በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ፍቅር የጠፋው ለምንድን ነው?

እውነተኛ ፍቅር የጠፋው ለምንድን ነው?

እውነተኛ ፍቅር የጠፋው ለምንድን ነው?

በተቃራኒ ጾታ መካከል ስላለው ፍቅር ምክር የሚሰጡ በርካታ ምንጮች አሉ። የሥነ ልቦና ሐኪሞችና አማካሪዎች ምክር ይለግሳሉ። ይህ ጉዳይ በቴሌቪዥን በሚቀርቡ ፕሮግራሞች ላይም በተደጋጋሚ ይነሳል።

ፍቅረኛ ማግኘት የሚቻልበትን ዘዴ እንጠቁማለን የሚሉ በርካታ የኢንተርኔት ድረ ገጾች አሉ። የሥነ ልቦና ጠበብቶችና ኮከብ ቆጣሪዎች ከሚሰጡት ምክር በተጨማሪ “ማራኪና አስደናቂ ምስጢሮች” እንደምታገኝ እንዲሁም “ወንድና ሴት ከሚያገናኙ የተዋጣላቸው ባለሙያዎች” ብሎም “ከፍቅር ዶክተሮች” ትምህርት መቅሰም እንደምትችል የሚናገሩ ድረ ገጾችን አንብበህ ይሆናል።

በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍትና መጽሔቶችም ከፍተኛ ገበያ ያላቸው ሲሆን ከእነዚህም አንዳንዶቹ ከእውነታው የራቁ ተስፋዎችን የያዙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ መጽሐፍ “ማንኛውም ሰው እንዲያፈቅርህ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ” እንደሚጠቁምህ ይናገራል። ሌላው ደግሞ “በአንድ ወር ውስጥ እንከን የማይወጣለት የትዳር ጓደኛ” እንዴት ማግኘት እንደምትችል እንደሚያሳይህ ይገልጻል። አንድ ወር ይረዝምብህ ይሆን? “በ90 ደቂቃ ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ” አንድን ሰው ለዘላለም እንዲወድህ ልታደርገው እንደምትችል የሚናገር መጽሐፍም አለ።

አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጠው ምክር የሚያስከፍለው ዋጋ አለ። ብዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ምክር ለማግኘት ገንዘብ ይከፍላሉ። ከዚያ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚያጋጥመው ምክሩ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር የስሜት ኪሳራ ይደርስባቸዋል።

ሆኖም መሬት ጠብ የማይል ምክር የሚሰጥ አንድ መጽሐፍ አለ። የማይጨበጡ ተስፋዎች ከመስጠትና ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ስሜት እንዲያድርባቸው ከማድረግ ይልቅ ስለ ፍቅር እውነታውን ይናገራል። የተጻፈው ከረጅም ጊዜ በፊት ቢሆንም ምክሩ ጊዜ ያለፈበት አይደለም። የመጽሐፉ ባለቤት በጥበቡም ሆነ በፍቅሩ ተወዳዳሪ የለውም። ምናልባት አንተም ይህ ውድ ስጦታ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ይኖርህ ይሆናል። ያለንበት ሁኔታም ሆነ አስተዳደጋችን ምንም ይሁን ምን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቅር ማወቅ ያለብንን ያስተምረናል። ምክሩ የሚገኘውም ያለ ክፍያ ነው።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ያስችለናል ማለት ነው? አይደለም። ምንም ያህል ብንጥር አንዳንዶች ሊቀርቡን አይፈልጉም። እውነተኛ ፍቅር ደግሞ በግድ የሚሆን ነገር አይደለም። (ማሕልየ መሓልይ 8:​4) ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተል ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች እናሳድጋለን፤ በእርግጥ ይህ ጊዜና ጥረት የሚጠይቅ ነገር ነው። እንዲህ ዓይነት ፍቅር መመሥረት የሚቻልበት መንገድ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል፤ በመጀመሪያ ግን በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ፍቅር የጠፋው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

“ፍቅር ይቀዘቅዛል”

ኢየሱስ ‘ስለ ዓለም መጨረሻ’ በተናገረው ትንቢት ላይ በጊዜያችን ስለሚታየው ሁኔታ በትክክል ተንብዮአል። በዓለም ላይ የፍቅር ተቃራኒ የሆኑት ክፋትና ጦርነት እንደሚስፋፉ ተናግሯል። አክሎም “ብዙዎች . . . እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም. . . የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​3-12) በዓለም ላይ፣ በቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሳይቀር እውነተኛ ፍቅር ጠፍቷል ቢባል አትስማማም?

ኢየሱስ ከተናገረው በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ “በመጨረሻው ዘመን” ሰዎች የሚኖራቸውን ማኅበራዊ ግንኙነት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቷል። “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-4) በብዙ አገሮች ውስጥ ሰዎች እነዚህን ባሕርያት ማሳየታቸው በጣም የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል።

እስቲ አስበው:- ኩሩና ምስጋና ቢስ የሆኑ፣ ታማኝነት የጎደላቸው፣ ስምህን የሚያጠፉ ወይም ከዳተኛ የሆኑ ሰዎችን መቅረብ ትፈልጋለህ? ራሳቸውን፣ ገንዘብን ወይም ተድላን ከሚወዱ ሰዎች ጋር መወዳጀትስ ትፈልጋለህ? ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ ሰዎች የግል ጥቅማቸውን የማሳካት ምኞት ስላላቸውና ስግብግብነት ስለሚያጠቃቸው ሌሎችን መቅረብ የሚፈልጉት በራስ ወዳድነት ተነሳስተው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእነዚህ ራቅ” የሚል ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጠናል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​5

በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሰዎች “ፍቅር የሌላቸው” ወይም አንድ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳስቀመጠው “ለቤተሰባቸው ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ የሚገልጸውን ሐሳብ ደግሞ እንመልከት። በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ያሳዝናል። እነዚህ ልጆች ብዙውን ጊዜ ስለ ፍቅር የሚማሩት ከመገናኛ ብዙኃን ነው። ሆኖም መገናኛ ብዙኃን የተሻለ ወዳጅነት ለመመሥረት ስለሚያስችለው ፍቅር ትክክለኛውን ነገር ያስተምራሉ?

ምናብ የፈጠረው ወይስ እውነተኛ ፍቅር?

በተወሰነ መጠን አብዛኞቻችን መገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። አንድ ተመራማሪ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ገና ከልጅነታችን ጀምሮ የጾታ ግንኙነትንና ፍቅርን በተመለከተ ተረቶችና በቀላሉ ከአእምሮ የማይወጡ ሐሳቦች በፊልምና በቴሌቪዥን፣ በመጽሐፍና በመጽሔት፣ በሬዲዮና በሙዚቃ፣ በማስታወቂያና በዜና እንኳ ሳይቀር ይዥጎደጎዱብናል።” አክለውም “አብዛኞቹ መገናኛ ብዙኃን የጾታ ግንኙነትንና ፍቅርን የሚያቀርቡበት መንገድ ተጨባጭነት የሌላቸው ተስፋዎች በአእምሯችን እንዲቀረጹ ወይም እንዲጠናከሩ የሚያደርግ ሲሆን አብዛኞቻችን ይህንን ሙሉ በሙሉ ከአእምሯችን ለማውጣት አስቸጋሪ ይሆንብናል። በዚህም ምክንያት በራሳችንም ሆነ በትዳር ጓደኞቻችን እንዳንደሰት ያደርጉናል” ብለዋል።

አዎን መጻሕፍት፣ ፊልሞችና ዘፈኖች ፍቅርን እምብዛም በትክክል አይገልጹትም። ለነገሩ ዋናው ዓላማቸው ማዝናናት እንጂ ማስተማር አይደለም። በዚህ ምክንያት ደራሲያን ገንዘብ የሚያስገኝላቸው እስከሆነ ድረስ የፍቅር ታሪኮችን ሲጽፉ ከእውነታው የራቁ ሐሳቦችንም ጨማምረው ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው የፈጠራ ሐሳብ ከእውነታው ጋር በቀላሉ የሚምታታ መሆኑ አሳዛኝ ነው። ከዚህም የተነሳ ሰዎች የመሠረቱት የፍቅር ግንኙነት በልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ ባሉት ገጸ ባሕርያት መካከል ከሚታየው ጋር አንድ ዓይነት አልሆን ሲላቸው ብዙ ጊዜ ለብስጭት ይዳረጋሉ። ታዲያ ምናብ የፈጠረውን ፍቅር ከእውነታው እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን የሚነገረውን ከእውነተኛው ፍቅር መለየት የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ በታች የቀረበውን ንጽጽር እንመልከት።

በልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ የሚገለጸው ፍቅር ከእውነተኛው ፍቅር ጋር ሲነጻጸር

በመጻሕፍት፣ በፊልሞች ወይም በድራማ የሚቀርቡት የፍቅር ታሪኮች የተለያዩ ቢሆኑም የታሪኩ ቅንብር ወይም ፎርሙላ እምብዛም አይለወጥም። ራይተር (ደራሲ) የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “አብዛኛው የፍቅር ድርሰት ተመሳሳይ የሆነ ፎርሙላ የተከተለ ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያት አለው። ታሪኩ አንድ ልጅ ከአንዲት ሴት ጋር ይገናኛል፤ ከዚያም በሆነ ምክንያት ይለያዩና በኋላ መልሶ ያገኛታል የሚለውን ፎርሙላ የተከተለ ይሆናል። በዚህ ዓይነቱ ፎርሙላ የተጻፈ ድርሰት የተፈጸመበት ሁኔታ ወይም ዘመን መቼም ይሁን መች ፎርሙላው ውጤታማ በመሆኑ ምንም ያህል ተደጋግሞ ቢቀርብ በተደራሲያኑ ዘንድ ይመረጣል።” እስቲ ይህን የተለመደ ፎርሙላ ቀረብ ብለን እንመልከተው።

አንድ ወጣት ከአንዲት ልጅ ጋር ይገናኛል:- መልከ መልካም የሆነ ልዑል ከአንዲት ቆንጆ ልጅ ጋር ይተዋወቅና ይዋደዳሉ። አንዲት የተዋጣላቸው ደራሲ ስለ ፍቅር ለመጻፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ምክር ሲሰጡ ሁለቱ ሰዎች “ገና ከተያዩበት ቅጽበት ጀምሮ በጣም እንደተዋደዱ ለአንባቢያችሁ በግልጽ መታየት ይኖርበታል” በማለት ተናግረዋል።

በመጀመሪያ እይታ ፍቅር ስለያዛቸው ሰዎች የሚነገረው ሐሳብ፣ እውነተኛ ፍቅር ለአንተ የሚሆነውን ትክክለኛ ሰው ስታገኝ በውስጥህ የሚፈጠር ከፍተኛ ስሜት እንደሆነ ይገልጻል፤ ይህ ማለት ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በድንገት እንደሚይዝና ምንም ዓይነት ጥረትም ሆነ ስለ ሌላኛው ሰው ማወቅ እንደማያስፈልግ የሚጠቁም ነው። ይሁን እንጂ እውነተኛ ፍቅር እንዲያው ስሜት ብቻ አይደለም። ፍቅር ስሜትን እንደሚጨምር እሙን ነው፤ ሆኖም በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራና በሰው ልጆች መካከል የሚመሠረት ትስስር ከመሆኑም በላይ ተገቢ እንክብካቤ ከተደረገለት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል።​—⁠ቈላስይስ 3:​14

ከዚህ በተጨማሪ አንድን ሰው በደንብ ለማ​ወቅ ጊዜ ያስፈልጋል። በመጀመሪያ እይታ ተስማሚ የሆነ የትዳር ጓደኛ አገኛለሁ ብሎ ማሰብ ከቅዥት የማይተናነስ ሲሆን ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ብስጭት ይመራል። በተጨማሪም የያዘኝ እውነተኛ ፍቅር ነው ብለህ ለመደምደም አትቸኩል፤ ምክንያቱም ይህ ዓይነቱ አመለካከት እውነተኛ ፍቅር መሆን አለመሆኑን ለማመዛዘን እንዳትችል ያደርግሃል። ተስማሚ የትዳር ጓደኛ መምረጥ በወረት ፍቅር ተሸንፎ እንዲያው በስሜት ከመነዳት የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ስለዚህ አትቸኩል። ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አስተዋይነት የጎደለው የትዳር ጓደኛ ምርጫ በሥራ ብቃት እንዲሁም በአእምሯዊም ሆነ በአካላዊ ጤንነት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ሌላው ቀርቶ ዕድሜን ሊያሳጥር ይችላል።

ወጣቱ ከልጅቷ ጋር ተለያየ:- አንድ ክፉ መስፍን ቆንጆዋን ሴት በመጥለፍ ከቤተ መንግሥቱ ጠፋ። ልዑሉ እሷን ለማግኘት ሕይወቱን አደጋ ላይ በመጣል ፍለጋውን ተያያዘው። የአሜሪካ የፍቅር ልብ ወለድ ደራሲዎች ማኅበር ቃል አቀባይ የሆነች አንዲት ሴት እንዲህ ትላለች:- “ታሪኩ በዋነኝነት የሚያጠነጥነው ሁለት የሚዋደዱ ሰዎች ፍቅራቸው የሠመረ እንዲሆን በሚያደርጉት ጥረት ላይ መሆን አለበት።” በአብዛኞቹ ታሪኮች ውስጥ እነዚህ ሰዎች ፍቅራቸው እንደሚሠምር ተደራሲያኑ ያውቃሉ። እነዚህ ፍቅረኛሞች አብዛኛውን ጊዜ በመካከላቸው ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ሙከራዎችን ሁሉ ያሸንፋሉ።

በእውነተኛው ሕይወት ውስጥ ግን በፍቅረኛሞቹ መካከል አለመግባባት ሊፈጠር አሊያም ደግሞ ሌሎች ሰዎች ግንኙነታቸውን ሊያሻክሩባቸው ይችላሉ። የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ከገንዘብ፣ ከሥራ፣ ከዘመዶችና ከጓደኞች ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። አንደኛው ወገን እንደተጠበቀው ሆኖ ሳይገኝ ሲቀርም ችግሮች ይነሳሉ። በልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ የሚጠቀሱት ጉድለቶች ጥቃቅን ሲሆኑ በእውነተኛው ሕይወት ግን ሁኔታው ሁልጊዜ እንዲህ አይደለም። በተጨማሪም በእኛ በኩል ጥረት ካላደረግን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ወይም በአስተዳደግ፣ በፍላጎት፣ በባሕርይና በአመለካከት ረገድ ያሉን ልዩነቶች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ችግር እውነተኛ ፍቅር ብቻ ሊወጣው አይችልም። ከዚህ ይልቅ ፍቅር መተባበርን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን የሚጨምር ሲሆን እነዚህ ደግሞ በተፈጥሮ የሚገኙ ወይም በቀላሉ ሊዳብሩ የሚችሉ ባሕርያት አይደሉም።​—⁠1 ቆሮንቶስ 13:​4-7

ወጣቱ ልጅቷን ያገኛታል:- ልዑሉ ቆንጆዋን ልጅ ካስጣላት በኋላ በመስፍኑ ላይ እርምጃ ይወስድበታል። ከዚያም ወጣቱና ልጅቷ ተጋብተው በሰላምና በደስታ ይኖራሉ። የፍቅር ታሪክ አዘጋጅ የሆኑ አንድ ሰው ደራሲ ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች “እስከ መጨረሻ በሰላምና በደስታ ኖሩ የሚል መደምደሚያ ያስፈልጋችኋል። . . . ፍቅረኛሞቹ አብረው በደስታ እንደሚኖሩ ለአንባቢው ግልጽ መሆን አለበት” የሚል ምክር ሰጥተዋል። የፍቅር ታሪክ ደራሲያን በጽሑፎቻቸው ውስጥ ገጸ ባሕርያቱ ከተጋቡ ከብዙ ዓመታት በኋላ የሚኖራቸውን ሕይወት ብዙውን ጊዜ አይገልጹም። በእነዚህ ጊዜያት አለመግባባትና ሌሎች በዛ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዲሁም ችግሮች ግንኙነታቸው እንዲፈተን አድርገው ሊሆን ይችላል። ፍቺን በተመለከተ የሚወጡ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ብዙ ጋብቻዎች በፈተናው ይወድቃሉ።

አዎን፣ በልብ ወለድ ታሪኮች ውስጥ የሚገለጸው ፍቅር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙም ጥረት የማይጠይቅ ሲሆን እውነተኛ ፍቅር ግን ከዚያ የተለየ ነው። በእነዚህ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብህ የማይሆን ነገር ተስፋ ከማድረግ ይጠብቅሃል። ተቻኩለህ ቃል ኪዳን በመግባት የኋላ ኋላ ከመቆጨትም ያድንሃል። እውነተኛና ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ፍቅር እንዴት ማዳበር እንደምትችል እንዲሁም በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚቀጥለው ርዕስ ያብ​ራራል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለሰዎች ፍቅር የሌላቸው በሌሎች ዘንድ እምብዛም አይወደዱም

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በልብ ወለድ ታሪኮች ውስጥ የሚገለጸው ፍቅር በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙም ጥረት የማይጠይቅ ሲሆን እውነተኛ ፍቅር ግን ከዚያ የተለየ ነው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በፍቅር ታሪክ ውስጥ የሚገኙት ዋነኞቹ ገጸ ባሕርያት

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የፍቅር ድርሰቶች በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛሉ። በዚህች አገር ውስጥ ከሚሸጡት ለስላሳ ሽፋን ያላቸው ድርሰቶች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የፍቅር ልብ ወለዶች ናቸው። የአሜሪካ የፍቅር ልብ ወለድ ደራሲዎች ማኅበር ባወጣው አኃዛዊ መረጃ መሠረት 90 በመቶ የሚሆኑት አንባቢያን ሴቶች ሲሆኑ እነርሱም በታሪኩ ውስጥ ከሚገኘው ዋነኛ ገጸ ባሕርይ ሦስት ነገሮችን ይኸውም ፈርጠም ያለ፣ መልከ መልካምና ጥሩ ችሎታ ያለው እንዲሆን ይጠብቃሉ። ዋና ገጸ ባሕርይ ከሆነችው ሴት የሚጠበቁት ሦስት ባሕርያት ደግሞ ጥሩ ችሎታ፣ መንፈሰ ጠንካራነትና ውበት ናቸው።

[በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መገናኛ ብዙኃን ስለ ፍቅር ትክክለኛውን ነገር አይገልጹም