ማንበብ ያለብኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ . . .
ማንበብ ያለብኝ ለምንድን ነው?
“ለማንበብ ትዕግሥቱ የለኝም። ከማነብ ይልቅ ቴሌቪዥን ባይ እመርጣለሁ።”—የ13 ዓመቷ ማርጋሪተ፣ ሩሲያ
“መጽሐፍ ከማንበብና የቅርጫት ኳስ ከመጫወት አንዱን ምረጥ ብባል የቅርጫት ኳስ መጫወትን እመርጣለሁ።”—የ19 ዓመቱ ኦስካር፣ ዩናይትድ ስቴትስ
እዚህ ድረስ ማንበብ ከቻልክ፣ ንባብ ልታዳብረው የሚገባ ጠቃሚ ክህሎት መሆኑን ተረድተሃል ማለት ነው። ያም ሆኖ ግን፣ መጻሕፍትን ሌላው ቀርቶ መጽሔቶችን እንኳ ማንበብ መድኃኒት እንደ መውሰድ አድርገህ ትመለከተው ይሆናል። መድኃኒቱ እንደሚጠቅምህ ብታውቅም ባትወስደው ትመርጣለህ።
ንቁ! መጽሔት በ11 አገሮች ለሚኖሩ ወጣቶች ማንበብን ፈታኝ ስላደረጉባቸው ነገሮችና ማንበባቸው ስላስገኘላቸው ጥቅሞች ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር። ወጣቶቹ የሰጡት መልስ የሚከተለውን ይመስላል:-
ማንበብ ከባድ ሥራ እንደሆነ የሚሰማህ/ሽ ለምንድን ነው?
“በአብዛኛው ለማንበብ ጊዜ አላገኝም።”—የ19 ዓመቷ ሴምሲሃን፣ ጀርመን
“ንባብ ጥረት ይጠይቃል። እኔ ደግሞ ስንፍና አለብኝ።”—የ19 ዓመቱ ኢዚክኤል፣ ፊሊፒንስ
“አሰልቺ ስለሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች እንዳነብ መገደድ አልፈልግም።”—የ15 ዓመቷ ክርስቺያን፣ እንግሊዝ
“ጥቂት ገጾች ያሉት መጽሐፍ ከሆነ የማንበብ ፍላጎቴ ይቀሰቀስ ይሆናል። መጽሐፉ ዳጎስ ያለ ከሆነ ግን ማንበብ ያስፈራኛል።”—የ18 ዓመቱ ኤሪኮ፣ ጃፓን
“ትኩረቴን ማሰባሰብ አልችልም። ሐሳቤ በቀላሉ በሌሎች ነገሮች ይሰረቃል።”—የ13 ዓመቱ ፍራንሲስኮ፣ ደቡብ አፍሪካ
መዝሙር 1:1-3) ይህን ማድረግ ያስቸግርሃል/ሻል? ከሆነስ ለምን?
ክርስቲያን ወጣቶች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ይበረታታሉ። (“መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ መጽሐፍ ነው! ዕድሜዬን ሙሉ ባነበው እንኳ የምጨርሰው አይመስለኝም!”—የ13 ዓመቷ አና፣ ሩሲያ
“አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በቀላሉ የሚገፉ አይደሉም፤ ደግሞም ያን ያህል አይማርኩኝም።”—የ11 ዓመቱ ጄዝሬል፣ ሕንድ
“በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ፈታኝ ሆኖብኛል፤ ምክንያቱም ጥሩ ፕሮግራም የለኝም።”—የ19 ዓመቷ ኤልሳ፣ እንግሊዝ
“የቤትና የትምህርት ቤት ሥራዎች ጊዜዬን ስላጣበቡት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስቸጋሪ ሆኖብኛል።”—የ14 ዓመቷ ሱሪሳዲ፣ ሜክሲኮ
“በትርፍ ሰዓት ከምሠራቸው ነገሮች ጊዜ ቆጥቤ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያስቸግረኛል።”—የ14 ዓመቱ ሾ፣ ጃፓን
ማንበብ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ሆኖም ለማንበብ ጥረት ማድረግ ምን ጥቅም አለው? አንተ/አንቺ በማንበብ የተጠቀምከው/ሽው እንዴት ነው?
“ማንበብ እውቀቴን አስፍቶልኛል፤ ይህም ከሰዎች ጋር በምነጋገርበት ጊዜ ይበልጥ በራሴ እንድተማመን አድርጎኛል።”—የ14 ዓመቷ ሞኒሻ፣ ሕንድ
“ንባብ ዘና ያለ ስሜት እንዲኖረኝና ባሉብኝ ችግሮች ላይ እንዳላተኩር ያደርገኛል።”—የ17 ዓመቷ አሊሰን፣ አውስትራሊያ
“ማንበብ መቼም ቢሆን ልጎበኛቸው የማልችላቸውን ቦታዎች እንዳውቅ ረድቶኛል።”—የ19 ዓመቱ ዱአን፣ ደቡብ አፍሪካ
“ማንበብ ሌሎች በነገሩኝ ከመመራት ይልቅ አንዳንድ ነገሮችን ራሴ መርምሬ እንዳውቅ ረድቶኛል።”—የ16 ዓመቱ አቢሁ፣ ሜክሲኮ
ንባብ እንድትወድ/ጂ የረዳህ/ሽ ምንድን ነው?
“ከትንሽነቴ ጀምሮ ወላጆቼ ድምፄን ከፍ አድርጌ እንዳነብ ያበረታቱኝ ነበር።”—የ18 ዓመቷ ታንያ፣ ሕንድ
“ወላጆቼ የማነባቸውን ነገሮች በዓይነ ሕሊናዬ እንድስል ያበረታቱኝ ነበር።”—የ18 ዓመቱ ዳኒየል፣ እንግሊዝ
“አባቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ እንደ መዝሙርና ምሳሌ ካሉት ይበልጥ ደስ ከሚሉኝ መጻሕፍት እንድጀምር ሐሳብ ያቀርብልኝ ነበር። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ሸክም ሳይሆን አስደሳች ነገር ሆኖልኛል።”—የ16 ዓመቷ ቻሪን፣ ደቡብ አፍሪካ
“አራት ዓመት ሲሆነኝ፣ ወላጆቼ ከተወለድኩ አንስቶ ያጠራቀሙልኝን መጻሕፍት ከማንበቢያ ጠረጴዛና መደርደሪያ ጋር ሰጡኝ።”—የ14 ዓመቷ አሪ፣ ጃፓን
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጠቃሚ እንደሆነ የሚሰማህ/ሽ ለምንድን ነው?
“ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የተሳሳቱ እምነቶች አሏቸው። ስለ እነዚህ ነገሮች እውነቱን ለማወቅ አንተው ራስህ መጽሐፍ ቅዱስን ብታነብ የተሻለ ነው።” (የሐዋርያት ሥራ 17:11)—የ15 ዓመቱ ማቲው፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በደንብ ማሰብ ይጠይቃል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ስለማምንበት ነገር በግልጽና በልበ ሙሉነት ለመናገር አስችሎኛል።” (1 ጢሞቴዎስ 4:13)—የ19 ዓመቷ ጄን፣ እንግሊዝ
“መጽሐፍ ቅዱስን ሳነብ ይሖዋ በቀጥታ እንደሚያነጋግረኝ ሆኖ ይሰማኛል። አንዳንድ ጊዜ ስሜቴ በጥልቅ ይነካል።” (ዕብራውያን 4:12)—የ15 ዓመቱ ኦበዳያ፣ ሕንድ
“መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ስለ እኔ ምን እንደሚያስብ ስለሚነግረኝና ጠቃሚ ምክሮችን ስለሚለግሰኝ ንባቤን እየወደድኩት ነው።” (ኢሳይያስ 48:17, 18)—የ14 ዓመቷ ቪክቶሪያ፣ ሩሲያ
መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የምታነበው/ቢው መቼ ነው?
“ፕሮግራም አለኝ። ሁልጊዜ ጠዋት ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ምዕራፍ አነባለሁ።”—የ17 ዓመቷ ላይስ፣ ብራዚል
“በባቡር ተሳፍሬ ወደ ትምህርት ቤት ስጓዝ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን አነባለሁ። ላለፉት አራት ዓመታት ይህን ሳደርግ ቆይቻለሁ።”—የ19 ዓመቱ ታይቺ፣ ጃፓን
“ሁልጊዜ ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ።”—የ15 ዓመቷ ማሪያ፣ ሩሲያ
“በየቀኑ ከመጠበቂያ ግንብ አሊያም ከንቁ! መጽሔት ላይ አራት ገጽ የማንበብ ልማድ አለኝ። በመሆኑም ቀጣዩ እትም ከመምጣቱ በፊት መጽሔቱን ሙሉ በሙሉ አንብቤ መጨረስ እችላለሁ።”—የ18 ዓመቱ ኤሪኮ፣ ጃፓን
“ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ።”—የ17 ዓመቱ ጄምስ፣ እንግሊዝ
ከላይ ያሉት አስተያየቶች፣ ንባብ በራስ የመተማመን ስሜትህን እንደሚጨምርልህና እውቀትህን እንደሚያሰፋልህ ያሳያሉ። መጽሐፍ ቅዱስንና ይህን መጽሔት ጨምሮ ሌሎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ደግሞ ‘ወደ እግዚአብሔር እንድትቀርብ’ ይረዳሃል። (ያዕቆብ 4:8) በመሆኑም ንባብ ፈታኝ ሊሆንብህ ቢችልም እንኳ ከማንበብ ወደ ኋላ አትበል!
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ የአምላክን ቃል ማንበብህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
▪ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማንበብ ‘ዘመኑን በሚገባ መዋጀት’ የምትችለው እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:15, 16
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የምታነበውን ከሌሎች ነገሮች ጋር አዛምድ
ያነበብካቸውን ነገሮች ከራስህም ሆነ ከአካባቢህ ሁኔታ ጋር ለማዛመድ ሞክር። እንደሚከተለው እያልክ ራስህን ጠይቅ:-
▪ ቀደም ብለህ ካነበብከው ነገር ጋር አዛምድ:- እየተገለጸ ያለው ሁኔታ ወይም ችግር ካነበብኳቸው ሌሎች መጻሕፍት፣ ጽሑፎች ወይም ታሪኮች ጋር ይመሳሰላል? የገጸ ባሕርያቱ ሁኔታ ታሪካቸውን ከማውቀው ሰዎች ጋር የሚመሳሰልበት ነገር አለ?
▪ ከራስህ ሁኔታ ጋር አዛምድ:- ይህ ጽሑፍ ከእኔ ሁኔታና ባሕል ወይም ካለብኝ ችግር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ጽሑፉ ያለብኝን ችግር እንድቋቋም አሊያም ሕይወቴን እንዳሻሽል ሊረዳኝ ይችላል?
▪ በአካባቢህ ካሉ ነገሮች ጋር አዛምድ:- ይህ ጽሑፍ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ አካባቢዬ፣ ስለ ተለያዩ ባሕሎች ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ስላሉት ችግሮች ምን ያስተምረኛል? ያገኘሁት መረጃ ስለ ፈጣሪ የሚያስተምረኝ ነገር ይኖራል?