በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ስልሳ ከመቶ የሚሆኑት የብራዚል ሕፃናት ሦስት ዓመት ሲሞላቸው የጥርስ መቦርቦር ያጋጥማቸዋል። ለዚህም መንስኤ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ጡጦ መጥባት ሲሆን በተለይም ሌሊት ጣፋጭ የበዛበት ነገር ሲጠጡ ስለሚያድሩና ጥርሳቸው አስፈላጊው ጽዳት ስለማይደረግለት ይበላሻል።—ፎልሃ ኦንላይን፣ ብራዚል

በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ከሚወልዱ ሴቶች ውስጥ 25 በመቶ የሚሆኑት የሚወልዱት በቀዶ ሕክምና ነው። በኒው ዮርክ ከተማ በቀዶ ሕክምና የሚወልዱት ሴቶች ቁጥር በ1980 ከነበረው በአምስት እጥፍ ጨምሯል። ለዚህ አንዱ ምክንያት በተፈለገው ጊዜ እንዲወልዱ ለማድረግ ቢሆንም ሳያስፈልግ እንደዚህ ያለውን ቀዶ ሕክምና ማከናወን “ከፍተኛ” አደጋ አለው።—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ባለፉት 100 ዓመታት የሜክሲኮ ሲቲ አማካይ ሙቀት በ4 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የጨመረ ሲሆን ዓለም አቀፉ አማካይ ሙቀት የጨመረው በ1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው። የዚህ መንስኤ የደኖች መጨፍጨፍና የከተማ መስፋፋት እንደሆኑ በመስኩ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።—ኤል ዩኒቨርሳል፣ ሜክሲኮ

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ትዳር ከሚመሠርቱ ሙሽሮች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከመጋባታቸው በፊት አብረው ሲኖሩ የነበሩ ናቸው። እንደዚህ ያሉት ባልና ሚስቶች የመፋታት ዕድላቸው አብረው መኖር ከመጀመራቸው በፊት ከሚጋቡት በእጥፍ ይበልጣል።—ሳይኮሎጂ ቱደይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

የሥራ ባልደረቦችን የሚያበሳጭ ልማድ

“በመሥሪያ ቤት የሥራ ባልደረቦቻችን ካሏቸው በጣም የሚያበሳጩ ልማዶች መካከል በስልክ ጮክ ብሎ ማውራት፣ የድምፅ ማጉያ ባለው ስልክ [መጠቀም] እንዲሁም ሁልጊዜ ስለ ሥራ መብዛት ማማረር በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው” በማለት ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል። በጣም ከሚያናድዱ ሌሎች አጉል ጠባዮች መካከል ደግሞ “በሥራ ባልደረቦች መካከል የሚፈጠር መከፋፈል፣ አርፍዶ ሥራ መግባት፣ ለብቻ ማውራት፣ በትናንሹ ተከፋፍለው በተሠሩ ቢሮዎች ውስጥ ባሉበት ሆነው ከጎናቸው ባለው ክፍል ውስጥ ካለው የሥራ ባልደረባ ጋር ማውራት፣ የሰውነትን ንጽሕና አለመጠበቅ እንዲሁም ምግብ ሲያላምጡ ድምፅ ማሰማት” ይገኙበታል። እንዲህ ያሉት መጥፎ ልማዶች በሠራተኛው ምርታማነት ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። ይሁን እንጂ የጥናቱ አዘጋጆች ላዘጋጁት ጥያቄ መልስ ከሰጡት ሠራተኞች አብዛኞቹ የሚያበሳጯቸውን ሰዎች አፍ አውጥተው ተናግረዋቸው አያውቁም። “ለዚህም በቂ ምክንያት አላቸው” ይላል ጋዜጣው። “እነሱ ራሳቸው የዚያኑ ያህል ሌሎችን የሚያበሳጩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው።”

በከተሞች የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

“በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከዓለም ሕዝብ መካከል ግማሹ የከተማ ነዋሪ ይሆናል” በማለት ሲቢሲ ኒውስ ይናገራል። የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ እንደሚገልጸው በከተማ ውስጥ የሚኖር ብዙ ሕዝብ ያላት ዩናይትድ ስቴትስ ስትሆን ከ10 ሰዎች መካከል 9 የሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ከ55 ዓመታት በፊት 10 ሚሊዮን ወይም ከዚያ በላይ ነዋሪዎች ያሏቸው ሁለት ከተሞች ኒው ዮርክና ቶኪዮ ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ጊዜ ግን ይህ ቁጥር ጨምሮ ከ10 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያሏቸው ከተሞች 20 የደረሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ጃካርታ፣ ሜክሲኮ ሲቲ፣ ሙምባይና ሳኦ ፖሎ ይገኙበታል። የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ኮፊ አናን “[የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር] እንዲህ ባለ ፍጥነት መጨመሩ በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ለውጥ እንዲካሄድ ግድ ይላል” ብለዋል።

በውትድርና ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች

የኮሪያ ሪፑብሊክ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ በውትድርና አገልግሎት ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸው ሰዎች መብት ሊጣስ እንደማይገባ ገልጿል። ኮሚቴው፣ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች በውትድርና አገልግሎት ምትክ የሲቪል አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ሐሳብ አቅርቧል። ዘ ኮሪያ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው ይህ ሐሳብ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ በቅርቡ ከተላለፈው የፍርድ ቤት ውሳኔ ጋር “የሚጋጭ” ነው። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአሁኑ ጊዜ የሚሠራበትን ወታደራዊ ሕግ የሚደግፍ ሲሆን በዚህ ሕግ ላይ በጦርነት ለመካፈል ሕሊናቸው የማይፈቅድላቸውን ሰዎች ግምት ውስጥ በማስገባት የተደረገ ዝግጅት የለም። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ እንደዚህ ያለው መብት በሕጉ ውስጥ እንዲካተት የማድረጉ ኃላፊነት የሕግ አውጪው ክፍል እንጂ የፍርድ ቤቶች እንዳልሆነ ገልጾ ነበር። በኮሪያ ሪፑብሊክ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ቁጥራቸው ከ500 እስከ 700 የሚደርስ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በየዓመቱ ወኅኒ ይወርዳሉ። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በዚህ ጉዳይ 10,000 ያህል የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።