በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ?

በተቃራኒ ጾታ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ ትችላለህ? ሀብታም መሆን ወይም መልክና ቁመናህን ማሳመር ይረዳህ ይሆን?

ወንዶችም ሆኑ ሴቶች፣ ማስታወቂያና መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ስለሚያሳድሩባቸው ተወዳጅ ለመሆን እነዚህ ነገሮች ሊኖሯቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል። እርግጥ ለመልካችን መጨነቃችን ተፈጥሯዊ ቢሆንም ውበት አላፊ በመሆኑ ዘላቂነት ያለው ጥምረት ለመመሥረት የሚያስችል ወሳኝ ነገር አይደለም። ሀብትም ቢሆን እንደዚሁ ነው። በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን የሚረዳው ትልቁ ነገር ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር ማሳየት ነው። ኢየሱስ “ስጡ፤ ይሰጣችኋል” በማለት አስተምሯል። (ሉቃስ 6:​38) በሌላ አባባል በሌሎች ዘንድ ለመወደድ ከፈለጋችሁ አፍቃሪዎች ሁኑ።

ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ በመመራት የዚህን ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። ፍቅር ኃይል ያለው እንደሆነና በዋነኝነት የሚገለጸውም በስሜት ሳይሆን ለሌሎች በሚያደርጋቸውና በሌሎች ላይ በማያደርጋቸው ነገሮች እንደሆነ ገልጿል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፣ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፅ ደስ አይሰኝም። ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4-7

አንድ ሰው የሚያበሳጨውን ነገር ተናግረህ ወይም አድርገህም እንኳ በደግነት ቢይዝህ ወይም ይበልጥ ቢያቀርብህ ምን ይሰማሃል? ከልብ የሚያስብልህ፣ በቀላሉ የማይናደድ እንዲሁም ይቅርታ ማድረግና እውነቱን መናገር ቀላል በማይሆንበት ጊዜም እንኳ እነዚህን ባሕርያት የሚያሳይ ሰው የበለጠ እንድትቀርበው አያደርግህም?

ስለዚህ አንተም ለሌሎች እንዲሁ አድርግ። ኢየሱስ “ሌሎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር እናንተም አድርጉላቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 7:​12) ፍቅር ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እንኳ ጥረት ማድረጉ የሚያስቆጭ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በቤተሰብህ፣ በጓደኞችህ፣ በትዳር ጓደኛህ ወይም በወደፊቱ የትዳር ጓደኛህ ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ ያደርግሃል። ከዚህ በተጨማሪም ትክክለኛውን ነገር ማድረግህ ይኸውም ለሌሎች መልካም ለማድረግ መጣጣርህ ደስታ ያስገኝልሃል። አዎን፣ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 20:​35

ስለ ፍቅር አስተማማኝ መረጃ ሊሰጠን ከሚችለው አካል መማር

ይሖዋ የፍቅር አምላክ ነው፤ ስለ ፍቅር ከእሱ የተሻለ እውቀት ሊሰጠን የሚችል የለም። (1 ዮሐንስ 4:​8) ፍቅሩ ለመማር ፈቃደኛ ለሆኑ ሁሉ ይህን ባሕርይ ለማስተማር ይገፋፋዋል። ሌሎችን ለመውደድም ሆነ በሌሎች ዘንድ ለመወደድ እንድንችል የሚረዱንን ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።

“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . ይሁን።” (ያዕቆብ 1:​19) ከ20, 000 በላይ በሚሆኑ ባልና ሚስቶች ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት ደስተኞች የሆኑት ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸው ጥሩ አድማጭ እንደሆኑ ታይቷል። በትዳር ውስጥ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ ነው። በሶሺዮሎጂ መስክ ፕሮፌሰር የሆኑ ሴት እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ወዳጅህ ስላለህበት ሁኔታ ምንም የማያውቅ ከሆነ ብቸኝነት ሊሰማህ ይችላል። ከዚህ የከፋው ደግሞ ግለሰቡ ስላለህበት ሁኔታ ቢያውቅም ስሜትህን የማይረዳልህ ከሆነ ነው።” አክለውም ሁለት ሰዎች በብዙ ነገሮች የተለያዩ ቢሆኑም እንኳ “የትዳር ጓደኛህ የሚሰማህን ነገርና በሕይወትህ ያጋጠሙህን ነገሮች የሚረዳልህ ከሆነ ያሉት ልዩነቶች እምብዛም ከባድ አይሆኑም።”

“ፍቅራችሁን የነፈጋችሁን እናንተ ናችሁ . . . ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱልን።” (2 ቆሮንቶስ 6:​12, 13) ልባችንን ከፍተን ለሌሎች ፍቅር ስናሳይ እንጠቀማለን። ከሃርቫርድ የሕክምና ትምህርት ቤት የተገኘ አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ጥሩ የሆነ ማለትም ከቤተሰብ፣ ከጓደኞችና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ደስተኞች ናቸው፤ እንዲሁም ብዙም የጤንነት ችግር እንደሌላቸውና ለረጅም ጊዜ መኖር እንደሚችሉ በርካታ ጥናቶች አሳይተዋል።”

“እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ።” (ዕብራውያን 10:​24, 25) ወዳጅ እንዲሆኑን የምንመርጣቸው ሰዎች ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። እውነተኛ ክርስቲያናዊ ፍቅር ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ይህ ባሕርይ በተግባር ሲውል የማየት አጋጣሚ ስለሚሰጥህ በሕይወትህ ውስጥ እንዴት ልትሠራበት እንደምትችልም ትማራለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ዓይነቱ ፍቅር የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መለያ ምልክት እንደሆነ ስለሚያውቁ አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ለማሳየት ይጥራሉ። (ዮሐንስ 13:​35) በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ ብትገኝ በጣም ደስ ይላቸዋል።

እንደማትወደድ የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ ወይም ራስህን አትንቀፍ። ይሖዋ ሁኔታህን እንደሚመለከት አስታውስ። በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የተገለጸችውን ልያን ታስታውሳለህ? ይሖዋ ሁኔታዋን ይመለከት ስለነበር ልጆች እንደ ውድ ሃብት ተደርገው በሚታዩበት ዘመን የስድስት ወንድ ልጆችና የአንዲት ሴት ልጅ እናት በመሆኗ በእጅጉ ተባርካለች! ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም የልያ ልጆች የእስራኤል ነገዶች አባቶች ሆነዋል። (ዘፍጥረት 29:​30-35፤ 30:​16-21) ልያ የአምላክ ፍቅራዊ አሳቢነት ምን ያህል አጽናንቷት እንደሚሆን መገመት አያዳግትም!

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በተገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ ማንም እንደማይወደድ አይሰማውም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ፍቅር በሰው ልጆች መካከል ይሰፍናል። (ኢሳይያስ 11:​9፤ 1 ዮሐንስ 4:​7-12) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውንና የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው አምላክ ያሳየንን ዓይነት ፍቅር በማዳበር በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመኖር እንደምንፈልግ ማሳየት እንችላለን። አዎን፣ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በሌሎች በመወደድ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር በማሳየትም ጭምር ነው።​—⁠ማቴዎስ 5:​46-48፤ 1 ጴጥሮስ 1:​22

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 20:​35

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመወደድ ከፈለጋችሁ ለሌሎች ፍቅር አሳዩ