በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ያህል ዕድሜ መኖር ትችላለህ?

ምን ያህል ዕድሜ መኖር ትችላለህ?

ምን ያህል ዕድሜ መኖር ትችላለህ?

ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል።ኢዮብ 33:25

ሻ አሥር ወይም ሃያ ዓመት ኖሮ ሲሞት ምናልባትም ውሾች የሚሠሩትን አብዛኞቹን ነገሮች አድርጎ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ዘሩን ተክቶ፣ ድመት አባሮ፣ አጥንት ቀብሮ እና የጌታውን ቤት ጠብቆ ይሆናል። ነገር ግን ሰው 70 ወይም 80 ዓመት ኖሮ ሲሞት፣ ያከናወናቸው ነገሮች ማድረግ ከሚችለው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው። አንድ ሰው ስፖርት የሚወድ ቢሆን ምናልባት ይበልጥ የሚሳካለት በአንዱ ወይም በሁለቱ የስፖርት ዓይነቶች ብቻ ይሆናል። ለሙዚቃ ፍቅር ቢኖረው ጥሩ አድርጎ የሚጫወተው አንዱን ወይም ሁለቱን የሙዚቃ መሣሪያ ብቻ ይሆናል። ሰዎችን በገዛ አገራቸው ቋንቋ ማነጋገር የሚወድ ቢሆን ጥርት አድርጎ የሚናገራቸው ቋንቋዎች ሁለት ወይም ሦስት ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። ሰው ከዚህ የበለጠ ዕድሜ መኖር ቢችል ኖሮ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመገናኘት፣ አዳዲስ ግኝቶች ላይ በመድረስና ወደ አምላክ ይበልጥ በመቅረብ በርካታ አስደሳች ነገሮችን ማድረግ በቻለ ነበር።

‘አምላክ ሰውን በብዙ ነገሮች መደሰት የሚያስችል አእምሮ እንዲኖረው አድርጎ ፈጥሮት ሲያበቃ የሕይወት ዘመኑን ለምን አሳጠረበት?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የሰው ዕድሜ አጭር መሆኑ ከፍጥረት ሥራ ዓላማ አንጻር ሲታይ እርስ በርሱ የሚጋጭ ይመስላል። ምናልባት እንዲህ ብለህ ትጠይቅም ይሆናል:- ‘አምላክ ሰውን በአንድ በኩል እንደ ፍትሕና ርኅራኄ ያሉ ግሩም ባሕርያትን እንዲያንጸባርቅ በሌላ በኩል ደግሞ ክፉ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌ እንዲኖረው አድርጎ የፈጠረው ለምንድን ነው?’

አንድ በጣም የምታምር፣ ነገር ግን ጎኗ ላይ የተጠረመሰች መኪና ብታይ መኪናዋ ስትሠራም እንደዚሁ ነበረች ብለህ ትደመድማለህ? በፍጹም! ‘መኪናዋ እንደዚህ ተደርጋ አልተሠራችም። ምንም እንኳ በጥሩ ሁኔታ የተሠራች ብትሆንም አንድ ሰው ጉዳት አድርሶባታል’ ብለህ እንደምትደመድም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም እጅግ አስደናቂ የሆነውን አፈጣጠራችንን ስንመለከት ጉድለት ኖሮን እንዳልተሠራን መደምደም እንችላለን። ዕድሜያችን አጭር የሆነበት ወይም ክፉ የምናደርግበት ምክንያት መኪናዋን ካጋጠማት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ፍጹም የነበረውን የሰው ሕይወት አንድ አካል እንዳበላሸው ግልጽ ነው። ይህንን ያደረገው ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ወንጀለኛ ማንነት በግልጽ ይጠቁመናል።

የሰው ልጅ ለዘላለም እንዲኖር ሆኖ የተፈጠረ ከሆነ የሰው ዘሮች በሙሉ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት የመኖር መብታቸውን ያሳጣቸው ማን ነው? የሰው ልጆች ሁሉ አባት የሆነው የመጀመሪያው ሰው እንደሆነ እሙን ነው። ከእርሱ ሌላ የመላውን የሰው ዘር ማለትም የዝርያዎቹን ጂን ሊያበላሽ የሚችል የለም። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት በአንድ ሰው [በመጀመሪያው ሰው በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ” በማለት ይህን ሐቅ በግልጽ አስቀምጦታል። (ሮሜ 5:12) ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሕይወታችን መበላሸት ተጠያቂው አዳም እንደሆነ ይናገራሉ። ታዲያ የሰው ልጅ የተፈጠረበት የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር?

የተፈጠርንበትን ዓላማ መረዳት

መጽሐፍ ቅዱስ ሞትን “ወደ ዓለም እንደ ገባ” አድርጎ መናገሩ የሰው ልጅ መጀመሪያ ላይ ለሞት እንዳልተፈጠረ ይጠቁማል። ሰዎች የሚያረጁትና የሚሞቱት የመጀመሪያው ሰው አዳም በአምላክ ላይ በማመጹ ምክንያት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እንስሳትን ብንወስድ ለዘላለም እንዲኖሩ ተደርገው አልተፈጠሩም።—ዘፍጥረት 3:21፤ 4:4፤ 9:3, 4

የሰዎችና የእንስሳት አፈጣጠር የተለያየ ነው። መላእክት ከሰው ልጆች የላቀ የሕይወት ዓይነት እንዳላቸው ሁሉ ሰዎችም ከእንስሳት የላቀ የሕይወት ዓይነት አላቸው። (ዕብራውያን 2:7) ከእንስሳት በተቃራኒ ሰዎች የተፈጠሩት “በእግዚአብሔር መልክ” ነው። (ዘፍጥረት 1:27) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አዳምን “የእግዚአብሔር ልጅ” በማለት ይጠራዋል። (ሉቃስ 3:38) ስለዚህ ሰው እንዲያረጅና እንዲሞት እንዳልተፈጠረ የሚያሳይ አሳማኝ ምክንያት አለ። አምላክ አይሞትም እንዲሁም ልጆቹን እንዲሞቱ አድርጎ አልፈጠራቸውም።—ዕንባቆም 1:12 NW፤ ሮሜ 8:20, 21

በፍጥረት መጀመሪያ አካባቢ የነበረውን ትውልድ፣ ታሪክ መመርመራችን አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ በተመለከተ ተጨማሪ ማስተዋል እንድናገኝ ያስችለናል። በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ሳያረጁ በመቶ ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖሩ ነበር። አዳም 930 ዓመታት ኖሯል። ከተወሰነ ትውልድ በኋላ የኖኅ ልጅ የነበረው ሴም 600 ዓመታት የኖረ ሲሆን የኖኅ የልጅ ልጅ የሆነው አርፋክስድ ደግሞ 438 ዓመታት ኖሯል። * (ዘፍጥረት 5:5፤ 11:10-13) ከዚያም በኋላ አብርሃም 175 ዓመታት መኖር ችሏል። (ዘፍጥረት 25:7) ኃጢአት የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ የሰው ልጅ ከፍጽምና በጣም እየራቀ በመምጣቱ ዕድሜውም አጭር ሊሆን ችሏል። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ መጀመሪያ ላይ የተፈጠረው ለዘላለም እንዲኖር ነበር። ‘ታዲያ አምላክ አሁንም ቢሆን የሰው ልጅ በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖር ይፈልጋል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳታችን የተገባ ነው።

ከእርጅና መገላገል

ይሖዋ አምላክ እርሱን ያልታዘዘ ማንኛውም ሰው ለሠራው ኃጢአት ሞት እንደ ደሞዝ እንደሚከፈለው ስለተናገረ የአዳም ልጆች ምንም ተስፋ ያላቸው አይመስሉም ነበር። (ዘፍጥረት 2:17) የሆነ ሆኖ ቅዱሳን ጽሑፎች ከእርጅና ነጻ እንድንወጣ አስፈላጊውን ዋጋ መክፈል የሚችል አንድ አካል እንዳለ በመናገር ተስፋ ይሰጡናል። እንዲህ ይላል:- “‘ቤዛ አግኝቼለታለሁና፣ ወደ ጒድጓድ እንዳይወርድ አድነው’ . . . ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል።” (ኢዮብ 33:24, 25፤ ኢሳይያስ 53:4, 12) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከእርጅና ነጻ መሆን እንድንችል ቤዛ እንደሚከፈልልን የሚገልጽ አስደሳች ተስፋ ይዟል!

ይህን ቤዛ መክፈል የሚችለው ማን ነው? ቤዛው በገንዘብ የሚተመን አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎችን አስመልክቶ ‘ለዘላለም እንዲኖር የሌላውን ሕይወት መቤዠት የሚችል ሰው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ወጆ የሚከፍልለት ማንም የለም’ ይላል። (መዝሙር 49:7-9) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ክርስቶስ ከገንዘብ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ነበረው። የአምላክ ልጅ እንደመሆኑ መጠን የአዳም ኃጢአት እንዳይተላለፍበት ጥበቃ ስለተደረገለት በምድር በነበረበት ወቅት ፍጹም የሆነ ሕይወት ነበረው። ኢየሱስ “ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት” መምጣቱን ተናግሯል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ “እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ” ብሎ ነበር።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 10:10

የኢየሱስ ስብከት ዋነኛ ጭብጥ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ ያተኮረ ነበር። ታማኝ ተከታዩ የነበረው ጴጥሮስ በአንድ ወቅት “አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት ነግሮታል። (ዮሐንስ 6:68) መጽሐፍ ቅዱስ የዘላለም ሕይወት ሲል ምን ማለቱ ነበር?

ለዘላለም መኖር

የኢየሱስ ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሚያስተዳድርበት መንግሥት ውስጥ ትልቅ ቦታ በመያዝ በሰማይ የዘላለም ሕይወት አግኝተው የመኖር ተስፋ ከፊታቸው ተዘርግቶላቸው ነበር። (ሉቃስ 22:29፤ ዮሐንስ 14:3) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማም በተደጋጋሚ ጊዜያት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:5፤ 6:10፤ ሉቃስ 23:43) ስለዚህ የኢየሱስ ተአምራቶችም ሆኑ ስለ ዘላለም ሕይወት ያስተማራቸው ትምህርቶች አምላክ ከረጅም ጊዜ በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል” ሲል ያስነገረውን ትንቢት የሚያጠናክሩ ናቸው። (ኢሳይያስ 25:8) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ የሰው ልጅ ለጥቂት ዓመታት ብቻ በወጣትነት አሳልፎ ወደ እርጅና የሚያዘግምበት ሁኔታ ያከትማል።

አምላክ ባዘጋጀው አዲስ ዓለም ውስጥ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ፍጽምና ደረጃ ላይ ሲደርሱ ከእርጅና ሙሉ በሙሉ ይገላገላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 8:21) እስቲ አስበው! ሰዎች በጥበብም ሆነ በተሞክሮ እያደጉ ይሄዳሉ። ሆኖም ዘመናት እያለፉ ቢሄዱም እንኳ በወጣትነት ዘመናቸው የሚኖራቸው አካላዊ ጥንካሬ እየሟሸሸ አይሄድም። ያንን ጊዜ ለማየት ትበቃ ይሆን?

ለምን ያህል ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ?

ኢየሱስ በትንቢት እንደተናገረው በአምላክ የፍርድ ቀን በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥራቸው በጣም አናሳ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። (ማቴዎስ 24:21, 22) ኢየሱስ “ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:13, 14

የዘላለም ሕይወት አግኝተው ከሚደሰቱት ሰዎች መካከል መሆን ከፈለግህ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት መጣር አለብህ። ለዚህም የመጀመሪያው እርምጃ አምላክን ማወቅ ነው። ኢየሱስ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተን . . . ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:3) እርግጥ ነው አምላክን በደንብ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ሆኖም እንዲህ ማድረጉ የሚያስቆጭ አይደለም። በየዕለቱ ምግብ ለመመገብ ገንዘብ ያስፈልጋል፤ ገንዘቡን ለማግኘት ደግሞ ጥረት ማድረግ የግድ ነው። ኢየሱስ የአምላክን እውቀት ከምግብ ጋር በማመሳሰል “ለሚጠፋ እንጀራ አትሥሩ፤ ነገር ግን የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር ምግብ ሥሩ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:27) ታዲያ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ምንም ያህል ቢደከምለት የሚያስቆጭ ነው?—ማቴዎስ 16:26

ኢየሱስ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:16) ታዲያ ለምን ያህል ጊዜ መኖር ትፈልጋለህ? ይህ የተመካው አንተ ለአምላክ ፍቅር በምትሰጠው ምላሽ ላይ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 አንዳንዶች በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የሚገኙት ዓመታት ወራት ብቻ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አርፋክስድ በ35 ዓመቱ ሳላን እንደወለደ ይናገራል። እነዚህን ዓመታት እነርሱ እንደሚሉት 35 ወራት እንደሆኑ አድርገን ከወሰድናቸው አርፋክስድ ሦስት ዓመት ሳይሞላው የልጅ አባት ሆኖ ነበር ማለት ነው። ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው። በተጨማሪም የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች የፀሐይ አቆጣጠር ከጨረቃ አቆጣጠር የተለየ እንደሆነ ይጠቁማሉ።—ዘፍጥረት 1:14-16፤ 7:11

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰው 80 ዓመት ኖሮ ሲሞት፣ ያከናወናቸው ነገሮች ማድረግ ከሚችለው በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰዎች ከእንስሳት የላቀ የሕይወት ዓይነት አላቸው

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህች መኪና ገና ስትሠራም እንደዚህ የተጠረመሰች ነበረች?

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ቃል ሰዎች ‘ወደ ወጣትነት ዘመን’ እንደሚመለሱ ይናገራል