በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መልእክቱ መድረስ አለበት

መልእክቱ መድረስ አለበት

መልእክቱ መድረስ አለበት

ቴሌግራም ከመፈልሰፉ በፊት የረጅም ርቀት የመልእክት ልውውጥ ማድረግ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነበር። ለዚህም የመልክአ ምድሩ አቀማመጥና ፈጣን የመጓጓዣ ዘዴዎች አለመኖራቸው አስተዋጽኦ አድርጓል። በደቡብ አሜሪካ ሰፊ ግዛት የነበራቸው ኢንካዎች ያጋጥሟቸው የነበሩትን ፈታኝ ሁኔታዎች እንመልከት።

ኢንካዎች በሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሱበት በ15ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ግዛታቸው የአሁኖቹን ቦሊቪያ፣ ቺሊ፣ አርጀንቲና፣ ኢኳዶር፣ ኮሎምቢያና ፔሩ የተወሰነ ክፍል ያካትት የነበረ ሲሆን በፔሩ የምትገኘው ኩዝኮ ጥንት ዋና ከተማቸው ነበረች። ረጃጅም ተራሮች፣ ጥቅጥቅ ያሉ ጫካዎችና የግዛቱ ስፋት ከቦታ ቦታ መጓጓዝን አስቸጋሪ ያደርጉት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ኢንካዎች ላማ ተብሎ ከሚጠራው እንስሳ ሌላ የጭነት ከብትም ሆነ ዕቃ ማጓጓዣ አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ቋንቋቸው በጽሑፍ አልሠፈረም። ታዲያ በዚህ ሰፊና የተለያዩ ሕዝቦችን ባቀፈ ግዛት ውስጥ እርስ በርስ መልእክት የሚለዋወጡት እንዴት ነበር?

ኢንካዎች ኬችዋ የተባለውን ቋንቋቸውን በግዛታቸው ሁሉ ለመግባቢያነት እንዲውል ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በርካታ መንገዶችን ሠርተዋል። በኤንዲስ ተራሮች አቋርጦ የሚያልፍ 5,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አውራ ጎዳና የዘረጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የፓስፊክ ውቅያኖስን ዳርቻ ተከትሎ የሚሄድ 4,000 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ትይዩ መንገድ ሠሩ። ሁለቱን መንገዶች የሚያገናኙ ሌሎች መንገዶችም ነበሩ። ኢንካዎች በረጃጅም ተራሮች ላይ ለመጓዝ ደረጃዎች ያሏቸው ጥርጊያ መንገዶችን፣ ረግረጋማ የሆኑ ቦታዎችን ለማቋረጥ ተንሳፋፊ ድልድዮችን፣ ሸለቆዎችን ለመሻገር ደግሞ ተንጠልጣይ ድልድዮችን ሠርተው ነበር። አንድ ተንጠልጣይ ድልድይ 45 ሜትር የሚያህል ርዝመት የነበረው ሲሆን ገመዱ የሰውን አካል የሚያህል ውፍረት ነበረው፤ ይህ ድልድይ እስከ 1880 ድረስ ለ500 ዓመታት ያህል አገልግሏል!

ኢንካዎች መልእክት የሚለዋወጡት በዋናው መንገድ ላይ በየተወሰነ ርቀት በሚቆሙ ቻስኪ ተብለው በሚጠሩ ሯጮች አማካኝነት ነበር። እያንዳንዱ ሯጭ ሦስት ወይም አራት ኪሎ ሜትር ከሮጠ በኋላ ለሚቀጥለው ሯጭ መልእክቱን ያስተላልፋል፤ እነዚህ ሯጮች በቀን ውስጥ በአጠቃላይ ከ160 ኪሎ ሜትር በላይ ይሸፍናሉ። በቃላቸው በርከት ያሉ መልእክቶችን የሚያስተላልፉ ሲሆን መልእክቱ መንግሥትን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ የያዘ በሚሆንበት ጊዜ ኪፑ በተባለ አስገራሚ መሣሪያ ይጠቀማሉ። ኪፑ ለማስታወስ እንዲረዳ ተብሎ ከገመድና የተለያዩ ቀለማት ካሏቸው ሲባጎዎች የሚዘጋጅ ውስብስብ የሆነ ዘዴ ነው። በሲባጎው ላይ ቋጠሮዎች ያሉ ሲሆን እነዚህ ቋጠሮዎች የአንድ ቤት፣ የአሥር ቤትና የመቶ ቤት ቁጥሮችን ያመለክታሉ። ስፔን ኢንካዎችን ድል ስታደርግ በኪፑ መጠቀም ስለቀረ መረጃ ለማስተላለፍ ያገለግል የነበረው ይህ ዘዴ ተረሳ።

‘በተራሮች ላይ የቆሙ ያማሩ እግሮች’

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የኬችዋ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ መልእክት ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ ምሥራች እየተሰበከላቸው ነው። ይህ መንግሥት ለተገዢዎቹ ሁሉ ሰላም የሚያመጣ ዓለም አቀፋዊ መስተዳድር ነው። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 24:14) በአንድ ወቅት የኢንካዎች ግዛት በነበረው አካባቢ መጓጓዝ አሁንም ቢሆን ቀላል አይደለም፤ ኬችዋ የተባለው ቋንቋቸውም ቢሆን እስካሁን ፊደል የለውም። ሆኖም የኬችዋን ቋንቋ የተማሩ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች አሁን በሚነገሩ የተለያዩ የኬችዋ ቀበሌኛዎች የተዘጋጁ ጽሑፎችንና የቴፕ ክሮችን ያሰራጫሉ።

የእነዚህ ወንጌላውያን ሥራ ‘በተራሮች ላይ የቆሙ፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች እንዴት ያማሩ ናቸው’ የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ትንቢት ያስታውሱናል።—ኢሳይያስ 52:7