ገነት የምትመስል አሸዋማ ደሴት
ገነት የምትመስል አሸዋማ ደሴት
በአውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ ! ዘጋቢ እንደጻፈው
በ1770 ብሪታንያዊው አሳሽ ካፕቴን ጀምስ ኩክ በአውስትራሊያ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ በመርከብ እየተጓዘ ነበር። ከአሁኗ ብሪዝበን ከተማ በሰሜን በኩል መቶ ሃምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲደርስ ከጊዜ በኋላ በየዓመቱ የ300, 000 ጎብኚዎች መስህብ የሆነች አንዲት ትልቅ አሸዋማ ደሴት አልፎ ሄደ። ይሁን እንጂ ኩክ ደሴቲቱን ፈጽሞ ልብ አላላትም። እንዲያውም እርሱም ሆነ ሌሎች ሰዎች ይህ ስፍራ ባሕረ ገብ መሬት እንጂ ደሴት አልመሰላቸውም ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ማቲው ፍሌንደርዝ የተባለ ሌላ አሳሽ ወደ ደሴቲቱ ዳርቻ መጥቶ ነበር። እርሱም “ከዚህች ባሕረ ገብ መሬት የባሰ ጠፍ መሬት ሊኖር አይችልም” በማለት ጽፏል።
ኩክም ሆነ ፍሌንደርዝ ከወርቃማው የባሕሩ ዳርቻና በአቅራቢያው ከተከመሩት የአሸዋ ቁልሎች ትንሽ ኪሎ ሜትሮች ዘልቀው ገብተው ቢሆን ኖሮ አስተያየታቸው ከዚህ ፈጽሞ የተለየ በሆነ ነበር። ከዚህም በላይ የዓለማችንን ያልተነካ ደን፣ ኩልል ባሉ ውኃዎች የተሞሉ ሐይቆችን፣ እጹብ ድንቅ ቀለም ያላቸው የአሸዋ ሸንተረሮችንና በመቶዎች የሚቆጠሩ የእንስሳ ዝርያዎችን መመልከት በቻሉ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ፍሬዘር ደሴት በመባል የምትታወቀው ይህቺ የዓለማችን ትልቋ አሸዋማ ደሴት ከአስደናቂነቷ የተነሳ በ1992 በዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ሰፍራለች። *
ተራሮች የወለዷት ደሴት
ፍሬዘር ደሴት 120 ኪሎ ሜትር ርዝመትና እስከ 25 ኪሎ ሜትር ወርድ ያላት ሲሆን አጠቃላይ ስፋቷ 160, 000 ሄክታር ይሆናል። ከባሕር ወለል በላይ 240 ሜትር ገደማ ከፍ ብለው የሚገኙት ግዙፍ የአሸዋ ቁልሎች ደሴቲቱን በዓለማችን በከፍታዋ ተወዳዳሪ ያልተገኘላት አሸዋማ ደሴት እንድትሆን አድርገዋታል። ይሁንና ይህቺ አስደናቂ ደሴት እንዴት ልትፈጠር ቻለች?
ደሴቲቱ እንድትገኝ ምክንያት የሆነው ሥፍር ቁጥር የሌለው አሸዋ የመጣው ግሬት ዲቫይዲንግ ሬንጅ በመባል ከሚታወቀውና በአውስትራሊያ ምሥራቃዊ ዳርቻ ተንጣሎ ከሚገኘው የተራራ ሠንሠለት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በጊዜ ሂደት፣ ከባድ ዝናብ የፈጠረው ጎርፍ በእነዚህ የተራራ ሠንሠለቶች ላይ ያለውን አለት እየሰባበረ መጀመሪያ ወደ ወንዞች ከዚያም ወደ ባሕር ይዞ ይገባል። የባሕር ሞገድ ደግሞ ስብርባሪውን አለት ከወዲያ ወዲህ እያላጋ ደቃቅ አሸዋ ካደረገው በኋላ አሸዋው ቀስ በቀስ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየተገፋ ወደ ባሕሩ ወለል ይጓዛል። በዚህ ጊዜ ደቃቁን አሸዋ ባሕረ ገብ መሬት አሊያም ውቅያኖስ ውስጥ የሚገኝ ትልቅ ቋጥኝ ይይዘውና እዚያው መቆለል ይጀምራል፤ ፍሬዘር ደሴት ልትገኝ የቻለችው በዚህ መንገድ ነው።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ የፓስፊክ ውቅያኖስ አዳዲስ አሸዋዎችን ወደ ዳርቻዎቹ ማምጣቱን አላቋረጠም። በዳርቻው ላይ የተከማቸው አሸዋ በንፋስ እየተነሳ በደሴቲቱ መካከለኛ ክፍል ይቆለላል። እነዚህ የአሸዋ ቁልሎች ደግሞ ያገኙትን ነገር ሁሉ እየሸፈኑ በዓመት 1 ሜትር ያህል ወደ ጎን ይንሸራተታሉ።
ጨው አልባ ሐይቆችና አስደናቂ ደን
የሚገርመው፣ በደሴቲቱ ላይ ባሉት የአሸዋ ቁልሎች የታጠሩ 40 ጨው አልባ ሐይቆች ይገኛሉ። ከእነዚህ ሐይቆች ውስጥ አንዳንዶቹ በትላልቅ የአሸዋ ቁልሎች አናት ላይ ባሉ ሰፋፊ ጉድጓዶች ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ይሁንና ውኃው እንዳይሰርግ የሚከለክለው ምንድን ነው? ከውኃው ሥር ተነጥፎ የሚገኘው የቅጠላ ቅጠል፣ የቅርፊትና የቅርንጫፍ ብስባሽ እንደገበር ሆኖ ስለያዘው ነው።
ይህቺ ደሴት፣ የከርሰ ምድር ውኃ ባለበት አካባቢ ከፍተኛ ጥልቀት ያላቸው ሸለቆዎች በሚኖሩበት ጊዜ የሚፈጠሩ ሐይቆችም አሏት። ጨው አልባው የከርሰ ምድር ውኃ ወደ እነዚህ ሸለቆዎች ውስጥ ይሰርግና በአሸዋ የተጣራ እጅግ ኩልል ያለ ኩሬ ይፈጥራል፤ ሐይቆቹ ከላይ ሲታዩ መስኮት ያላቸው ይመስላሉ።
የደሴቲቱ ሐይቆች በየዓመቱ 1, 500 ሚሊ ሜትር የሚሆን ዝናብ ያገኛሉ። ከሐይቆች ሞልቶ የተረፈው አሊያም ወደ አሸዋ ውስጥ ሊሰርግ ያልቻለው ውኃ ትንንሽ ጅረቶችን
በመሥራት ወደ ባሕሩ ይፈስሳል። አንድ ወንዝ ብቻ በሰዓት 5 ሚሊዮን ሊትር የሚሆን ውኃ ለፓስፊክ ውቅያኖስ ይገብራል።ውኃ በበቂ መጠን መኖሩ ፍሬዘር ደሴትን ልምላሜ አላብሷታል። አብዛኛውን ጊዜ ጥቅጥቅ ያለ ደን ለም ባልሆነ አሸዋማ አካባቢ ሲበቅል አይታይም። ሆኖም ፍሬዘር ደሴት አሸዋማ ቢሆኑም ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎች ከሚገኙባቸው ጥቂት የዓለማችን አካባቢዎች አንዷ ናት። በአንድ ወቅት ደኑ በጣም ጥቅጥቅ ከማለቱ የተነሳ ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት የዛፍ ቆራጮች መጥረቢያ ድምጽ ሲያስተጋባበት ቆይቷል። በእነዚህ ጊዜያት ብላክበት፣ ካውሪ እንዲሁም ታሎዉድ የተባሉ የዛፍ ዓይነቶች መተዳደሪያቸውን በደኑ ላይ ያደረጉ ሰዎችን ትኩረት የሚስቡ ነበሩ። በ1929 አንድ ግለሰብ እንደሚከተለው ሲል ተናግሮ ነበር:- “በደኑ ውስጥ የሚጓዝ ሰው ከ45 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ሕያው የሆኑ ግዙፍ የዛፍ ግድግዳዎችን ያገኛል . . . የጫካው ነገሥታት የሆኑት እነዚህ ዛፎች ግንዳቸው መሃል ለመሃል ሲለካ ከ2 እስከ 3 ሜትር ይደርሳል።” እንደ ሳቲኔይ እና ተርፐንታይን የመሳሰሉት ዛፎች ስዊዝ ቦይን ለመሥራት አገልግለዋል። ሆኖም በፍሬዘር ደሴት ላይ ሲካሄድ የነበረው የደን ጭፍጨፋ በአሁኑ ጊዜ ታግዷል።
አሳዛኝ ክስተቶችን ያስተናገደች ገነት
ደሴቲቱ ስሟን ያገኘችው ከአንድ አሳዛኝ ታሪክ ነው። በ1836 ካፕቴን ጀምስ ፍሬዘርና ባለቤቱ ኢላይዛ፣ ስተርሊንግ ካስል የተሰኘችው መርከብ ካጋጠማት አደጋ ተርፈው እንደምንም ወደዚህች ደሴት መድረስ ቻሉ። ያም ሆኖ የደሴቲቱ ተወላጆች ካፒቴኑን ገደሉት፤ ኢላይዛ ግን በሕይወት ለመትረፍ በቃች። ለዚህ አሳዛኝ ታሪክ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ታላቋ አሸዋማ ደሴት በመባል ትጠራ የነበረችው ደሴት ስሟ ተቀይሮ ፍሬዘር ደሴት ተባለች።
የደሴቲቱ ተወላጆችም ቢሆን አሳዛኝ ሁኔታዎች ገጥመዋቸዋል። በአንድ ወቅት እስከ 2, 000 የሚሆኑ አቦርጅኖች በፍሬዘር ደሴት ላይ ይኖሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ፈርጠም ያሉና ጠንካሮች እንደነበሩ ይነገራል። መኖሪያቸውንም ገሪ ወይም ደግሞ ገነት በማለት ይጠሯት ነበር። ደሴቲቱ የተገኘችበትን ሁኔታ አስመልክቶ የሚነገር አንድ የአቦርጅኖች አፈ ታሪክ በምድር ላይ ካሉት ቦታዎች ሁሉ እጅግ ውብ የሆነች ተደርጋ እንደተሠራች ይገልጻል። የሚያሳዝነው ግን አውሮፓውያን ይዘዋቸው በመጡት በሽታዎች ሳቢያ በርካታ ሰዎች አለቁ። ከዚህም በላይ ቀሪዎቹ አቦርጅኖች በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በዋናው የአገሪቱ ክፍል ወዳሉ የሰፈራ ጣቢያዎች እንዲዘዋወሩ ተደረገ።
ውብ መኖሪያ
በአሁኑ ጊዜ ይህች ደሴት የዱር እንስሳት መኖሪያ ሆናለች። በዚህች ደሴት ላይ ከሚገኙት በሰፊው የታወቁ እንስሳት መካከል ዲንጎ በመባል የሚጠራው የአውስትራሊያ የዱር ውሻ ይገኝበታል። በዋናው አህጉር ከሚገኙት ለማዳ ውሾች በተለየ መልኩ በምሥራቃዊው አውስትራሊያ፣ በፍሬዘር ደሴት ላይ የሚኖሩት ዲንጎዎች ምርጥ ዝርያዎች እንደሆኑ ተደርገው ይታሰባሉ። ዲንጎዎች ከለማዳ ውሾች ጋር ሊመሳሰሉ ቢችሉም አንድ ዓይነት ግን አይደሉም። ስለሆነም በጥንቃቄና በአክብሮት ሊያዙ ይገባል።
በደሴቲቱ ላይ ከ300 ዓይነት በላይ ዝርያ ያላቸው ወፎች ይገኛሉ። ብራህሚኒ ካይትስ እና ሆደ-ነጭ የባሕር ንሥሮች በባሕሩ ዳርቻ ላይ ሲያንዣብቡ ይታያሉ። አብረቅራቂ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው የዓሣ ዓመቴዎች ደግሞ በሐይቆቹ አናት ላይ በዝግታ ይንሳፈፋሉ። በስደት ወደ አካባቢው ከሚመጡት ወፎች መካከል በሳይቤርያ ተፈልፍለው በክረምት ወደ ደቡብ የሚፈልሱት ሞንጎልያን ሳንድ ፕለቨርስ ይገኙበታል። እነዚህ ወፎች ጉዟቸውን ከማገባደዳቸው በፊት በፍሬዘር ደሴት ላይ ለትንሽ ጊዜ እረፍት ያደርጋሉ። በተጨማሪም 30, 000 አሊያም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ቁራ የሚያህሉ ጭንቅላተ-ግራጫ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ወቅታቸውን ጠብቀው የባሕር ዛፍ አበባዎችን ለመቅሰም ወደ ደሴቲቱ ይጎርፋሉ።
በፍሬዘር ደሴት ዙሪያ በሚገኘው ባሕር ውስጥ፣ ከበረዷማው አንታርክቲክ ተነስተው ወደሚራቡበትና ልጆችን ወደሚወልዱበት ወደ ግሬት ባርየር ሪፍ ሲጓዙ እግረ መንገዳቸውን ጎራ የሚሉትን ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪዎች ጨምሮ ሌሎች የውኃ ውስጥ እንስሳት ሲርመሰመሱ ይታያል። እነዚህ ግዙፍ ዓሣ ነባሪዎች ወደ አንታርክቲክ በሚያደርጉት የመልስ ጉዞ ላይ ከውኃው ተወርውረው ሲወጡና ሲጠልቁ ከርቀት ላያቸው በእርግጥም ለማራኪዋ ደሴት በአክብሮት እጅ የሚነሱ ይመስላሉ!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.4 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሚያሰፍረው ከባዮሎጂ፣ ከሥነ ምድር (ጂኦሎጂካል) አሊያም ከሳይንስ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ባሕላዊና ተፈጥሯዊ አካባቢዎች ነው።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኙ ካርታዎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት )
ፓስፊክ ውቅያኖስ
ፍሬዘር ደሴት
[በገጽ 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በስተ ቀኝ በኩል፣ ከላይ ወደ ታች:-
የከርነን ጅረት ወደ ውቅያኖስ የሚገባበት ቦታ
በፍሬዘር ደሴት ላይ አርባ የሚያክሉ ጨው አልባ ሐይቆች ይገኛሉ
እምብዛም ያልተለመደው በአሸዋ ላይ የበቀለ ጥቅጥቅ ያለ ደን
[ምንጭ]
ሁሉም ፎቶዎች:- Courtesy of Tourism Queensland
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዲንጎ እና ኮኣላ
[ምንጭ]
Courtesy of Tourism Queensland
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዓለማችን በርዝመቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለትና 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፍሬዘር ደሴት የባሕር ዳርቻ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሆደ-ነጭ የባሕር ንሥር
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኩካቡራዎች
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጰልቃኖች
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ አንታርክቲክ በመጓዝ ላይ ያሉ ሃምፕባክ ዓሣ ነባሪዎች ለተወሰነ ጊዜ እዚህ አካባቢ ቆይታ ያደርጋሉ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ንስር:- ©GBRMPA; ከጰልቃኖች በስተቀር ሌሎቹ ፎቶዎች:- Courtesy of Tourism Queensland