በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐር—ተወዳዳሪ የሌለው ምርጥ ክር

ሐር—ተወዳዳሪ የሌለው ምርጥ ክር

ሐር—ተወዳዳሪ የሌለው ምርጥ ክር

ጃፓን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

የጃፓኑን ኪሞኖ፣ የሕንዱን ሳሪ እንዲሁም የኮሪያውን ሃንቦክ ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉትን የሚያማምሩ ልብሶች አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ልብሶች የሚዘጋጁት የክሮች ሁሉ ንጉሥ ተብሎ ከሚጠራው አብረቅራቂ የሐር ክር ነው። ከጥንቶቹ ንጉሣዊ ቤተሰቦች አንስቶ በዘመናችን እስካሉት ተራ ሰዎች ድረስ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች የሐር ጨርቅ ውበት ይማርካቸዋል። ይሁን እንጂ ሐር እንደዛሬው እንደልብ የማይገኝበት ዘመን ነበር።

በጥንት ዘመን የሐር ምርት በቻይና ብቻ የተወሰነ ነበር። በዘመኑ ከቻይናውያን ሌላ አመራረቱን የሚያውቅ አልነበረም፤ እንዲያውም የሐር ትልን ምስጢር ያወጣ ሰው አገር እንደከዳ ተቆጥሮ ሊገደል ይችል ነበር። ይህም የሐር ዋጋ ውድ እንዲሆን አድርጎታል። ለምሳሌ ያህል፣ በሮም ግዛት በሙሉ ሐር በጣም ውድ ነገር ነበር።

ከጊዜ በኋላ ፋርስ፣ ከቻይና የሚመጣውን ሐር በሙሉ በቁጥጥሯ ሥር አደረገችው። በዚህ ጊዜም ቢሆን ሐር ዋጋው ውድ ሆኖ የቀጠለ ሲሆን ከፋርስ ነጋዴዎች አልፎ ለመግዛት የተደረጉት ጥረቶችም አልተሳኩም። ከዚያም የባይዛንቲየሙ ንጉሠ ነገሥት ጀስቲንያን አንድ መላ ፈጠረ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ550 አካባቢ ምስጢራዊ ተልእኮ ያላቸው ሁለት መነኮሳትን ወደ ቻይና ላከ። እነሱም ከሁለት ዓመት በኋላ ሲመለሱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን ውድ ሀብት፣ ማለትም የሐር ትል ዕንቁላሎች፣ ውስጡ ክፍት በሆነው የቀርከሃ ከዘራቸው ውስጥ በድብቅ ይዘው ነበር። በዚህ ሁኔታ የሐር ትል ምስጢር ወጣ። ቻይናም ብቸኛዋ የሐር አምራች መሆኗ አከተመ።

ሐር የሚመረትበት ምስጢር

ሐር የሚሠሩት የሐር ትሎች (የሐር ትል ዝርያ ያላቸው አባ ጨጓሬዎች) ናቸው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐር ትል ዓይነቶች ያሉ ቢሆንም ጥራት ያለው ሐር የሚሠራው ዝርያ ሳይንሳዊ ስሙ ቦምቢክስ ሞሪ ይባላል። የሐር ጨርቅ ለማምረት ብዛት ያላቸው የዚህ ትል ዝርያዎች የሚያስፈልጉ ሲሆን ይህም የሐር ትል እርባታ እንዲቋቋም ምክንያት ሆኗል። ጉንማ በሚባለው የጃፓን ክፍለ ግዛት የሚኖረው የሾይቺ ካዋሃራዳ ቤተሰብ በዚያች አገር አድካሚ በሆነው የሐር ትል እርባታ ከተሰማሩት 2,000 ገደማ የሚሆኑ ቤተሰቦች አንዱ ነው። ይህ ሰው ለሐር ትል እርባታ ምቹ የሆነውን ባለ ሁለት ፎቅ ቤቱን የሠራው ከበታቹ ችምችም ብለው የበቀሉ የእንጆሪ ዝርያ የሆኑ ዛፎች ባሉበት አቀበት ላይ ነው (1)

እንስቷ የሐር ትል እያንዳንዳቸው የስፒል አናት የሚያህሉ 500 ያህል ዕንቁላሎች ትጥላለች (2)። ከ20 ቀናት ገደማ በኋላ ዕንቁላሎቹ ይፈለፈላሉ። ጥቃቅኖቹ የሐር ትሎች በልተው የማይጠግቡ ናቸው። ቀን ከሌት የእንጆሪ ዝርያ የሆነውን ዛፍ ቅጠሎች የሚበሉ ሲሆን ከዚህ ቅጠል በቀር ሌላ የሚበሉት ነገር የለም (3, 4)። የሐር ትሎቹ በተወለዱ በ18 ቀናት ውስጥ መጀመሪያ ከነበራቸው መጠን በ70 እጥፍ የሚያድጉ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ቆዳቸውን አራት ጊዜ ይቀይራሉ።

ሚስተር ካዋሃራዳ 120,000 የሚሆኑ የሐር ትሎች ያረባል። የሐር ትሎቹ ቅጠሎቹን በሚበሉበት ጊዜ የሚፈጠረው ድምፅ ኃይለኛ ዝናብ በቅጠሎች ላይ ሲያርፍ የሚያሰማውን ድምፅ ይመስላል። የሐር ትሉ ሲያድግ ክብደቱ መጀመሪያ የነበረውን 10,000 ጊዜ ያህል ይሆናል! በዚህ ወቅት የሐር ክር ለመፍተል ዝግጁ ነው።

ድምፅ አልባ ፈታዮች

የሐር ትል እድገቱን ሲጨርስ ገላው የሚያብረቀርቅ መልክ ይኖረዋል፤ ይህም መፍተል የሚጀምርበት ዕድሜ ላይ መድረሱን ያመለክታል። የሐር ትሎች ሲቁነጠነጡና ክራቸውን እየፈተሉ የሚያስቀምጡበት ቦታ ፍለጋ ሲወራጩ፣ በውስጡ አራት ማዕዘን የሆኑ በርካታ ትናንሽ ክፍሎች ባሉት ሣጥን መሳይ ነገር ውስጥ እነሱን ማስፈር የሚቻልበት ጊዜ ደርሷል ማለት ነው። የሐር ትሎቹ በዚህ ሣጥን መሳይ ነገር ውስጥ ሆነው ቀጭን ነጭ ክራቸውን በማውጣት (5) ሰውነታቸው ላይ መጠቅለል ይጀምራሉ።

በካዋሃራዳ የእርባታ ጣቢያ ያሉት 120,000 የሐር ትሎች በሙሉ በተመሳሳይ ጊዜ መፍተል ስለሚጀምሩ ካዋሃራዳ ሥራ በጣም የሚበዛበት በዚህ ወቅት ነው። በቤቱ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የተሠራ ቀዝቀዝ ያለና ነፋስ እንደ ልብ የሚያገኝ ቆጥ አለ፤ በዚህ ቆጥ ላይ በውስጣቸው ትናንሽ ክፍሎች ያሏቸውና ለሐር ትሎቹ መስፈሪያ የሚሆኑ ብዙ ሣጥኖች መደዳውን ተደርድረዋል (6)

የሐር ትሎቹ መፍተል እስከሚጀምሩበት ጊዜ ድረስ በውስጣቸው አስደናቂ ለውጥ ሲካሄድ ቆይቷል። የሐር ትሉ የበላቸው ቅጠሎች ከተፈጩ በኋላ በቁመቱ ልክ በተዘረጉ ሁለት ዕጢዎች ውስጥ በመጠራቀም ፋይብሮን ተብሎ ወደሚጠራ የፕሮቲን ዓይነት ይቀየራሉ። ይህ ፕሮቲን ከዕጢዎቹ ውስጥ ተገፍቶ ሲወጣ ሙጫ የሚመስል ነገር ይቀባል። ፋይብሮን የሚባሉት ክሮች በሐር ትሉ አፍ በኩል ከመውጣታቸው በፊት ሙጫ መሰሉ ፕሮቲን ሁለቱን ክሮች እርስ በርስ ያጣብቃቸዋል። የፈሳሽ መልክ ይዞ የሚወጣው ይህ ሐር ነፋስ ሲያገኘው ይደርቅና አንድ ነጠላ ክር ይሆናል።

ትሉ ሐሩን ማውጣት ከጀመረ ማቆሚያ የለውም። በደቂቃ ከ30 እስከ 40 ሴንቲ ሜትር የሚፈትል ሲሆን በሚፈትልበት ጊዜም ጭንቅላቱን ያለማቋረጥ ያወዛውዛል። በአንድ ጽሑፍ ላይ በቀረበው ግምት መሠረት የሐር ትሉ ዙሪያውን የሚሸፍነውን የሐር ልቃቂት ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ ጭንቅላቱን 150,000 ጊዜ ያህል ያወዛውዛል። የሐር ትሉ ለሁለት ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ ከፈተለ በኋላ 1,500 ሜትር ርዝማኔ ያለው ወጥ የሐር ክር ያመርታል። ይህም የአንድን ሰማይ ጠቀስ ፎቅ አራት እጥፍ ይሆናል።

ሚስተር ካዋሃራዳ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ 120,000 የሐር ልቃቂቶችን የሚያመርት ሲሆን ይህም ለክር ዝግጅት ተጭኖ ይላካል። የጃፓን ባሕላዊ ልብስ የሆነውን አንድ ኪሞኖ ለመሥራት 9,000 የሐር ልቃቂት የሚፈጅ ሲሆን አንድ ክራቫት ለመሥራት 140፣ አንድ የአንገት ልብስ ለመሥራት ደግሞ ከ100 በላይ የሐር ልቃቂት ያስፈልጋል።

የሐር ጨርቅ አሠራር

ከሐር ልቃቂት ላይ ክሩን የመተርተሩ ሂደት ማጠንጠን ተብሎ ይጠራል። ሐር ማጠንጠን የተጀመረው እንዴት ይሆን? ይህን በሚመለከት ብዙ ተረቶችና አፈ ታሪኮች አሉ። አንዱ አፈ ታሪክ እንደሚገልጸው ከሆነ ሺ ሊንግ ሻይ የተባለች የቻይና እቴጌ የእንጆሪ ዝርያ በሆነው ዛፍ ጥላ ሥር ተቀምጣ ሻይ ስትጠጣ የሐር ልቃቂት ከዛፉ ላይ ወድቆ በምትጠጣው ሻይ ውስጥ ገባ። እሷም ልታወጣው ስትሞክር በጣም ለስላሳ የሐር ክር እንደሆነ ተመለከተች። ይህም በዛሬው ጊዜ በማሽን ለሚከናወነው የማጠንጠን ሥራ መነሻ እንደሆነ ይነገራል።

ልቃቂቶቹ በገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ እንዲያወጡ በውስጣቸው ያሉት ዕጮች ከመፈልፈላቸው በፊት መገደል አለባቸው። አምራቾቹ ይህን ደስ የማይል ሥራ ለመፈጸም ልቃቂቶቹን ሙቀት ውስጥ ይከቷቸዋል። እንከን ያለባቸው ልቃቂቶች ተመርጠው ይወገዱና የቀሩት ለሐር ክር ዝግጅቱ ተለይተው ይቀመጣሉ። በመጀመሪያ ክሮቹን እርስ በርስ ያጣበቃቸው ሙጫ መሰል ፕሮቲን ሟምቶ እንዲፍታቱ ልቃቂቶቹ በፈላ ውኃ ወይም እንፋሎት ውስጥ ይጨመራሉ። ከዚያም የክሩ ጫፍ በሚሽከረከር ብሩሽ ይያዛል (7)። በሚፈለገው የክር ውፍረት መሠረት ሁለቱ ወይም ሦስቱ ነጠላ ክሮች አንድ ላይ ተፈትለው አንድ ክር ይወጣቸዋል። ክሩ በሚጠነጠንበት ጊዜ እንዲደርቅ ይደረጋል። ይህ የመጀመሪያ ጥንጥን እንደገና በትልቁ ተጠንጥኖ የሚፈለገው ርዝማኔና ክብደት ያለው ቱባ ይወጣዋል (8, 9)

ከልስላሴው የተነሳ ጉንጭህን ልትዳብስበት የቃጣህ የሐር ጨርቅ አጋጥሞህ ይሆናል። ልስላሴውን ወይም ሻካራነቱን የሚወስነው ምን ይሆን? ለዚህ አንዱ ምክንያት የሐር ክሩን የሸፈነው ሙጫ መሰል ልባስ የለቀቀበት መጠን ነው። ሙጫው በደንብ ያልለቀቀው ሐር ሻካራ ሲሆን ለማቅለምም አስቸጋሪ ነው። ሽፎን የሚባለው የጨርቅ ዓይነት ሙጫ መሰሉ ፕሮቲን በደንብ ያልለቀቀ ስለሆነ ከርዳዳ ነው።

ልስላሴውን የሚወስነው ሁለተኛው ነገር ደግሞ በቱባው ላይ ያሉት ክሮች የተገመዱበት መጠን ነው። ሃቡታ የሚባለው የጃፓን ጨርቅ ሲነኩት የማይሻክርና ለስላሳ ነው። ክሩ እምብዛም አይገመድም። በተቃራኒው ደግሞ ክሬፕ የሚባለው የጨርቅ ዓይነት ክሩ ብዙ ጊዜ ስለሚገመድ ደረቅና የተጨማተረ ነው።

በሐር ጨርቅ ዝግጅት ውስጥ ሌላው አስፈላጊ ነገር ቀለም መንከር ነው። የሐር ጨርቅ በቀላሉ ቀለም ይቀበላል። የሐር ክር መገኛ የሆነው ፋይብሮን ቀለሙ ዘልቆ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ ጨርቁ እንደማይለቅ ሆኖ እንዲቀልም ያደርገዋል። በተጨማሪም ሰው ሠራሽ ከሆኑ ክሮች በተቃራኒ ሐር የኤሌትሪክ ኃይል ያላቸው ኔጋቲቭ እና ፖዘቲቭ አቶሞች ስላሉት ማንኛውንም ቀለም መያዝ ይችላል። ሐር በጨርቅ መልክ ሳይዘጋጅ በፊት ገና ክር እያለ ቀለም ሊነከር ይችላል (10)፤ አለዚያም ጨርቁ ተሠርቶ ካለቀ በኋላ ማቅለም ይቻላል። የጃፓን ባሕላዊ ልብሶችን ለማቅለም የሚሠራበት ዩዜን ተብሎ የሚጠራው የታወቀ ዘዴ የሐር ጨርቁ ከተሠራ በኋላ ውብ የሆኑ ንድፎች ይሣሉበትና በእጅ ቀለም ይቀባል።

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የሐር ምርት እንደ ቻይና እና ሕንድ ባሉት አገሮች የተወሰነ ቢሆንም ውብ የሆኑ የሐር ጨርቅ ንድፎች በማውጣት ረገድ ዓለምን በመምራት ላይ ያሉት የፈረንሳይና የጣሊያን ፋሽን ንድፍ አውጪዎች ናቸው። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ሬዮን እና ናይሎን የሚባሉት ሰው ሠራሽ ክሮች ዋጋቸው ውድ ያልሆኑ ልብሶችን በመሥራት ለገበያ ለማቅረብ አስችለዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በጥራቱ ሐርን የሚወዳደር የለም። በዮኮሃማ፣ ጃፓን የሚገኝ የሐር ሙዚየም ኃላፊ “በሳይንስ መስክ ከፍተኛ መሻሻል በሚታይበት በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሐር በሰው ሠራሽ ዘዴ ሊመረት አልቻለም” በማለት ይናገራሉ። “ከሞለኪዩል ቀመሩ ጀምሮ ስለ ሐር ጠቅላላ አሠራር ጠንቅቀን ብናውቅም ልንኮርጀው ግን አልቻልንም። እኔ ይህን ጉዳይ የሐር ምስጢር ነው እላለሁ።”

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሐር ክር ባሕርይ

ጠንካራ:- የሐር ክር ተመሳሳይ ውፍረት ካለው የብረት ሽቦ ጋር ተመጣጣኝ ጥንካሬ አለው።

አብረቅራቂ መልክ:- ሐር እንደ ዕንቁ የሚያምር አንጸባራቂ መልክ አለው። ለዚህም ምክንያቱ ፋይብሮን የተነባበረና በውስጡ የሚያልፈውን ብርሃን ወደተለያየ አቅጣጫ የሚበትን መሆኑ ነው።

ሰውነትን የማይሻክር ልስላሴ:- ሐርን የሚያስገኘው አሚኖ አሲድ ለስላሳ ነው። ሐር የተለያዩ የቆዳ በሽታዎችን ለመከላከል እንደሚረዳ ይነገርለታል። አንዳንድ መዋቢያ ቅባቶች ከሐር ዱቄት የተሠሩ ናቸው።

እርጥበት ይመጥጣል:- ከሐር ጨርቅ የተሠራ ልብስ ከለበስህ በክሮቹ መካከል የሚገኙት አሚኖ አሲዶችና ጥቃቅን ክፍተቶች የሰውነትህን ላብ በመምጠጥ ወደ ውጭ ስለሚያስወጡት በሞቃት ወቅትም ቢሆን ላብና ሙቀት እንዳያስቸግርህ ይረዳል።

ሙቀት ይቋቋማል:- ሐር በቀላሉ የማይቃጠል ሲሆን በእሳት ቢያያዝ መርዛማ ጢስ አያወጣም።

ጎጂ ጨረር ይከላከላል:- ሐር አልትራቫዮሌት የሚባለውን ጎጂ የፀሐይ ጨረር ውጦ ስለሚያስቀር ቆዳን ከጉዳት ይጠብቃል።

ሲተሻሽ ኤሌክትሪክ አይፈጥርም:- ሐር በውስጡ ኔጋቲቭና ፖዘቲቭ አቶሞች ስላሉትና እርጥበት የሚመጥ በመሆኑ እንደ ሌሎቹ ጨርቆች ሲተሻሽ ኤሌክትሪክ አይፈጥርም።

ለሐር ጨርቅ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ

እጥበት:- አብዛኛውን ጊዜ የሐር ጨርቆች ደረቅ እጥበት ቢደረግላቸው የተሻለ ነው። በቤት የሚታጠቡ ከሆነ ግን 30 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ያህል ሙቀት ባለው ውኃ ውስጥ ኃይለኛ ባልሆነ ሳሙና ማጠብ ይቻላል። ጨርቁ ሳይታሽና ሳይጨመቅ በጥንቃቄ መታጠብ ይኖርበታል። ከዚያም በነፋስ ብቻ እንዲደርቅ አስጡት።

መተኮስ:- የሐር ጨርቅ ሲተኮስ በላዩ ላይ ሌላ ጨርቅ መደረብ ያስፈልጋል። በልብሱ ላይ ያሉትን ክሮች አቅጣጫ በመከተል በ130 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ተኩሱት። በእንፋሎት የምትጠቀሙ ከሆነ በጣም አነስተኛ ሊሆን ይገባል፤ አለዚያም ጨርሶ በእንፋሎት አትጠቀሙ።

ልብሱ ላይ የተፈናጠቀ ቆሻሻን ማጽዳት:- ወዲያው የሐር ልብሱን በሌላ ደረቅ ልብስ ላይ ደፍታችሁ ዘርጉት። እርጥብ ጨርቅ በመጠቀም ልብሱን ከኋላው በኩል መታ መታ በማድረግ አጽዱት እንጂ አትፈትጉት። ከዚያም በደረቅ እጥበት አሳጥቡት።

አቀማመጥ:- የሐር ልብስ እርጥበት በሌለበት፣ ብል በማይደርስበትና ብርሃን በሌለበት ቦታ ሊቀመጥ ይገባል። በስፖንጅ በተጠቀለሉ መስቀያዎች ስቀሉት፤ አሊያም ጠፍጣፋ ቦታ ላይ በተቻለ መጠን ብዙ ሳይተጣጠፍ አስቀምጡት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐር ክር ልቃቂቶች

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ የሥዕል ምንጮች]

ከ7 እስከ 9 ያሉት ፎቶግራፎች:- Matsuida Machi, Annaka City, Gunma Prefecture, Japan; 10 እና ጎልቶ የሚታየው ንድፍ:- Kiryu City, Gunma Prefecture, Japan