በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሌሎች የመወደድ ፍላጎት

በሌሎች የመወደድ ፍላጎት

በሌሎች የመወደድ ፍላጎት

ከረጅም ጊዜ በፊት አንዲት ልያ የተባለች ልጃገረድ አሁን ቱርክ ተብላ በምትጠራው አገር ውስጥ በምትገኝ ከተማ ትኖር ነበር። ልያ መልኳ ብዙም የማያምር ሲሆን ታናሽ እህቷ ራሔል ግን ቆንጆ ነበረች።

ራሔልን በጣም የሚወዳት አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው እሷን ለማግባት ሲል ለሰባት ዓመታት አባቷን ለማገልገል ተስማማ። ይሁን እንጂ በሠርጉ ዕለት ምሽት ላይ የልጆቹ አባት በራሔል ፈንታ ልያን ዳረለት። ልያ፣ አባቷ ስለተጠቀመበት ዘዴ ምን እንደተሰማት የተገለጸ ነገር ባይኖርም ትዳር በዚህ ሁኔታ መጀመር እንደሌለበት ግን ሳታውቅ አትቀርም።

ሙሽራው ምን እንደተፈጸመ ሲያውቅ በሁኔታው ቅሬታ እንደተሰማው ገለጸ። አባትየውም በባሕሉ መሠረት መጀመሪያ ማግባት ያለባት ትልቋ ልጅ እንደሆነች ገለጸለት። በዚህ መንገድ ልያ ታናሽ እህቷን ይወድ ለነበረ ሰው በተንኮል ተዳረች፤ በዚያ ላይ ደግሞ ይህ ሰው ታናሽ እህቷንም አገባት። ልያ ከእሷ ይበልጥ እህቷ መወደዷን ስታይ ምን ያህል እንደምታዝን መገመት አያዳግትም! ልያ ከጋብቻዋ በፊት ስላሳለፈችው የፍቅር ጊዜም ሆነ ስለ ሠርጓ ቀን ልታወራው የምትችለው ምንም አስደሳች ትዝታ የላትም። የራሔልን ያህል ለመፈቀር ትጓጓ እንደነበር መገመት አያዳግትም! በመሆኑም ልያ፣ ሁኔታውን መለወጥ ባትችልም እንኳ እንደማትፈለግና እንደማትወደድ ተሰምቷት ሊሆን ይችላል። *

በዛሬው ጊዜ፣ ብዙዎች በተወሰነ ደረጃ የልያ ዓይነት ስሜት ሊኖራቸው ይችላል። ሁላችንም ቢሆን የማፍቀርም ሆነ የመፈቀር ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ምናልባት የሚያፈቅረን የትዳር ጓደኛ ለማግኘት እንጓጓ ይሆናል። ወላጆቻችን፣ ልጆቻችን፣ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን እንዲሁም ጓደኞቻችን እንዲወዱንም እንፈልጋለን። ልክ እንደ ልያ እኛም ሌሎች የተወደዱትን ያህል የሚወደን ሰው እንደሌለ ይሰማን ይሆናል።

ከልጅነታችን ጀምሮ ቆንጆ የሆኑ ሁለት ሰዎች እንደተዋደዱና ቀሪ ሕይወታቸውን በደስታ እንዳሳለፉ የሚናገሩ የፍቅር ታሪኮችን ሰምተናል። ዘፋኞች ስለ ፍቅር ይዘፍናሉ፤ ገጣሚዎችም በጽሑፋቸው ያወድሱታል። ሆኖም ስለዚህ ጉዳይ የሚያጠኑ አንድ ተማራማሪ “የፍቅርን ያህል በከፍተኛ ጉጉትና ተስፋ ተጀምሮ በሐዘን የሚደመደም ነገር የለም” ብለዋል። በእርግጥም አብዛኛውን ጊዜ ከዘላቂ ደስታ ይልቅ የመረረ ሐዘን የሚያስከትልብን በጣም ከምንቀርባቸው ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ነው። በብዙ አገሮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከሚፈጸሙት ጋብቻዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በፍቺ ሲያበቁ ካልተፋቱት መካከል ደግሞ አብዛኞቹ ባለትዳሮች ፈጽሞ ደስተኞች አይደሉም።

በብዙ አገሮች ውስጥ በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦችና ሰላም የጠፋባቸው ትዳሮች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ ሁኔታው እንደዚህ ባሉ ቤተሰቦች ውስጥ የሚገኙትንም ልጆች ለሥቃይ ዳርጓቸዋል። ይሁን እንጂ ልጆች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ የሚንከባከባቸው አፍቃሪ ቤተሰብ ይፈልጋሉ። ታዲያ ፍቅር የጠፋው ለምንድን ነው? ስለዚህ ውድ ባሕርይ ማን ሊያሳውቀን ይችላል? የሚቀጥሉት ርዕሶች እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ይህ ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 29 እና 30 ላይ ይገኛል።