በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእርግጥ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው?

በእርግጥ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው?

የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

በእርግጥ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው?

ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን በእርግጠኝነት “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎታል። (ማቴዎስ 16:16) ይህ ጥቅስ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ከሚናገሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል አንዱ ሲሆን ሃይማኖተኛ በሆኑ ሰዎች አእምሮ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች የአምላክ ልጅ ተብሎ የተጠራው ለምን እንደሆነ ማስረዳት ይከብዳቸዋል። ሁለቱንም ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። ሌሎች ደግሞ ኢየሱስ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ሰው፣ ጠቢብ ምናልባትም እውነተኛ የአምላክ ነቢይ ከመሆን ያለፈ ሥልጣን እንደሌለው ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚያስተምረው ምንድን ነው? በዚህ ረገድ ያለህ እምነት ለውጥ ያመጣል?

የአምላክ የበኩር ልጅ

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ብቻውን የነበረበት ወቅት እንደነበር ይናገራል። አምላክ ከፍቅር ተነሳስቶ ለሌሎች ሕይወትን በመስጠት አባት ለመሆን ወሰነ፤ ይህ ሲባል ግን የእርሱ አባትነት ሰዎች አባት እንደሚሆኑት ዓይነት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን የመፍጠር ኃይሉን ተጠቅሞ የማሰብ ችሎታ ያለው ሕያው መንፈሳዊ አካል ፈጠረ፤ ‘የእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ’ የሆነው ይህ መንፈሳዊ አካል በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ በመባል ይታወቃል። (ራእይ 3:​14 የ1954 ትርጉም ፤ ምሳሌ 8:​22) ኢየሱስ ምንም ነገር ከመፈጠሩ በፊት በአምላክ በቀጥታ ስለተፈጠረ ‘አንድያ ልጅ’ እንዲሁም “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው።​—⁠ዮሐንስ 1:​14፤ ቈላስይስ 1:​15

ኢየሱስ ከአምላክ ፍጥረታት ሁሉ በኩር እንደመሆኑ መጠን “ብቻውን አምላክ” የተባለውን ፈጣሪ መሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:​17) በአንጻሩ ግን አምላክ ብዙ መብቶችን ለልጁ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ‘ሁሉን ነገር’ ሌላው ቀርቶ መላእክትን እንኳ የፈጠረው በክርስቶስ በኩል ነው። ለእነዚህም መላእክት ሕይወት የሰጣቸው ይሖዋ በመሆኑ “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለው ተጠርተዋል።​—⁠ቈላስይስ 1:​16፤ ኢዮብ 1:6 የግርጌ ማስታወሻ፤ 38:7 የግርጌ ማስታወሻ

አምላክ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ካዘጋጃት በኋላ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ” ያለው ለበኩር ልጁ ሳይሆን አይቀርም። (ዘፍጥረት 1:​26፤ ምሳሌ 8:​22-​31) ስለዚህ ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰብዓዊ ልጁን አዳምንም ቢሆን የፈጠረው ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ በተባለው መንፈሳዊ ፍጡር አማካኝነት ነው።​—⁠ሉቃስ 3:​38

ኢየሱስ የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ ሆነ

ሐዋርያው ዮሐንስ የተቀጠረው ጊዜ ሲደርስ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ “ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:​14) አምላክ የኢየሱስን ሕይወት ከሰማይ ወስዶ በተአምራዊ መንገድ አይሁዳዊት ድንግል ወደነበረችው ወደ ማርያም ማኅፀን በማዛወር ኢየሱስ የነበረውን መንፈሳዊ ተፈጥሮ ወደ ሰብዓዊ አካል ለውጦታል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ ሰው ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ቀጥሏል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ሕይወቱን ያገኘው ከአምላክ እንጂ ከማንኛውም ሰው ባለመሆኑ ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ሆኖ ተወልዷል። በመሆኑም መልአኩ ገብርኤል ለማርያም “ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” ብሏታል።​—⁠ሉቃስ 1:​35፤ ዕብራውያን 7:​26

ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በነበረበት ጊዜ የአምላክ ልጅ ስለመሆኑ ከራሱ ከአብ ዘንድ ግልጽ ማረጋገጫ አግኝቶ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በሚጠመቅበት ጊዜ ሰማያት ተከፍተው “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሲነገር ሰምቷል። (ማቴዎስ 3:​16, 17) ዮሐንስ ለደቀ መዛሙርቱ “አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ” ማለቱ ምንም አያስደንቅም።​—⁠ዮሐንስ 1:​34

ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን የአምላክ ልጅ ወይም መሲሕ መሆኑ እንዲታወቅለት በየአደባባዩ አላወጀም። (ማርቆስ 8:​29, 30) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ትምህርቶቹን በማዳመጥ፣ አኗኗሩን በመመልከትና በሕዝብ ፊት የሠራቸውን ብዙ ተአምራት በማስተዋል መሲሕ መሆኑን ራሳቸው እንዲደመድሙ ይፈልግ ነበር። ለምሳሌ ‘በተለያዩ በሽታዎች የታመሙትንና በክፉ ደዌ የሚሠቃዩትን ሁሉ’ ፈውሷል። (ማቴዎስ 4:​24, 25፤ 7:​28, 29፤ 12:15) ኢየሱስ ማየትም ሆነ መስማት የተሳናቸው፣ የአካል ጉዳተኞችና የታመሙ ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ሲመጡ ይፈውሳቸው ነበር። ሌላው ይቅርና ሙታንን እንኳ አስነስቷል! (ማቴዎስ 11:​4-6) ደቀ መዛሙርቱ፣ ኢየሱስ በተአምር ውኃ ላይ ሲሄድም ሆነ ማዕበል በተነሳ ጊዜ ነፋሱንና ሞገዱን ጸጥ ሲያደርግ በዓይናቸው ተመልክተዋል። ደቀ መዛሙርቱ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው መመልከታቸው “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” እንዲሉት አነሳስቷቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 14:24-​33

የአምላክ ልጅ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

አምላክ አንድያ ልጁን ከሰማይ ወደ ምድር ከላከው በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲሞት የፈቀደው ለምንድን ነው? ይህን ያደረገው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ” ብሎ ነው። (ዮሐንስ 3:​16) አዎን፣ ኢየሱስ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ መስጠት’ የሚችለው ከሞተ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 20:28) በእርግጥም በታሪክ ዘመን ሁሉ ከይሖዋና ከበኩር ልጁ ሌላ ለሰው ዘር ታላቅ ፍቅር ያሳየ አንድም አካል የለም።​—⁠ሮሜ 8:​32

ኢየሱስ ከሞተም በኋላ ቢሆን በጣም ልዩና አስገራሚ በሆነ መንገድ ‘የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ተገልጧል።’ ይህም የተከናወነው ‘ከሙታን ተነስቶ’ ወይም በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት በማግኘት የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ በሆነ ጊዜ ነው። (ሮሜ 1:4፤ 1 ጴጥሮስ 3:​18) ከዚያም ኢየሱስ ከአባቱ ጎን በመሆን 1, 900 ለሚያክሉ ዓመታት በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምድርን ሁሉ የሚያስተዳድረው የሰማይ አገዛዝ ማለትም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀምሯል።​—⁠መዝሙር 2:​7, 8፤ ዳንኤል 7:​13, 14

ኃያል በሆነው በአምላክ ልጅ ዘንድ ሞገስ ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ ትምህርቶቹን እንድትመረምርና በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ እንድታደርጋቸው እናበረታታሃለን። ኢየሱስ ራሱ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 17:3) አዎን፣ አንድ ሰው የአምላክን ልጅ በተመለከተ የሚያምነው ነገር በእርግጥ ለውጥ ያመጣል!​—⁠ዮሐንስ 3:​18፤ 14:6፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​19

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው እንዴት ነው?​—⁠ዮሐንስ 1:3, 14፤ ራእይ 3:14

▪ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን እንድታምን የሚያደርግህ ምንድን ነው?​—⁠ማቴዎስ 3:16, 17

▪ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ማመንህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?​—⁠ዮሐንስ 3:16፤ 14:6፤ 17:3

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ ያስተማራቸው ጥበብ ያዘሉ ትምህርቶችና የፈጸማቸው አስገራሚ ተአምራት ተራ ሰው እንዳልነበር ያረጋግጣሉ