በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

“[ልጅ ሳለሁ] ስለ ወደፊቱ አልጨነቅም ነበር። ሆኖም ከትምህርት ቤት የምመረቅበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ በገሐዱ ዓለም ሥራ መያዝና ወጪዎቼን ራሴ መሸፈን እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ።”—የ17 ዓመቱ አሌክስ

ልጅ ሳለህ፣ ስታድግ ምን እንደምትሆን ታስብ ነበር? በዚያን ጊዜ ስለነበሩህ ግቦች አሁን ምን ይሰማሃል? ራስህን ስለምትችልበት መንገድ ስታስብ ግራ ይገባሃል? እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ይህ ጉዳይ የሚያሳስበው አንተን ብቻ አይደለም። ከሪየር ኮቺንግ ዮር ኪድስ የተባለው መጽሐፍ “ሥራን በተመለከተ ውሳኔ ማድረግ፣ ወጣቶች ከሚገጥሟቸው አስቸጋሪ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው” በማለት ይናገራል።

በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ መያዝ አሁን በአእምሮህ ውስጥ ከናካቴው የሌለ ነገር ሊሆን ይችላል። ምናልባት ይበልጥ የምታስበው ስለ መዝናናት ይሆናል። እርግጥ መዝናናት በራሱ ምንም ችግር የለውም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ” በማለት ይናገራል። (መክብብ 11:9) ሆኖም የወደፊት ሕይወትህን እንዴት እንደምትጠቀምበት ማሰብ መጀመር ያለብህ አሁን ነው። ምሳሌ 14:15 “አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። አንተስ እርምጃህን ማስተዋል የምትችለው እንዴት ነው?

“ለምታደርገው ነገር ሁሉ ዕቅድ ይኑርህ”

ከቤትህ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ለመሄድ ዕቅድ አውጥተሃል እንበል። የተሻለ መንገድ ለመምረጥ በመጀመሪያ ካርታ ትመለከት ይሆናል። የወደፊት ሕይወትህን በተመለከተ ዕቅድ ስታወጣም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ማይክል “በጣም ብዙ አማራጮች አሏችሁ” በማለት ተናግሯል። ከእነዚህ ሁሉ የተሻለውን መምረጥ የምትችሉት እንዴት ነው? ማይክል “የምታደርጉት ምርጫ የተመካው በግባችሁ ላይ ነው” ብሏል።

ግብ ሲባል ልትደርስበት የምትፈልገው ነገር ማለት ነው። ያለ ዓላማ የምትባዝን ከሆነ ግብህ ላይ መድረስ አትችልም። በምሳሌያዊ አነጋገር ካርታ አውጥተህ በመመልከት ወዴት እንደምትሄድ ዕቅድ ማውጣቱ እጅግ የተሻለ ነው። እንዲህ ካደረግህ በምሳሌ 4:26 ላይ ያለውን “የእግርህን ጐዳና አስተካክል” የሚለውን ምክር ተከትለሃል ማለት ነው። የ1980 ትርጉም ይህንን ሐሳብ “ለምታደርገው ነገር ሁሉ ዕቅድ ይኑርህ” በማለት ይገልጸዋል።

በመጪዎቹ ዓመታት አምልኮን፣ ሥራን፣ ጋብቻን፣ ቤተሰብንና ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ ብዙ አስፈላጊ ውሳኔዎችን ታደርጋለህ። ዕቅድ ካለህ ጥበብ የተንጸባረቀበት ምርጫ ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። ሆኖም በሕይወትህ ውስጥ ዕቅድ ስታወጣ ችላ ማለት የሌለብህ አንድ ነገር አለ።

“በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ”

እውነተኛ ደስታ ማግኘት ከፈለግህ ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት የሰጠውን ምክር መከተል አለብህ። (መክብብ 12:1) በሕይወትህ ውስጥ የምትመርጠው ጎዳና አምላክን ለማስደሰት ያለህን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት።

በዚህ መንገድ ምርጫ ማድረግህ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በራእይ 4:11 ላይ እንዲህ ይላል:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።” አዎን፣ በሰማይም ሆነ በምድር የሚገኙት ሁሉም ፍጥረታት ፈጣሪያቸውን ለማመስገን የሚያነሳሳ ምክንያት አላቸው። “ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ” ስለሰጠህ አመስጋኝ ነህ? (የሐዋርያት ሥራ 17:25) ይሖዋ አምላክ ለሰጠህ ነገሮች ያለህ አድናቆት አንተም በበኩልህ አንድ ነገር እንድታደርግ አይገፋፋህም?

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ወጣቶች ፈጣሪያቸውን በማሰብ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመሳተፍ መርጠዋል። የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሁሉ የላቀ ግብ እንደሆነና ሥፍር ቁጥር የሌለው በረከት እንደሚያስገኝ የተረጋገጠ ነው። (ሚልክያስ 3:10) ሆኖም ቀደም ብለህ ዕቅድ ማውጣት አለብህ። ለምሳሌ ‘በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስካፈል ራሴን የምረዳበት ምን ዓይነት ችሎታና ሙያ አለኝ?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።

አሁን ሃያ ሰባት ዓመት የሆናት ኬሊ ዕቅድ ማውጣት የጀመረችው ቀደም ብላ ነበር። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመካፈል ግብ ነበራት። ኬሊ ወደ ሃያዎቹ ዕድሜ እየተቃረበች ስትመጣ ሥራን በተመለከተ ዕቅድ ማውጣት ጀመረች። እንዲህ ትላለች:- “በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል የሚያስችለኝን የሥራ ዓይነት መምረጥ ነበረብኝ።”

ኬሊ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለች በጥርስ ሕክምና መስክ በረዳትነት ሞያ ሠለጠነች። እንዲያውም ከምትኖርበት ግዛት አንደኛ ወጣች። ይሁንና ያገኘችው ስኬት ዋነኛ ግቧን እንድትረሳ አላደረጋትም። ኬሊ እንዲህ ትላለች:- “የምፈልገው የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ነው፤ የተቀሩት ነገሮች ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጡ ናቸው።” ኬሊ አሁንም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ነች። “ከዚህ የተሻለ ውሳኔ ላደርግ እንደማልችል ይሰማኛል” በማለት ትናገራለች።

ምክር ጠይቅ

በማታውቀው አካባቢ እየተጓዝክ ከሆነ ካርታ ቢኖርህም እንኳ አንድ ቦታ ላይ ስትደርስ አቅጣጫ መጠየቅህ አይቀርም። ስለ ወደፊቱ ዕቅድ በምታወጣበት ጊዜም የሌሎችን ምክር በመጠየቅ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችላለህ። ምሳሌ 20:18 “ምክር ጠይቀህ ዕቅድ አውጣ” ይላል። እርግጥ ወላጆችህ ጠቃሚ ምክር ሊሰጡህ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። አኗኗራቸው አምላካዊ ጥበብ የሚንጸባረቅበት የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ምክር መጠየቅም ትችላለህ። ሮቤርቶ “በጉባኤያችሁ ውስጥ ወይም በአቅራቢያችሁ የሚገኙ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አዋቂዎችን ምክር መጠየቅ ትችላላችሁ። ፈጽሞ ያላሰባችሁትን ነገር ሊጠቁሟችሁ ይችላሉ” በማለት ይናገራል።

ከማንም በበለጠ ይሖዋ አምላክ፣ በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ደስታ የሚያስገኝልህን ምርጫ እንድታደርግ ሊረዳህ ይፈልጋል። ስለዚህ የወደፊቱ ሕይወትህን በተመለከተ ‘የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማስተዋል’ እንዲረዳህ ጠይቀው። (ኤፌሶን 5:17) በፍጹም ልብህ በይሖዋ የምትታመን ከሆነ “እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

www.watchtower.org/ypa በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” የሚሉትን ተከታታይ ርዕሶች ማግኘት ይቻላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ምን ዓይነት ችሎታና ሞያ አለህ?

▪ በእነዚህ ችሎታዎች ተጠቅመህ ይሖዋን ለማወደስ የምትችልበት መንገድ ይኖራል?

▪ በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች በየትኛው ልትካፈል ትፈልጋለህ?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማያዛልቅ አካሄድ

መጽሐፍ ቅዱስ “ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ” በማለት ይናገራል። ወደ ብልጽግና የሚወስደው ጎዳና ጉድጓድ እንደበዛበት መንገድ ነው! ውሎ አድሮ ለስጋትና ለመንፈሳዊ ውድቀት ሊዳርገን እንዲሁም በዕዳ እንድንዘፈቅ ሊያደርገን ስለሚችል ይህ ዓይነቱ አካሄድ አያዛልቅም።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቅኚነት

የዘወትር አቅኚ የሚባለው በየወሩ ቢያንስ 70 ሰዓት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ የሚያሳልፍ የተጠመቀና ጥሩ ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን ነው። አቅኚዎች የሚያገኙት ሥልጠና እና በአገልግሎት የሚያካብቱት ተሞክሮ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

የቤቴል አገልግሎት

የቤቴል ቤተሰብ አባላት በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት፣ በማተምና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመላክ ረገድ እገዛ ያደርጋሉ። እያንዳንዱ የቤቴል ሥራ ቅዱስ አገልግሎት ነው።

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል

አንዳንድ አቅኚዎች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ችለዋል። ዓለም አቀፍ አገልግሎት

ዓለም አቀፍ አገልጋዮች የመንግሥት አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመገንባት ወደ ሌሎች አገሮች ይሄዳሉ። ይህ ደግሞ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ይገነቡ የነበሩት ሰዎች ካከናወኑት ሥራ ጋር የሚመሳሰል ቅዱስ አገልግሎት ነው።—1 ነገሥት 8:13-18

የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት

በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቃቱን ያሟሉ ያላገቡ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ድርጅታዊ አሠራርንና በሕዝብ ፊት ንግግር ማቅረብን አስመልክቶ ለስምንት ሳምንታት ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ከዚያም አንዳንዶቹ በራሳቸው አገር ሌሎች ደግሞ በባዕድ አገር እንዲያገለግሉ ይመደባሉ።

የሚስዮናዊነት አገልግሎት

ጥሩ ጤንነትና አካላዊም ሆነ የመንፈስ ጥንካሬ ያላቸው ብቁ አቅኚዎች በባዕድ አገር ለማገልገል ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ሚስዮናውያን አስደሳችና አርኪ ሕይወት ይመራሉ።

ሌሎች ደግሞ ሌላ ቋንቋ በመማር በባዕድ አገር ወይም የተማሩትን ቋንቋ በሚጠቀም ጉባኤ ውስጥ ያገለግላሉ።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሕይወቴን እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?

ይህ ዲቪዲ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ሲሆን በብሪታንያ፣ በብራዚል፣ በዩናይትድ ስቴትስና በጀርመን የሚገኙ ወጣቶች ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው ያሳያል፤ ይህ ፊልም በቅርቡ በተለያዩ ቋንቋዎች ይወጣል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የምታደርጉት ምርጫ የተመካው በግባችሁ ላይ ነው።”—የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ማይክል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከዚህ የተሻለ ውሳኔ ላደርግ እንደማልችል ይሰማኛል።”—ላለፉት 6 ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለችው ኬሊ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ አዋቂዎችን ምክር መጠየቅ ትችላላችሁ።”—የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ሮቤርቶ