በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በየአምስት ሴኮንዱ አንድ ሕፃን ማለትም በየዓመቱ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሕፃናት በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ምክንያት ይሞታሉ።”—ጀምስ ቲ ሞሪስ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ

ነሐሴ 2005 ደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስን በመታችውና ካትሪና የሚል ስያሜ በተሰጣት ዝናብ የቀላቀለች አውሎ ነፋስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ1,300 እንደሚበልጥ ይፋ ሆኗል።—ዘ ዋሽንግተን ፖስት፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ጥቅምት 2005 ሰሜን ፓኪስታንንና ሕንድን የመታው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ74,000 የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል።—ቢቢሲ የዜና አገልግሎት፣ ብሪታንያ

አንድ ዘገባ እንደሚጠቁመው “በዓለም ዙሪያ በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ በየዓመቱ 1.2 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ይሞታሉ።”የደቡብ አፍሪካ የሕክምና መጽሔት፣ ደቡብ አፍሪካ

አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ቅርሶች

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣናት ፔሩ በቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ወቅት የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናትን ያስጌጡ የሥነ ጥበብ ውጤቶችን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ግራ ተጋብተዋል። ባለፉት ስድስት ዓመታት 200 ቤተ ክርስቲያኖች በሌቦች ተዘርፈዋል። ኩዝኮ በተባለች ከተማ ብቻ እንኳን ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ 5,000 ገደማ የሚሆኑ የሥነ ጥበብ ውጤቶች ተዘርፈዋል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ከዘይት ቀለም የተሠሩ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ሥዕሎች ናቸው። በአገሪቱ በጠቅላላ ምን ያህል የሥነ ጥበብ ውጤቶች እንደጠፉ በትክክል የሚያውቅ ሰው የለም። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የሥነ ጥበብ ውጤት የሆኑ ንብረቶቻቸውን ከዘራፊዎች ለማዳን ሲሉ ይደብቋቸዋል፤ የተደበቁት ግን ምቹ ባልሆነ ቦታ ነው። እንዲያውም በአንድ ደብር ውስጥ ከተደበቁት የዘይት ቀለም ቅብ ሥዕሎች መካከል አንዱ በአይጥ ተበልቷል።

ፊንላንድ የገጠማት የባለሙያዎች እጥረት

በፊንላንድ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ አናጺዎች፣ ቧምቧ ሠራተኞች፣ በያጆች፣ ግንበኞች፣ መካኒኮች፣ ማሽን አንቀሳቃሾችና ነርሶች የመሳሰሉ መሠረታዊ የሙያ ሥልጠናዎችን ያገኙ ሠራተኞችን በጣም ይፈልጋሉ። ለምን? ይህ የሆነው ለከፍተኛ ትምህርት ትልቅ ትኩረት በመሰጠቱ ምክንያት እንደሆነ ሄልሲንጊን ሳኖማት የተባለ ጋዜጣ ዘግቧል። ፌዴሬሽን ኦቭ ፊኒሽ ሪቴይለርስ የተባለ መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆኑት ሄይኪ ሮፖኔን “ትውልዱን በሙሉ ዶክተር እንዲሁም የሥነ ጥበብና የሳይንስ ምሁር እንዲሆን ማድረግ ተገቢ አይደለም” ብለዋል። አክለውም “ሙያዊ ሥልጠና ይበልጥ ከፍተኛ ግምት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

በፈረንሳይ ጥሩ የፍርድ ውሳኔ ተሰጠ

የፈረንሳይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 1, 2005 ላይ የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፖሊስ በ1996 የይሖዋ ምሥክሮችን “ኑፋቄ” ብሎ ለመሰየም የተጠቀመበትን ሰነድ ለይሖዋ ምሥክሮች እንዲያሳዩ ትእዛዝ አስተላልፏል። ሰነዱ የተዘጋጀው በዝግ ስብሰባ ሲሆን ‘ለአገርና ለሕዝብ ደኅንነት’ በሚል ምክንያት በውስጡ ያለው ሐሳብ በምስጢር እንዲያዝ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ስለሚያስከትሏቸው “ውጤቶች” በሰነዱ ላይ “የተሰጠው ግምታዊ ሐሳብ . . . የረባ እንዳልሆነ” ተገንዝቧል። ቢሆንም በዚህ ሰነድ ምክንያት በፈረንሳይ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ መድልዎ ሲፈጸምባቸው ቆይቷል።

“ታላቅ አረንጓዴ ግንብ”

የግጦሽ መሬት መራቆት፣ ድርቅ፣ የደኖች መጨፍጨፍና የውኃ ምንጮችን ከሚገባው በላይ መጠቀም በጣም ሰፊ የሆነ የቻይና ምድር ወደ አቧራማነት እንዲቀየር አድርጓል። ስለዚህ የቻይና ባለ ሥልጣናት “ከዓለም ትልቁን ሥነ ምህዳራዊ ፕሮጀክት” እንደጀመሩ ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ዘግቧል። “አፈሩ እንዳይሸረሸር ለማገድ ሲባል ‘ታላቅ አረንጓዴ ግንብ’ ተብሎ በሚጠራው በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ዛፎች ተተክለዋል።” እንዲሁም አፈሩን ለመያዝ ሲባል ሣርና ቁጥቋጦዎች እየተተከሉ ነው። በ1978 በተጀመረው በዚህ ፕሮጀክት 35 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዛፎችና ድርቅን መቋቋም በሚችሉ ተክሎች ለመሸፈን ታቅዶ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተከናውኗል።