጉዳት ከማድረስ ልማድ በስተጀርባ ያሉትን ችግሮች የሚገልጹ ርዕሰ ትምህርቶችን የያዙ ንቁ! መጽሔቶች ባለፉት ጊዜያት ወጥተዋል። ለምሳሌ ያህል “የስሜት መለዋወጥ የሚያስከትለውን ችግር መረዳት” (ጥር 8, 2004 [እንግሊዝኛ])፣ “በመንፈስ ጭንቀት ለሚሠቃዩ ወጣቶች የሚሆን እርዳታ” (መስከረም 2001)፣ “የተዛባ ያመጋገብ ልማድ መንስኤ ምንድን ነው?” (ጥር 22, 1999 [እንግሊዝኛ]) የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶችና “የወጣቶች ጥያቄ . . . የአልኮል ሱሰኛ ወላጆች​—⁠ችግሩን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” (ነሐሴ 8, 1992 [እንግሊዝኛ]) የሚለውን ርዕስ መመልከት ይቻላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ጭንቀት በሚሰማሽ ጊዜ ሰውነትሽን ከመቁረጥ ይልቅ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

▪ ሰውነትሽን የመቁረጥ ችግር ካለብሽ ምስጢርሽን ለማን ብታካፍዪ ጥሩ ነው?

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሰውነታቸው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሰዎችን መርዳት

በገዛ ሰውነቷ ላይ ጉዳት የማድረስ ችግር ያለባትን የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ እንዴት መርዳት ትችላለህ? ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች ምስጢራቸውን የሚያካፍሉት ሰው በጣም ስለሚፈልጉ ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆንህን ልታሳይ ትችላለህ። ‘ለክፉ ቀን የተወለደ ወዳጅ’ ለመሆን ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 17:17) መጀመሪያ ላይ ልትደናገጥ እንደምትችልና ወዲያውኑ ድርጊቱ እንዲቆም እንደምትፈልግ የተረጋገጠ ነው። እንዲህ ማድረግህ ግን ችግሩ ያለባት ሴት እንድትርቅህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ይህ ልማድ ያለባት ሴት ድርጊቷን እንድታቆም ከመንገር የበለጠ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል። ችግሮቹን መቋቋም የምትችልባቸውን ሌሎች መንገዶች እንድታውቅ ለመርዳት ጥበበኛ መሆን ያስፈልጋል። (ምሳሌ 16:23) ከዚህም በላይ ችግሩን ማስወገድ ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ስለዚህ ትዕግሥተኛና “ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ” ሰው ሁን።​—⁠ያዕቆብ 1:19

ወጣት ከሆንክ ችግሩ ያለባትን ሴት በራስህ መንገድ መርዳት እንደምትችል ሊሰማህ አይገባም። ምናልባት ለዚህ ችግር ምክንያት የሆነ ሌላ ነገር ወይም ደግሞ ሕክምና የሚያስፈልገው ሕመም ሊኖር እንደሚችል አስታውስ። እንዲሁም ይህ ልማድ ያለባት ሴት ራሷን የማጥፋት እቅድ ባይኖራትም እንኳን ድርጊቱ ለሕይወቷ አስጊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ችግሯን ለጎለመሱና አሳቢ ለሆኑ ትልልቅ ሰዎች እንድትናገር ማሳሰቡ ጥሩ ነው።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

ምስጢርን ለሚወዱት ሰው ማካፈል ያለውን ጥቅምና የጸሎትን አስፈላጊነት ፈጽሞ አቅልለሽ አትመልከቺ