በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ በአንድ ዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ዓይነት የአእምሮ መታወክ የሚደርስበት ሲሆን ከሁለት ሰዎች አንዱ ደግሞ በሕይወቱ ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ ይህ ችግር ያጋጥመዋል።”—ሳይንስ ኒውስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በመስከረም 2004፣ ሃሪኬን ኢቫን የተባለው አውሎ ነፋስ በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ ከ15 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው 24 ሞገዶችን አስነስቶ ነበር። ከእነዚህም መካከል ትልቁ 27.7 ሜትር ከፍታ ነበረው።—ሳይንስ መጽሔት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

መኪና እየነዱ በሞባይል ስልኮች መጠቀም ሆስፒታል ገብቶ እስከ መታከም የሚያደርሱ አደጋዎች በአራት እጥፍ እንዲጨምሩ ያደርጋል። አሽከርካሪው የሚጠቀምበት ሞባይል ስልክ በእጅ የሚያዘውም ይሁን በመኪናው ላይ የተገጠመ ምንም ልዩነት አያመጣም።—ቢ ኤም ጄ፣ ብሪታንያ

▪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችን እንዲረዳቸው ተብሎ የተዘጋጀ አንድ አዲስ የቋንቋዎች ዝርዝር በአሁኑ ጊዜ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው 6,912 ቋንቋዎች እንዳሉ መዝግቧል።—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

▪ በፖላንድ ከሚኖሩ ሴቶች 30 በመቶ የሚሆኑት በእርግዝና ወቅትና ጡት በሚያጠቡባቸው ዓመታት ሲጋራ ማጨስ ልጆቻቸውን እንደሚጎዳ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ማጨሳቸውን አያቆሙም።—ዥድሮቬ መጽሔት፣ ፖላንድ

ሰዎች ስለ ሀብት ያላቸው አመለካከት

በአውስትራሊያ የሚገኝ አንድ ድርጅት ሰዎች ስለ ሀብት ያላቸውን አመለካከት ለማወቅ ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው ከ20 ሚሊየነሮች ውስጥ ራሱን እንደ ባለጠጋ የሚቆጥረው አንዱ ብቻ መሆኑን ኤቢሲ ኒውስ ኦንላይን ዘግቧል። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ክላይቭ ሃሚልተን እንደተናገሩት “ሀብታችን እየጨመረ በሄደ መጠን ከገቢያችን የምናገኘው ደስታ እየቀነሰ ይሄዳል።” እንዲያውም ከፍተኛ ገቢ ካላቸው ሰዎች መካከል በኑሯቸው ሙሉ በሙሉ ደስተኞች የሆኑት 13 በመቶ ብቻ ናቸው። ሀሚልተን እንዳሉት “በሕይወታችን ውስጥ ደስታ የሚያስገኙት ሌሎች ነገሮች እንደሆኑ እየታወቀ ኅብረተሰባችን ከምንም ነገር በላይ ገንዘብን የሚያሳድደው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል።”

በሕዋ ላይ የቀሩ ሳተላይቶች

“አሽከርካሪዎች ነዳጅ ሲያልቅባቸው መኪናቸውን በመንገድ ላይ ትተው የሚሄዱ ቢሆን ኖሮ እንዴት እንደሚያናድድ አስቡት” በማለት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይናገራል። ሆኖም በሕዋ ላይ ተጥለው በቀሩ ሳተላይቶች ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ መሣሪያዎች ወደ ጠፈር ከሚላኩ አዳዲስ መንኮራኩሮች ጋር በመጋጨት አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ። በሕዋ ውስጥ ለመገናኛ ስርጭት ሳተላይቶች ተመራጭ በሆነው አካባቢ አቅራቢያ ከ60 ሴንቲ ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው 1,120 ሳተላይቶች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉት 300 ብቻ ናቸው። በመሬት ዙሪያ በተለያየ ከፍታ ላይ ተትተው በመሽከርከር ላይ ካሉት አደገኛ የሆኑ ነገሮች መካከል መሥራት ያቆሙ 32 የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ይገኛሉ።

የጦር መሣሪያዎችና ጦርነት

ቀዝቃዛው ጦርነት ሲያበቃ የጦር መሣሪያ ሽያጭ አሽቆልቁሎ ነበር። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ንግዱ እንደገና ተጧጡፏል። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም ባወጣው ዘገባ መሠረት በ2004 በዓለም ዙሪያ ለወታደራዊ ወጪ የተመደበው ባጀት አንድ ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ደርሷል። ይህ ገንዘብ በፕላኔታችን ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ሰው (ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ) ቢከፋፈል ሁሉም ሰው በግለሰብ ደረጃ 162 የአሜሪካ ዶላር ይደርሰዋል። ከላይ የተጠቀሰው ምንጭ ባወጣው ዘገባ መሠረት በ2004 19 ውጊያዎች የተካሄዱ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከ1,000 ለሚበልጡ ሰዎች መሞት ምክንያት ሆነዋል። ከእነዚህ ውጊያዎች መካከል 16ቱ ከ10 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የተካሄዱ ናቸው።

ሁለት ዓይነት ነዳጅ የሚጠቀሙ መኪናዎች

በብራዚል እየተሸጡ ካሉት አዳዲስ መኪናዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሁለት ዓይነት ነዳጅ የሚጠቀሙ መሆናቸውን ቬጃ የተሰኘ መጽሔት ዘግቧል። እነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት በቤንዚን፣ የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት በሆነ አልኮል ወይም በተፈለገው መጠን ሁለቱንም በመቀላቀል በሚገኝ ነዳጅ ነው። ከ2003 እስከ 2004 ባለው ጊዜ የአልኮል ነዳጅ ሽያጭ በ34 በመቶ ጨምሯል። የአልኮል ነዳጅ መጠቀም የተጀመረው የአየር ብክለትን ለመቀነስ በማሰብ ሳይሆን ለአብዛኞቹ ባለ መኪናዎች ዋጋው ስለሚረክስላቸው ብቻ ነው። ሁለት ዓይነት ነዳጅ የሚጠቀሙ መኪናዎች “ተጠቃሚውን በነዳጅ እጥረትና በዋጋ አለመረጋጋት ሳቢያ ከሚፈጠረው ችግር” ሊገላግሉት እንደሚችሉ ራፋኤል ሺዱማን የተባሉት የብራዚል የመሠረተ ልማት ማዕከል ዲሬክተር ያብራራሉ። “የአልኮል ዋጋ ከጨመረ ወደ ቤንዚን መመለስ ትችላላችሁ፤ የቤንዚን ዋጋ ከናረ ደግሞ ወደ አልኮል መዞር ትችላላችሁ” ብለዋል።