በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፒልግሪሞች እና ፒዩሪታኖች እነማን ነበሩ?

ፒልግሪሞች እና ፒዩሪታኖች እነማን ነበሩ?

ፒልግሪሞች እና ፒዩሪታኖች እነማን ነበሩ?

በሰሜን አሜሪካ የባሕር ዳርቻ በምትገኘው በፕሊመዝ ከተማ ማሳቹሴትስ፣ 1620 የሚል ቁጥር የተቀረጸበት ቋጥኝ ይገኛል። ይህ ቋጥኝ ፕሊመዝ ሮክ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ከ400 ዓመታት በፊት የተወሰኑ አውሮፓውያን በመርከብ ተጉዘው ከመጡ በኋላ የወረዱት በዚህ ቋጥኝ አቅራቢያ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። እነዚህ ሰዎች ፒልግሪሞች ወይም የፒልግሪም አባቶች በመባል ይታወቃሉ።

እንግዳ ተቀባይ የሆኑት ፒልግሪሞች ካመረቱት ሰብል ላይ ድግስ አዘጋጅተው የአገሩ ተወላጆች የሆኑትን አሜሪካውያን ይጋብዟቸው እንደነበር የሚነገረውን ታሪክ ብዙ ሰዎች ያውቁታል። ይሁን እንጂ ፒልግሪሞች እነማን ነበሩ? ወደ ሰሜን አሜሪካ የፈለሱትስ ለምን ነበር? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሄንሪ ስምንተኛ የእንግሊዝ ንጉሥ ወደነበረበት ዘመን መለስ እንበል።

በእንግሊዝ የነበረው ሃይማኖታዊ አለመረጋጋት

ፒልግሪሞች ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመጓዛቸው 100 ከማይሞሉ ዓመታት በፊት እንግሊዛውያን የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታዮች የነበሩ ሲሆን ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛም የእምነት ጠበቃ የሚል ከፍተኛ ማዕረግ ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ ሊቀ ጳጳስ ክሌመንት ሰባተኛ፣ ሄንሪ የአራጎን ተወላጅ ከሆነችው ከካትሪን ጋር የመሠረተውን ጋብቻ ለማፍረስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሄንሪ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የነበረው ግንኙነት ሻከረ። ካትሪን ንጉሡ ካሉት ስድስት ሚስቶች መካከል የመጀመሪያዋ ነበረች።

ሄንሪ በቤተሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እየታገለ በነበረበት ወቅት፣ በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ተሃድሶ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እያናወጣት ነበር። መጀመሪያ ላይ ሄንሪ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ማዕረግ ማጣት ስላልፈለገ የተሐድሶ አራማጆቹ ወደ እንግሊዝ እንዲገቡ አልፈቀደም። በኋላ ላይ ግን ሐሳቡን ለወጠ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋብቻውን ለማፍረስ ፈቃደኛ ስላልሆነች ሄንሪ ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን ሥልጣን እንድታጣ አደረገ። በ1534፣ ሊቀ ጳጳሱ በእንግሊዝ ካቶሊኮች ላይ የነበራቸውን ሥልጣን በመሻር ራሱን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ራስ አድርጎ ሾመ። ብዙም ሳይቆይ ገዳማትን መዝጋትና ንብረቶቻቸውን መሸጥ ጀመረ። ሄንሪ በ1547 ሲሞት እንግሊዝ የፕሮቴስታንት አገር ሆና ነበር።

የሄንሪ ልጅ ኤድዋርድ ስድስተኛም ቢሆን ከሮም ሊቀ ጳጳስ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማደስ አልሞከረም። ኤድዋርድ በ1553 ከሞተ በኋላ፣ ሄንሪ የአራጎን ተወላጅ ከሆነችው ከካትሪን የወለዳትና የሮም ካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበረችው ሜሪ ንግሥት ሆነች፤ እርሷም ሕዝቡ ለሊቀ ጳጳሱ ሥልጣን እንዲገዛ ለማድረግ ሞከረች። ንግሥት ሜሪ በርካታ ፕሮቴስታንቶች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደረገች ሲሆን ከ300 በላይ ሰዎች በእንጨት ላይ ተቃጥለው እንዲሞቱ በማድረጓ ደም አፍሳሿ ሜሪ የሚል ስም አትርፋለች። ያም ሆኖ ግን በወቅቱ ተቀስቅሶ የነበረውን ኃይለኛ የለውጥ ማዕበል ማስቆም አልቻለችም። ሜሪ በ1558 ስትሞት የአባቷ ልጅ የሆነችው ቀዳማዊት ኤሊዛቤት በእርሷ ቦታ ተተካች፤ ኤሊዛቤት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሊቀ ጳጳሱ በእንግሊዝ ሃይማኖታዊ ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ የማሳደርም ሆነ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን እንዳይኖራቸው አደረገች።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ፕሮቴስታንቶች ከሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መገንጠሉ ብቻ በቂ እንዳልሆነና የካቶሊክ ርዝራዦች በሙሉ ተጠራርገው መጥፋት እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያንን አምልኮ ለማጥራት ይፈልጉ ስለነበር ፒዩሪታኖች (የጠራ እምነት ተከታዮች) የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። አንዳንድ ፒዩሪታኖች ደግሞ ጳጳሳት እንደማያስፈልጉና እያንዳንዱ ጉባኤ ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ተገንጥሎ ራሱን ማስተዳደር እንዳለበት ተሰማቸው። እነዚህ ሰዎች ሴፓራቲስቶች (ተገንጣዮች) ተብለው ተጠሩ።

በኤሊዛቤት የግዛት ዘመን፣ ተቀባይነት ያገኘውን የቤተ ክርስቲያን አደረጃጀት የሚቃወሙ ፒዩሪታኖች ብቅ አሉ። ንግሥቲቷ የአንዳንድ ቀሳውስት አለባበስ ለቦታው ተገቢ አለመሆኑ ስላበሳጫት በ1564 የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ የቀሳውስቱን አለባበስ በተመለከተ ሥርዓት እንዲያወጡ መመሪያ ሰጠች። ፒዩሪታኖች የካቶሊክ ቀሳውስት ዓይነት አለባበስ ሊመጣ እንደሆነ ስለተሰማቸው ትእዛዙን ለመቀበል አሻፈረን አሉ። ጥንታዊው የጳጳሳትና የሊቀ ጳጳሳት ሥልጣን ተዋረድ ደግሞ የበለጠ ውዝግብ አስነሳ። ኤሊዛቤት ጳጳሳቱ በነበራቸው ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ በማድረግ እርሷን የቤተ ክርስቲያኒቷ ራስ አድርገው መቀበላቸውን በመሃላ እንዲያረጋግጡ ጠየቀች።

ሴፓራቲስቶች ፒልግሪሞች ሆኑ

በ1603 ቀዳማዊ ጄምስ በኤሊዛቤት እግር ተተክቶ ንጉሥ ሲሆን ሴፓራቲስቶች ለእርሱ ሥልጣን እንዲገዙ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ ጀመረ። በ1608፣ በስክሩቢ ከተማ የሚኖሩ ሴፓራቲስቶች ሃይማኖታዊ ነጻነት ለማግኘት ሲሉ ወደ ሆላንድ ሸሹ። ከጊዜ በኋላ ግን፣ በዚያች አገር ሌሎች ሃይማኖቶችም እንዲኖሩ መፈቀዱና ልቅ ሥነ ምግባር በቸልታ መታየቱ ሴፓራቲስቶችን በእንግሊዝ ከገጠማቸው ሁኔታ ይበልጥ ረበሻቸው። በመሆኑም አውሮፓን ለቅቀው በሰሜን አሜሪካ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ወሰኑ። የዚህ ቡድን አባላት ለእምነታቸው ሲሉ ቤታቸውን ትተው ወደ ሩቅ ቦታ ለመጓዝ ፈቃደኞች በመሆናቸው ከጊዜ በኋላ ፒልግሪሞች የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

ፒልግሪሞች (በመካከላቸው በርከት ያሉ ሴፓራቲስቶች ይገኛሉ) የብሪታንያ ቅኝ ግዛት በሆነችው በቨርጂኒያ ለመስፈር ፈቃድ ስላገኙ በመስከረም ወር 1620 ሜይፍላወር በተባለች መርከብ ተሳፍረው ወደ ሰሜን አሜሪካ ጉዞ ጀመሩ። በግምት 100 የሚሆኑ ትላልቅ ሰዎችና ልጆች በሰ​ሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ለሁለት ወራት ያህል ከኃይለኛ ማዕበል ጋር እየታገሉ ሲጓዙ ከቆዩ በኋላ ከቨርጂኒያ በስተ ሰሜን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቆ ወደሚገኘው ኬፕ ኮድ የተባለ ቦታ ደረሱ። በዚያም፣ አንድ ማኅበረሰብ ለማቋቋምና ለሕጎቹ እየተገዙ ለመኖር እንደሚፈልጉ የሚገልጸውን የሜይፍላወር ስምምነት በመባል የሚታወቅ ሰነድ አዘጋጁ። ታኅሣሥ 21, 1620 በዚያው አካባቢ በምትገኘው በፕሊመዝ ሰፈሩ።

ሕይወት በአሜሪካ

ስደተኞቹ ሰሜን አሜሪካ ሲደርሱ ለክረምቱ ወራት አልተዘጋጁም ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ ከቡድኑ አባላት ግማሽ ያህሉ ሞቱ። ሆኖም ጸደይ ሲጠባ እፎይታ አገኙ። የተረፉት ሰዎች በቂ ቤቶችን ከመሥራታቸውም በላይ በአካባቢው የሚበቅሉ የእህል ዝርያዎችን እንዴት ማምረት እንደሚቻል የአገሩ ተወላጅ ከሆኑት አሜሪካውያን ተማሩ። በ1621 የመከር ወቅት ስደተኞቹ እጅግ የተትረፈረፈ ምርት በማግኘታቸው ላገኙት በረከት አምላክን ለማመስገን አንድ ቀን መደቡ። በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎች ቦታዎችም የሚከበረው ታንክስጊቪንግ የተባለው በዓል የጀመረው ከዚህ ነው። እያደር ብዙ ስደተኞች ወደዚህ ቦታ ስለመጡ ከ15 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የፕሊመዝ ሕዝብ ብዛት ከ2, 000 በላይ ሆነ።

በዚህ መሃል፣ በእንግሊዝ የነበሩ አንዳንድ ፒዩሪታኖችም ሴፓራቲስቶቹ እንዳደረጉት ከአትላንቲክ ባሻገር ወደምትገኘው “ተስፋይቱ ምድር” ቢሄዱ የተሻለ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል አሰቡ። በ1630 በቡድን ሆነው በመጓዝ ከፕሊመዝ በስተ ሰሜን በሚገኘው አካባቢ የማሳቹሴትስ ቤይ ግዛት የሚባለውን የሰፈራ መንደር አቋቋሙ። በ1640 ወደ 20, 000 የሚጠጉ የእንግሊዝ ስደተኞች በኒው ኢንግላንድ ይኖሩ ነበር። በ1691 የማሳቹሴትስ ቤይ ግዛት ተስፋፍቶ ፕሊመዝን ከተቆጣጠረ በኋላ ሴፓራቲስት ተብለው ይጠሩ የነበሩት ፒልግሪሞች ራሳቸውን ከሌሎች መገንጠላቸው አከተመ። ፒዩሪታኖች የኒው ኢንግላንድን ሃይማኖታዊ ሕይወት ስለተቆጣጠሩት ቦስተን የአካባቢው ሃይማኖታዊ ማዕከል ሆነች። እነዚህ ሰዎች አምልኳቸውን የሚያካሂዱት እንዴት ነበር?

የፒዩሪታኖች አምልኮ

በአሜሪካ የሰፈሩት ፒዩሪታኖች መጀመሪያ ላይ በእንጨት የታነጹ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ሠርተው እሁድ እሁድ ጠዋት እዚያ ይሰበሰቡ ነበር። እነዚህ ቤቶች አየሩ ጥሩ በሚሆንበት ወቅት ደህና ነበሩ፤ ክረምት ሲገባ ግን አጥባቂ የሚባሉት ፒዩሪታኖች እንኳ አየሩን ተቋቁመው በዚያ የሚካሄደውን ስብከት ማዳመጥ ፈታኝ ይሆንባቸው ነበር። የመ​ሰብሰቢያ ቦታዎቹ ማሞቂያ ስላልነበራቸው ብዙም ሳይቆይ ተሰብሳቢዎቹ በብርድ ተቆራምደው መንቀጥቀጥ ይጀምራሉ። ብዙውን ጊዜ ሰባኪዎቹ እጆቻቸውን እያንቀሳቀሱ ሲናገሩ በቤቱ ውስጥ ካለው ቅዝቃዜ የተነሳ ቆፈን እንዳይዛቸው ሲሉ ጓንት ያደርጉ ነበር።

ፒዩሪታኖች እምነታቸው የተመሠረተው ጆን ካልቪን በተባለው ፈረንሳዊ የፕሮቴስታንት ሃይማኖታዊ ተሃድሶ አራማጅ ትምህርቶች ላይ ነበር። የሰው እድል አስቀድሞ ተወስኗል የሚለውን እምነት ይቀበሉ የነበረ ሲሆን አምላክ የትኞቹን የሰው ዘሮች እንደሚያድንና የትኞቹን ወደ ዘላለማዊ የሲኦል መቃጠያ እንደሚያስገባቸው አስቀድሞ ወስኗል የሚል እምነት ነበራቸው። እንደ እነርሱ አመለካከት ሰዎች ምንም ቢያደርጉ በአምላክ ዘንድ ያላቸውን ስም መለወጥ አይችሉም። አንድ ሰው ሲሞት በሰማይ አስደሳች ሕይወት ያግኝ ወይም እንደ ጧፍ ለዘላለም ይቃጠል የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

ውሎ አድሮ ግን የፕሮቴስታንት ሰባኪዎች ንስሐ ስለመግባት ማስተማር ጀመሩ። አምላክ መሐሪ ቢሆንም እንኳ ሕግጋቱን የማይታዘዙ ሰዎች በቀጥታ ወደ ሲኦል እንደሚወርዱ ያስጠነቅቁ ነበር። እነዚህ ሰባኪዎች ሕዝቡ፣ ለሚመሩባቸው ሕግጋት ታዛዥ እንዲሆን ለማድረግ ሲሉ ስለ እሳታማ ሲኦል ያስተምሩ ነበር። በ18ኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ጆናታን ኤድዋርድስ የተባለ ሰባኪ በአንድ ወቅት “በተቆጣ አምላክ እጅ ውስጥ የገቡ ኃጢአተኞች” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ሲኦልን አስመልክቶ የሰጠው ማብራሪያ በጣም አስፈሪ ከመሆኑ የተነሳ ሌሎች ቀሳውስት ይህንን ስብከት ሰምተው የተጨነቁትን የጉባኤው አባላት ማጽናናት አስፈልጓቸው ነበር።

ከሌላ ቦታ መጥተው በማሳቹሴትስ የሚሰብኩ ወንጌላውያን እንዲህ የሚያደርጉት ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ነበር። ባለ ሥልጣናቱ ሜሪ ዳየር የተባለችን አንዲት ሰባኪ ሦስት ጊዜ ቢያባርሯትም ተመልሳ እየመጣች አመለካከቷን መስበኳን ቀጠለች። በመጨረሻም ሰኔ 1, 1660 ቦስተን ውስጥ ሰቀሏት። ፊሊፕ ራክሊፍ የተባለው ሰውም የፒዩሪታን መሪዎች በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን ቅንዓት የተሞላበት እርምጃ ሳይዘነጋው አልቀረም። መንግሥትንና የሴለምን ቤተ ክርስቲያን በመቃወም ባደረገው ስብከት የተነሳ ካስገረፉት በኋላ ቅጣት ተበየነበት። ከዚያም ሁኔታውን እንዳይረሳው ለማድረግ ከአገር ከመባረሩ በፊት ሁለቱንም ጆሮዎቹን ቆረጡበት። ፒዩሪታኖች ከሌሎች ጋር ተቻችለው መኖር አለመቻላቸው ሰዎች ከማሳቹሴትስ እንዲሸሹ ያደረገ ሲሆን ይህም ሌሎች ግዛቶች እንዲቋቋሙ መንገድ ከፍቷል።

እብሪት ዓመጽን አስከተለ

በርካታ ፒዩሪታኖች ራሳቸውን የአምላክ “ምርጦች” እንደሆኑ አድርገው ስለሚቆጥሩ የአገሩን ተወላጆች በምድሩ ላይ ለመኖር መብት እንደሌላቸው ከሰው ያነሱ ፍጥረታት አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። ይህ አመለካከት ቅሬታ በመፍጠሩ አንዳንድ የአገሪቱ ተወላጆች ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። በዚህም ምክንያት የፒዩሪታን መሪዎች የሰንበትን ሕግ በማላላት ወንዶች ወደ አምልኮ ቦታ ሲሄዱ መሣሪያ እንዲታጠቁ ፈቀዱላቸው። ከዚያም በ1675 ነገሮች ይበልጥ ተባባሱ።

የዋፓኖአግ የአሜሪካ ሕንዶች መሪ የሆነው ሜታኮሜት (ንጉሥ ፊሊፕ በመባልም ይታወቃል) ሕዝቡ ክልሉን እያጣ እንደሆነ ስለተሰማው የፒዩሪታን ሰፈራ ቦታዎችን በመውረር ቤቶችን ማቃጠልና ሰፋሪዎቹን መግደል ጀመረ። ፒዩሪታኖቹም በምላሹ የበቀል እርምጃ ወሰዱ፤ በዚህ ሁኔታ ውጊያው ለወራት ያህል ቀጠለ። በነሐሴ ወር 1676 ፒዩሪታኖቹ ንጉሥ ፊሊፕን በሮድ ደሴት ያዙት። አንገቱን ከቀሉት በኋላ ሆድ ዕቃውን አውጥተው በድኑን አራት ቦታ ቆራረጡት። በዚህ መንገድ ንጉሥ ፊሊፕ ያካሄደው ጦርነት ሲደመደም የኒው ኢንግላንድ ተወላጅ የሆኑት ሕዝቦችም በነጻነት የመኖራቸው ነገር አከተመለት።

በ18ኛው መቶ ዘመን የፒዩሪታኖች ቅንዓት በሌላም መንገድ ይገለጽ ጀመር። በማሳቹሴትስ የሚገኙ አንዳንድ አገልጋዮች የእንግሊዝን አገዛዝ በማውገዝ ነጻ የመውጣት ፍላጎት እንዲቀሰቀስ አደረጉ። አብዮትን በተመለከተ በሚያደርጉት ውይይት ውስጥ ፖለቲካና ሃይማኖትን ይቀላቅሉ ነበር።

ፒዩሪታኖች አብዛኛውን ጊዜ ጠንክረው የሚሠሩ፣ ደፋሮችና ለሃይማኖታቸው ያደሩ ሰዎች ነበሩ። ሰዎች አሁንም እንኳ “የፒዩሪታኖች ባሕርይ” እና “የፒዩሪታኖች ታማኝነት” ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ። ይሁን እንጂ ቅን ልቦና ብቻውን አንድን ሰው ከሐሰት ትምህርቶች የጠራ እንዲሆን አያደርገውም። ኢየሱስ ክርስቶስ ፖለቲካን ከሃይማኖት ጋር አልቀላቀለም። (ዮሐንስ 6:15፤ 18:36) ጭካኔም ቢሆን “የማይወድ ግን እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” ከሚለው መሠረታዊ ሐቅ ጋር ይጋጫል።​—⁠1 ዮሐንስ 4:8

ያለህበት ሃይማኖት እሳታማ ሲኦል እንዳለ፣ የሰው እድል አስቀድሞ እንደተወሰነ ወይም ሌሎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ መሠረተ ትምህርቶችን ያስተምራል? የሃይማኖትህ መሪዎች በፖለቲካ ጉዳዮች ይካፈላሉ? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናትህ በእውነት የጠራውንና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን “ንጹሕና ነውር የሌለበት ሃይማኖት” ለማ​ግኘት ይረዳሃል።​—⁠ያዕቆብ 1:​27

[ በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ፒዩሪታኖች እና የሲኦል እሳት

ፒዩሪታኖች ሲኦል መቃጠያ ቦታ እንደሆነ ሲያስተምሩ ከአምላክ ቃል ጋር እየተጋጩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ምንም እንደማያውቁና ሊሠቃዩ ወይም ሊደሰቱ እንደማይችሉ ይናገራል። (መክብብ 9:5, 10) ከዚህም በላይ ሰዎችን በእሳት ማሠቃየት እውነተኛው አምላክ ‘ፈጽሞ ያላሰበው’ ነገር ነው። (ኤርምያስ 19:5፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ከዚህ ይልቅ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲለውጡ ይለምናቸዋል፤ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችንም ቢሆን የሚይዘው በርኅራኄ ነው። (ሕዝቅኤል 33:11) የፒዩሪታን ሰባኪዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ አምላክ ጨካኝና ተበቃይ እንደሆነ አድርገው በመስበክ ከእነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች ጋር የሚጋጭ ነገር ያስተምሩ ነበር። ከዚህም በላይ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት በኃይል መጠቀምን ጨምሮ ጭካኔን ያበረታቱ ነበር።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1620 ፒልግሪሞች ሰሜን አሜሪካ ሲደርሱ

[ምንጭ]

Harper’s Encyclopædia of United States History

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1621 የመጀመሪያውን ታንክስጊቪንግ በዓል ሲያከብሩ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በማሳቹሴትስ የሚገኝ የፒዩሪታኖች መሰብሰቢያ ቦታ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆን ካልቪን

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጆናታን ኤድዋርድስ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መሣሪያ የታጠቁ ፒዩሪታን ባልና ሚስት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Library of Congress, Prints & Photographs Division

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ በስተ ግራ:- Snark/Art Resource, NY; ከላይ በስተ ቀኝ:- Harper’s Encyclopædia of United States History; ጆን ካልቪን:- Portrait in Paul Henry’s Life of Calvin, from the book The History of Protestantism (Vol. II); ጆናታን ኤድዋርድስ:- Dictionary of American Portraits/Dover

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፎቶግራፎቹ:- North Wind Picture Archives