በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ውጥረት “ከውጥረት እረፍት ማግኘት!” የሚል ርዕስ ያለው ተከታታይ ትምህርት የወጣው በጣም በሚያስፈልገኝ ወቅት ላይ ነው! (ሚያዝያ 2005) ትምህርቱ የተሰጠው ያለብኝን ውጥረት በሚገባ መወጣት ባለመቻሌ የአእምሮ መቃወስ ሊያጋጥመኝ ነው ብዬ ባሰብኩበት ሰዓት ላይ ነው። ያቀረባችኋቸው ሐሳቦች በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥተዋል።

ስም አልተጠቀሰም፣ ዩናይትድ ስቴትስ

አንድ ሴሚናር ላይ ተገኝቼ ውጥረትን መቋቋምን በተመለከተ አጠር ያለ ንግግር አቅርቤ ገና መመለሴ ነው። በዚህ ግሩም መጽሔት በመጠቀም ስለ ውጥረት መንስኤ፣ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶችና ችግሩን ለመቋቋም ምን እንደሚረዳ መናገር ችያለሁ!

ጄ. ኤል.፣ ጀርመን

ተስፋ ተሰጥቷል . . . “ዳግም እንደማገኘው ተስፋ ተሰጥቷል!” የሚል ርዕስ ያለውን ተሞክሮ በማንበቤ በጣም ተደስቻለሁ። (የካቲት 2005) አሁን የ11 ዓመት ልጅ ነኝ፤ ቀደም ሲል ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት ለመናገር ብዙም አልደፍርም ነበር። የሮሳሊያ ፊሊፕስን ታሪክ ካነበብኩ በኋላ ግን ይሖዋ እንደሚረዳኝ ተገነዘብኩ። ልክ እንደ ሮሳሊያ ደፋር የምሥራቹ ሰባኪ መሆን እፈልጋለሁ።

ፒ. ፒ.፣ ፖላንድ

ዕድሜዬ 27 ዓመት ሲሆን እናቴ በሞት ያንቀላፋችው ከ24 ዓመት በፊት ነው። የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩበት ጊዜ ጀምሮ በድጋሚ እንደማገኛት ጠንካራ እምነት አዳብሬያለሁ። እንዲህ ለመሰሉት ጽሑፎች ይሖዋንና የንቁ! መጽሔት አዘጋጆችን አመሰግናለሁ፤ እንዲሁም ሮሳሊያ አስደሳች የሆነ ተሞክሮዋን ስላካፈለችን አመሰግናታለሁ።

ኤ. ኤፍ.፣ ቬኔዙዌላ

አዞ “አዞ ትፈራለህ?” የሚለው ርዕስ ልቤን በጣም ነክቶታል። (ግንቦት 2005) ከበፊቱም ቢሆን አዞ አስደናቂ ፍጥረት እንደሆነ አምን ነበር። ሰዎች ልክ እንደ እኔ አዞ እንዲወዱ የሚያደርጓቸውን በርካታ አስደናቂ እውነታዎች ማንበቤ አስደስቶኛል። ከአሁኑ ይበልጥ ስለ አዞ ማወቅ የምንችልበትን ይሖዋ የሚያዘጋጀውን አዲስ ዓለም በናፍቆት እጠባበቃለሁ!

ኤል. አይ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የወጣቶች ጥያቄ . . . ከመጥፎ ልጆች ጋር የገጠምኩት ምን ነክቶኝ ነው? (ነሐሴ 2005) ለአሥር ዓመታት ያህል ‘በጌታ ሥራ’ ስካፈል የቆየሁ ቢሆንም እንዲህ ዓይነቱን ባሕርይ እንዴት ማስተካከል እንደምችል አላውቅም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ስሜታዊ ብስለት እንዳልነበረኝ ብገነዘብም ችግሬን ማሸነፍ ስለምችልበት መንገድ አላውቅም ነበር። ይሖዋ በዚህ ሥርዓት ውስጥ መልካም ምግባር እንዲኖረን የሚረዱ እንዲህ የመሰሉ ርዕሰ ትምህርቶችን ስለሚያዘጋጅልን አመሰግነዋለሁ።

ጄ. ኤፍ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በዚህ ርዕስ ውስጥ ‘የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማያውቁ ሰዎችን ሙሉ በሙሉ መራቅ እንደማይገባ’ ተገልጿል። ይህንን ጉዳይ በደንብ ልታብራሩልኝ ትችላላችሁ? አንድ ክርስቲያን አማኝ ካልሆነ ሰው ጋር የቅርብ ጓደኝነት ቢመሠርትስ? ነገሩ አሳሳቢ አይሆንም?

ዲ. ፒ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- ርዕሰ ትምህርቱ ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች ጋር የቅርብ ጓደኝነት እንዲመሠርቱ አያበረታታም። አዎን፣ “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ይሠራል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) እንዲህ ሲባል ግን ከማያምኑ ሰዎች ፈጽሞ እንርቃለን ማለት አይደለም። ርዕሰ ትምህርቱ ውስጥ እንደተብራራው መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት ባልደረቦቻችን ብቻ ሳይሆን ‘ለሰው ሁሉ መልካም እንድናደርግ’ ያሳስበናል። (ገላትያ 6:10) ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን ለሰዎች ከልብ እንድናስብና አክብሮት እንድናሳያቸው ይጠይቅብናል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ፍላጎት ከሌላቸው ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት የጠበቀ ቅርርብ አልመሠረተም። (ዮሐንስ 15:14) ቢሆንም ከሰዎች ጋር ይቀራረብ የነበረ ከመሆኑም በላይ እንዴት ከእነርሱ ጋር መወያየትና መግባባት እንደሚችል ያውቅ ነበር። በዚህ ምክንያት ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት የሚችልበትን አጋጣሚ አግኝቷል። (ለምሳሌ ያህል በሉቃስ 7:36-50 ላይ የሚገኘውን ዘገባ ተመልከት።) እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ለማያምኑ ሰዎች ምንጊዜም አክብሮት ሊኖረን ይገባል። የምንፈልገው ‘ሰላማውያን ለመሆንና ለሰዎች ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና ለማሳየት’ ነው።​—⁠ቲቶ 3:2