ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በብራዚል ከ1997 እስከ 2004 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የሰውነትን ክብደት ለመቀነስ ብሎ አምፊታሚን የሚባለውን የምግብ ፍላጎት የሚያሳጣ ኃይል ሰጪ መድኃኒት የመጠቀም ልማድ 500 በመቶ ከፍ ብሏል።—ፎልሃ ኦንላይን፣ ብራዚል
▪ የአውሮፕላን አብራሪዎች አዘውትረው ለጠፈር ጨረሮች ስለሚጋለጡ ሳይሆን አይቀርም፣ ካታራክት በሚባለው የዓይን ሕመም የመጠቃት አጋጣሚያቸው ከሌሎች ሰዎች በሦስት እጥፍ ሊበልጥ ይችላል።—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ በሚቀጥለው አሥር ዓመት ውስጥ ከ1.27 ቢሊዮን ከሚበልጡት በእስያ የሚገኙ ልጆች መካከል ግማሾቹ እንደ ንጹሕ ውኃ፣ ምግብ፣ ሕክምና፣ ትምህርትና መጠለያ ያሉትን መሠረታዊ ነገሮች አያገኙም።—ፕላን ኤዥያ ሪጅናል ኦፊስ፣ ታይላንድ
▪ በአጫሾች አካባቢ የሚገኙ ሰዎች ‘ማንም ሰው ከሚገምተው በላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስባቸዋል።’ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮሎራዶ ግዛት በምትገኘው በፖዌብሎ ከተማ፣ በቢሮና በምግብ ቤቶች እንዲሁም በሌሎች ሕንጻዎች ውስጥ ማጨስ ከተከለከለ በኋላ ባለፉት 18 ወራት ውስጥ ከነዋሪዎቹ መካከል የልብ ሕመም ያጋጠማቸው ሰዎች ቁጥር 27 በመቶ ቀንሷል።—ታይም፣ ዩናይትድ ስቴትስ
በስፔን የጋብቻ መፍረስ እያሻቀበ ነው
በ2000፣ በስፔን ከሁለት ጋብቻዎች አንዱ በመለያየትና በፍቺ ይፈርስ ነበር። በ2004 ግን በዚህ አገር ከተፈጸሙት ሦስት ጋብቻዎች ውስጥ ሁለቱ ፈርሰዋል። መፋታትን የሚፈቅደው ሕግ በ1981 ከጸደቀ ወዲህ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሆኑ ልጆች ወላጆቻቸው ሲለያዩ ተመልክተዋል። ለጋብቻ መፍረስ መጨመር መንስኤው ምንድን ነው? ፐትሪሺያ ማርቲኔዝ የተባሉት የሥነ ልቦና ሐኪም እንደሚሉት ከሆነ “ለጋብቻ አለመጽናት መንስኤ ከሆኑት ነገሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱት የባሕል ልዩነት፣ የሃይማኖታዊና የሥነ ምግባራዊ መሥፈርቶች መጥፋት፣ ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም መግባታቸውና ባሎች በቤት ውስጥ ሥራ ሚስቶቻቸውን ለማገዝ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ይገኙበታል።”
ከመጠን ያለፈ ውፍረት በቻይና
ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ እንደሚናገረው ቻይና ውስጥ “በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአደገኛ ሁኔታ ክብደታቸው የጨመረ 200 ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ።” በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦች የሚሸጡባቸው መደብሮች “በብዙ ከተሞች ውስጥ እንደ አሸን ፈልተዋል፤ ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ብዙም አካላዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሲሆን ከቀድሞው የበለጠ በመኪና ይጓዛሉ። ከዚህም በላይ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ በኮምፒውተር በመጠቀምና የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ቁጭ ብለው የሚያሳልፉት ጊዜ ጨምሯል።” ከልክ በላይ የሚወፍሩ ልጆች ቁጥር በየዓመቱ 8 በመቶ እየጨመረ ሲሆን በሻንግሃይ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ከሆኑት ልጆች መካከል 15 በመቶዎቹ ከመጠን በላይ ወፍራም ናቸው።
ወንዙ በአደገኛ መድኃኒቶችና ዕፆች የሚጠቀሙ ሰዎች መበራከታቸውን አመለከተ
ኢንቫይሮሜንታል ሄልዝ በተሰኘው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንደዘገበው በጣሊያን ፖ በሚባል ወንዝ አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ ባለ ሥልጣናቱ ከገመቱት በላይ የኮኬይን ተጠቃሚ መሆኑን ከወንዙ የተወሰደው ናሙና አመልክቷል። የኮኬይን ተጠቃሚዎች ቤንዞይሌክጎኒን የሚባል የኮኬይን ክፍል የሆነ ንጥረ ነገር ከሽንታቸው ጋር ይወጣል። ይህ ንጥረ ነገር በሽንት ውስጥ መገኘቱ አብዛኛውን ጊዜ ግለሰቡ ኮኬይን ለመውሰዱ እንደ ማስረጃ ሆኖ ለፍርድ ለማቅረብ ያገለግላል። ከፍሳሽ ቆሻሻ ጋር ወንዙ ውስጥ የገባው ኬሚካል የአካባቢው ሕዝብ በየቀኑ 4 ኪሎ ግራም የሚሆን ኮኬይን እንደሚወስድ ያመለክታል፤ ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረው ግምታዊ አኃዝ 80 ጊዜ የሚበልጥ ነው።
ማትረፍ እየተቻለ የሚሞቱ ሕፃናት
“በዚህ ዓመት 11 ሚሊዮን የሚሆኑ አምስት ዓመት ያልሞላቸው ሕፃናት አብዛኛውን ጊዜ አስቀድሞ በመከላከል ሊድኑ በሚችሉ ሕመሞች ሳቢያ ይሞታሉ” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት የ2005 ሪፖርት ዘግቧል። ከእነዚህ መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት የሚሞቱት ጊዜያቸው ሳይደርስ በመወለድ፣ በቁስል ማመርቀዝ፣ በወሊድ ጊዜ በመታፈን፣ በታችኛው የመተንፈሻ አካሎች መታመም (በዋነኝነት የሳምባ ምች)፣ በተቅማጥ፣ በወባ፣ በኩፍኝ፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስና በመሳሰሉት አራስ ሕፃናትን በሚያጠቁ ከበድ ያሉ ሕመሞች ምክንያት ነው። “በእነዚህ ሕመሞች ሳቢያ ከሚሞቱት ሕፃናት አብዛኞቹን በአሁኑ ጊዜ በሚገኙ በቀላሉ የሚሰጡ፣ ርካሽና ውጤታማ የሆኑ የሕክምና ዘዴዎች ተጠቅሞ ማትረፍ ይቻላል” በማለት ሪፖርቱ ይናገራል። በተጨማሪም በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ሴቶች ከእርግዝና ወይም ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚሞቱ ሲሆን በአብዛኛው ይህ የሚሆነው “የሠለጠነ የጤና ባለሞያ እርዳታ ከማጣት” ነው።