በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዓለምን ያዳረሰ ዘር

ዓለምን ያዳረሰ ዘር

ዓለምን ያዳረሰ ዘር

“ኦል አባውት ኮፊ” የተሰኘው መጽሐፍ አንድ ግለሰብ ለቡና ችግኝ ያደረገው እንክብካቤ “ከቡና ተክል መስፋፋት ጋር በተያያዘ በታሪክ ውስጥ እጅግ አስደናቂ ምዕራፍ” እንደሆነ ይገልጻል። ይህ አነስተኛ ተክል በዛሬው ጊዜ 70 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለሚያስገኘው የቡና ኢንዱስትሪ መጀመር የጎላ ድርሻ ያለው ሲሆን “ሳይንቲፊክ አሜሪካን” የተሰኘው መጽሔት እንዳሰፈረውም በዓለም ላይ በዶላር በሚካሄደው ግብይት ከቡና የሚበልጠው ነዳጅ ዘይት ብቻ ነው።

አስደናቂው የቡና ታሪክ የሚጀምረው ወፍ ዘራሽ የቡና ተክል መገኛ ከሆኑት የኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከዓለም የቡና ምርት ውስጥ ሁለት ሦስተኛው የሚገኘው ኮፊ አረቢካ ተብሎ ከሚጠራው የዚህ የቡና ተክል ዝርያ ነው። የተቆላ ቡና ማዘጋጀት የተጀመረው መቼ እንደሆነ በእርግጠኝነት አይታወቅም። ሆኖም ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ15ኛው መቶ ዘመን በአረብ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ኮፊ አረቢካን ማልማት ተጀምሮ ነበር። በወቅቱ ለዘር የሚሆን የቡና ፍሬ ወደ ውጪ አገር እንዳይላክ ተከልክሎ የነበረ ቢሆንም በ1616 የደች መንግሥት የቡና ችግኞች አሊያም ለዘር የሚሆኑ ፍሬዎች ማግኘት ቻለ። ብዙም ሳይቆይ በሲሎን (አሁን ስሪ ላንካ ተብላለች) እንዲሁም በጃቫ (አሁን የኢንዶኔዢያ ክፍል ሆናለች) የቡና እርሻ ተቋቋመ።

በ1706 የደች መንግሥት በጃቫ የነበረውን ለጋ የቡና ተክል በኔዘርላንድ፣ አምስተርዳም ወደሚገኝ የእርሻ ጣቢያ አዛወረው። ዛፉም በዚህ ቦታ ተስማምቶት ጥሩ ሆኖ አደገ። ከዚያም ከዚህ ዛፍ ፍሬ የተገኙ የቡና ተክሎች በሱሪናምና በካሪቢያን ወደሚገኙ የደች ቅኝ ግዛቶች በመርከብ ተወሰዱ። በ1714 የአምስተርዳም ከንቲባ ከእነዚህ ዛፎች ውስጥ አንዱን ለፈረንሳይ ንጉሥ ሉዊስ 14ኛ ሰጣቸው። ንጉሡም ይህንን ተክል በፓሪስ ከተማ በሚገኘው ዣርደ ዴ ፕላንት የተባለ የንጉሣዊ ቤተሰቦች የአትክልት ሥፍራ በመስተዋት ቤት ውስጥ አስተከሉት።

ፈረንሳዮች የቡና ንግድ ለመጀመር በጣም ጓጉተው ስለነበር የቡና ዘርና ዛፎች በመግዛት በመርከብ ወደ ሬዩኒየን ደሴት አስመጡ። ሆኖም ዘሮቹ አልበቀሉም፤ አንዳንድ የመረጃ ምንጮች እንደሚያሳዩት ዛፎቹም ቢሆኑ ከአንዱ በስተቀር በሙሉ ደረቁ። ያም ሆኖ ግን በ1720 ከዚያ አንድ እግር የቡና ተክል የተገኙ 15, 000 ዘሮች በመተከላቸው የኋላ ኋላ የቡና እርሻ ተጀመረ። እነዚህ የቡና ዛፎች እንደ ውድ ሀብት ይታዩ ስለነበር አንዷን ዛፍ እንኳን ሲቆርጥ የተገኘ ሰው የሞት ቅጣት ይበየንበት ነበር! ፈረንሳዮች በካሪቢያንም የቡና እርሻ ለማቋቋም በማሰብ ሁለት ጊዜ ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።

ለእረፍት ፓሪስ ሄዶ የነበረ ጋብሪል ማቲየ ደ ክሊየ የተባለ የፈረንሳይ ባሕር ኃይል ባልደረባ እረፍቱን ጨርሶ ሲመለስ ማርቲኒክ በሚገኘው የግል ይዞታው ላይ የሚተክለው አንድ የቡና ተክል ይዞ ለመመለስ ቆርጦ ተነሳ። በግንቦት ወር 1723 የፓሪሱ ዛፍ ዝርያ የሆነ የቡና ችግኝ ይዞ ወደ ማርቲኒክ ደሴት በመርከብ ተጓዘ።

ደ ክሊየ የሚሳሳለት ችግኝ በደመናማ ቀንም ጭምር የፀሐይን ሙቀት ማግኘት እንዲችል በጉዞ ላይ በነበረበት ወቅት በከፊል ከመስተዋት በተሠራ ሣጥን ውስጥ እንዳስቀመጠው ኦል አባውት ኮፊ የተሰኘው መጽሐፍ ይገልጻል። በደ ክሊየ ጥረት ቅናት ያደረበትና እንዳይሳካለት ለማድረግ የፈለገ አብሮት የሚጓዝ አንድ ግለሰብ ችግኙን ሊነጥቀው ቢሞክርም አልሆነለትም። ችግኙ ምንም ጉዳት አልደረሰበትም። ከዚህም ሌላ የቱኒዚያ የባሕር ወንበዴዎች አደጋ ጥለውባቸውና ኃይለኛ ማዕበል አጋጥሟቸው ነበር፤ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ንፋስ ባለመኖሩ ምክንያት መርከቧ ዶልደርምዝ ላይ በቆመች ጊዜ ንጹሕ ውኃ ማግኘት አስቸጋሪ ሆነ። የቡናው ችግኝ ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሞ መቆየት ችሎ ነበር። ደ ክሊየ “ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ ያህል ውኃ በመታጣቱ የምትደርሰኝን አነስተኛ ውኃ፣ የተስፋዬ መሠረትና የደስታዬ ምንጭ ለሆነው ችግኝ ለማካፈል ተገድጄ ነበር” በማለት ጽፏል።

ደ ክሊየ ለችግኙ ያሳየው ፍቅር ያለ ዋጋ አልቀረም። ችግኙ በደህና ማርቲኒክ የደረሰ ሲሆን ሞቃታማው የአየር ጠባይ ስለተመቸው አድጎ ተባዛ። ጎርደን ሪግሌ፣ ኮፊ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “ከብራዚል፣ ከፍሬንች ጊያና እንዲሁም ከሱሪናም በስተቀር በአሜሪካ የሚገኙት አገሮች በሙሉ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የቡና ተክል ያገኙት በማርቲኒክ ካደገው ከዚህ ዛፍ ነው” በማለት ጽፈዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ብራዚልና ፍሬንች ጊያናም የቡና ተክል ማግኘት ፈለጉ። የደች መንግሥት በሱሪናም ባለው እርሻው ላይ ከአምስተርዳም የተገኘው የቡና ተክል ዝርያ የነበረው ቢሆንም ዛፎቹ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው ነበር። ይሁን እንጂ በ1722 ከባድ ወንጀል ፈጽሞ ወደ ሱሪናም የሸሸ አንድ ግለሰብ የተወሰኑ የቡና ዘሮች ሰርቆ መጣ። የፍሬንች ጊያና ባለ ሥልጣናት ወንጀለኛው ያመጣውን ዘር ከሰጣቸው ከወንጀሉ ነጻ ሊያደርጉት ተስማሙ፤ ግለሰቡንም ወደ ትውልድ አገሩ መልሰው ላኩት።

ሊያድጉ የሚችሉ የቡና ዘሮችን ወይም ችግኞችን በድብቅ ወደ ብራዚል ለማስገባት የተደረጉት ሙከራዎች መጀመሪያ ላይ አልተሳኩም ነበር። ከዚያም ሱሪናምና ፍሬንች ጊያና የድንበር ውዝግብ ስላጋጠማቸው ብራዚልን እንድታስታርቃቸው ጠየቋት። በዚህ ጊዜ ብራዚል፣ ፍራንሴስኩ ዴ ማሉ ዴ ፓልየታ የተባለውን የጦር ሠራዊት ሹም የድንበር ውዝግቡን እንዲፈታ እና ጥቂት የቡና ችግኞችን ወደ ትውልድ አገሩ ይዞ እንዲመለስ ተልእኮ በመስጠት ወደ ፍሬንች ጊያና ላከችው።

የማስታረቅ ተልእኮው የተሳካ ሲሆን አገረ ገዢውም ለፓልየታ የስንብት የራት ግብዣ አደረገለት። የገዢው ባለቤትም ለዚህ የክብር እንግዳ አድናቆቷን ለመግለጽ ለፓልየታ የሚያምር እቅፍ አበባ አበረከተችለት። ይሁን እንጂ በአበቦቹ መሃል ሊያድጉ የሚችሉ የቡና ዘሮችና ችግኞችን በድብቅ አስቀምጣ ነበር። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኘው የብራዚል የቡና ኢንዱስትሪ የተጀመረው በ1727 ሲሆን መነሻውም ከእቅፍ አበባ ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ መንገድ በ1706 ከጃቫ ወደ አምስተርዳም የተወሰደው ለጋ የቡና ተክልና በፓሪስ ያፈሩት የዚህ ተክል ዝርያዎች በማዕከላዊና በደቡብ አሜሪካ ለተስፋፋው የቡና ልማት መሠረት ሆነዋል። ሪግሌ “በዚህም ምክንያት መላው የአረቢካ ቡና ኢንዱስትሪ የተመሠረተው በጣም ውስን በሆነ የቡና ዝርያ ነው” ብለዋል።

በዛሬው ጊዜ 80 በሚያህሉ አገሮች ከ25 ሚሊዮን በላይ በሆኑ የቤተሰብ የእርሻ ቦታዎች ላይ 15 ቢሊዮን የቡና ዛፎች እንደለሙ ይገመታል። ከእነዚህ እርሻዎች የሚገኘው ምርትም ለተጠቃሚው ሕዝብ በየቀኑ 2.25 ቢሊዮን ስኒ ቡና ለማቅረብ አስችሏል።

ዛሬ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከሚፈለገው በላይ የቡና ምርት መትረፍረፉ ችግር አስከትሏል። ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ጥብቅ የዋጋ ትመና ደንቦች ሁኔታውን ያወሳሰቡት ሲሆን እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ላይ ተዳምረው በብዙ አገሮች የሚኖሩ ቡና አምራቾችን ለድህነትና ከእጅ ወደ አፍ ለሆነ ኑሮ ዳርገዋቸዋል። ከ300 ዓመታት ገደማ በፊት ደ ክሊየ አንዲት እግር ችግኝ እንዳትደርቅበት የነበረችውን ጥቂት ውኃ በማካፈል ያደረገውን እንክብካቤ ስናስብ ዛሬ የቡና ምርት ይህን ያህል መትረፍረፉ ያስገርማል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በጣም የታወቁት ሁለት የቡና ዝርያዎች

ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተሰኘው መጽሔት “እሸት የቡና ፍሬ ሩቢያኬ ከተባሉት ተክሎች የሚመደብ ሲሆን በዚህ የተክል ቤተሰብ ውስጥ ኮፊ ከተባለው ዝርያ ቢያንስ 66ቱ ይገኛሉ” በማለት ይናገራል። “ገበያ ላይ የዋሉት የቡና ዝርያዎች ሁለት ሲሆኑ አንደኛው ከዓለም የቡና ምርት ውስጥ ሁለት ሦስተኛውን የሚይዘው ኮፊ አረቢካ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ሮበስታ ቡና ተብሎ የሚጠራው ከዓለም የቡና ምርት ውስጥ አንድ ሦስተኛውን የሚይዘው ኮፊ ካኔፎራ ነው።”

ሮበስታ ቡና ኃይለኛ መዓዛ ያለው ሲሆን ብዙውን ጊዜም የተዘጋጀ ቡና (ኢንስታንት ኮፊ) ለመሥራት ይውላል። ዛፉ ብዙ ፍሬ የሚያፈራና በሽታንም መቋቋም የሚችል ነው። የሮበስታ ቡና ዛፍ ቁመቱ እስከ 12 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ይህም ካልተከረከመውና አነስተኛ ምርት ከሚሰጠው እንዲሁም በቀላሉ በበሽታ ከሚጠቃው የአረቢካ ቡና ዛፍ በእጥፍ ይረዝማል ማለት ነው። የሮበስታ ቡና ፍሬ የካፌይን ይዘቱ እስከ 2.8 በመቶ የሚደርስ ሲሆን የአረቢካ ቡና ፍሬ ግን የካፌይን ይዘቱ ከ1.5 በመቶ አይበልጥም። አረቢካ ቡና 44 ክሮሞዞሞች ሲኖሩት ሮበስታ እና ሌሎችም ወፍ ዘራሽ የቡና ዝርያዎች ደግሞ 22 ክሮሞዞሞች ቢኖሯቸውም አንዳንዶቹን ማዳቀል ተችሏል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቡና በካቶሊኮች ዘንድ ተቀባይነት አገኘ

በ17ኛው መቶ ዘመን ቡና ወደ አውሮፓ ሲደርስ አንዳንድ የካቶሊክ ቀሳውስት በሰይጣን የተዘጋጀ መጠጥ ብለው ሰየሙት። ቀሳውስቱ ክርስቶስ ቀድሶታል ብለው የሚያምኑትን የወይን ጠጅን የሚተካ መጠጥ እንደሆነ አድርገው ተመልክተውት ነበር። ይሁንና ሊቀ ጳጳስ ክሌመንት 8ኛ ይህንን መጠጥ ከቀመሱት በኋላ ስለ ቡና የነበራቸውን አመለካከት እንደለወጡ ኮፊ የተሰኘው መጽሐፍ ይገልጻል። ጳጳሱ በምሳሌያዊ ሁኔታ ቡናን “በማጥመቅ” ማለትም በካቶሊኮች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ የተፈጠረውን ሃይማኖታዊ ውዝግብ ፈተውታል።

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ ካርታ/ግራፍ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቡና የተሰራጨው እንዴት ነው?

1.  15ኛው መቶ ዘመን አረቢካ ቡና በአረብ ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ መመረት ጀመረ

2.  1616 የደች መንግሥት የቡና ዛፎች አሊያም ሊያድጉ የሚችሉ ዘሮች አገኘ

3.  1699 የደች መንግሥት ዛፎቹን ወደ ጃቫ እና በምሥራቅ ኢንዶኔዢያ ወደሚገኙ ሌሎች ደሴቶች ወሰዳቸው

4.  18ኛው መቶ ዘመን በማዕከላዊ አሜሪካ እና በካሪቢያን ቡና ይመረት ጀመር

5.  1718 ፈረንሳዮች የቡና ተክልን ወደ ሬዩኒየን ደሴት ወሰዱ

6.  1723 ጋብሪል ማቲየ ደ ክሊየ የቡና ተክል ከፈረንሳይ ወደ ማርቲኒክ ደሴት ወሰደ

7.  19ኛው መቶ ዘመን ቡና በሐዋይ መመረት ጀመረ

[ምንጭ]

Source: From the book “Uncommon Grounds”

[በገጽ 18, 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

በ1723 ጋብሪል ማቲየ ደ ክሊየ ወደ ማርቲኒክ ሲጓዝ የሚጠጣውን ውኃ ከቡና ተክል ጋር ተካፍሎ ለመጠጣት ተገድዶ ነበር

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል መግለጫ]

ካርታ:- © 1996 Visual Language; ደ ክሊየ:- Tea & Coffee Trade Journal