በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፎቶግራፍ ጥበብ ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?

የፎቶግራፍ ጥበብ ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?

የፎቶግራፍ ጥበብ ወደ ሕልውና የመጣው እንዴት ነው?

ስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንደጻፈው

ጃምባቲስታ ዴላ ፖርታ የተባለውን ጣሊያናዊ የፊዚክስ ሊቅ (1535?-1615) ሥራ ሊጎበኙ የሄዱ ሰዎች ባዩት ነገር በጣም እንደደነገጡ በአፈ ታሪክ ይነገራል። ከፊት ለፊታቸው ባለው ግድግዳ ላይ ጭንቅላታቸው ወደ ታች የተዘቀዘቀ ትንንሽ ሰዎች ወዲያ ወዲህ ሲሉ ይታያል። ተመልካቾቹ በፍርሐት እየተንቀጠቀጡ ከክፍሉ ተሯሩጠው ወጡ። ዴላ ፖርታ አስማተኛ ነው ተብሎ ተከሰሰ።

ዴላ ፖርታ ጨለማ ክፍሉን በማሳየት እንግዶቹን ለማዝናናት ያደረገው ጥረት ይህን አስከትሎበታል። ይህ ጨለማ ክፍል በላቲን ቋንቋ ካሜራ ኦብስኩራ ይባላል። የዚህን ካሜራ አሠራር መረዳት አስቸጋሪ አይደለም። ይሁን እንጂ የሚያስገኘው ውጤት በጣም አስደናቂ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ካሜራው የሚሠራው እንዴት ነው?

የብርሃን ጨረር በጣም ጠባብ በሆነ ቀዳዳ በኩል አልፎ ጨለማ ክፍል ወይም ጥቁር ሣጥን ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ከውጭ ያለው ነገር ምስል ፊት ለፊት ባለው ግድግዳ ላይ ተገልብጦ ይታያል። የዴላ ፖርታ እንግዶች የተመለከቱት ከክፍሉ ውጭ ያሉ ተዋንያን ትርኢታቸውን ሲያቀርቡ ነበር። ይህ ዓይነቱ ካሜራ ለዘመናችን ካሜራ መንገድ ጠራጊ ነበር። አንተም የራሳቸው ካሜራ ካላቸው ወይም ቢያንስ አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ የሚጣል ዋጋው ርካሽ የሆነ ፎቶግራፍ ማንሻ ከሚጠቀሙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንዱ ልትሆን ትችላለህ።

ካሜራ ኦብስኩራ በዴላ ፖርታም ዘመን ቢሆን አዲስ ነገር አልነበረም። አርስቶትል (384-322 ከክርስቶስ ልደት በፊት) እንዲህ ያለ ምስል ማውጣት ስለሚቻልበት መንገድ ተረድቶ ነበር። አልሐሰን የተባለው የ10ኛው መቶ ዘመን የአረብ ምሑር ስለዚህ ካሜራ አሠራር ግልጽ ማብራሪያ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ሊዮናርዶ ዳ ቪንቺ የተባለው የ15ኛው መቶ ዘመን ሠዓሊም ካሜራው ስለሚሠራበት መንገድ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ አስፍሯል። በ16ኛው መቶ ዘመን ሌንስ መፈልሰፉ የዚህን ካሜራ ምስል ጥራት በእጅጉ ያሻሻለው ከመሆኑም በላይ በርካታ ሠዓሊዎች የሥዕሎቻቸውን መጠንና ገጽታ በትክክል ለማስቀመጥ ተጠቅመውበታል። ይሁን እንጂ ምስሎቹን አትሞ በቋሚነት ለማስቀረት የተደረገው ጥረት እስከ 19ኛው መቶ ዘመን ድረስ ሳይሳካ ቆይቷል።

የዓለማችን የመጀመሪያው ፎቶግራፍ አንሺ

ዦሴፍ ኒሴፎር ኒየፕስ የተባለው ፈረንሳዊ የፊዚክስ ሊቅ ፎቶግራፎችን አትሞ በቋሚነት ማስቀረት የሚቻልበትን ዘዴ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የጀመረው በ1816 ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን የተሳካ ሙከራ ያደረገው ለኅትመት ሥራ በሚያገለግለውና ሊቶግራፊ በሚባለው አሠራር ላይ ምርምር ሲያደርግ የብርሃን ጨረር ሲያርፍበት መልኩን የሚለውጥ የይሁዳ ቅጥራን የሚባል ንጥረ ነገር ባገኘ ጊዜ ነበር። በ1820ዎቹ አጋማሽ ላይ ቅጥራን የተለቀለቀ ሳህን በካሜራ ኦብስኩራ ውስጥ አደረገና ይህን ካሜራ የመኖሪያ አካባቢውን የተወሰነ ክፍል በሚያሳይ ቦታ ላይ አስቀምጦ ለስምንት ሰዓት ያህል ብርሃን እንዲያርፍበት አደረገ። በዘመናችን ካሉ አማተር ፎቶግራፍ አንሺዎች መካከል ጀማሪ ነው የሚባለው እንኳ ኒየፕስ ያነሳውን የአንድ ሕንጻ፣ ዛፍ ወይም ግርግም ደብዛዛ ምስል ተመልክቶ ሊደሰት አይችልም። ኒየፕስ ግን በጣም ተደስቶ ነበር። ምክንያቱም እርሱ ያነሳው ምስል የመጀመሪያው ቋሚ ፎቶግራፍ ሳይሆን አይቀርም።

ኒየፕስ ይህን ዘዴውን ይበልጥ ለማሻሻል ሲል በ1829 ሉዊ ዳጌር ከተባለ ታታሪ ባለ ሀብት ጋር በሽርክና መሥራት ጀመረ። ኒየፕስ በ1833 ከሞተ በኋላ በነበሩት ዓመታት ዳጌር ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እድገት አስገኝቷል። በመዳብ ሳህኖች ላይ ሲልቨር አዮዳይድ የተባለ ንጥረ ነገር መቀባት ጀመረ። ይህ ንጥረ ነገር የብርሃን ጨረር ሲያርፍበት ከቅጥራን የበለጠ መልኩን የመለወጥ ችሎታ ነበረው። በሳህኑ ላይ ብርሃን ካረፈበት በኋላ የሜርኩሪ ጭስ ሲጨስበት በጣም ደብዛዛ የነበረው ምስል እየጎላ እንደሚመጣ በአጋጣሚ ተገነዘበ። ይህም ሳህኑን ብርሃን ላይ የሚቆይበትን ጊዜ በእጅጉ ለመቀነስ አስቻለ። ጥቂት ቆየት ብሎ ዳጌር ሳህኑ በጨው ቢታጠብ ፎቶግራፉ በጊዜ ሒደት መጥቆሩን እንደሚያቆም ሲገነዘብ የፎቶግራፍ ጥበብ የመላውን ዓለም ቀልብ የሚስብበት ደረጃ ላይ ደረሰ።

ግኝቱ ለዓለም ይፋ ሆነ

ዳጌረታይፕ በመባል የሚታወቀው አዲሱ የዳጌር ግኝት በ1839 ለሕዝብ ይፋ ሲሆን የፈጠረው ስሜት ከተጠበቀው በላይ ነበር። ሄልሙት ገርንስሃይም የተባሉ ምሑር ዘ ሂስትሪ ኦቭ ፎቶግራፊ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ “የዳጌረታይፕን ያህል የሕዝብን ትኩረት የሳበና በአንድ ጊዜ ዓለምን ያጥለቀለቀ ግኝት ኖሮ አያውቅም” ብለዋል። ይህ አዲስ ግኝት ለሕዝብ ይፋ በሆነበት ዕለት የዓይን ምሥክር የነበሩ አንድ ሰው እንዲህ ብለዋል:- “ከአንድ ሰዓት በኋላ የመነጽር መሸጫ ቤቶች በሙሉ በሰው ተጥለቀለቁ። ሆኖም ባለ ሱቆቹ የዳጌረታይፕ ባለቤት ለመሆን ፈልገው ሱቆቻቸውን ላጨናነቁት በርካታ ሰዎች የሚዳረስ መሣሪያ ማቅረብ አልቻሉም። ከጥቂት ቀናት በኋላ በፓሪስ አደባባዮች በሙሉ በአብያተ ክርስቲያናትና በቤተ መንግሥታት ላይ ያነጣጠሩ ባለ ሦስት እግር ጥቁር ሣጥኖችን ማየት ትችሉ ነበር። የከተማዋ የፊዚክስና የኬሚስትሪ ሊቃውንት እንዲሁም ሌሎች የተማሩ ሰዎች ብር ቅብ ሳህኖችን ሲወለውሉ ይታዩ ነበር። የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የግሮሰሪ ባለቤቶች ሳይቀሩ ለዚህ ዘመናዊ የቅንጦት መሣሪያ ንብረታቸውን ከመሠዋት ወደኋላ አላሉም።” የፓሪስ ጋዜጦች ይህን ዘመን አመጣሽ ፋሽን ዳጌሬቲፓማኒ ብለው መጥራት ጀመሩ።

የዳጌረታይፖች አሠራር በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሣ ጆን ኸርሽል የተባሉት የብሪታንያ ሳይንቲስት “ተአምር ተብለው ቢጠሩ የሚበዛባቸው አይሆንም” ብለዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ምትሐታዊ ኃይል እንዳላቸው አድርገው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ይህን አዲስ ግኝት እጃቸውን ዘርግተው የተቀበሉት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም። በ1856 የኔፕልስ ንጉሥ “ከቡዳ” ጋር ግንኙነት አለው ብለው አስበው ሳይሆን አይቀርም ፎቶግራፍ ማንሳትን አግደዋል። ፖል ደላሮሽ የተባለ ፈረንሳዊ ሠዓሊ ዳጌረታይፕን ከተመለከተ በኋላ “ከዛሬ ጀምሮ የሥዕል ሞያ አበቃለት” ብሏል። በተጨማሪም ሠዓሊዎች ይህን አዲስ ግኝት በእንጀራቸው እንደመጣ ጠላት አድርገው ስለቆጠሩት ከፍተኛ ሥጋት አድሮባቸው ነበር። አንድ ሃያሲ “ፎቶግራፍ በዓይን የሚታየውን ገጽታ በትክክል ቀርጾ ስለሚያስቀር ግለሰቡ ስለ ውበት ያለውን ግንዛቤ ዋጋ ሊያሳጣው ይችላል” በማለት የአንዳንዶችን ሥጋት ገልጸዋል። በተጨማሪም ፎቶግራፍ እውነታውን ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ ሰዎች አለን ብለው የሚያስቡት ውበትና ወጣትነት እነርሱ እንደሚሉት አለመሆኑን ያጋልጣል በሚል ትችት ተሰንዝሮበታል።

ዳጌርና ቶልበት

ዊልያም ሄንሪ ፎክስ ቶልበት የተባለ እንግሊዛዊ የፊዚክስ ሊቅ የፎቶግራፍን ጥበብ የፈለሰፈው እርሱ እንደሆነ አድርጎ ያስብ ስለነበር የዳጌር ግኝት ይፋ መሆኑ አስገረመው። ቶልበት፣ ሲልቨር ክሎራይድ የተባለ ንጥረ ነገር የተቀባ ወረቀት በካሜራ ኦብስኩራ ውስጥ ይጨምር ነበር። ይህን ፊልም በሌላ ቅብ ወረቀት ላይ ከደረበ በኋላ ፀሐይ በማስመታት ትክክለኛው ምስል እንዲገኝ ያደርግ ነበር።

ይህ የቶልበት ግኝት መጀመሪያ ላይ እምብዛም ተቀባይነት የሌለውና ጥራቱም ዝቅ ያለ ይምሰል እንጂ ማሻሻያ ለማድረግ የበለጠ ተስፋ ነበረው። ከአንድ ፊልም በርካታ ቅጂዎችን ማግኘት የሚቻል ከመሆኑም በላይ የወረቀት ፎቶግራፎች በቀላሉ ከሚሰበሩት ዳጌረታይፖች የበለጠ ርካሽና ለአያያዝም ቀላል ነበሩ። የዘመናችን የፎቶግራፍ ጥበብ በቶልበት ግኝት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ዳጌረታይፕ መጀመሪያ ላይ ሰፊ ተቀባይነት ቢያገኝም አሁን ፈጽሞ የለም።

ይሁን እንጂ የፎቶግራፍን ጥበብ የፈለሰፍኩት እኔ ነኝ የሚሉት ኒየፕስ፣ ዳጌርና ቶልበት ብቻ አይደሉም። ዳጌር በ1839 ግኝቱን ለሕዝብ ይፋ ካደረገ በኋላ በሰሜናዊው ንፍቀ ክበብ ከምትገኘው ከኖርዌይ አንስቶ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ እስካለችው እስከ ብራዚል ድረስ ቢያንስ 24 የሚያህሉ ሰዎች የፎቶግራፍን ጥበብ የፈለሰፉት እነርሱ እንደሆኑ ተናግረዋል።

የፎቶግራፍ ጥበብ ያስከተላቸው ከፍተኛ ለውጦች

ጃኮብ ኦገስት ሪኢስ የተባለ አንድ የማኅበራዊ ተሃድሶ አራማጅ የፎቶግራፍ ጥበብ ገና እንደተፈለሰፈ የሰዎችን የድህነትና የመከራ ሕይወት ወደ አደባባይ ለማውጣት የሚያስችል ጥሩ መሣሪያ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ይህ ሰው በ1880 የማግኒዝየም ዱቄት በመጥበሻ ላይ ሲቃጠል የሚፈጠረውን ብርሃን እንደ ፍላሽ በመጠቀም የኒው ዮርክን ጎስቋላ መኖሪያዎች የማታ ገጽታ ማንሳት ጀመረ። ይህ ዘዴው አደገኛ ነበር። ይሠራበት የነበረው ቤት ሁለት ጊዜ በእሳት ከመያያዙም በላይ አንድ ጊዜ የራሱን ልብስ አቃጥሏል። ቲዎዶር ሩዝቬልት ወደ ኋይት ሐውስ ሲገቡ በርካታ ማኅበራዊ ለውጦችን እንዲያደርጉ ከገፋፏቸው ምክንያቶች አንዱ የዚህ ሰው ፎቶግራፎች እንደሆኑ ይነገራል። በተጨማሪም ዊልያም ሄንሪ ጃክሰን ያነሳቸው አስደናቂ ፎቶግራፎች ባሳደሩት ከፍተኛ ተጽዕኖ ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት በ1872 በዓለም የመጀመሪያ የሆነውን የሎውስቶን የተባለ ብሔራዊ ፓርክ ለማቋቋም ተነሳስቷል።

ሁሉም ሰው የሚያገኘው ነገር ሆነ

እስከ 1880ዎቹ መገባደጃ ድረስ የፎቶግራፍ ጥበብ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅና በጣም ውስብስብ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ሰዎች የሚደፍሩት ሞያ ሊሆን አልቻለም። ይሁን እንጂ ጆርጅ ኢስትማን በ1888 የሚጠቀለል ፊልም የሚጎርስና አጠቃቀሙ ቀላል የሆነ ኮዳክ የተባለ ሣጥን መሰል ካሜራ በፈለሰፈ ጊዜ የፎቶግራፍ ጥበብ ብዙ አማተር ፎቶግራፍ አንሺዎችን የሚስብ ሞያ ሆነ።

ደንበኛው ፎቶግራፍ አንስቶ ፊልሙን ከጨረሰ በኋላ ካሜራውን እንዳለ ወደ ፋብሪካው ይልክ ነበር። እዚያም ፊልሙ ከታጠበ በኋላ ካሜራው ሌላ ፊልም ገብቶበት ከታጠቡት ፎቶግራፎች ጋር ይመለስለታል። ይህ ሁሉ የሚደረገው እምብዛም ውድ ባልሆነ ዋጋ ነበር። “እናንተ ብቻ የካሜራውን ማንሻ ተጫኑ፣ የቀረውን ለእኛ ተዉት” የሚለው የኮዳክ ኩባንያ መፈክር የተጋነነ አልነበረም።

በዚህ መንገድ የፎቶግራፍ ጥበብ ለብዙኃኑ መዳረስ ቻለ። በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ፎቶግራፎች የሚነሱ መሆናቸው ይህ ጥበብ ያገኘው ተቀባይነት ዛሬም ቢሆን እንዳልቀነሰ ያሳያል። በአሁኑ ጊዜ በሜጋፒክስል የሚለካ ጥራት ያለው ፎቶግራፍ የሚያነሱ ዲጂታል ካሜራዎች ብቅ ማለታቸው የፎቶግራፍ ጥበብ ያለው ተወዳጅነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲህ ዓይነቱ ካሜራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፎቶግራፎችን ሊይዝ የሚችል ትንሽ ካርድ አለው። የቤት ውስጥ ኮምፒውተርና ማተሚያ እንኳን በመጠቀም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ፎቶግራፎች ማተም ይቻላል። በእርግጥም የፎቶግራፍ ጥበብ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ የደረሰው በጣም ረዥም ጉዞ ተጉዞ እንደሆነ አያጠራጥርም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፓሪስ ዳጌረታይፕ ፎቶግራፍ፣ 1845 ገደማ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያው እንደሆነ የሚገመተው ፎቶግራፍ ቅጂ፣ 1826 ገደማ

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በርካታ ሠዓሊያን ይጠቀሙበት የነበረው የካሜራ ኦብስኩራ ሥዕል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒየፕስ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በ1844 በዳጌረታይፕ የተነሳው የሉዊ ዳጌር ፎቶግራፍ እና ካሜራው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የዊልያም ቶልበት ፎቶ ቤት በ1845 ገደማ፤ እና ካሜራዎቹ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ጆርጅ ኢስትማን ኮዳክ ቁ. 2 ካሜራ ይዞ በ1890 የተነሳው ፎቶግራፍ እንዲሁም ቁ. 1 ካሜራው ከነፊልም መጠቅለያው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥራት ያለው ፎቶግራፍ የሚያነሱ ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዊልያም ሄንሪ ጃክሰን ያነሳው የሎውስቶን የተባለው ብሔራዊ ፓርክ ፎቶግራፍ፣ 1871

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ፓሪስ ከሩቅ ስትታይ:- Photo by Bernard Hoffman/Time Life Pictures/Getty Images; የኒየፕስ ፎቶግራፍ:- Photo by Joseph Niepce/Getty Images; ካሜራ ኦብስኩራ:- Culver Pictures

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ገጽ 23:- የቶልበት ፎቶ ቤት:- Photo by William Henry Fox Talbot & Nicholaas Henneman/Getty Images; የቶልበት ካሜራ:- Photo by Spencer Arnold/Getty Images; ኮዳክ ፎቶ፣ ኮዳክ ካሜራ እና ዳጌር ካሜራ:- Courtesy George Eastman House; የሎውስቶን:- Library of Congress, Prints & Photographs Division, LC-USZ62-52482