በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለየት ያለ ውበት ያለው ባሕላዊ የአትክልት ቦታ

ለየት ያለ ውበት ያለው ባሕላዊ የአትክልት ቦታ

ለየት ያለ ውበት ያለው ባሕላዊ የአትክልት ቦታ

ጓዴሎፕ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ውብ በሆነ ስፍራ ቢኖሩም አካባቢው ያለውን አስደሳች ገጽታ ማጣጣም አልቻሉም። እነዚህ ሰዎች፣ ከ17ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ከትውልድ አገራቸው ታፍነው ወደ ጓዴሎፕና ማርቲኒክ የተወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምስኪን አፍሪካውያን ናቸው። ቀሪውን የሕይወት ዘመናቸው በአብዛኛው ያሳልፉ የነበረው በእነዚህ የካሪቢያን ደሴቶች ላይ በሚገኙ የሸንኮራ አገዳ ማሳዎች በባርነት በመሥራት ነበር።

በደሴቶቹ ላይ የሚገኙት በርካታ የእርሻ ባለቤቶች ለባሮቻቸው ምግብ ስለማይሰጧቸው ባሮቹ የራሳቸውን የጓሮ አትክልት ያለሙ ነበር። በሥራ በጣም የሚደክሙ ቢሆንም ቢያንስ ቢያንስ የሚወዷቸውን ምግቦች ማምረት ችለዋል። እነዚህ ባሮች ካሳቫ፣ ስኳር ድንችና ጌቶቻቸው ከሚሰጧቸው ምግብ ይበልጥ ጣፋጭና ጠቃሚ የሆኑ ሌሎች አትክልቶችን ያመርቱ ነበር። እንዲሁም መድኃኒትነት ያላቸውን ቅጠላ ቅጠሎችና ምግብ ውስጥ የሚጨመሩ ቅመሞችን ያለሙ ነበር።

በ1848 የፈረንሳይ መንግሥት የባሪያ ሥርዓትን ከደሴቶቹ ላይ ቢያስወግድም ነጻ የወጡት ዜጎች የጓሮ አትክልት ማልማታቸውን አላቆሙም። አብዛኞቹ የእነዚህ ጠንካራ ሠራተኛ አፍሪካውያን ዝርያ የሆኑት የጓዴሎፕና የማርቲኒክ ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ጊዜ ክሪዮል ተብለው የሚጠሩትን የአትክልት ቦታዎች ማልማት ቀጥለዋል።

ትንሽ ደን

በባርነት ሥር ያሉ ቤተሰቦች ሁለት ዓይነት የአትክልት ቦታዎች ያዘጋጁ ነበር። በአብዛኛው ቅጠላ ቅጠል ያመርቱ የነበረው ከቤቱ ጥቂት ራቅ ብለው ነው። “የጓሮ አትክልት” የሚባለው (የአካባቢው ነዋሪዎች ዠርደ ደ ካዝ ብለው ይጠሩታል) ደግሞ ከቤቱ አጠገብ የሚዘጋጅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ክሪዮል የአትክልት ቦታ ከሚባለው ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህ የአትክልት ቦታ እርስ በርስ ተጠላልፈው የሚገኙ በርካታ የአበባ፣ የሣርና የዛፍ ዓይነቶች እንዲሁም ደን ውስጥ እንደሚታየው ዓይነት ጥቅጥቅ ያለ ቁጥቋጦ ይገኛል። በአትክልት ያልተሸፈነ አንድም ክፍት ቦታ የለም፤ ስለዚህ መጀመሪያ ስታየው ቦታው ለዓይን ደስ የሚል ቢሆንም በሥርዓት የተያዘ ላይመስልህ ይችላል። ሆኖም ይህ የአትክልት ቦታ በሚገባ የተደራጀና የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ከመሆኑም በላይ ባለቤቱን ወደ ሁሉም አትክልቶች የሚያደርሱት ቀጫጭን መንገዶች አሉት።

የአትክልት ቦታው ከቤቱ ጓሮ አንስቶ ፊት ለፊት እስከሚገኘው ውብ የእንግዳ ማስተናገጃ ያለውን ቦታ ይይዛል። እንግዶች በሚመጡበት ጊዜ ቤተሰቡ ክሮቶን በተባለ የሚያምር ተክል፣ የጥሩንባ ቅርጽ ባለው ወርቃማ አበባ፣ በባለ ደማቅ ቅጠሉ ቦጋንቢልና ኢክሶራ በተባለ ተክል መካከል ያስተናግዳቸዋል።

መድኃኒትነት ያላቸው አትክልቶች በአብዛኛው የሚተከሉት የቤቱ ጥላ በሚያርፍበት ቦታ ላይ ነው። በደሴቶቹ ላይ ባሕላዊ ሕክምና ከሚሰጥባቸው አትክልቶች መካከል ባዝል፣ ቀረፋ፣ ጎትዊድ፣ ላውሮና ጃክ ኢን ዘ ቡሽ (ነፍሳት የሚበላ ተክል) ይገኙባቸዋል። በዚህ ባሕላዊ የአትክልት ቦታ ጠጅ ሣርም የሚበቅል ሲሆን ይህን ሣር አድርቆ በማጨስ ትንኞችን ማባረር ይቻላል።

በደሴቶቹ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች መድኃኒትነት ስላላቸው አትክልቶች ያውቃሉ። ቀደም ባሉት ዘመናት አንድ ሰው ቢታመም ወይም ቢቆስል ብዙውን ጊዜ ሐኪሞችን በቅርብ ማግኘት አይቻልም ነበር። ስለዚህ ሰዎች ክሪዮል የአትክልት ቦታ ውስጥ ያሉትን ቅጠላ ቅጠሎች በመጠቀም ራሳቸውን ያክሙ ነበር። እነዚህ ተክሎች አሁንም ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ቢሆንም ያለ እውቀት እነዚህን መድኃኒቶች መውሰድ ለአደጋ ሊያጋልጥ ይችላል። ከእነዚህ ዕፅዋት የሚዘጋጀው መድኃኒት በትክክል ካልተወሰደ በሽተኛውን ከመፈወስ ይልቅ ሕመሙን ሊያባብስበት ይችላል። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የደሴቶቹ ነዋሪዎች በአብዛኛው የሚታከሙት በዚህ ረገድ ሥልጠና ወዳገኙ ሰዎች በመሄድ ነው።

ከቤቱ ጓሮ የሚገኘው የክሪዮል አትክልት ቦታ ዋነኛ ክፍል የሚያገለግለው ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችን ለማልማት ነው። በዚህ ቦታ ስኳር ድንች፣ ደበርጃን፣ በቆሎ፣ ስፕሊን አማራንት፣ የተለያዩ የሰላጣ ዓይነቶችና ሌሎች እህሎች እንዲሁም እነዚህ ምግቦች ውስጥ የሚጨመሩ ቅመሞች በአቅራቢያቸው ተተክለው ታገኛለህ። በተጨማሪም ሙዝ፣ ብሬድ ፍሩት፣ አቮካዶ፣ ዘይቱን ወይም ማንጎ ሊኖር ይችላል።

ይህን ውብ ቦታ እንጎብኝ

ወደ ክሪዮል የአትክልት ቦታ ገብተህ ዞር ዞር እያልክ ስትመለከት የእያንዳንዱ ተክል ውበት ቀረብ ብለህ እንድታየው ይጋብዝሃል። የአትክልት ቦታው ውስጥ ገብተህ ቀለማቸው በፀሐይ ብርሃን ደምቆ የሚታየውን በሥርዓት የበቀሉ አበቦችና ቅጠሎች ስትመለከት በጣም ትደነቃለህ። እንዲሁም ነፋሱ የአበቦቹን ሽታ በመቀላቀል የሚፈጥረው መዓዛ ሽቶን ያስንቃል። አንተ በመጎብኘት ብቻ ደስ መሰኘት የምትችል ከሆነ፣ የአትክልት ቦታውን ያዘጋጀውና በየዕለቱ የሚመለከተው ባለቤቱ ደግሞ ምን ያህል ሊደሰት እንደሚችል ገምት!

ክሪዮል የአትክልት ቦታ ወደፊት ይኖር ይሆን? አንዳንድ የደሴቶቹ ነዋሪዎች ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ያለውን አስደሳችና ጠቃሚ ባሕል የመውረስ ፍላጎት እንደማይታይበት በምሬት ይናገራሉ። የሆነ ሆኖ በርካታ ወጣቶችና በዕድሜ የገፉ ሰዎች ለአትክልት ቦታው ውበትና ለባሕላዊ ትርጉሙ ላቅ ያለ ግምት አላቸው። እያንዳንዱ ክሪዮል የአትክልት ቦታ፣ አፍሪካውያን ባሮች በመጥፎ ሁኔታ ሥር የነበሩ ቢሆንም ውብና ጠቃሚ ነገር እንደፈጠሩ የሚያሳይ ማስታወሻ ነው።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ክሪዮል” ምን ማለት ነው?

በመጀመሪያ “ክሪዮል” የሚለው ቃል በሰሜን፣ በደቡብና በመካከለኛው አሜሪካ በሚገኙ አገሮች ውስጥ የተወለዱትን የአውሮፓ ዝርያዎች ያመለክት ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ቃሉ የተለያየ ትርጉም ይሰጠው ጀመር። አንዳንድ የሄይቲ ነዋሪዎች “ክሪዮል” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት በጣም ማራኪ የሆነን ወይም ከፍተኛ ጥራት ያለውን ነገር ለመግለጽ ነው። በጃማይካ፣ በሄይቲና በሌሎች አገሮች የሚነገሩ አንዳንድ ቋንቋዎችም ክሪዮል ይባላሉ። በመሠረቱ ክሪዮል የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች እርስ በርስ ለመግባባት የፈጠሩት ቋንቋ ሲሆን ከጊዜ በኋላ የተናጋሪዎቹ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኗል።

በተጨማሪም “ክሪዮል” የሚለው ቃል በበርካታ የካሪቢያን ደሴቶች ላይ የሚገኘውን ለየት ያለ የአኗኗር ዘይቤ ወይም ባሕል ለማመልከትም ማገልገል ጀምሯል። ክሪዮል ከሚለው ቃል ጋር ተያያዥነት ያለው ክሪኦዮ የሚለው ስፓንኛ ቃል በፖርቶ ሪኮና በዶሚኒካን ሪፐብሊክ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ሐሳብ ያስተላልፋል። በካሪቢያን ደሴቶች የሚገኙ የአገሬው ተወላጆች እንዲሁም የአፍሪካውያንና የአውሮፓውያን ዝርያዎች ባለፉት መቶ ዘመናት እርስ በእርስ በመቀላቀላቸውና በመጋባታቸው የሚያምሩ ልጆች መውለድና አስደናቂ ባሕል ማዳበር ችለዋል። በጓዴሎፕና በማርቲኒክ የሚገኙት ክሪዮል የአትክልት ቦታዎች ስያሜያቸውን ያገኙት እንዲህ ካሉት ባሕሎች በመነሳት ነው።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክብ ቅርጽ ውስጥ ያሉት ፎቶዎች (ከላይ ጀምሮ):- አልፒኒያ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ አናናስ፣ ካካዎ እና ቡና