በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ከአንባቢዎቻችን

ሥራ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? (ጥቅምት 2005) ዝቅተኛ ነው ተብሎ የሚታሰበውን ጨምሮ እያንዳንዱን የሥራ ዕድል ስለ መከታተል ለሰጣችሁት ሐሳብ አመሰግናለሁ። በቅርቡ፣ ለክርስቲያናዊ አገልግሎቴ ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንድችል የሙሉ ቀን ሥራዬን ትቼ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ ለመሥራት ፈልጌ ነበር። ይሁን እንጂ ሥራ በጣም አማርጥ ነበር። በኋላም አንድ ሥራ አገኘሁና መሥራት ጀመርኩ። ሥራው ዝቅተኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ቢሆንም እንኳ እርካታ ለማግኘት እየጣርኩ ነው። ሌላው ቢቀር ወደ ቤት ስመለስ አእምሮዬ ስለማይደክም የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን በትኩረት ማከናወን እችላለሁ።

ኤም. አይ.፣ ጃፓን

ሜይ ዴይለአንተ ምን ትርጉም አለው? (ሐምሌ 2005) የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ የተቃረብኩ ሲሆን በትምህርት ቤታችን በየዓመቱ የሜይ ዴይ በዓል ይከበራል። የሁለተኛ ደረጃና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሙሉ ከበዓሉ በፊት የሚደረገውን የልምምድ ፕሮግራም እንዲመለከቱ ይጋበዛሉ። ከዚህ ቀደም በልምምዱ ላይ እገኝ ነበር፤ እህቴ ግን በበዓሉ ላይ የሚከናወነው ሥነ ሥርዓት ሕሊናዋን ይረብሻት ነበር። ይህ ርዕስ እሷ ትክክል እንደነበረች እንድገነዘብ ረድቶኛል! በጣም አመሰግናችኋለሁ። ጽሑፉ የወጣው በሚያስፈልገኝ ጊዜ ነው!

ኬ. ሲ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የተጫዋችነት ባሕርይን በማዳበር ሕመምን መቋቋም (ሰኔ 2005) ላለፉት ስድስት ዓመታት ከማኅፀን ካንሰር ጋር ስታገል ቆይቻለሁ፤ ለበርካታ ጊዜያት ቀዶ ሕክምና የተደረገልኝ ከመሆኑም በላይ ኬሞቴራፒ የተባለውን ሕክምና ወስጃለሁ። እኔም እንደ ኮንቺ ጉባኤዬን ለመደገፍና ትልልቅ ስብሰባዎችን ጨምሮ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የቻልኩትን ያህል እጥራለሁ። ካንሰር ከባድ በሽታ ነው፤ ስለዚህ እኛ የካንሰር በሽተኞች በየጊዜው ዶክተሮች የሚነግሩንን አሳዛኝ ዜና እንዴት አድርገን መቀበል እንደምንችል ኮንቺ ለሰጠችው አስተያየት አመስጋኝ ነኝ። የኮንቺ ተሞክሮ በጣም አበረታቶኛል!

ቢ. ኤፍ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ሉፐስ በተባለ በሽታ የምሠቃይ ሲሆን ለተወሰነ ጊዜ የመርሳት ችግር አጋጥሞኝ ነበር። ከበሽታዬ እያገገምኩ ስመጣ ተጫዋች ለመሆን ጥረት አደርጌያለሁ። ሰሞኑን ጨጓራዬን ለመታከም ሆስፒታል ስገባም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ጥሬያለሁ። “መታመም ቀልድ አይደለም፤ ሆኖም ምንጊዜም ተጫዋች ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባችሁ” በሚለው የኮንቺ አነጋገር እስማማለሁ።

ኤም. ኤ.፣ ቬኔዙዌላ

ከዓለም አካባቢ (ኅዳር 2005) አስተያየት መስጠት የፈለግኩት “የቪታሚን ኪኒኖችና ካንሰር” ስለሚለው ርዕስ ሲሆን ብዙ የምግብ ጥናት ባለሙያዎች በተጠቀሰው የዶክተር ሱሊቫን አመለካከት እንደማይስማሙ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። ሥፍር ቁጥር በሌላቸው ሳይንሳዊ ጽሑፎች ላይ የሚወጡ ሪፖርቶችም ሆኑ በጣም ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የጠቀሳችኋቸው ኪኒኖች አንዳንድ የካንሰር ዓይነቶችን ለመከላከልና ለማከም እንደሚረዱ ተረጋግጧል። እንዲህ ዓይነት ለአንድ ወገን የሚያደላ መረጃ ማውጣት የንቁ! መጽሔትን ገለልተኛ አቋም አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ይሰማኛል።

ኤ. ቢ.፣ ኔዘርላንድ

“የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- እኚህ አንባቢ እንደገለጹት በመጽሔታችን ላይ የተዘረዘሩት ኪኒኖች ለካንሰር በሽተኞች በተወሰነ መጠን ጥሩ ውጤት እንዳስገኙ ጥናቶች ይጠቁማሉ። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ለተፈጠረው አለመግባባት እናዝናለን። “ንቁ!” የሕክምና ጉዳዮችን በተመለከተ ገለልተኛ አቋም ያለው መጽሔት ነው። አንባቢዎቻችንን ያሳስባቸዋል የምንለውን ከጤና ጋር የተያያዘ መረጃ አቀረብን ማለት ሐሳቡን እንደግፋለን ማለት አይደለም። እንዲሁም ብዙ ጊዜ እንደሚገጥመን፣ በአንድ የጥናት መስክ የተሠማሩ ባለሙያ የተናገሩትን አሊያም ከአንድ ጽሑፍ ላይ ያገኘነውን ሐሳብ ስንጠቅስ ሌሎች ጽሑፎችም ሆኑ ባለሙያዎች የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል እናውቃለን። ጤንነትን በተመለከተ በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ ማድረግ ለአንባቢዎቻችን የተተወ ጉዳይ ነው።