ሙፍሎንን ለማየት ያደረግነው ጥረት
ሙፍሎንን ለማየት ያደረግነው ጥረት
በአንድ የግንቦት ወር ጠዋት ላይ ካርታችንንና ካሜራችንን ይዘን፣ ባርኔጣችንን አድርገንና ጠንካራ ጫማ ተጫምተን ለመንገዱ አመቺ በሆነ መኪና ላይ ተሳፍረን ጉዟችንን ጀመርን። የምንጓዘው በቆጵሮስ ደሴት ትሮዶስ በሚባል ተራራ ላይ ወዳለው የፓፎስ ጫካ ሲሆን ዓላማችን ብርቅዬ የሆነውን ሙፍሎንን ለማየት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እንስሳ ምንድን ነው?
ሙፍሎን በመላው የሜዲትራኒያን አካባቢ ከሚገኙ የተለያዩ የዱር በግ ዝርያዎች መካከል አንዱ ነው። ልናየው የጓጓነው ሙፍሎን ግን በቆጵሮስ ብቻ የሚገኝ ሲሆን የአጋዘንን ውበትና የፍየልን ቅልጥፍና አጣምሮ የያዘ እንስሳ እንደሆነ ይነገራል። የሥነ እንስሳ ተመራማሪዎች ኦቪስ ግመሊኒ ኦፊዮን ብለው ሲጠሯቸው ቆጵሮሳውያን ደግሞ አግሪኖ ይሏቸዋል። የሚገኙትም ራቅ ባሉ ተራራማ አካባቢዎች ብቻ ነው።
ዋናውን መንገድ ለቅቀን በተራራው ግርጌና በሚያምረው ሸለቆ ውስጥ መጓዝ ጀመርን። መንደሮቹ የተቆረቆሩት በኮረብታዎች ላይ ሲሆን ሸለቆዎችም በተክሎች ተሸፍነዋል። ይሁን እንጂ ብዙም ሳንጓዝ መንገዱ ወጣ ገባ እየሆነ መጣ፤ እንዲያውም ዥው ባለ ገደል አፋፍ ላይ የነዳንባቸው ጊዜያት ነበሩ። በመጨረሻም ያሰብንበት ጫካ ደረስን። አሁን የምንገኘው 60, 000 ሄክታር በሚሸፍነው የጥድና የዝግባ ደን ውስጥ ነው። ቡና አዝዘን አረንጓዴ የደንብ ልብስ ከለበሰ የደን ባለሙያ ጋር ጨዋታ ጀመርን። አንትርያስ የተባለው ይህ ሰው ስለ ሙፍሎኖች በስሜት ያወራን ጀመር።
በቆጵሮስ ካሉ የዱር አጥቢ እንስሳት መካከል ብዙ ቁጥር ያላቸው ሙፍሎኖች እንደሆኑ አንትርያስ ነገረን። ከዚህ ቀደም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሙፍሎኖች በደሴቲቱ ላይ ይኖሩ ነበር። እነዚህን የዱር በጎች አስመልክቶ የተሠሩ የግሪኮ-ሮማ የስነ ሥዕል ሥራዎች ከመኖራቸውም ሌላ በመካከለኛው ዘመን የተጻፉ ጽሑፎች መኳንንቶች እነዚህን እንስሳት በማደን ይዝናኑ እንደነበር ያሳያሉ።
አንትርያስ ወደ አንድ አጥር እየመራን ስለ ሙፍሎኖች ታሪክ ብዙ ነገሮችን አጫወተን። ለምሳሌ የእንስሳቱ ቁጥር በጣም እየቀነሰ የመጣው ለአደን የሚያገለግል ጠመንጃ ከመጣ በኋላ እንደሆነ ነገረን። በቆጵሮስ አደንን አስመልክቶ የወጣው ሕግ በ1938 እስከተሻሻለበት ጊዜ ድረስ እነዚህ እንስሳት በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ ነበር። ከዚያ በኋላ የደን ባለሙያዎችና ፖሊሶች በመተባበር ሕገ ወጥ አደንን ለማስቀረት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ አዳኞች ከነአካቴው ወደ ጫካው እንዳይገቡ ተከለከለ። እነዚህና ከ1960 ወዲህ የተወሰዱ ሌሎች እርምጃዎች በአካባቢው የሙፍሎኖች ቁጥር ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ አየን
አንትርያስን ተከትለን ወደ አጥሩ በመጠጋት በቁጥቋጦዎቹና በዛፎቹ መካከል አተኩረን መመልከት ጀመርን። በኋላም ጸጥ እንድንል ምልክት ሰጠንና
ከፊታችን እየመራ ዳገቱን ይዞን ወጣ። እዚያ ሆነን ሦስት ሴት ሙፍሎኖችና ሁለት ግልገሎች በአንድ ገላጣ መስክ ላይ ሲግጡ ተመለከትን። ትላልቆቹ ወደ 90 ሴንቲ ሜትር ቁመት ሲኖራቸው መልካቸው ቡናማ ዓይነት ሆኖ ወደ ሆዳቸው አካባቢ አመድማ ይመስላሉ።እነዚህ እንስሳት የሚመገቧቸው ተክሎች በዚህ ወቅት እንደ ልብ ስለሚገኙ ትላልቆቹ ለእኛ ብዙም ትኩረት ሳይሰጡ መጋጣቸውን ቀጠሉ። ግልገሎቹ ግን ቡረቃቸውን አቁመው ወደ እኛ ትንሽ ራመድ አሉ። እኛም በጣም ደስ አለን! ይሁን እንጂ ከመካከላችን የአንዱ ካሜራ ብልጭ ሲል ደንብረው ሁሉም ከመቅጽበት ወደ ጫካው ሮጠው ገቡ።
ባየነው ነገር በጣም ስለተደሰትን በዱሩ ውስጥ ሙፍሎኖችን እንደምናገኝ ተስፋ አድርገን በእግራችን ለመጓዝ እቅድ አወጣን። አንትርያስ እንስሶቹ ብዙውን ጊዜ ጎሕ ሲቀድ ግጦሽ ፍለጋ ወደ ጫካው ዳርቻ ስለሚወጡ በዚያን ጊዜ ብንሞክር የተሻለ እንደሆነ ሐሳብ አቀረበ። እኛም እነርሱን ለማየት በሚያስችለው ተራራ ላይ ድንኳናችንን ተክለን ሌሊቱን እዚያው ለማሳለፍ ወሰንን። ሙፍሎኖች በሞቃት ወራት ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ የሚያዘወትሩ ሲሆን በክረምት ወራት ተራሮች በበረዶ ስለሚሸፈኑ የሚበሏቸውን ተክሎች ፍለጋ ከጫካው ወጥተው ሜዳ ላይ ይታያሉ።
የመራቢያ ጊዜያቸው የሚጀምረው ሞቃታማው ወቅት ካለፈ በኋላ ነው። በክረምት ወቅት ሙፍሎኖች ከ10 እስከ 20 በመሆን በመንጋ ይንቀሳቀሳሉ። በሚያዝያ ወይም በግንቦት አካባቢ ሴቶቹ በሚወልዱበት ጊዜ መንጋው በአነስተኛ ቡድኖች ይከፋፈላል። ይህም ልክ እኛ መጀመሪያ ላይ እንዳየናቸው ማለት ነው። ወንዱ ግን አብዛኛውን ጊዜ የሚግጠው ብቻውን ነው።
የጫካ በግ!
በሚቀጥለው ቀን ጠዋት አቀበቱን በመኪናችን ከወጣን በኋላ በአንድ ሜዳማ ቦታ አቆምናት። ከዚያም ፀሐይዋ በደንብ ከመውጣቷ በፊት ወደ ጫካው በእግራችን መጓዝ ጀመርን። ጫካው እረጭ ያለ ከመሆኑም በላይ ከዛፎቹ ላይ ጤዛ ይንጠባጠባል። ጸጥታው ስላስደሰተን ትንሽ ቆም አልን። በዚህ አጋጣሚ በጣም የሚያምርና ደልደል ያለ ወንድ ሙፍሎን አየን። በክረምት ወራት እጅብ ብሎ የነበረው ፀጉሩ በመርገፍ ላይ ነው። ጉሮሮው አካባቢ ጥቁር ፀጉር ሸፍኖታል። በኩራት አንገቱን ዞር በማድረግ ትኩር ብሎ ወደ እኛ ተመለከተና ጠረናችንን ለመለየት አካባቢውን ማሽተት ጀመረ። ሁለቱ ወፍራምና ጠምዛዛ ቀንዶቹ ቢያንስ የ40 ሴንቲ ሜትር ርዝመት አላቸው! ትናንት አይተናቸው ከነበሩት ሴት ሙፍሎኖች ወፈር ስለሚል ወደ 35 ኪሎ ግራም ሳይመዝን አይቀርም።
ሁላችንም ምንም ድምፅ ሳናሰማ ፀጥ ብለን ቆየን። የሆነ ሆኖ ይህ ተጠራጣሪ እንስሳ መኖራችንን በጠረን በመለየቱ አንገቱን እያወዛወዘ ቁልቁል ወረደ። በእነዚህ ሁለት ቀናት ያየናቸውና የተማርናቸው ነገሮች እንዴት የሚመስጡ ናቸው! ይህ ጉብኝት “የዱር አራዊት ሁሉ፣ በሺ ተራራዎች ላይ ያለውም እንስሳ የእኔ ነውና” ብሎ ለተናገረው ፈጣሪ ያለን አድናቆት እንዲጨምር አድርጎልናል።—መዝሙር 50:10
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የቆጵሮስ ሙፍሎን (ከጀርባ ያለው) እና የአውሮፓ ሙፍሎን
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከላይ በስተ ቀኝ:- Oxford Scientific/photolibrary/Niall Benvie; የአውሮፓ ሙፍሎን:- Oxford Scientific/photolibrary