በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ከመሞቴ በፊት አምላክን ማገልገል እፈልጋለሁ’

‘ከመሞቴ በፊት አምላክን ማገልገል እፈልጋለሁ’

‘ከመሞቴ በፊት አምላክን ማገልገል እፈልጋለሁ’

የሜሚ ፍሪ ታሪክ

በ1990 በላይቤሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድ፣ የክራን ጎሣ አባል የሆነችው የ12 ዓመቷ ሜሚ እና ቤተሰቧ በዋናው ከተማ በሞንሮቪያ ከሚገኘው ቤታቸው መውጣት አልቻሉም። ሜሚ እንዲህ ትላለች:- “ከጐረቤት የፍንዳታ ድምጽ ሰማን። የጐረቤታችን ቤት በሚሳይል ተመትቶ ስለነበር ቤቱ በእሳት መጋየት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ነበልባሉ ወደ እኛም ቤት ደረሰና ቤታችን በእሳት ተያያዘ።” በኃይለኛው ጦርነት መሃል ሜሚ፣ እናቷና የእናቷ ታናሽ ወንድም ከቤታቸው በመውጣት ሸሹ።

ሜሚ “በድንገት የሆነ ነገር መታኝ” በማለት ታስታውሳለች።

እናቷም “ምን ሆንሽ?” በማለት ጠየቀቻት።

“አንድ ነገር መትቶኛል! ጥይት ነው መሰለኝ” በማለት መለሰች።

ሜሚ ከፍተኛ ሥቃይ ስለተሰማት መሬት ላይ ወድቃ “አምላክ ሆይ፣ እባክህ ስማኝ። መሞቻዬ የደረሰ ይመስለኛል፤ ሆኖም ከመሞቴ በፊት አንተን ማገልገል እፈልጋለሁ” በማለት ጸለየች። ከዚያም ራሷን ሳተች።

የአካባቢው ነዋሪዎች ሜሚ የሞተች ስለመሰላቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የባሕር ዳርቻ ወስደው ሊቀብሯት ፈለጉ። ይሁን እንጂ እናቷ በአካባቢያቸው ወዳለ ሆስፒታል እንዲወስዷት ወተወተቻቸው። የሚያሳዝነው ግን ሆስፒታሉ ሕክምና ለማግኘት የሚጎርፉትን የቆሰሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ለማስተናገድ ዝግጁ አልነበረም። ቆስሎ የነበረው የሜሚ አጎት በዚያን ዕለት ማታ ላይ አረፈ፤ ሜሚ ግን ከወገቧ በታች ሽባ ብትሆንም መትረፍ ቻለች።

በሰውነቷ ውስጥ ደም መፍሰሱን የቀጠለ ሲሆን ይህ ደግሞ ክፉኛ ያሰቃያት ነበር። ከአራት ወራት በኋላ ዶክተሮች ጥይቱ ያለበትን ቦታ ለማግኘት ራጅ አነሷት። ጥይቱ በልቧና በሳንባዋ መካከል ተቀርቅሯል። ቀዶ ጥገና ማድረግ በጣም አደገኛ ሊሆን ስለሚችል የሜሚ እናት ወደ ባሕላዊ ሐኪም ወሰደቻት። ሜሚ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ስል በሆነ ምላጭ ሰውነቴን ከቀደደው በኋላ አፉን ቁስሉ ላይ በማድረግ ጥይቱን መጥጦ ለማውጣት ሞከረ። ከዚያም ከአፉ ውስጥ ጥይት በማውጣት ‘ይኸውና’ አለን። እኛም ሒሳቡን ከፍለን ወጣን።”

ሆኖም ሰውየው የተናገረው ውሸት ነበር። ተጨማሪ የራጅ ምርመራዎች ጥይቱ ሰውነቷ ውስጥ እንዳለ አሳዩ። ስለዚህ ሜሚና እናቷ ወደ ባሕላዊው ሐኪም ተመልሰው ሄዱ፤ ሆኖም ሰውየው በራጅ ምርመራ አማካኝነት ጥይቱ አለመኖሩን ለማወቅ ተጨማሪ ዘጠኝ ወራት እንደሚያስፈልግ በመንገር አሳምኖ ላካቸው። ወደ ቤታቸው በመመለስ በትዕግሥት መጠበቅ ጀመሩ። በዚህ መሃል ሜሚ ሕመሟን ለማስታገስ የተለያዩ መድኃኒቶች ትወስድ ነበር። ከዘጠኝ ወራት በኋላ ተጨማሪ የራጅ ምርመራ አደረገች። ጥይቱ አሁንም በሰውነቷ ውስጥ እንዳለ ነበር። ባሕላዊው ሐኪምም ሸሽቶ አመለጠ።

በዚህ ወቅት ሜሚ በጥይት ከተመታች አንድ ዓመት ተኩል ሆኗት ነበር። አንድ ዘመዷ ወደ አንዲት ጠንቋይ ወሰዳት። ጠንቋይዋ ግን እነርሱን ከመርዳት ይልቅ ሜሚ ወይም እናቷ በአንድ የተወሰነ ቀን እንደሚሞቱ ነገረቻቸው። ሜሚ በዚህ ጊዜ የ13 ዓመት ልጅ ነበረች። “ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ። ሆኖም ጠንቋይዋ ባለችው ቀን ማናችንም አልሞትንም” በማለት ሜሚ ትናገራለች።

አጎቷ ሜሚን ወደ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ወሰዳት፤ ይህ ሰው ሜሚ ሽባ የሆነችው በድግምት እንጂ በጥይት ምክንያት እንዳልሆነ ራእይ መመልከቱን ነገራቸው። ሜሚ እርሱ የሚሰጣትን መመሪያ ተከትላ አንድ ዓይነት የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ብታከናውን በአንድ ሳምንት ውስጥ በእግሯ መሄድ እንደምትችል ቃል ገባላት። ሜሚ እንዲህ ትላለች:- “በውቅያኖስ ውስጥ ብዙ ጊዜ በጠበል ታጠብኩ፣ ጾምኩ፣ በየምሽቱ እኩለ ሌሊት ላይ ለብዙ ሰዓታት መሬት ላይ ተንከባለልኩ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጥረቶች ሁሉ ከንቱ ነበሩ፤ ሁኔታዬም ቢሆን ምንም አልተለወጠም።”

ውሎ አድሮ ግን ተጨማሪ የሕክምና መስጫ ተቋማት ሥራ በመጀመራቸው ሜሚ ከብዙ ውጣ ውረድና ከረጅም ጊዜ በኋላ ጥይቱን ማስወጣት ቻለች። ምንም ፋታ በማይሰጥ ሕመም ከሁለት ዓመት በላይ ተሠቃይታለች። “ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሥቃዩ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ተወገደ፤ እንዲሁም መተንፈስ ቀላል ሆነልኝ። በከፊል ሽባ ብሆንም እንኳ አራት እግር ባለው ምርኩዝ በመታገዝ ለመቆም ችያለሁ” በማለት ሜሚ ታስታውሳለች።

ሜሚ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች

ሜሚ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ እናቷ ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። ልጇ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ እንደምትወድ ስለምታውቅ ምሥክሮቹን ወደ ቤቷ እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ሜሚ ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነች። ሆኖም ከብዙ ወራት በኋላ ወደ ሆስፒታሉ በመመለሷ ምክንያት ከምሥክሮቹ ጋር የነበራት ግንኙነት ተቋረጠ።

ሜሚ መጽሐፍ ቅዱስን ለማወቅ ያላት ጉጉት ግን እንዳለ ነበር። በዚህ ምክንያት የአንድ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት መሪ ሊረዳት እንደሚፈልግ ሲነግራት እርዳታውን ተቀበለች። የሰንበት ትምህርት እየተማሩ ሳለ አብሯቸው የሚማር ልጅ “ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል ነው?” ብሎ አስተማሪውን ጠየቀው።

አስተማሪውም “አዎን፣ እኩል ናቸው። ሆኖም ኢየሱስ ከአምላክ ጋር ሙሉ በሙሉ እኩል ነው ማለት አይደለም” ብሎ መለሰለት።

ሜሚ ‘ሙሉ በሙሉ እኩል አይደለም?’ ‘ይህ ትርጉም የማይሰጥ ነገር ነው። አንድ የሆነ ስህተት አለ’ ብላ አሰበች። ሜሚ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየተማረች እንዳልሆነ ስለገባት ከጊዜ በኋላ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር የነበራትን ግንኙነት አቆመች።

በ1996 በሞንሮቪያ በድጋሚ ዓመጽ ተቀሰቀሰ። ሜሚ ሁለት ተጨማሪ የቤተሰቧን አባላት ያጣች ከመሆኑም በላይ የምትኖርበት ቤት ለሁለተኛ ጊዜ በእሳት ተቃጠለ። ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ከሜሚ ጋር ተገናኙ። ሜሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንደገና ቀጠለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ስትገኝ፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች የመንግሥት አዳራሹን ሲያጸዱ በመመልከቷ በጣም ተደነቀች። በዚያው ዓመት ጥቂት ቆየት ብሎ “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በመገኘቷ በጣም ተደሰተች፤ የይሖዋ ምሥክሮች በዛ ብለው የተገኙበትን ስብሰባ ስትመለከት ይህ የመጀመሪያዋ ነበር።

“በጣም ነበር የገረመኝ። ምሥክሮቹ ምንም እንኳ ከተለያየ ጎሣ የመጡ ቢሆኑም አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር ነበራቸው። ሁሉም ነገር በደንብ የተደራጀ ነበር” ስትል ሜሚ ተናግራለች።

አምላክን ለማገልገል ያላትን ፍላጎት ማሟላት

በ1998 በድጋሚ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ሜሚና እናቷ ጎረቤት አገር ወደሆነችው ኮት ዲቩዋር በመሸሽ የሰላም ከተማ የስደተኞች መጠለያ በተባለው ካምፕ ውስጥ ከሌሎች 6, 000 ላይቤሪያውያን ጋር መኖር ጀመሩ። ሜሚ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናቷን የቀጠለች ሲሆን ፈጣን እድገትም አደረገች። ብዙም ሳይቆይ እምነቷን ለሌሎች ማካፈል ፈለገች። መንፈሳዊ ወንድሞቿና እህቶቿ ተሽከርካሪ ወንበሯን እየገፉ በአገልግሎት መካፈል እንድትችል ረድተዋታል። በዚህ መንገድ ሜሚ ለሌሎች በርካታ ስደተኞች ጥሩ ምሥክርነት መስጠት ችላለች።

ሜሚ የምትኖርበት አካባቢ ከመንግሥት አዳራሹ ስድስት ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ያለባት አካላዊ ችግር ወደ መንግሥት አዳራሹ የምታደርገውን ጉዞ አስቸጋሪ ቢያደርግባትም እንኳ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ትገኛለች። ግንቦት 14, 2000 በተደረገው የልዩ ስብሰባ ቀን ላይ ለመገኘትና ራሷን ለአምላክ መወሰኗን በውኃ ጥምቀት ለማሳየት ከ190 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛለች። (ማቴዎስ 28:​19, 20) ሜሚን ለማጥመቅ ተሸክመው ወደ ወንዙ ሲወስዷት የተመለከቱት በርካታ ሰዎች ዓይናቸው እንባ አቅርሮ ነበር። ከውኃው ስትወጣ ፊቷ በደስታ ያበራ ነበር።

አሁን በጋና የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የምትኖረው ሜሚ የወደፊት ግቧ የዘወትር አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ነው። እናቷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ከመሆኑም በላይ የተማረችውን ለሌሎች እያካፈለች ነው። ሁለቱም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል፤ የድዳውም አንደበት በደስታ ይዘምራል” የሚለው ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ።​—⁠ኢሳይያስ 35:​5-7

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሜሚ ሰውነት ውስጥ የወጣው ጥይት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሜሚን ለማጥመቅ ወደ ወንዙ ሲወስዷት

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእናቷ ከኤማ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠኑ