ከአንባቢዎቻችን
ከአንባቢዎቻችን
እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ “እንዳትጭበረበር ተጠንቀቅ!” የሚለውን ርዕስ በማውጣታችሁ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆንኩ ለመግለጽ ቃላቶች ያጥሩኛል። (መስከረም 2004) በቤቴ ውስጥ አነስተኛ የንግድ ሥራ የማንቀሳቅስ ሲሆን ተጭበርብሬም አውቃለሁ። ልክ በመጽሔቱ ላይ እንደተጠቀሰው የውርደትና የጥፋተኝነት ስሜት የተሰማኝ ከመሆኑም በላይ በመሞኘቴ አፍሬ ነበር። ተከታታይ በሆነው ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የሰፈረውን ምክር ተግባራዊ አደረግሁ። ጥፋቴን አምኜ የተቀበልኩ ከመሆኑም ሌላ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ በተጨማሪም የጉባኤ ሽማግሌ ከሆነ አንድ ጓደኛዬ ጋር ተወያየሁ። ከዚህ ርዕስ ባገኘሁት እርዳታ ችግሩን መርሳት ችያለሁ። እንዴት ያለ በረከት ነው!
ቲ. ጂ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የወጣቶች ጥያቄ . . . ከመጥፎ ልጆች ጋር እንዳልገጥም ምን ማድረግ ይኖርብኛል? (መስከረም 2005) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጥልቅ እውቀት በሌለው አንድ “መጥፎ” ሰው ተማርኬ ነበር። በመጽሔቱ ላይ የቀረበው ሐሳብ በመንፈሳዊ ከደከመ ሰው ጋር መግጠም ያለውን አደጋ እንድገነዘብ ረድቶኛል። ይሖዋ እንደሚያስብልን ማወቅ በጣም ያጽናናል። በሚያስፈልገኝ ወቅት ለሰጣችሁኝ እርዳታ አመሰግናለሁ።
ኤ. ቢ. ኬ.፣ ዛምቢያ
ይህ ርዕስ ጓደኞቼን መለወጥ እንዳለብኝ እንድገነዘብ አስችሎኛል። እንዲህ ማድረጉ ከባድ ቢሆንም እንኳ በተደጋጋሚ ማንበብ እንድችል በቅርብ ያስቀመጥኩት ይህ ርዕሰ ትምህርት ይበልጥ ጥንካሬ እንዳገኝ እየረዳኝ ነው። ለእኛ ለወጣቶች ስለምትሰጡን እርዳታና ማበረታቻ አመሰግናለሁ።
ኤል. አር.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት—ለድንግል ማርያም ጸሎት ማቅረብ ተገቢ ነው? (ጥቅምት 2005) እናንት የይሖዋ ምሥክሮች እንከን የሌለው ምግባር ስላላችሁ አደንቃችኋለሁ፤ ከዚህም በላይ መጽሔቶቻችሁ በጣም ጠቅመውኛል። ይሁን እንጂ እንዴት የማርያምን እርዳታ መጠየቅ አይኖርብንም ትላላችሁ? ከአብ ጋር ሰላም እንዲኖረን ታማልደናለች።
ኢ. አር.፣ ስፔን
“የንቁ!” መጽሔት አዘጋጆች መልስ:- በርዕሰ ትምህርቱ ላይ እንደተብራራው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ አምላክ እንጂ ወደ ሌላ ወደ ማንም መጸለይ እንዳለብን የሚጠቁም ሐሳብ አናገኝም። የካቶሊክ ቄስና ጸሐፊ የሆኑት አንድሩ ግሪሌ እንደተናገሩት “የማርያም አምልኮ፣ የክርስትናን እምነት የእናት እንስት አማልክት ከነበሯቸው የጥንት ሃይማኖቶች ጋር በቀጥታ ያዛምዳል።” ስለዚህ ለማርያም የሚቀርበው አምልኮ መሠረቱ አረማዊ እምነት እንጂ ክርስትና አይደለም። ይህ ሐሳብ ለብዙ አንባቢዎቻችን አዲስ ሊሆንባቸው ይችላል፤ በመሆኑም እነዚህ አንባቢዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትምህርት ለማወቅ ምርምር እንዲያደርጉ እናበረታታቸዋለን። ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ቀደም ካቶሊኮች የነበሩ ቢሆንም የአምላክን ቃል ሲያጠኑ አምላክ ብቸኛ አማላጃችን በሆነው በኢየሱስ ካልሆነ በቀር በሌላ በማንም በኩል እንድንጸልይ እንደማይፈልግ ተምረዋል። (ዕብራውያን 7:25) ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” * የተሰኘውን መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ይመልከቱ። “አምላክ የሚቀበለው አምልኮ” የሚል ርዕስ ያለው ይህ ምዕራፍ እምነቶቻችን ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማሙ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያብራራል።
የተጫዋችነት ባሕርይን በማዳበር ሕመምን መቋቋም (ሰኔ 2005) ባለቤቴ ጉበቷ ሥራውን በማቆሙ ምክንያት ታኅሣሥ 2002 ላይ ሞተች። በሽታው ለስምንት ወር ገደማ አሰቃይቷታል። ያም ሆኖ ግን የምታወራው አዎንታዊ ስለሆኑ ነገሮች ብቻ ከመሆኑም በላይ የሚያስቁ ተሞክሮዎች ትነግረን ነበር። እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ ሁልጊዜ ደስተኛ ለመሆን ትጥር ነበር። ይህን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ምክንያቷ ምን እንደሆነ ተረድቻለሁ። እኛ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ እንደሚያስፈልገን ሁሉ እርሷም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ሊኖራት ያስፈልግ ነበር። በኮንቺ ሕይወት ላይ እንደታየው ይህ አመለካከት ባለቤቴ ጥሩ ስሜት እንዲኖራት አስችሏት መሆን አለበት። ባለቤቴ እንደዚያ እንድትሆን ያደረጋትን ምክንያት እንዳውቅ ስለረዳችሁኝ አመሰግናለሁ።
ዲ. ኤች.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ከአንባቢዎቻችን “ከአንባቢዎቻችን” የሚለውን ዓምድ ለማንበብ ሁልጊዜ እጓጓለሁ። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የጻፈውን ደብዳቤ አነብና ‘እኔም እንደዚህ ተሰምቶኛል!’ ብዬ አስባለሁ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ‘ይህን ሐሳብ ልብ ሳልለው ቀርቼ ይሆን?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ከዚያም ርዕሰ ትምህርቱን እንደገና የማነበው ሲሆን እንዲህ ማድረጌም አብዛኛውን ጊዜ በትምህርቱ እንድገረምና እንድበረታታ ያደርገኛል።
ኤም. ቲ.፣ ጃፓን
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።