መንፈስ ቅዱስ አካል ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
መንፈስ ቅዱስ አካል ነው?
የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ መክፈቻ ቃላት ‘የአምላክ ኃይል’ ተብሎ የተተረጎመውን መንፈስ ቅዱስን ‘በውሆች ላይ ወዲያ ወዲህ ይል’ እንደነበር ይናገራሉ። (ዘፍጥረት 1:2 NW) ስለ ኢየሱስ ጥምቀት የሚተርከው ዘገባ አምላክ ‘በሰማይ’ እንደነበር መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በኢየሱስ ላይ ‘እንደ እርግብ እንደወረደ’ ይገልጻል። (ማቴዎስ 3:16, 17) በተጨማሪም ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ “አጽናኝ” እንደሆነ ተናግሯል።—ዮሐንስ 14:16
እነዚህና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሐሳቦች አንዳንድ ሰዎች ‘አምላክ፣ ኢየሱስና መላእክት ራሳቸውን የቻሉ መንፈሳዊ አካላት እንደሆኑ ሁሉ መንፈስ ቅዱስም አካል ነው’ ወደሚል መደምደሚያ እንዲደርሱ አድርገዋቸዋል። እንዲያውም ለዘመናት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መንፈስ ቅዱስ አካል እንደሆነ ሲያስተምሩ ኖረዋል። ይህ መሠረተ ትምህርት ለረጅም ዘመናት የቆየ ቢሆንም ብዙ ምዕመናን ግራ ተጋብተዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው ጋር አይስማሙም። ለምሳሌ ያህል፣ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት መንፈስ ቅዱስ “ለአምላክ መገኘት ወይም ለኃይሉ መገለጫ እንጂ በራሱ ሕልውና ያለው አንድ አካል አይደለም” የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብ አንድ ቅን ሰው፣ ቤተ ክርስቲያን ‘መንፈስ ቅዱስ አካል ነው’ እያለች በግልጥ የምታስተምረው ትምህርት ትክክል አለመሆኑን መገንዘቡ አይቀርም። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ተመልከት።
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚናገረው የኢየሱስ እናት ማርያም የቅርብ ዘመዷን ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ስትሄድ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ያለው ጽንስ ዘለለ፤ “ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች።” (ሉቃስ 1:41) አካል የሆነ ነገር በሌላ አካል ውስጥ ‘ይሞላል’ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?
2. መጥምቁ ዮሐንስ ለደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣው ስለ ኢየሱስ ሲነግራቸው እንዲህ ብሏል:- “እኔ . . . በውሃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን ጫማውን መሸከም የማይገባኝ፣ ከእኔ የሚበልጥ ኀያል ከእኔ በኋላ ይመጣል። እርሱም በመንፈስ ቅዱስ . . . ያጠምቃችኋል።” (ማቴዎስ 3:11) ዮሐንስ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ስለማጥመቅ ሲናገር መንፈስ ቅዱስን አካል እንደሆነ አድርጎ እንዳላሰበው ግልጽ ነው።
3. ሐዋርያው ጴጥሮስ ለአንድ ሮማዊ መቶ አለቃና ለቤተሰቡ በሰበከ ጊዜ አምላክ ኢየሱስን “በመንፈስ ቅዱስና በኀይል” እንደቀባው ተናግሮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 10:38) ብዙም ሳይቆይ በመቶ አለቃውና በቤተሰቡ ላይ “መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው።” ዘገባው በመቀጠል ብዙ ሰዎች “የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ” እንደተገረሙ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 10:44, 45) እዚህ ላይ የሰፈሩት ቃላትም መንፈስ ቅዱስ አካል ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ይቃረናሉ።
የአምላክ ቃል አካል ያልሆኑ ነገሮችን አካል እንደሆኑ አድርጎ መግለጹ አዲስ ነገር አይደለም። በዚህ መንገድ ከተገለጹት ነገሮች መካከል ጥበብ፣ ኃጢአት፣ ሞትና ጸጋ ይገኙበታል። (ምሳሌ 8:1–9:6፤ ሮሜ 5:14, 17, 21፤ 6:12) ኢየሱስ ራሱ “እንግዲህ የጥበብ ትክክለኛነት በልጆቿ” ማለትም በምታስገኛቸው ግሩም ውጤቶች “ተረጋገጠ” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 7:35) ጥበብ አካል ስላልሆነች ልጆች ሊኖሯት አይችልም! በተመሳሳይም መንፈስ ቅዱስ በአንዳንድ ቦታዎች አካል እንደሆነ ተደርጎ መጠቀሱ ብቻ አካል ነው ሊያስብለው አይችልም።
መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ሲል በሥራ ላይ ያለውን የአምላክን ኃይል እየጠቀሰ ነው። በመሆኑም ከዕብራይስጡ በትክክል የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን መንፈስ በሥራ ላይ ያለ ‘የአምላክ ኃይል’ ብሎታል። (ዘፍጥረት 1:2 NW) ይህ ሐሳብ ከመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ሚክያስ 3:8፤ ሉቃስ 1:35፤ የሐዋርያት ሥራ 10:38
ብዙዎች ካላቸው እምነት በተቃራኒ አምላክ ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ አይገኝም። ከዚህ ይልቅ ‘ማደሪያው’ ወይም መኖሪያው በሆነው መንፈሳዊ ግዛቱ ውስጥ ይኖራል። (1 ነገሥት 8:39፤ 2 ዜና መዋዕል 6:39) ከዚህም በተጨማሪ ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክ የሚኖርበትና “ዙፋኑ” የሚገኝበት አንድ ቦታ እንዳለ ይናገራሉ። (1 ነገሥት 22:19፤ ኢሳይያስ 6:1፤ ዳንኤል 7:9፤ ራእይ 4:1-3) ይሁን እንጂ ‘በማደሪያው’ ሆኖ በሥራ ላይ ያለውን ኃይሉን በመጠቀም በጽንፈ ዓለም ውስጥ ወደሚገኝ ወደ ማንኛውም ቦታ መድረስ ይችላል።—መዝሙር 139:7
በ1879፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ቻርልስ ኢቭዝ አምላክ አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ሆኖ ኃይሉን የመጠቀም ችሎታ እንዳለው የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ተናግረዋል። እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “ለምሳሌ ያህል ‘ፀሐይ ቤት ውስጥ እንድትገባ መጋረጃውን ክፈተው’ እንላለን። በዚህ ጊዜ ራሷ ፀሐይዋ ወደ ቤታችን ትግባ እያልን እንዳልሆነ እሙን ነው። ከዚህ ይልቅ ከፀሐይዋ የሚፈነጥቀውን ጨረር መጥቀሳችን ነው።” በተመሳሳይም አምላክ በሥራ ላይ ያለውን ኃይሉን በሚጠቀምበት ቦታ ላይ የግድ መገኘት አያስፈልገውም። ወደፈለገበት ቦታ መድረስ የሚችለውን ቅዱስ መንፈሱን ይጠቀማል። በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በሥራ ላይ ያለ የአምላክ ኃይል መሆኑን መገንዘብህ ይሖዋ የገባውን ቃል በሙሉ እንደሚፈጽም እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል።
ይህን አስተውለኸዋል?
▪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስ አካል እንደሆነ ያስተምራል?—የሐዋርያት ሥራ 10:44, 45
▪ መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?—ዘፍጥረት 1:2
▪ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እስከ የትኛው ጽንፍ መድረስ ይችላል?—መዝሙር 139:7