እርጅናን ማስቀረት ትችላለህ?
እርጅናን ማስቀረት ትችላለህ?
“ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ . . . ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።”—መዝሙር 90:10 የ1980 ትርጉም
ምንጊዜም ወጣት እንደሆንክ ብትኖር ምን እንደሚሰማህ እስቲ አስብ። የተሟላ ጤንነትና ፈጣን አእምሮ ይዘህ ለዘላለም ስትኖር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ወደፊት እንዲህ ያለ አስደሳች ሕይወት ይመጣል ቢባል የሕልም እንጀራ መስሎ ይታይሃል? እስቲ ደግሞ የሚከተለውን አስገራሚ እውነታ ተመልከት:- አንዳንድ የፓሮት (የበቀቀን) ዝርያዎች መቶ ዓመት ሲኖሩ አይጦች ግን ያላቸው ዕድሜ ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ነው። በመሆኑም እንዲህ ያለው የዕድሜ ልዩነት አንዳንድ የሥነ ሕይወት ሊቃውንት ‘እርጅና መንስኤ አለው፤ መንስኤ ካለው ደግሞ መፍትሔም ይኖረዋል’ ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል።
እርጅናን በተሳካ መንገድ ለመከላከል የሚያስችል መድኃኒት ለማግኘት የሚደረገው ጥረት የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎችን ትኩረት ስቧል። በተጨማሪም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተወለዱና አሁን ዕድሜያቸው 60ዎቹ ውስጥ የገባ ሰዎች እርጅናን ለማዘግየት የሚቻልበትን መፍትሔ የማግኘቱ ጉዳይ በጣም እያሳሰባቸው ነው።
በጄኔቲክስ፣ በሞለኪዩላር ባዮሎጂ፣ በእንስሳት ሕይወት ጥናት እንዲሁም በጄሮንቶሎጂ (ስለ እርጅና የሚያጠና ሳይንስ) መስክ የተሰማሩ በርካታ ተመራማሪዎች ስለ እርጅና ለሚደረገው ጥናት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡ ነው። ስቲቨን ኦስታድ ኋይ ዊ ኤጅ (የምናረጅበት ምክንያት) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “በአሁኑ ጊዜ ስለ እርጅና የሚያጠኑ ምሁራን ሲሰበሰቡ የተወሰነ የደስታ ስሜት ይነበብባቸዋል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “የእርጅናን መሠረታዊ ምክንያትና ሂደቱን ወደ መረዳት እየተቃረብን ነው” ብለዋል።
እርጅናን በሚመለከት የተለያዩ አመለካከቶች ይሰነዘራሉ። አንደኛው አመለካከት ሴሎች እንደ አላቂ ዕቃ በጊዜ ሂደት ያልቃሉ የሚለው ሲሆን ሌላው ደግሞ ሴሎች የተወሰነ ደረጃ ላይ ሲደርሱ እንዲያረጁ የሚያደርግ ፕሮግራም ተቀርጾባቸዋል የሚል ነው። ከዚህም በላይ እርጅና የሚከሰተው በሁለቱም ምክንያቶች የተነሳ እንደሆነ የሚናገሩም አሉ። የእርጅናን መንስኤም ሆነ ሂደት ምን ያህል መረዳት ይቻላል? እርጅናን ለማስቀረት የሚያስችል ፍቱን መድኃኒት ይኖራል ብለን እንድንጠብቅ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አለ?
[በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኝ ቻርት/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሚኖሩበት ዘመን
ንብ
90 ቀናት
↓
አይጥ
3 ዓመት
↓
ውሻ
15 ዓመት
↓
ዝንጀሮ
30 ዓመት
↓
አርጃኖ
50 ዓመት
↓
ዝሆን
70 ዓመት
↓
ሰው
80 ዓመት
↓
በቀቀን
100 ዓመት
↓
ኤሊ
150 ዓመት
↓
የሴኮያ ዛፍ
3,000 ዓመት
↓
ብሪስልኮን የተባለው የጥድ ዝርያ
4,700 ዓመት
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዳንድ የበቀቀን ዝርያዎች 100 ዓመት ሲኖሩ ሰዎች ግን 80 ዓመት ገደማ ብቻ ይኖራሉ። ተመራማሪዎች “የእርጅና መንስኤ ምንድን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ