በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት ከጾታ ብልግና መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

በትምህርት ቤት ከጾታ ብልግና መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

በትምህርት ቤት ከጾታ ብልግና መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

“ልጆች በየዕለቱ ስለ ጾታ ግንኙነት ያወራሉ። ሴቶች ተማሪዎች ጭምር ወንዶቹን ቀርበው ይጠይቋቸውና እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ ወሲብ ይፈጽማሉ።”— አይሊን፣ 16 ዓመት

“በትምህርት ቤታችን ውስጥ ግብረ ሰዶማውያን በሌሎች ተማሪዎች ፊት አስጸያፊ ነገሮችን ያደርጋሉ፤ ይህም እንደ ተራ ነገር ይታያል።”— ማይክል፣ 15 ዓመት  *

የክፍል ጓደኞችህ ብዙውን ጊዜ ስለ ጾታ ጉዳይ ማውራት ይቀናቸዋል? አንዳንዶቹስ ከማውራት ያለፈ ድርጊት ይፈጽማሉ? ነገሩ እንዲህ ከሆነ ትምህርት ቤቷን “ልቅ የጾታ ግንኙነት የሚያሳይ ፊልም ከሚተወንበትና ከሚቀረጽበት ስፍራ” ጋር ያመሳሰለችውን የአንዲት ወጣት ስሜት ሳትጋራት አትቀርም። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ትምህርት ቤቶች ለወጣቶች ስለ ወሲብ ለማውራት አልፎ ተርፎም ድርጊቱን ለመፈጸም የሚያስችሉ ምቹ አጋጣሚዎችን እየፈጠሩላቸው ነው።

የክፍል ጓደኞችህ ምንም ዓይነት ስሜታዊ ቅርርብ ሳይኖራቸው የጾታ ግንኙነት ስለመፈጸም ሲያወሩ ሰምተህ ይሆናል። አንዳንዴም ልጆች እምብዛም ከማያውቁት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። በሌሎች አጋጣሚዎች ደግሞ በኢንተርኔት ካገኟቸው ፍጹም የማያውቋቸው ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት ለማድረግ ይቀጣጠራሉ። በማንኛውም መልኩ ይሁን እነዚህ ልጆች እንዲህ ዓይነቱን የጾታ ግንኙነት ማድረግ የሚፈልጉት ፍቅር ከሚፈጥረው የስሜት ቅርርብ ለመሸሽ ሲሉ ነው። ዳንዬል የምትባል አንዲት የ19 ዓመት ወጣት ሁኔታውን አስመልክታ ስትናገር “ይህ ቅርርብ ሁለት ሰዎች ያላቸውን ሥጋዊ ፍላጎት ከማርካት የዘለለ አይደለም” ብላለች።

ስሜታዊ ቅርርብ ሳይኖር የጾታ ፍላጎትን ለማርካት ብቻ ተብሎ የሚደረግ ወሲብ በብዙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ አያስደንቅም። አንዲት የ17 ዓመት ወጣት በትምህርት ቤቷ በሚታተመው ጋዜጣ ላይ እንደሚከተለው ስትል የታዘበችውን አስፍራለች:- “ቅዳሜና እሁድ ካለፈ በኋላ የትምህርት ቤቱ መተላለፊያዎች በቅርብ ስለተፈጸመ የጾታ ግንኙነት ዝርዝር ጉዳዮችን እያነሱ በስሜት በሚነጋገሩ ጓደኛሞች ሁካታ ይሞላሉ።”

የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ለመጠበቅ የምትጣጣር ወጣት ከሆንክ ከጾታ ግንኙነት በስተቀር ወሬ የሌላቸው በሚመስሉ ልጆች መከበብህ ባይተዋርነት እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። ከእነርሱ ጋር መቀላቀል ካልቻልክ ደግሞ የፌዝ ዒላማ መሆንህ አይቀርም። በአንዳንድ መልኩ እንዲህ ማድረጋቸው ያን ያህል የሚያስደንቅ አይደለም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች መንገዳችሁን ባለማወቃቸው ምክንያት “ይሰድቧችኋል” በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 4:​3, 4) ያም ሆኖ እንዲፌዝበት የሚፈልግ ሰው የለም። ታዲያ በትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ጾታ ግንኙነት ከማውራትም ሆነ ድርጊቱን ከመፈጸም መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው? በዚህ አቋምህ እንድትኮራስ ምን ሊረዳህ ይችላል? በመጀመሪያ የጾታ ፈተና ያን ያህል ከባድ የሆነው ለምን እንደሆነ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው።

ራስህን እወቅ

ስትጎረምስ በአካልህም ሆነ በስሜትህ ላይ ብዙ ዓይነት ለውጦች ይከሰታሉ። በዚህ ወቅት ከፍተኛ የጾታ ፍላጎት ያድርብሃል። ይህ ደግሞ ምንም ስህተት የለውም። ስለዚህ በትምህርት ቤትህ ውስጥ በሚገኙት ተቃራኒ ጾታ ባላቸው ሰዎች ብትማረክ የሥነ ምግባር ንጽሕናህን ጠብቀህ ለመኖር አቅሙ እንደሌለህ አሊያም መጥፎ ሰው እንደሆንክ ሊሰማህ አይገባም። ንጹሕ ሆነህ መቀጠል ከፈለግህ ትችላለህ!

የጉርምስና ዕድሜ ከሚያስከትልብህ ውስጣዊ ትግል በተጨማሪ ሌላም ልታውቀው የሚገባ ነገር አለ። ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ሰዎች ስንባል ሁላችንም መጥፎ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌ አለን። ሌላው ቀርቶ ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ “ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ” በማለት ስሜቱን በግልጽ ተናግሯል። ጳውሎስ አለፍጽምና “ጐስቋላ” መሆኑ እንዲሰማው እንዳደረገውም ገልጿል። (ሮሜ 7:​23, 24) ይሁንና ያለበትን ትግል በድል መወጣት ችሏል፤ አንተም ብትሆን ትችላለህ!

የክፍል ጓደኞችህን ስሜት ለመረዳት ሞክር

ቀደም ሲል እንደተገለጸው የክፍል ጓደኞችህ ዘወትር ስለ ጾታ ጉዳዮች ያወሩ ወይም ደግሞ ፈጸምን ስላሉት አንድ ዓይነት የጾታ ብልግና በጉራ ይለፍፉ ይሆናል። እነዚህ ልጆች መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብህም። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ሆኖም የክፍል ጓደኞችህን እንደ ጠላት አድርገህ መመልከት አይኖርብህም። ለምን?

የክፍል ጓደኞችህ አንተ የሚሰማህ ዓይነት ስሜት አላቸው። በተጨማሪም መጥፎ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌ ይኖራቸዋል። ይሁንና ከአንተ በተለየ መልኩ አንዳንዶቹ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ወይም ደግሞ እርስ በርስ ‘ፍቅር ከሌላቸው’ ቤተሰቦች የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-4) አንዳንዶቹ የክፍል ጓደኞችህ ጥሩ ወላጆች ሊሰጡ የሚገባቸውን ፍቅራዊ ተግሣጽና ሥነ ምግባራዊ ሥልጠና ሳያገኙ ቀርተውም ይሆናል።​—⁠ኤፌሶን 6:⁠4

የክፍል ጓደኞችህ የላቀ የጥበብ ምንጭ የሆነውን የአምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንተ ስላልተማሩ ለስሜት መሸነፍ የሚያስከትለውን አደጋ አያውቁ ይሆናል። (ሮሜ 1:26, 27) ሁኔታው ወላጆች ልጆቻቸውን መኪና መንዳት ሳያስተምሩ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው መኪና ሰጥተው በተጨናነቀ አውራ ጎዳና ላይ እንዲያሽከረክሩ ብቻቸውን የለቀቋቸው ያህል ነው። ልጆቹ መኪናውን ማሽከርከራቸው ለጊዜው ያስደስታቸው ይሆናል፤ አደጋ መከሰቱ ግን አይቀርም። ታዲያ የክፍል ጓደኞችህ አንተ ባለህበት ስለ ጾታ ጉዳይ ማውራት ቢጀምሩ ወይም ደግሞ በመጥፎ ምግባራቸው እንድትተባበራቸው ቢገፋፉህ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

በብልግና ወሬዎች ከመካፈል ተቆጠብ

የክፍል ጓደኞችህ ስለ ጾታ ብልግና ማውራት ሲጀምሩ አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራስህ ላለመሳብ ስትል ሁኔታውን ለመስማት አሊያም አብረህ ለማውራት ትፈተን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ማድረግህ ለእነርሱ ምን መልእክት እንደሚያስተላልፍ አስብ። በወሬያቸው መሳብህ እውነተኛ ማንነትህን ወይም ምን ዓይነት ሰው ለመሆን እንደምትፈልግ የሚያሳይ አይሆንም?

ታዲያ ጭውውታችሁ ስለ ጾታ ብልግናዎች ወደ ማውራት ቢቀየር ምን ማድረግ ይገባሃል? ወዲያውኑ ተነስተህ መሄድ አይኖርብህም? እንዴታ! (ኤፌሶን 5:​3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 22:3) ይህን ጭውውት አቋርጠህ መሄድህ ሥርዓት እንደሚጎድልህ ሳይሆን አስተዋይ መሆንህን የሚያሳይ ነው።

የብልግና ወሬ ሲነሳ ከዚያ አካባቢ ዞር በማለትህ ልትቆጭ አይገባም። ስለ ጾታ ግንኙነት ባይሆንም እንኳ አንድ ርዕሰ ጉዳይ እምብዛም ካልማረከህ አሊያም ስለዚያ ነገር ሐሳብ መስጠት ካልፈለግህ ምንም ሳትሸማቀቅ ትተህ እንደምትሄድ እሙን ነው። ለምሳሌ ያህል በክፍልህ ካሉት ተማሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰብሰብ ብለው በመሣሪያ የታገዘ ዝርፊያ ስለመፈጸም ያወራሉ እንበል። በዚህ ጊዜ አብረሃቸው መቆየትና ዕቅዳቸውን መስማት ትፈልጋለህ? እንዲህ ማድረግህ እንደ ተባባሪ ሊያስቆጥርህ ይችላል። ስለሆነም ከዚህ ሁኔታ በጥበብ መራቅ ትመርጥ ይሆናል። ስለ ሥነ ምግባር ብልግና ማውራት ሲጀመርም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ትችላለህ። ብዙውን ጊዜ ሌሎቹ ተመጻዳቂ እንደሆንክ ተሰምቷቸው እንዲያፌዙብህ የሚጋብዝ ነገር ሳታደርግ ከቦታው የምትርቅበትን መንገድ ፈልግ።

እርግጥ ነው፣ እንዲህ የመሰለ ሁኔታ ሲያጋጥም ከቦታው ዞር ማለት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ክፍል ውስጥ አጠገብህ እንዲቀመጡ የተመደቡት ልጆች ስለ ጾታ ጉዳዮች እንድታዋራቸው ለማድረግ ይጥሩ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ሲገጥምህ ጠንከር ባለ ሆኖም ትሕትና በተላበሰ አነጋገር እንዲህ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ልትነግራቸው ትችላለህ። ይህ የማይሠራ ከሆነ ልክ እንደ ብሬንዳ ማድረግ ትችል ይሆናል። “ወደ መምህራችን ሄጄ ቦታ እንዲቀይረኝ በዘዴ ጠየቅኩት” ብላለች።

አስተዋይ ሁን

ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ አንዳንድ የክፍል ጓደኞችህ በሚያደርጓቸው አስጸያፊ ጭውውቶች ለምን እንደማትካፈል ለማወቅ መፈለጋቸው አይቀርም። የሥነ ምግባር አቋምህን ለማወቅ ከፈለጉ እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብህ ማስተዋል ይኖርብሃል። እርግጥ አንዳንዶቹ የሚጠይቁህ ሊያሾፉብህ እንጂ አመለካከትህን ለማወቅ ፈልገው ላይሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ልጅ በቅን ልቦና ተነሳስቶ ጥያቄ ካቀረበልህ ስለምታምንባቸው ነገሮች በልበ ሙሉነት ንገረው። በዚህ ረገድ ብዙ ወጣቶች በመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች መመራት የሚያመጣቸውን ጥቅሞች ለክፍል ጓደኞቻቸው ለማስረዳት ሲሉ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለውን መጽሐፍ ይጠቀማሉ። *

ቆራጥ ሁን

አንድ አብሮህ የሚማር ልጅ ደፍሮ ተገቢ ያልሆነ ቦታ ሊነካህ ወይም ሊስምህ ቢሞክርስ? እንዲህ ዓይነቱን ሰው ችላ ብለህ ማለፍህ እርሱ ወይም እርሷ በመጥፎ ምግባራቸው እንዲገፉበት የልብ ልብ ሊሰጣቸው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነች ሴት እንድትይዘውና እንድትስመው ስለፈቀደ አንድ ወጣት ይናገራል። ይህ ወጣት የጾታ ፍላጎትን በሚቀሰቅሱ የሚያግባቡ ቃላት ስታነጋግረው ዝም ብሎ አዳምጧታል። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ፣ . . . ሳያንገራግር ተከተላት።”​—⁠ምሳሌ 7:​13-​23

በአንጻሩ ግን ዮሴፍ ተመሳሳይ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ያደረገውን ተመልከት። የጌታው ሚስት እርሱን ለማባበል የቻለችውን ሁሉ ብታደርግም እርሱ ግን ያቀረበችለትን ግብዣ ፈጽሞ አልተቀበለም። በመጨረሻ ልትይዘው ሞከረች፤ በዚህ ጊዜ ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ጥሏት ሸሸ።​—⁠ዘፍጥረት 39:​7-​12

የክፍል ጓደኛህ ወይም ሌላ ሰው ያለአግባብ ሊነካህ ቢሞክር ልክ እንደ ዮሴፍ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርብህ ይሆናል። “አንድ ልጅ ሊነካኝ ቢሞክር አርፎ እንዲቀመጥ እነግረዋለሁ። አልሰማ ካለ እጁን እንዲሰበስብ በመንገር እጮኽበታለሁ” ስትል አይሊን ተናግራለች። ቀጠል አድርጋም በትምህርት ቤቷ ስላሉ ወጣት ወንዶች ስትናገር “አንተ ራስህ እንዲያከብሩህ ካላደረግህ በስተቀር እነርሱ አያከብሩህም” ብላለች።

የብልግና ንግግሮችን ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆንህ በክፍል ጓደኞችህ ዘንድ አክብሮት ያስገኝልሃል፤ አስፈላጊ ሆኖ ስታገኘው ያለህን የሥነ ምግባር አቋም በአክብሮት ግለጽ እንዲሁም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሲቀርቡህ በጥብቅ ከመቃወም ወደኋላ አትበል። እንዲህ ማድረግህ የሚያስገኝልህ ሌላው ጥቅም ደግሞ ለራስህ ጥሩ ግምት እንዲኖርህ ማስቻሉ ነው። ከሁሉም በላይ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልሃል!​—⁠ምሳሌ 27:⁠11

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.22 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ከብልግና ወሬዎች ለመራቅ ለራስህ ምን ምክንያቶችን ማቅረብ ትችላለህ?

▪ አንድ የክፍል ጓደኛህ አቀራረቡ ካላማረህ ምን ትለዋለህ? ምንስ ማድረግ ይኖርብሃል?

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጭውውቱ ስለ ጾታ ብልግና ወደ ማውራት ከተቀየረ ስፍራውን ለቅቀህ ሂድ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሰው አቀራረቡ ካላማረህ ተቃውሞህን ከመግለጽ ወደኋላ አትበል