በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሴት ልጃችሁ ስለ ወር አበባ በቅድሚያ አውቃ እንድትዘጋጅ መርዳት

ሴት ልጃችሁ ስለ ወር አበባ በቅድሚያ አውቃ እንድትዘጋጅ መርዳት

ሴት ልጃችሁ ስለ ወር አበባ በቅድሚያ አውቃ እንድትዘጋጅ መርዳት

ልጃገረዶች ለአቅመ ሔዋን የሚደርሱበት ዕድሜ ብዙ ለውጦች የሚካሄዱበት ጊዜ ነው። ልጃገረዶች በዚህ የእድገት ወቅት ከሚያጋጥሟቸው ለውጦች መካከል ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው የወር አበባ መጀመር ነው።

ልጃገረዶች የወር አበባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ ሊጨነቁ እንዲሁም የተዘበራረቀ ስሜት ሊኖራቸው ይችላል። ለአቅመ ሔዋን ከመድረስ ጋር ተያይዘው እንደሚከሰቱት ሌሎች ለውጦች ሁሉ የወር አበባ መጀመርም ግራ የሚያጋባ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በርካታ ልጃገረዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባቸው ሲመጣ ፍርሃትና ጭንቀት የሚሰማቸው አንድም ትክክለኛ እውቀት ስለሌላቸው፣ አሊያም ደግሞ ምንም ስለማያውቁ ነው።

ስለ ወር አበባ ቀደም ብለው ያወቁ ልጃገረዶች ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባቸው ሲመጣ እምብዛም ጭንቀትና ግራ መጋባት አይሰማቸውም። ይሁን እንጂ ብዙ ልጃገረዶች ስለ ጉዳዩ በቅድሚያ አውቀው እንደማይዘጋጁ ጥናቶች ያሳያሉ። ከ23 አገሮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተካተቱበት አንድ ጥናት ላይ ለጥያቄ ከቀረቡት ሴት ልጆች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የወር አበባቸው ከመጀመሩ በፊት ስለ ጉዳዩ ምንም ሰምተው እንደማያውቁ ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የወር አበባቸው ሲመጣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም ነበር።

የወር አበባቸው ስለጀመረበት ጊዜ በጣም አጥላልተው ከተናገሩት ሴቶች መካከል አንዳንዶቹ ከዚያ በፊት ስለዚህ ወርሐዊ ዑደት ምንም ትምህርት ያላገኙ ናቸው። በአንድ ጥናት ላይ የተሳተፉት ሴቶች የወር አበባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ “በፍርሃት ራድኩ፤” “አስደንጋጭ ገጠመኝ ነበር፤” “አፍሬ ነበር” እና “በጣም ፈርቼ ነበር” ብለዋል።

ብዙውን ጊዜ ደም የሚፈሰው ሕመም ወይም ቁስል ሲኖር በመሆኑ በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች ደም ሲያዩ ይፈራሉ። በመሆኑም ልጃገረዶች በቅድሚያ ተገቢ ማብራሪያ ካልተሰጣቸውና ዝግጅት ካላደረጉ፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው አስተሳሰብ ወይም መሠረተ ቢስ በሆነ እምነት አሊያም ባለማወቅ የተነሳ የወር አበባን ከበሽታና ከቁስል ጋር አያይዘው ቢያዩት ወይም ደግሞ እንደሚያሳፍር ነገር ቢቆጥሩት ምንም አያስገርምም።

ሴት ልጃችሁ፣ የወር አበባ መፍሰስ በሁሉም ጤነኛ ልጃገረዶች ላይ የሚደርስ የተለመደ ነገር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋታል። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን በዚህ ምክንያት የሚያጋጥማትን ማንኛውም ዓይነት ጭንቀት ወይም ፍርሃት እንድታስወግድ ልትረዷት ትችላላችሁ። ግን እንዴት?

ወላጆች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ

ስለ ወር አበባ እውቀት የሚገኝባቸው ብዙ ምንጮች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የትምህርት ቤት መምህራን፣ የጤና ባለሞያዎች፣ ጽሑፎች እንዲሁም ትምህርት ሰጪ ፊልሞች ይገኙበታል። ብዙ ወላጆች እነዚህ ምንጮች ብዙውን ጊዜ ስለ ወር አበባ ተፈጥሯዊ ዑደትና በዚህ ጊዜ ሊኖር ስለሚገባው የንጽሕና አጠባበቅ በጣም ጠቃሚ እውቀት እንደሚሰጡ ተገንዝበዋል። ያም ሆኖ ልጃገረዶች እነዚህ ምንጮች ያልዳሰሷቸው ጥያቄዎችና ችግሮች ይኖሯቸው ይሆናል። የወር አበባቸው ሲመጣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ቢያውቁ እንኳ ከወር አበባ መምጣት ጋር ተያይዘው የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ስሜቶች እንዴት መቋቋም እንዳለባቸው በትክክል አያውቁም።

ሴት አያቶች፣ ታላላቅ እህቶች፣ በተለይም ደግሞ እናቶች ልጃገረዶቹ የሚያስፈልጋቸውን እንዲሁም ከሌላ ምንጭ የማያገኙትን ተጨማሪ እውቀትና ስሜታዊ ድጋፍ ሊሰጧቸው ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ ልጃገረዶች ስለ ወር አበባ ከማንም በላይ ጥሩ የእውቀት ምንጭ አድርገው የሚመለከቱት እናቶቻቸውን ነው።

ስለ አባቶችስ ምን ለማለት ይቻላል? ብዙ ልጃገረዶች ለአባቶቻቸው ስለ ወር አበባ መናገር ያሳፍራቸዋል። አንዳንዶቹ ልጃገረዶች በተዘዋዋሪም ቢሆን አባቶቻቸው ድጋፍ እንዲሰጧቸውና ችግራቸውን እንዲረዱላቸው የሚፈልጉ ሲሆን ሌሎቹ ግን አባቶቻቸው በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ባይገቡባቸው ይመርጣሉ።

ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት በብዙ አገሮች በነጠላ አባቶች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥራቸው ጨምሯል። * በመሆኑም እያደር ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ አባቶች ሴት ልጆቻቸውን ስለ ወር አበባ ማስተማርን መልመድ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ አባቶች ስለ ወር አበባና ሴት ልጆቻቸው ስለሚያጋጥሟቸው ሌሎች አካላዊም ሆኑ ስሜታዊ ለውጦች መሠረታዊ እውቀት ሊኖራቸው ያስፈልጋል። አባቶች በዚህ ረገድ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክርና እርዳታ ለማግኘት እናቶቸውን ወይም እህቶቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ።

ውይይቱ መጀመር ያለበት መቼ ነው?

እንደ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ደቡብ ኮሪያና አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ ክፍሎች ባሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮች ውስጥ የወር አበባ የሚጀምርበት አማካይ ዕድሜ በ12 እና በ13 ዓመት መካከል ያለው ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ገና በ8 ዓመት ወይም በጣም ዘግይቶ በ16 ወይም በ17 ዓመት ሊጀምር ይችላል። በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮች አንጻር ሲታይ በአንዳንድ የአፍሪካና የእስያ አገሮች የወር አበባ የሚጀምርበት አማካይ ዕድሜ ከፍ ያለ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በናይጄሪያ አማካዩ ዕድሜ 15 ዓመት ነው። የወር አበባ በሚጀምርበት ዕድሜ ላይ ልዩነት የሚያመጡ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከእነዚህም መካከል የዘር ውርስ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የአመጋገብ ሁኔታ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ የሚኖሩበት ቦታ ከፍታና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ያም ሆነ ይህ ሴት ልጃችሁ የወር አበባ ማየት ከመጀመሯ በፊት ከእሷ ጋር ስለ ጉዳዩ መነጋገር ብትጀምሩ የተሻለ ነው። ለዚህም ሲባል አካላዊ ለውጦችንና የወር አበባን የሚመለከቱ ጭውውቶችን፣ ቀደም ብላችሁ ምናልባትም ሴት ልጃችሁ 8 ዓመት ገደማ ሲሆናት ልትጀምሩ ትችላላችሁ። እንዲህ ዓይነቱን ጭውውት ለመጀመር 8 ዓመት በጣም እንደፈጠነ ይሰማችሁ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሴት ልጃችሁ ከስምንት እስከ አሥር ዓመት ባለው ዕድሜ ላይ ስትሆን የተለያዩ ሆርሞኖች በሰውነቷ ውስጥ ስለሚጨምሩ ውስጣዊ አካሏ ማደግ ጀምሮ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ እንደ ጡት ማጎጥጎጥና በሰውነቷ ላይ ተጨማሪ ፀጉር እንደ ማብቀል የመሳሰሉትን ለአቅመ ሔዋን ከመድረስ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ውጫዊ የሆኑ አካላዊ ለውጦች ልትመለከቱ ትችላላችሁ። አብዛኞቹ ልጃገረዶች የወር አበባ ማየት ሊጀምሩ አካባቢ በቁመትና በክብደት ፈጣን ለውጥ ያሳያሉ።

ስለ ጉዳዩ በምን መንገድ ልታወያዩአቸው ትችላላችሁ?

የወር አበባ ወደሚጀምርበት ዕድሜ የተቃረቡ ልጃገረዶች ብዙውን ጊዜ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ይጓጓሉ። ምናልባት በትምህርት ቤታቸው የሚማሩ ሌሎች ልጃገረዶች ስለ ወር አበባ ሲወያዩ ሰምተው ይሆናል። ማወቅ የሚፈልጓቸው ነገሮች ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ምን ብለው እንደሚጠይቁ ይቸግራቸው ይሆናል። ስለ ጉዳዩ አንስቶ ማውራት ሊያሳፍራቸው ይችላል።

ለወላጆችም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እናቶች፣ ልጆቻቸው ስለ ወር አበባ እንዲያውቁ በመርዳት ረገድ ቀዳሚውን ቦታ ቢይዙም እነሱም ቢሆኑ ስለዚህ ጉዳይ ለማስተማር ብቃት እንደሌላቸው ሊሰማቸውና ሊያፍሩ ይችላሉ። አንቺም እናት እንደመሆንሽ የሚሰማሽ ነገር ከዚህ የተለየ ላይሆን ይችላል። ታዲያ ስለ ወር አበባ መጀመርና በአጠቃላይም ስለዚህ ወርሐዊ ዑደት ከሴት ልጅሽ ጋር ለመወያየት ምን ብለሽ ብትጀምሪ ይሻላል?

የወር አበባ ወደሚጀምርበት ዕድሜ ቢቃረቡም ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ያልገቡ ልጃገረዶች ያልተወሳሰበና ግልጽ የሆነ ሐሳብ ቢሰጣቸው በቀላሉ ሊረዱት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የወር አበባ በየስንት ጊዜው እንደሚመጣ፣ ሲመጣ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ወይም ደግሞ ምን ያህል ደም እንደሚፈሳቸው መግለጽ ይቻላል። በመሆኑም ለሴት ልጅሽ ስለ ወር አበባ ትምህርት መስጠት ስትጀምሪ የወር አበባ ሲመጣ ማድረግ በሚኖርባት ይበልጥ አስፈላጊና ተግባራዊ ነገር ላይ ትኩረት ብታደርጊ የተሻለ ነው። በተጨማሪም “የወር አበባ ሲጀምር ምን ዓይነት ስሜት ይኖራል?” ወይም ደግሞ “በዚህ ጊዜ ምን መጠበቅ ይኖርብኛል?” እንደሚሉት ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ሊያስፈልግሽ ይችላል።

ቆየት ብሎም ስለ ወር አበባ ተፈጥሯዊ ዑደት ዝርዝር ጉዳዮችን ለመወያየት ትፈልጊ ይሆናል። በአብዛኛው በዚህ ጉዳይ ላይ ትምህርት ለመስጠት የሚረዱሽን ነገሮች ከጤና ተቋማት ወይም ደግሞ ከመጻሕፍት ቤቶችና መደብሮች ልታገኚ ትችያለሽ። እንደነዚህ ያሉት የማመሳከሪያ ጽሑፎች ስለ ዝርዝር ጉዳዮች ማብራሪያ ለመስጠት ሊጠቅሙ ይችላሉ። አንዳንድ ልጃገረዶች እነዚህን መጻሕፍት ራሳቸው ቢያነቡ ይመርጡ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ ከእናቶቻቸው ጋር ሆነው ማንበብ ላያሸማቅቃቸው ይችላል።

ጭውውቱን ለመጀመር ጸጥ ያለ ቦታ ምረጪ። ስለ ልጅሽ ማደግና ለአቅመ ሔዋን መድረስ በማንሳት ውይይቱን ቀለል ባሉ ጉዳዮች ጀምሪ። ምናልባትም “በቅርቡ ሁሉም ልጃገረዶች የሚያጋጥማቸው ተፈጥሯዊ ነገር አንቺም ያጋጥምሻል። ይህ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?” ልትያት ትችያለሽ። ወይም ደግሞ አንዲት እናት ቀጥሎ እንደቀረበው የሚመስል የግል አስተያየቷን በመስጠት ልትጀምር ትችላለች:- “በአንቺ ዕድሜ ሳለሁ የወር አበባ ሲመጣ ምን ሊያጋጥመኝ እንደሚችል አስብ ነበር። በትምህርት ቤት ከጓደኞቼ ጋር በዚህ ርዕስ ዙሪያ እናወራ ነበር። ጓደኞችሽ ስለዚህ ጉዳይ ሲያወሩ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?” በዚህ መንገድ ልጅሽ ስለ ወር አበባ ምን ያህል እንደምታውቅ ከተረዳሽ በኋላ በደንብ ያልገባት ነገር ካለ ሐቁን አስረጃት። ውይይቱን ስትጀምሪ ከልጅሽ ብዙ ምላሽ ላታገኚ እንደምትችይና አብዛኛውን ነገር አንቺው መናገር ሊኖርብሽ እንደሚችል ጠብቂ።

አንቺም ሴት እንደመሆንሽ መጠን የወር አበባሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመጣ ጭንቀትና ሥጋት አጋጥሞሽ ይሆናል፤ በዚህ ርዕስ ላይ ከልጅሽ ጋር ስትወያዪ የራስሽን ተሞክሮ ልትነግሪያት ትችያለሽ። አንቺ በዚያን ጊዜ ስለ የትኞቹ ነገሮች ማወቅ ነበረብሽ? ምንስ ለማወቅ ፈልገሽ ነበር? የጠቀመሽ ምን ዓይነት እውቀት ነበር? ከዚህ በመነሳት የወር አበባ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ስላለው ቦታ እንዲሁም አስቸጋሪ ስለሆኑት ጎኖቹ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራት ለማድረግ ጣሪ። ለምትጠይቅሽ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ዝግጁ ሁኚ።

ቀጣይነት ያለው ትምህርት

ስለ ወር አበባ የሚሰጠው ትምህርት በአንድ ጊዜ ውይይት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሂደት እንደሆነ ተደርጎ መታየት ይገባዋል። በአንድ ቀን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ተወያይታችሁ መጨረስ አያስፈልጋችሁም። ለአንዲት ታዳጊ ልጅ በአንድ ጊዜ ብዙ እውቀት ለመስጠት ብትሞክሪ መረዳት ከምትችለው በላይ ሊሆንባት ይችላል። ልጆች ነገሮችን የሚማሩት ቀስ በቀስ ነው። በተጨማሪም በተለያዩ ወቅቶች እየደጋገሙ ማስተማር ሊያስፈልግ ይችላል። ወጣት ልጃገረዶች እያደጉ ሲሄዱ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ለመረዳት ያላቸው ችሎታም ይጨምራል።

ሌላው ነገር ደግሞ ልጅሽ ስለ ወር አበባ ያላት አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚቀያየር መሆኑ ነው። ልጅሽ የወር አበባዋ እየደጋገመ ሲመጣ ተሞክሮ እያገኘች ስለምትሄድ የሚያሳስባት ነገርም ሆነ ጥያቄዋ ይቀየራል። ስለዚህ ለልጅሽ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሐሳብ ማካፈልና ለጥያቄዋም መልስ መስጠት ያስፈልግሻል። በመሆኑም ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሁም የልጅሽን ዕድሜና የመረዳት ችሎታ ያገናዘበ ሐሳብ በመስጠት ላይ ትኩረት አድርጊ።

በርዕሱ ላይ ውይይት ለመጀመር ቀዳሚ ሁኚ

ሴት ልጅሽ ስለዚህ ጉዳይ እንዲነሳባት እንደማትፈልግ ብታሳይስ? ስለ ግል ጉዳይዋ ለመነጋገር ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች። ወይም ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመነጋገርና ጥያቄ ለመጠየቅ ድፍረት እስክታገኝ ድረስ ጊዜ ያስፈልጋት ይሆናል። ምናልባትም ማወቅ የሚያስፈልጋትን ነገር ሁሉ ቀደም ብላ እንዳወቀች ልትናገር ትችላለች።

በዩናይትድ ስቴትስ የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑ ልጃገረዶች በተሳተፉበት አንድ ጥናት ላይ ከተሳታፊዎቹ ውስጥ አብዛኞቹ የወር አበባቸው ለሚጀምርበት ጊዜ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ እንደሚሰማቸው ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ጥያቄ ሲቀርብላቸው እውቀታቸው የተሟላ እንዳልሆነ እንዲሁም በተለያዩ ባሕላዊ አስተሳሰቦችና መሠረተ ቢስ እምነቶች ላይ የተመሠረቱ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንደ እውነት አድርገው እንደተቀበሉ ግልጽ ሆኗል። ስለዚህ ልጅሽ የወር አበባዋ ሲጀምር ምን ማድረግ እንዳለባት ጠንቅቃ እንደምታውቅ ብትናገርም ስለዚህ ጉዳይ መነጋገራችሁ ይጠቅማታል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ሆነሽ አጭር ውይይት መጀመርና ውይይቱ እንዲቀጥል ማድረግ ያለብሽ አንቺ ነሽ። በእርግጥም በዚህ ርዕስ ላይ ከሴት ልጅሽ ጋር መነጋገር የወላጅነት ኃላፊነትሽ ነው። ይህን ርዕስ በማንሳት ስታወዪያት እርዳታሽ እንደሚያስፈልጋት አፍ አውጥታ ባትናገርም እንኳ እርዳታሽ ያስፈልጋታል። ውይይቱን ምን ብለሽ እንደምትቀጥይ ግራ ቢገባሽና ብቃት እንደሌለሽ ቢሰማሽም ተስፋ አትቁረጪ፤ እንዲሁም ትዕግሥተኛ ሁኚ። ከጊዜ በኋላ ሴት ልጅሽ የአንቺ ጥረት ምን ያህል እንደጠቀማት መገንዘቧ አይቀርም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.12 በ2003 ጃፓን ውስጥ በነጠላ አባቶች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር ከምንጊዜውም ይበልጥ ከፍ ብሎ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ በነጠላ ወላጅ ከሚተዳደሩ 6 ቤተሰቦች ውስጥ አንዱ በአባት ብቻ የሚተዳደር ነው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ልጃችሁ የወር አበባ ማየት ከመጀመሯ አስቀድሞ ጉዳዩን አንስቶ መወያየቱ የተሻለ ነው

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከሴት ልጅሽ ጋር ስለ ወር አበባ መነጋገር የምትችይባቸው መንገዶች

ስለ ጉዳዩ ቀደም ብላ የምታውቀው ነገር ካለ ጠይቀሽ ተረጂ። በትክክል ያልተረዳችው ነገር ካለ አስረጃት። አንቺም ሆንሽ ልጅሽ በዚህ ርዕስ ላይ ትክክለኛ እውቀት እንዳላችሁ አረጋግጪ።

ተሞክሮሽን ንገሪያት። የወር አበባሽ በጀመረበት ወቅት የነበረሽን ስሜት በመንገር ለልጅሽ በጣም የሚያስፈልጋትን ስሜታዊ ድጋፍ ልትሰጫት ትችያለሽ።

ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሐሳብ አካፍያት። ወጣት ልጃገረዶች ከሚጠይቋቸው የተለመዱ ጥያቄዎች መካከል “የወር አበባዬ ትምህርት ቤት እያለሁ ቢመጣብኝ ምን አደርጋለሁ?” “በወር አበባዬ ጊዜ ምን ዓይነት የንጽሕና መጠበቂያ መጠቀም ይኖርብኛል?” “አጠቃቀሙስ እንዴት ነው?” የሚሉት ይገኙበታል።

ሐቁን ግልጽ በሆነ መንገድ ንገሪያት። ለልጅሽ የምታስተምሪያት ነገር ዕድሜዋንና የመረዳት አቅሟን ያገናዘበ ይሁን።

ቀጣይነት ያለው ትምህርት ስጫት። ልጅሽ የወር አበባዋ የሚጀምርበት ዕድሜ ላይ ከመድረሷ በፊት ስለ ጉዳዩ መነጋገር ጀምሪ። እንዲሁም የወር አበባዋ መምጣት ከጀመረ በኋላም እንደ አስፈላጊነቱ ስለ ጉዳዩ መነጋገራችሁን ቀጥሉ።

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የልጅሽን ስሜት ተረጂላት። ምናልባት ስለ ግል ጉዳይዋ ለመነጋገር ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች