በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አባካኝ ከመሆን መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?

አባካኝ ከመሆን መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

አባካኝ ከመሆን መቆጠብ የምችለው እንዴት ነው?

“ብዙውን ጊዜ፣ ያን ያህል የማያስፈልገኝን ዕቃ የመግዛት አቅሙ እንኳ ሳይኖረኝ በቅናሽ ዋጋ ስላገኘሁት ብቻ ልገዛው አስባለሁ።”—አና፣ ብራዚል *

“አንዳንድ ጊዜ ጓደኞቼ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ ነገሮችን አብረን እንድናደርግ ይጠይቁኛል። ከጓደኞቼ ጋር መደሰት እፈልጋለሁ። ማንም ‘ገንዘብ ስለሌለኝ መሄድ አልችልም’ ማለት አይፈልግም።”—ጆን፣ አውስትራሊያ

ወጪዎችህን ለመሸፈን የሚያስችል በቂ ገንዘብ መቼም ቢሆን ኖሮህ እንደማያውቅ ይሰማሃል? ወላጆችህ የሚሰጡህ የኪስ ገንዘብ ትንሽ ከፍ ቢልልህ ኖሮ የፈለግኸውን የኮምፒውተር ጨዋታ መግዛት እንደምትችል ይሰማህ ይሆናል። አሊያም ደሞዝ ቢጨመርልህ “ያስፈልገኛል” ያልከውን ጫማ ልትገዛ እንደምትችል ታስባለህ። ይሁን እንጂ፣ የሚያስፈልገኝን ያህል ገንዘብ የለኝም ብለህ ከምታዝን በእጅህ የሚገባውን ገንዘብ እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደምትችል ለምን አትማርም?

ከወላጆችህ ጋር የምትኖር ወጣት ከሆንክ ስለ ገንዘብ አያያዝ መማሩን ከቤት ከወጣህ በኋላ እንደምትደርስበት ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ማድረጉ የፓራሹትን አጠቃቀም ሳይረዱ ከሄሊኮፕተር ከመወርወር ተለይቶ አይታይም። እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው ከሄሊኮፕተር ተወርውሮ ወደ መሬት እየወረደ ሳለ ሕይወቱን ለማትረፍ ምን ማድረግ እንዳለበት መገንዘብ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ገና ሄሊኮፕተሩ ላይ እያለ ስለ ፓራሹት አጠቃቀም መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን ቢማር ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

በተመሳሳይም ገንዘብ ነክ የሆኑ ችግሮች እስኪያጋጥሙህ ከመጠበቅ ይልቅ ቀደም ብለህ ስለ ገንዘብ አያያዝ መማርህ ከሁሉ የተሻለ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ” ጽፏል። (መክብብ 7:12) ሆኖም ገንዘብ ጥላ ከለላ የሚሆንልህ አያያዙን እስካወቅህበት ድረስ ብቻ ነው። እንዲህ ካደረግህ በራስ የመተማመን ስሜትህ የሚያድግ ከመሆኑም በላይ ወላጆችህ ለአንተ ያላቸው አክብሮትም ይጨምራል።

መሠረታዊ ነገሮችን ተማር

ቤት ማስተዳደር ምን ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ወላጆችህን ጠይቀሃቸው ታውቃለህ? ለአብነት ያህል፣ በየወሩ ለመብራትና ለውኃ ምን ያህል እንደሚከፍሉ ታውቃለህ? ለመኪና፣ ለአስቤዛ፣ ለቤት ኪራይ ወይም ለባንክ ብድር ክፍያስ ስንት እንደሚያወጡ ታውቃለህ? እንደነዚህ ስላሉ ዝርዝር ጉዳዮች ማወቅ አሰልቺ እንደሆነ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም ለእነዚህ ወጪዎች መምጣት አንደኛው ምክንያት አንተ መሆንህን አትርሳ። ከዚህም በላይ ራስህን ችለህ ከቤት ስትወጣ እነዚህን የመሳሰሉ ወጪዎችን የምትሸፍነው አንተው ራስህ ነህ። ስለዚህ ለእነዚህ ነገሮች የሚወጣው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ ከወዲሁ ብታውቅ የተሻለ ነው። ወላጆችህ አንዳንድ ወጪዎቻቸውን እንዲነግሩህ ጠይቃቸው። ከዚያም ወጪዎቹን ለመሸፈን በጀት የሚያወጡት እንዴት እንደሆነ ሲያብራሩልህ በጥሞና አዳምጥ።

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ፤ አስተዋዮችም መመሪያ ያግኙበት” ይላል። (ምሳሌ 1:5) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አና “አባቴ እንዴት አድርጌ በጀት ማውጣት እንደምችል ያስተማረኝ ከመሆኑም ሌላ የቤተሰቡን ገቢ አብቃቅቶ ለመጠቀም የተደራጁ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነም አሳይቶኛል” በማለት ተናግራለች። እናቷም ተግባራዊ የሆኑ ሌሎች ትምህርቶችን አስተምራታለች። አና “እናቴ፣ አንድን ዕቃ ከመግዛት በፊት የተለያዩ ቦታዎች ጠይቆ ዋጋውን ማወዳደር ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አሳይታኛለች” ስትል ተናግራለች። አክላም “እማማ በትንሽ ገንዘብ ተአምር ትሠራለች” ብላለች። ታዲያ አና ከዚህ ያገኘችው ጥቅም ምንድን ነው? “አሁን የራሴን ገንዘብ በሚገባ መያዝ እችላለሁ። ገንዘብ እንዳላባክን ስለምጠነቀቅ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ አልገባም፤ ይህ ደግሞ ነጻነትና የአእምሮ ሰላም እንዲኖረኝ አስችሎኛል።”

ገንዘብ እንድታባክን የሚያደርጉህ ነገሮች

የኪስ ገንዘብ ወይም ደሞዝ የምታገኘው በተለይ ከወላጆችህ ጋር እየኖርክ ከሆነ ገንዘብ ላለማባከን ጥንቃቄ ማድረግ የመናገሩን ያህል ቀላል እንደማይሆንልህ የታወቀ ነው። ለምን? ምክንያቱም ብዙውን ወጪ የሚሸፍኑት ወላጆችህ ናቸው። ስለሆነም አብዛኛውን ገንዘብህን እንደ ልብህ ለማውጣት ሊያመችህ ይችላል። ደግሞም ገንዘብ ኖሮ የፈለጉትን ነገር ማድረግ የሚያስደስት ነው። በሕንድ የሚገኝ ፓሬሽ የተባለ ወጣት “ለእኔ፣ ገንዘብ ማውጣትና የፈለግኩትን ማድረግ ቀላልና አስደሳች ነገር ነው” ብሏል። በአውስትራሊያ የምትኖረው ሣራም እንዲሁ ይሰማታል። “ዕቃ መግዛት ደስታ ይሰጠኛል” ብላለች።

ከዚህም በተጨማሪ ጓደኞችህ ከሚገባው በላይ ወጪ እንድታወጣ ተጽዕኖ ያሳድሩብህ ይሆናል። የ21 ዓመቷ ኤሌና እንዲህ ብላለች:- “በጓደኞቼ ዘንድ፣ ገበያ ወጥቶ ዕቃ መግዛት እንደ አንድ ትልቅ መዝናኛ እየተቆጠረ ነው። ከእነርሱ ጋር አንድ ቦታ ስሄድ ‘ደስታ ለማግኘት ገንዘብ መበተን የግድ ነው’ የተባለ ይመስላል።”

ከጓደኞችህ ጋር ተመሳስለህ ለመኖር መፈለግህ ተፈጥሯዊ ነው። ሆኖም እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ:- ‘ከጓደኞቼ ጋር ስሆን ገንዘብ የማወጣው አቅሙ ስላለኝ ነው? ወይስ ማውጣት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ?’ ብዙ ሰዎች ገንዘብ የሚያወጡት የጓደኞቻቸውንና የሚቀርቧቸውን ሌሎች ሰዎች አክብሮት ለማትረፍ ብለው ነው። እንዲህ ያለው ዝንባሌ በተለይ በዱቤ የምትጠቀም ከሆነ ከባድ የገንዘብ ችግር ሊያስከትልብህ ይችላል። ሱዚ ኦርመን የተባሉ አንዲት የገንዘብ ነክ ጉዳዮች አማካሪ “ሰዎችን በማንነትህ ሳይሆን ባለህ ገንዘብ መጠን ለመማረክ የምትፈልግ ከሆነ በዕዳ የመዘፈቅ እድልህ በጣም ከፍተኛ ነው” ብለዋል።

የወር ደሞዝህን በአንድ ጀምበር ከማሟጠጥ ይልቅ የኤሌናን ዓይነት የመፍትሔ እርምጃ ለምን አትወስድም? ኤሌና እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “ከጓደኞቼ ጋር ወደ አንድ ቦታ በምወጣበት ጊዜ ምን ምን ነገሮችን እንደማደርግ አስቀድሜ በመወሰን ወጪዬ ምን ያህል እንደሚሆን አሰላለሁ። ደሞዜ በቀጥታ በባንክ ሒሳቤ ውስጥ ስለሚገባ ለዚያ ዓላማ የምፈልገውን ያህል ገንዘብ ብቻ ከባንክ አወጣለሁ። በተጨማሪም ገበያ በምወጣበት ጊዜ በገንዘብ አያያዝ ረገድ ጠንቃቃ ከሆኑት እንዲሁም የተለያየ ሱቅ ገብቼ ዋጋ እንዳወዳድርና ያየሁትን ሁሉ ከመግዛት እንድቆጠብ ከሚያበረታቱኝ ጓደኞቼ ጋር መሄዱን ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”—ምሳሌ 13:20

ወላጆችህ አይቻልም የሚሉህ ለምን ይሆን?

የኪስ ገንዘብ ወይም ደሞዝ ባይኖርህም እንኳ ወላጆችህ ቤት ሳለህ ከገንዘብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጠቃሚ ትምህርቶች መቅሰም ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ወላጆችህ ገንዘብ እንዲሰጡህ ወይም ደግሞ አንድ ነገር እንዲገዙልህ ስትጠይቃቸው ‘አይቻልም’ ይሉ ይሆናል። ለምን? አንደኛው ምክንያት በዚያ ወቅት አንተ የምትፈልገውን ነገር ለመግዛት ስላላቀዱ ሊሆን ይችላል። ወላጆችህ የጠየቅኻቸውን ቢያደርጉልህ ደስ የሚላቸው ቢሆንም እንኳ አይቻልም በማለታቸው ራስን በመግዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ እየተዉልህ ነው። ራስን መግዛት ደግሞ በገንዘብ አያያዝ የተዋጣልን እንድንሆን የሚረዳ ወሳኝ ባሕርይ ነው።

ወላጆችህ የጠየቅኻቸውን ነገር ለማድረግ አቅሙ አላቸው እንበል። ያም ሆኖ ግን ‘አይቻልም’ ይሉ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ንፉግ እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል። ሆኖም እስቲ ይህን ልብ በል:- ደስታህ የተመካው የምትፈልገውን ሁሉ በማግኘትህ ላይ እንዳልሆነ በማሳየት ጠቃሚ ትምህርት ሊሰጡህ እየጣሩ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም፤ ብልጽግናም የሚወድ፣ በትርፉ አይረካም” ሲል ተናግሯል።—መክብብ 5:10

የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት፣ የሚፈልጉትን ሁሉ ወላጆቻቸው የሚገዙላቸው ብዙ ወጣቶች ከሚያጋጥማቸው ሁኔታ ማየት ይቻላል። እነዚህ ወጣቶች የሚፈልጉት ሁሉ ተደርጎላቸው እንኳ ብዙም ሳይቆዩ ፈጽሞ እንዳልረኩ ይገነዘባሉ። የፈለገውን ያህል ብዛት ያለው ነገር ቢያጋብሱም ሁልጊዜ ሌላ አንድ ነገር መጨመር እንዳለበት ይሰማቸዋል። የጠየቁት ሁሉ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ ወጣቶች ትልቅ ሰው ሲሆኑ ምንም ነገር ቢደረግላቸው የማያመሰግኑ ይሆናሉ። ሰሎሞን “ባሪያውን [ወይም ልጁን] ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማቀማጠል የሚያሳድግ የኋላ ኋላ እንደ ጌታ ያደርገዋል” በማለት አስጠንቅቋል።—ምሳሌ 29:21 የ1954 ትርጉም

ገንዘብ ጊዜ ነው

በአንዳንድ ባሕሎች “ጊዜ ገንዘብ ነው” የሚል አባባል አለ። ይህ አባባል ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ጊዜ ማጥፋታቸው የግድ እንደሆነና ጊዜ ማባከን ገንዘብ እንደማባከን እንደሚቆጠር ያሳያል። ‘ገንዘብ ጊዜ ነው’ የሚለው የዚህ አባባል ተገላቢጦሽም እውነት ነው። ገንዘብ የምታባክን ከሆነ ያንን ብር ለማግኘት ያጠፋኸውን ጊዜም እያባከንክ መሆኑ እሙን ነው። ገንዘብ ከማባከን መቆጠብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ስታውቅ ጊዜህንም እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደምትችል ትማራለህ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?

ኤሌና የሰጠችውን አስተያየት ተመልከት። “ወጪ እንዳላበዛ መጠንቀቄ ምን ያህል መሥራት እንዳለብኝ እንድወስን አስችሎኛል። ተግባራዊ ሊሆን የሚችል በጀት አውጥቼ በዚያው መሠረት ከተመራሁ የተከመሩ ዕዳዎችን ለመክፈል ብዬ ረጅም ሰዓት መሥራት አይኖርብኝም። ጊዜዬንና ሕይወቴን ይበልጥ መቆጣጠር ችያለሁ።” ኑሮህን እንዲህ አድርገህ መምራት ብትችል ደስ አይልህም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ገንዘብ ከማባከን መቆጠብ አስቸጋሪ ሆኖብሃል? ለምን?

▪ የገንዘብ ፍቅርን ማስወገድ ያለብህ ለምንድን ነው?—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል ]

መፍትሔው ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ነው?

ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘትህ ለማባከን ችግርህ መፍትሔ እንደሚሆን ይሰማሃል? ሱዚ ኦርመን የተባሉት የገንዘብ ነክ ጉዳዮች አማካሪ “ሁላችንም ዳጎስ ያለ ደሞዝ ብናገኝ የገንዘብ ችግራችንን ማቃለል እንደምንችል ይሰማናል፤ እውነታው ግን ይኼ አይደለም” ብለዋል።

በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- መኪና ስትይዝ ዓይንህን ጨፍነህ የመንዳት ልማድ ቢኖርህ ወይም መኪናውን መቆጣጠር ቢሳንህ ተጨማሪ ነዳጅ መቅዳትህ ከአደጋ ነጻ እንድትሆን ያደርግሃል? መሄድ ወደምትፈልግበት ቦታስ ያለ ምንም ችግር መድረስ ትችላለህ? በተመሳሳይም ገንዘብህን እንዴት መያዝ እንዳለብህ እስካልተማርክ ድረስ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘትህ በራሱ ሁኔታዎችን ሊያስተካክልልህ አይችልም።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሰንጠረዥ]

ገንዘብ የማባከን ችግርህን አሸንፍ

ባለፈው ወር ምን ያህል ገንዘብ አወጣህ? ይህን ያህል ገንዘብ ያወጣኸው ለምን ነገር ነው? አታውቀውም? ገንዘብህን የምታወጣበት መንገድ ሕይወትህን ከመቆጣጠሩ በፊት ወጪህን መቆጣጠር የምትችልበት ዘዴ እነሆ:-

መዝገብ ይኑርህ። ቢያንስ ለአንድ ወር ገቢህንና ይህን ገቢ ያገኘህበትን ቀን መዝግበህ ያዝ። የገዛኸውን እያንዳንዱን ዕቃ ከነዋጋው ጻፍ። ከዚያም በወሩ መጨረሻ ላይ፣ ያገኘኸውን ጠቅላላ ገንዘብም ይሁን ያወጣኸውን ወጪ ደምር።

በጀት አውጣ። በአንድ ባዶ ወረቀት ላይ ሦስት ረድፍ ያለው ሰንጠረዥ አዘጋጅ። በመጀመሪያው ረድፍ ላይ በወሩ ውስጥ የምታገኛቸውን ገቢዎች ሁሉ መዝግብ። ከዚያም ከላይ በተጠቀሰው መዝገብ ላይ የጻፍከውን ዝርዝር መሠረት አድርገህ ገንዘብህን ለምን ለምን ነገሮች ለማውጣት እንዳቀድክ በሁለተኛው ረድፍ ላይ ጻፍ። ወሩ እየገፋ ሲሄድ አስቀድመህ ላቀድካቸው ነገሮች በእርግጥ ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣህ በሦስተኛው ረድፍ ላይ ጻፍ። በተጨማሪም ከእቅድህ ውጪ ያወጣሃቸውን ወጪዎች በሙሉ መዝግብ።

እቅድህን አስተካክል። ለአንዳንድ ነገሮች አስቀድመህ ካሰብከው የበለጠ ወጪ ካወጣህና ዕዳ ውስጥ ከገባህ እቅድህን አስተካክል። ዕዳህን ክፈል፤ ከዚያም በዚህ መንገድ ገንዘብህን በአግባቡ ለመያዝ ጥረት አድርግ።

[ሠንጠረዥ]

ቆርጠህ ተጠቀምበት!

ወርሃዊ በጀት

ገቢ ወጪ በእርግጥ የወጣው ገንዘብ

የኪስ ገንዘብ ምግብ

የትርፍ ሰዓት ሥራ ልብስ

ሌላ ስልክ

መዝናኛ

መዋጮ

ተቀማጭ ገንዘብ

ሌላ

 

 

ጠቅላላ ድምር ጠቅላላ ድምር ጠቅላላ ድምር

ብር ብር ብር

[ሥዕል]

ገንዘብ ካባከንክ ያንን ገንዘብ ለማግኘት ያጠፋኸውን ጊዜ ጭምር እያባከንክ መሆንህን አትዘንጋ

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆችህ በጀት የሚያወጡበትን መንገድ እንዲያሳዩህ ለምን አትጠይቃቸውም?