የድንገተኛ አደጋ ጥሪ—ለንደን
የድንገተኛ አደጋ ጥሪ—ለንደን
ብሪታንያ የሚገኘው የ ንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው
“ግባችን ለንደን ከተማ ውስጥ እስከ 1, 600 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ክልል ለሚገኙ በጣም የታመሙና ከባድ አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በስምንት ደቂቃ መድረስ ነው። እርዳታ የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ ቢጨምርም 75 በመቶ ያህል ተሳክቶልናል” በማለት የለንደን አምቡላንስ አገልግሎት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ሮብ አሽፈርድ ተናግረዋል።
በቴምዝ ወንዝ ደቡባዊ ዳርቻ ባለው ዋተርሉ በተባለ ባቡር ጣቢያ አካባቢ የሚገኘውን የለንደን ማዕከላዊ አምቡላንስ መቆጣጠሪያ እንድጎበኝ ግብዣ ቀርቦልኝ ነበር። በአውሮፓ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ይህ ማዕከል በየዕለቱ ወደ 3, 000 የሚጠጉ የድንገተኛ አደጋ ጥሪዎችን ያስተናግዳል። እነዚህ ጥሪዎች የሚመጡት ከ300 የሚበልጡ ቋንቋዎች ከሚናገሩ ሰባት ሚሊዮን የሚያህሉ ነዋሪዎች ነው። በመቆጣጠሪያ ክፍሉ ውስጥ ያሉት 300 ሠራተኞች የሚከሰተውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የተደራጁት እንዴት ነው?
ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጥሪዎች መለየት
አንዲት ኦፕሬተር ወደ “999” የሚደወሉ የድንገተኛ አደጋ ጥሪዎችን ስታስተናግድ ተመለከትኩ፤ በብሪታንያ ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም እርዳታ ለመጠየቅ የሚደወለው 999 ነው። ኦፕሬተሯ በፍጥነት ችግሩ የት እንደተከሰተና ለቦታው የሚቀርበው መንገድ የትኛው እንደሆነ ታረጋግጣለች። ወዲያውኑ የመንገድ ካርታ ኮምፒውተሯ ላይ ይወጣል። ችግሩ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ተከታታይ ጥያቄዎች ታቀርባለች:- እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ስንት ሰዎች ናቸው? ዕድሜያቸው ስንት ነው? ጾታቸውስ? ራሳቸውን ስተዋል? ይተነፍሳሉ? ደረታቸው ላይ ሕመም ይሰማቸዋል? ደም ይፈሳቸዋል?
ኦፕሬተሯ እነዚህን መረጃዎች ኮምፒውተሯ ላይ ስትጽፍ ኮምፒውተሩ ወዲያውኑ የችግሩን ክብደት የሚጠቁም ምልክት ያሳያታል። ችግሩ ለሕይወት አስጊ ከሆነ ቀይ ምልክት
ይታያል፤ ብርቱካንማ ቀለም ከታየ ሁኔታው ከባድ ቢሆንም ወዲያውኑ ለሞት አይዳርግም ማለት ነው፤ አረንጓዴ ቀለም የሚጠቁመው ደግሞ ችግሩ ለሕይወት የሚያሰጋ ወይም ከባድ አለመሆኑን ነው። ኦፕሬተሯ ያገኘችውን ውጤት ለተጎጂዎቹ የሚያስፈልገውን እርዳታ ለሚያዘጋጀው የሥራ ባልደረባዋ ታስተላልፍለታለች።በቦታው ተገኝቶ መርዳት
ማዕከሉ 395 አምቡላንሶችና በፍጥነት መድረስ የሚችሉ 60 መኪኖች አሉት። የድንገተኛ አደጋ ጥሪ እንደደረሰ ችግሩ በደረሰበት አካባቢ የሚገኝ ለሁኔታው የሚስማማ ተሽከርካሪ ይላካል። እንዲሁም የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው አካባቢዎች በቀላሉ ማለፍ በሚችሉ ሞተር ብስክሌቶች የሚንቀሳቀሱ የሕክምና እርዳታ ሰጪዎች ዝግጁ ሆነው ይጠብቃሉ። ከዚህም በላይ እነዚህን የሕክምና እርዳታ ሰጪዎች እንዲያግዙ በሚጠሩበት ጊዜ ወዲያው መገኘት የሚችሉ 24 ሰዓት ሙሉ ተዘጋጀተው የሚጠብቁ 12 ዶክተሮች አሉ።
በማዕከሉ ሳለሁ፣ የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት አንድ አውራ ጎዳና ላይ ከባድ አደጋ እንደደረሰ የአካባቢው ፖሊሶች ሪፖርት አደረጉ። ፖሊስ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት የደወለው አምቡላንስ በቦታው እያለ ነበር። ለምን መደወል አስፈለገ? ሄሊኮፕተር ሊያስፈልግ ስለሚችል ሠራተኞቹ ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ለማሳሰብ ነበር። ይህ ቀይ ሄሊኮፕተር ድንገተኛ አደጋ ወደተከሰተባቸው ቦታዎች በዓመት ወደ 1, 000 የሚጠጉ በረራዎችን ያደርጋል። ሄሊኮፕተሩ የሚጓዘው የሕክምና ርዳታ ሰጪዎችንና ዶክተሮችን ይዞ ነው፤ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ባለሙያዎች ተጎጂዎቹ አስቸኳይ ርዳታ እንዲያገኙ ወደ ሮያል ለንደን ሆስፒታል እንዲሄዱ ያደርጋሉ።
በ2004 ላይ አንድ ሌላ ዘዴ ተቀየሰ። በለንደኑ ሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ በብስክሌት አምቡላንስ የሙከራ አገልግሎት መስጠት ተጀመረ፤ ይህም ከከተማው በስተ ምዕራብ የሚገኘው የአምቡላንስ አገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍ መሆኑ ነው። ይህን ኃላፊነት የሚወጣው የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ሲሆን ይህ ቡድን በብስክሌቶች የሚጠቀም በመሆኑ አምቡላንሶችን ለሌሎች ተግባሮች ማዋል ተችሏል። እያንዳንዱ ብስክሌት ሰማያዊ መብራትና የሚጮህ መሣሪያ አለው፤ እንዲሁም የልብ ምት እንዲጀምር የሚረዳ መሣሪያ፣ ኦክሲጅንና የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 35 ኪሎ ግራም መሸከም የሚችል ዕቃ መጫኛ አለው።
በብስክሌት የአምቡላንስ አገልግሎት የሚሰጠው ክፍል በተከፈተ በጥቂት ቀናት ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ታየ። በሂትሮ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ቁጥር 4 ውስጥ የነበረች አንዲት የ35 ዓመት ሴት ታመመችና መተንፈስ አቆመች። ችግሩ እንደደረሰ በ999 ሪፖርት ሲደረግ ሁለት የሕክምና እርዳታ ሰጪዎች በፍጥነት በቦታው በመገኘት ለሴትየዋ ኦክሲጅን ሰጧትና ወዲያውኑ መተንፈስ እንድትጀምር ረዷት። ከዚያም ቅርብ ወደሆነው ሆስፒታል በአፋጣኝ በአምቡላንስ ተወሰደች። ይህች ሴት ካገገመች በኋላ ወደ ሕክምና ርዳታ ሰጪዎቹ ሄዳ ሕይወቷን ስላተረፉላት አመሰገነቻቸው።
የሚሰጠው አገልግሎት እየሰፋ መጥቷል
በ999 ስልክ ቁጥር የሚደውሉት ሰዎች እንግሊዝኛ የማይችሉ ከሆነ ጥሪው ወደ አስተርጓሚ ይተላለፋል። እርግጥ የደወለው ሰው በመጨነቁ ምክንያት ቶሎ ቶሎ የሚያወራ ከሆነ የሚናገረው ቋንቋ ምን እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል!
ድንገተኛ አደጋ ሲደርስ ምን መደረግ እንዳለበት የሰዉን ግንዛቤ ለማስፋት የእንግሊዝኛ ትርጉም የተጻፈበት አንድ አጭር ፊልም በተለያዩ ቋንቋዎች በዲቪዲ ተዘጋጅቷል። ፊልሙ የተዘጋጀው የደቡብ እስያ ተወላጅ የሆኑ የለንደን ነዋሪዎች “መተንፈስ ያቆመ ሰው መተንፈስ እንዲጀመር መርዳት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲማሩ” ለማበረታታት እንደሆነ የለንደን አምቡላንስ አገልግሎት ድርጅት የሚያዘጋጀው ኤልኤኤስ ኒውስ የተባለው ጽሑፍ ዘግቧል። የተዘጋጀው ዲቪዲ 999 ሲደወል ምን እንደሚከናወን ጭምር ያሳያል።
የተለያዩ አገራት ተወላጆች በሚኖሩባት በእንግሊዝ ዋና ከተማ የሚገኙ ሰዎች፣ ድንገተኛ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልገው አንድም ሰው ይሁን በርካታ ሰዎች እንዲሁም ያሉት ከመሬት በታችም ይሁን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ላይ፣ ለሚያገኙት ፈጣን ምላሽ በጣም አመስጋኞች ናቸው። ፈቃደኛ ሠራተኛ የሆኑ አንድ ሐኪም በለንደን የአምቡላንስ አገልግሎት ውስጥ የሚሠሩትን ባለሙያዎች በተመለከተ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “እነዚህ ሰዎች አብሬያቸው ከሠራኋቸው ምርጥ የሕክምና ባለሙያዎች መካከል ይመደባሉ” ብለዋል። እንዲህ ያለው ምስጋና በዓለም ትልቁ ለሆነውና በነጻ የአምቡላንስ አገልግሎት ለሚሰጠው ድርጅት ሠራተኞች ጥሩ ማበረታቻ ነው።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ችግሮችና እንቅፋቶች
ለግል ጉዳያቸው መረጃ ለማግኘት፣ ቀላል ስለሆኑ ሕመሞችና ጉዳቶች ለመጠየቅ እንዲሁም በስህተት ወይም ለቀልድ ሲሉ 999 የሚደውሉ ሰዎች ማዕከሉ ላይ ችግር ይፈጥራሉ። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ አንዳንድ ሕመምተኞች፣ ቤተሰቦቻቸውና ሌሎች ሰዎች ሊረዷቸው በሄዱት የሕክምና ባለሙያዎች ላይ መጥፎ ቃል የሚሰነዝሩ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት የሚያደርሱባቸው መሆኑ ነው! ሰዎቹ የሚበሳጩት ስለሚጨነቁ ወይም አደገኛ ዕፅ ስለሚጠቀሙ አሊያም ደግሞ አፋጣኝ እርዳታ እንዳልተደረገላቸው ስለሚሰማቸው ሊሆን ይችላል። ችግሮቹን በቀላሉ መፍታት ባይቻልም ሕዝቡን ማስተማሩ ነገሮች እንዲሻሻሉ አድርጓል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ማዕከሉ በየዕለቱ ወደ 3, 000 የሚጠጉ የድንገተኛ አደጋ ጥሪዎችን ያስተናግዳል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁሉም ፎቶዎች:- Courtesy of London Ambulance Service NHS Trust