ሰላማዊ መሆን ይቻላል?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ሰላማዊ መሆን ይቻላል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ዝነኛ በሆነው የተራራ ስብከቱ ላይ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው” በማለት ተናግሯል። እንዲሁም “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:5, 9) ሰላማዊ መሆን ከሰው ጋር ካለመጋጨት ወይም የተረጋጉ ከመሆን የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ሰላማዊ የሆነ ሰው ወዳጃዊ ለመሆን ይጥራል፤ እንዲሁም ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል።
ከላይ የተጠቀሱት የኢየሱስ ቃላት በጊዜያችን ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ? አንዳንዶች በዚህ ዘመናዊ ዓለም ስኬት ማግኘት የሚፈልግ ሰው የሚያስፈራ፣ ቁጡና ዓመጸኛ መሆን አለበት ይላሉ። ቁጡ ሰው ሲያጋጥመን አጸፋውን መመለስ ጥበብ ይሆናል? ወይስ ሰላማዊ መሆን ይቻላል? “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ልናስብባቸው የሚገባው ለምን እንደሆነ የሚያሳዩ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።
▪ ሰላም ያለው ልብ ያስገኛል ምሳሌ 14:30 “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” ይላል። ቁጣና ከፍተኛ ጥላቻ በአንጎል ውስጥ ለሚፈጠር ደም መፍሰስ ወይም ደም መርጋት አሊያም ለልብ ድካም ሊያጋልጡ እንደሚችሉ በርካታ የሕክምና ሪፖርቶች ይጠቁማሉ። በቅርቡ አንድ የሕክምና መጽሔት የልብ በሽታ ስላለባቸው ሰዎች ሲናገር በቁጣ መገንፈልን ከመርዝ ጋር አነጻጽሮታል። አክሎም “በጣም መናደድ በጠና እንድንታመም ሊያደርገን ይችላል” ሲል ተናግሯል። ሰላማውያን ለመሆን የሚጥሩ ሰዎች ግን “ሰላም ያለው ልብ” ስለሚኖራቸው ይጠቀማሉ።
በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የቬትናም ቋንቋ ተናጋሪዎች ባሉበት አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ የሆኑት 61 ዓመት የሆናቸው ጂም ለዚህ ምሳሌ ይሆኑናል። እንዲህ በማለት ይናገራሉ:- “ለስድስት ዓመታት በውትድርና አገልግሎት ከማሳለፌም በላይ ለሦስት ጊዜያት በቬትናም የጦርነት ግዳጄን ስለተወጣሁ ዓመጽ፣ ቁጣና ጥላቻ ምን እንደሆኑ ከራሴ ተሞክሮ ለማየት ችያለሁ። የቀድሞው ሕይወቴ ስለሚያስጨንቀኝ እንቅልፍ ይነሳኝ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የመንፈስ ጭንቀት የያዘኝ ሲሆን፣ በጨጓራና በነርቭ ሕመም ምክንያት ጤና አጣሁ።” ታዲያ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ያገኙት እንዴት ነው? “መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በማጥናቴ ሕይወቴ ሊተርፍ ችሏል። አምላክ ሰላም የሰፈነበት አዲስ ዓለም ለማምጣት ያለውን ዓላማ ማወቄና ‘አዲሱን ሰው’ እንዴት መልበስ እንደምችል መማሬ ሰላም ያለው ልብ እንዳገኝ ረድቶኛል። በዚህም ምክንያት ጤንነቴ በጣም ተሻሽሏል” ሲሉ ተናግረዋል። (ኤፌሶን 4:22-24፤ ኢሳይያስ 65:17፤ ሚክያስ 4:1-4) ሌሎችም ከራሳቸው ተሞክሮ በመነሳት ሰላማዊ መሆን ስሜታዊ፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነትን ያሻሽላል ወደሚል መደምደሚያ ደርሰዋል።—ምሳሌ 15:13
▪ አስደሳች ግንኙነት ለመመሥረት ያስችላል ሰላማዊ ስንሆን ከሌሎች ጋር አስደሳች ግንኙነት ለመመሥረት ኤፌሶን 4:31) ብዙውን ጊዜ ቁጡ የሆኑ ሰዎችን በባሕርያቸው ምክንያት ሌሎች ስለሚሸሿቸው የሚተማመኑበት ጓደኛ አይኖራቸውም። ምሳሌ 15:18 “ግልፍተኛ ሰው ጠብ ያነሣሣል፤ ታጋሽ ሰው ግን ጠብን ያበርዳል” ይላል።
እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ቁጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋር . . . አስወግዱ” ይላል። (በኒው ዮርክ ሲቲ የሚኖረውና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው የ42 ዓመቱ አንዲ ያደገው ጠበኝነት በተስፋፋበት አካባቢ ነበር። እንዲህ ይላል:- “የቦክስ ሥልጠና ማድረግ የጀመርኩት የስምንት ዓመት ልጅ ሆኜ ነው። ተፎካካሪዎቼን እንደ ሰዎች አልቆጥራቸውም ነበር። ከዚህ ይልቅ ‘መምታት ወይም መመታት’ የሚል አቋም ነበረኝ። ብዙም ሳይቆይ ከወረበሎች ጋር ገጠምኩ። በየሰፈሩ በሚደረገው ድብድብ እንካፈል ነበር። ብዙ ጊዜ ጭንቅላቴ ላይ ሽጉጥ የተደገነብኝ ከመሆኑም ሌላ ጩቤም ተመዞብኝ ያውቃል። ከጓደኞቼ ጋር የነበረኝ ግንኙነት በአብዛኛው የማያስተማምንና በፍርሃት ላይ የተመሠረተ ነበር።”
አንዲ ሰላማዊ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው? እንዲህ ይላል:- “በአንድ ወቅት፣ በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተገኘሁ፤ እዚያም በመካከላቸው ያለውን ፍቅር ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደብኝም። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከእነዚህ ሰላም ወዳድ ሕዝቦች ጋር መሆኔ፣ ሰላም ያለው ልብ እንዲኖረኝና እያደር ደግሞ የቀድሞ አስተሳሰቤን ከነጭራሹ እንዳስወግድ ረድቶኛል። በመሆኑም ከብዙዎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ችያለሁ።”
▪ ለወደፊት ተስፋ ይሰጣል ከሁሉም በላይ ሰላማዊ መሆን ያለብን ለፈጣሪያችን ፈቃድ አክብሮት እንዳለን ለማሳየት ነው፤ እርሱም ፈቃዱን አሳውቆናል። የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ “ሰላምን ፈልጋት፤ ተከተላትም” የሚል ምክር ይሰጠናል። (መዝሙር 34:14) የአምላክን ሕልውና መቀበል፣ ከዚያም ሕይወት ሰጪ የሆነውን ትምህርት መማርና መታዘዝ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና ለመመሥረት ያስችለናል። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና ስንመሠርት “የእግዚአብሔር[ን] ሰላም” እናገኛለን። ሕይወት የሚያመጣቸው የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ ይህ ሰላም የበለጠ ኃይል አለው።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
ከዚህም በተጨማሪ ሰላማውያን በመሆን፣ ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደምንፈልግ ለይሖዋ ማሳየት እንችላለን። አምላክ በሰጠን ተስፋ መሠረት ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ከእርሱ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተን መኖር እንደምንችል አሁን እናሳያለን። ክፉዎች ሲወገዱና ኢየሱስ እንዳለው የዋሆች ‘ምድርን ሲወርሱ’ ማየት እንችላለን። ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው!—መዝሙር 37:10, 11፤ ምሳሌ 2:20-22
አዎን፣ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ያላቸውን ጠቀሜታ በግልጽ መመልከት እንችላለን። ሰላም ያለው ልብ እንድናገኝ፣ አስደሳች ግንኙነት እንድንመሠርትና ለወደፊት ደግሞ ጠንካራ ተስፋ እንዲኖረን ያደርጋል። “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” የሚለውን ምክር በተግባር ለማዋል የተቻለንን ሁሉ የምናደርግ ከሆነ ከላይ ያሉትን በረከቶች ልናገኝ እንችላለን።—ሮሜ 12:18
[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ጤንነቴ በጣም ተሻሽሏል።”—ጂም
[በገጽ 29 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
“ከብዙዎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ችያለሁ።”—አንዲ